21/05/2023
✥✥✥ ?✥✥✥
➗➗➗➗➗➗➗➗➗
✅ የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ፡፡ ስድስት ቀን ሥራ፡፡ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ነው፡፡
አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም፥ ገረድህም፥ ከብትህም፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ፤ እግዚአብሔርም በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርንም፥ ባሕርንም ያለባቸውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐርፏልና፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል ቀድሶታልም፡፡”
ዘጸ. ፳፥፲–፲፩፡፡
➛ ሰንበት የተባረከ ቀን ነው፡፡ በጌታም ዘንድ የዕረፍት ቀን ነው፡፡ ይህ ትእዛዛት ከመጻፋቸው በፊት እግዚአብሔር ለሕዝቡ ለእሥራኤል የሰጠው ቀዳማዊ ትእዛዝ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ ይፈጽመው ዘንድ ከመሰጠቱ በፊት እግዚአብሔር ራሱ በተግባር የፈጸመው ትእዛዝ ነው ሊባልም ይችላል፡፡ እንግዲህ በዚህ መሠረት ቀዳማዊ ትእዛዝ መሆኑን ካረጋገጥን፤ እግዚአብሔርንም ከሥራው ሁሉ በማረፍ ሰንበትን ለእረፍት የባረከውና የቀደሰው መሆኑን ካወቅን እኛ ደግሞ የበለጠ ልናከብረውና በሥራም ልንፈጽመው የሚገባን አይደለምን? በመጽሐፍም ደግሞ “እግዚአብሔርም ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ በእርሱ አርፏልና፡፡” በማለት የተነገረው ቃል ይህን ትእዛዝ በዓለም መጀመሪያ እግዚአብሔር አምላክ የስድስቱ ቀናት ተግባሩን ከፈጸመ በኋላ በማረፍ ለዕረፍት የሠራልን መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡ ዘፍ. ፪፥፫፡፡
➤መጽሐፍ “እግዚአብሔር እርሱ ዐርፎበታልና ሰባተኛውን ቀን ባረከው” ይላል፡፡ ነገር ግን “ዐርፎአልና” የሚለው ቃል ትርጉምና ፍች ያስፈልገዋል፡፡ እግዚአብሔር በባሕርዩ ድካም የሚስማማውና ዕረፍትም የሚያስፈልገው አይደለም፤ ታዲያ “ዐርፎአልና” የተባለው ምን ለማለት ተፈልጎ ነው? ስለ ዕረፍት የሚነገረው አድካሚ ሥራ ላለበት ነው፡፡ እግዚአብሔር ዐርፏልና ሲባል የትኛውን አድካሚ ሥራ ሠርቶ ነው? የሚል ጥያቄ መነሣቱ አይቀርም፡፡እግዚአብሔር ዓለም ለመፍጠር ትእዛዝ ከመስጠትና ከመናገር በቀር ያደረገው አንዳች ነገር እንደሌለ መጻሕፍት ይመሠክራሉ፡፡ ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት “እርሱ ተናግሯልና፥ ሆኑም፤ እርሱም አዘዘ፥ ጸኑም” በማለት የተናገረው ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ መዝ. ፴፪፥፱፡፡
➤በዚህ መሠረት እርሱ “ብርሃን ይሁን” ባለ ጊዜ ይሆን ነበር፤ “ከሰማይ በታች ያሉ ውኆች ይሰብሰቡ” ባለ ጊዜም እንዲሁ ይሰበሰቡ ነበር፤ ምድርም ዘርን ታብቅል ባለጊዜ ታበቅል ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ ከቃሉ የተነሣ ከመሆን በቀር በእግዚአብሔር ላይ ያስከተሉት ድካም አልነበረም፡፡ነገር ግን የማዳን ሥራው በእርግጥ አድካሚ እንደነበር ደግሞ እናስተውላለን፡፡ እርሱ ሰውን ለማዳን ሰው መሆን ነበረበት፤ መለኮታዊ ልዕልናውን ትቶ ክብሩን በፈቃዱ ዝቅ አድርጎ በትሕትና አርአያ ገብርን መንሣት ነበረበት፤ ከኃጢአት በቀር ሰው የሠራውን ሁሉ መሥራት ነበረበት፤ መሰደብ፣ መንገላታት፣ መሰቀልና መከራን ሁሉ ለመቀበል፣ መሞትና ከሙታን መነሣት ሁሉ በእርሱ መፈጸም ነበረባቸው፡፡ በዚያ የመጨረሻው የመከራ ቀን፤ በዕለተ ዓርብ የኃጢኣትን ኃይል፣ ሞትንም በሞት ድል ነሥቶ የኃጢኣት ደመወዝ የሆነውን ሞትን አስወገደው፡፡ ሮሜ ፮፥፳፫፡፡
➤ይህንንም በዕለተ ሰንበት /እሑድ/ በትንሣኤው አተመው፤ ፍጹም የሆነውም የእግዚአብሔር ዕረፍት የሰው ልጆችን መዳን ማረጋገጥ ነውና፡፡ ከዚህ በመነሣት ነው እሑድ ሰንበተ ክርስቲያን ወይም የጌታ ቀን የተባለው፡፡ ቅዱስ ዳዊትም “ዛቲ ይእቲ ዕለት ኅሪት ዕለተ መድኃኒት እንተ ባቲ ንትፈሣህ ወንትሐሠይ፤ ይህች እንደሰትባት ዘንድ እግዚአብሔር ያዘጋጃት ቀን ናት” በማለት መናገሩ ለዚሁ ነው፡፡መዝ. ፻፲፰፡፡
➤ሰንበትን ማክበር ከዐሠርቱ ትዕዛዛት በፊት በተግባር የነበረ ነው፡፡ በመሆኑም እግዚአብሔር ለሙሴ በሰጠው ጽላት ላይ በጻፈው ጊዜ “ትቀድሰው ዘንድ አስበው” በማለት እሥራኤል ቀድሞውኑ የሚያውቁትን ይህን ትእዛዝ እንዲያስታውሱት አድርጓል፡፡ ዐሠርቱን ትእዛዛት የምናገኘው በኦሪት ዘጸአት ምዕራፍ ፳ ሲሆን እግዚአብሔር ሥራውን ፈጽሞ /የመፍጠር ሥራውን/ በተግባር ከገለጠው በተጨማሪ በትእዛዝ መልክ ሰንበትን ማክበር እንደሚገባ የተነገረው በዘጸአት ምዕራፍ ፲፮ ነው፡፡
➤እግዚአብሔር ለእሥራኤል ኅብስተ መናን ከሰማይ ባዘነበላቸው ጊዜ በየዕለቱ የሚበቃቸውን ያህል ይሰበስቡ ነበር፡፡ በስድስተኛው ቀን ግን በሌሎቹ ዕለታት ከሚለቅሙት በእጥፍ ይለቅሙ እንደነበር ተጽፏል፡፡ ነቢዩ ሙሴም “እግዚአብሔር የተናገረው ይህ ነው፡- ነገ ዕረፍት፥ ለእግዚአብሔርም የተቀደሰ ሰንበት ነው፤ የምትጋግሩትን ጋግሩ፤ የምትቀቅሉትንም ቀቅሉ፤ የተረፈውን ሁሉ ለነገ አንዲጠበቅ አኑሩት አላቸው፡፡ ዘጸ . ፲፮፥፳፫፡፡ እንደታዘዙትም አኖሩት፤ አልሸተተም፣ ትልም አልሆነበትም፤ ሙሴም “የእግዚአብሔር ሰንበት ዛሬ ነውና ብሉት፤ ዛሬ በሜዳ አታገኙትም፡፡ ስድስት ቀን ልቀሙት፤ ሰባተኛው ቀን ግን ሰንበት ነው በእርሱ አይገኝም፤ . . . እግዚአብሔር ሰንበትን እንደሰጣችሁ ዕዩ፤ ስለዚህ በስድስተኛው ቀን የሁለት ቀን እንጀራ ሰጣችሁ፤ ሰው ሁሉ በሥፍራው ይቀመጥ፤ በሰባተኛው ቀን ማንም ከሥፍራው አይሂድ . . . ሕዝቡም በሰባተኛው ቀን ዐረፈ፡፡ዘጸ. ፲፮፥፴ - ፴፪፡፡
➤በዚሁ መሠረትም እነርሱ ሰንበትን ቀደሱት፤ በሰንበትም ምንም ነገር አልሠሩትም፤ ምግባቸውን ፍለጋ እንኳ ከቤት አልወጡም፤ ምግብም አላበሰሉም፤ ዐረፉበት እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ የዓርብን እንጀራ በእጥፍ አብዝቶ ሰጣቸው፤ ባረካቸውም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የሰንበትን አከባበር ከመና አሰባሰብ ጋር አያይዞ አዘዘ፤ ይህ የሚያስረዳን ከዐሥርቱ ትእዛዛት አንዱ ክፍል ሆኖ ከመሰጠቱ አስቀድሞ ሰንበትን ማክበር በእሥራኤል ዘንድ የሚታወቅና በሥራም ላይ የነበረ መሆኑን ነው፡፡
➤እግዚአብሔር ከሌሎች ትእዛዛት ሁሉ በፊት ያስቀደመው ሰንበትን ስለማከበር የሰጠውን ትእዛዝ ነው፡፡ ይህ ትእዛዝ ደግሞ ጥብቅ ነው፡፡ ይኸውም ሰንበትን ያላከበረ ሰው እንዲገደል በተሰጠው ትእዛዝ ይታወቃል፡፡ እግዚአብሔርም ለሙሴ “ለእናንተ ቅዱስ ነውና ሰንበትን ጠብቁ፤ የሚያረክሰውም ሁሉ ፈጽሞ ይገደል፥ ሥራንም በእርሱ የሠራ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጥፋ፡፡ . . . ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የዕረፍት ሰንበት ነው፤ በሰንበት ቀን የሚሠራው ሁሉ ፈጽሞ ይገደል፡፡” ሲል የተናገረው ቃል የዚህን ትእዛዝ ጥብቅነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ዘጸ. ፴፩፥፲፬ - ፲፭፡፡
➤በተጨማሪም “ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር የዕረፍት ሰንበት የተቀደሰ ቀን ይሆንላችኋል፤ የሚሠራበትም ሁሉ ይገደል፡፡ በማደሪያዎቻችሁ ውስጥ በሰንበት ቀን እሳትን አታንድዱ፡፡” በማለት የተነገረው የዚህን ትዕዛዝ ክብደት የሚያመለክት ነው፡፡ ዘጸ. ፴፭፥፪፡፡
➤ነቢዩ ሕዝቅኤልም ሰንበትን ስለሚሽሩ ሰዎች ብዙ ጊዜ ተናግሯል፡፡ “ልጆች ግን ዐመፁብኝ . . . በሥርዓቴም አልሄዱም፥ ሰንበታቴን አረከሱ፤ በዚህም ጊዜ፡- መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ ቁጣዬንም በምድረ በዳ እፈጽምባቸዋለሁ” ሲል ተናግሯልና እያለ መልእክቱን አስተላልፏል፡፡ ሕዝ ፳፥፳፩፡፡
➤ነቢዩ ሙሴ “እግዚአብሔር ሰንበትን እንደሰጣችሁ እዩ” በማለት መናገሩ የዚህን ስጦታ ዓላማና ምክንያት አስተውሉት ለማለት ነው፡፡ ሰንበትም የእግዚአብሔር ስጦታ እንጂ በሰው ልጆች ላይ የተጫነ ሸክም ወይም ዕዳ አይደለም፡፡ የፈጠረን እግዚአብሔር ደካማ ባሕሪያችንን ስለሚያውቅ ከሳምንቱ ዕለታት አንዱን ሰንበት አድርጎ ለዕረፍት ሰጠን፡፡ ከድካማችን የተነሣም በየዕለቱ መሥራት አንችልምና ሰንበትን ማክበር ለሥጋም ጠቃሚ ነው፡፡
ዘዳ. ፭፥፲፬-፲፭፡፡እግዚአብሔር ሰንበትን የሰጠበት ሌላው ምክንያት ሰው በዚህ ዓለም ሲኖር ለሥጋዊ ፍላጎቱ ብቻ ሲቃትትና ሲደክም ሥጋውንም ብቻ ሲያስብና ለሥጋዊ እርካታ ብቻ ሲሠራ እንዲውል ብቻ ሳይሆን ሥጋውን አሳርፎ የነፍስ ሥራ እንዲሠራበት በዚህ ዓለም ባረፈው ዕረፍት የማያልፈውን ሰማያዊ ዕረፍተ ነፍስ እንዲያስብ፣ እንዲመኘው፣ እንዲለምንና በሕይወት ዘመኑም ስለሰጠው መንፈሳዊ በረከት እግዚአብሔርን እንዲያመሰግንበት ጭምር ነው፡፡ ማር. ፪፥፳፯፡፡
➤አምላካችን እግዚአብሔር እንደተናገረው ሁሉ ሰንበት የዘለዓለማዊና የመንፈሳዊ ዕረፍት ምልክት ሆኖ የተሰጠ ጸጋ ነው፡፡ “እኔ የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቁ ዘንድ በእኔና በእናንተ ዘንድ ለልጅ ልጃችሁ ምልክት ነውና ሰንበቶቼን ፈጽሞ ጠብቁ፡፡” እንዲል፡፡ ዘጸ. ፴፩፥፲፫፡፡
➤ ሰንበት የሚመጣው አማናዊ ዕረፍት ምሳሌ ሆኖ የተሰጠ የብሉይ ኪዳን ሕግ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ሕግ መሠረት በሰንበት ዕረፍተ ሥጋ ይደረጋል፡፡ ይህም በኋላ ዘመን በክርስቶስ ቤዛነት ለተገኘው ድኅነት ለዕረፍተ ነፍስ ምሳሌ ነበር፡፡ በሐዲስ ኪዳን የተገለጠው የክርስቶስ ትንሣኤ በሰንበተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፤ ሰንበተ ክርስቲያንም የሰው ልጆች ለዘለዓለም ዐርፈው ከእግዚአብሔር ጋር በደስታ የሚኖሩበት ምሥጢረ ትንሣኤ የተገለጠበት የድኅነት ዕለት ነው፡፡እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን በፈጠረ ጊዜ በሰባተኛው ቀን ማረፉ፣ የማዳን ሥራውን ፈጽሞ ሞትን ድል በማድረግ ለእኛ የሰጠው የሰንበተ ክርስቲያን ምሳሌ ነበር፡፡ ሰንበተ ክርስቲያን የተባለ እሑድም ለዘለዓለም የምናርፍበትን የዕረፍት ቀን የሚያመለክት ነው፡፡ “በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው” እንደተባለው ሞት በተሻረበት ትንሣኤ ስንነሣ ያንጊዜ እኛም የዘለዓለሙን ዕረፍት እናርፋለን፡፡
፩ቆሮ. ፲፭-፳፬-፳፰፡፡
➤ስለሆነም የክርስቲያኖች ሰንበት ከቅዳሜ እሑድ ወደ መሆን ተቀየረ ወይም ተለወጠ፤ ሰንበተ ክርስቲያንም ተባለ፡፡ ይኸውም እሑድ ከበረ ማለት እንጂ ቅዳሜ ፈጽሞ ተሻረ ማለት አይደለም፡፡ “በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ” የሚለው ትእዛዝ በሰንበት ተኝታችሁ ዋሉ፣ ሥራ ፈታችሁ ተቀመጡ የሚል ትርጉም ያለው አልነበረም፡፡ በሌሎች ቀናት ከሚሠራው ሥራ ለየት ያለ መንፈሳዊና መልካም ሥራ እንዲሠራበት የተሰጠ ነው እንጂ፡፡ ሰንበትም በስንፍና ያለአንዳች ሥራ የሚያሳልፉት ሳይሆን መልካም ሥራ እንዲሠራበት የተሰጠ ነው እንጂ፡፡ ሰንበትም በስንፍና ያለአንዳች ሥራ የሚያሳልፉት ሳይሆን መልካም ተግባር እየፈጸሙ በመንፈሳዊ ሥራ ተጠምደው የሚያከብሩት የጌታ ቀን ነው፡፡ አይሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይከራከሩት የነበረው በሰንበት ለምን መልካምና መንፈሳዊ ሥራ ሠራህ? ለምን አስተማርክ? ለምን ድውያንን ፈወስክ? በማለት ነበር፡፡
ማቴ. ፲፪፥፲፤ ሉቃ. ፲፬፥፫፡፡መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጌታ ቀን የተባለች ሰንበትን በመንፈሳዊ ሥራ ተጠምዶ ማሳለፍ እንደሚገባ ለማስተማር ብዙ ድውያንን ይፈውስና በምኩራብ በመገኘት ያስተምር ነበር፡፡ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ዕውር የነበረውን ሰው የፈወሰው በዕለተ ሰንበት ነበር፡፡ “ኢየሱስም ጭቃ አድርጎ ዓይኖቹን የከፈተበት ሰንበት ነበር፡፡” እንዲል፡፡ ዮሐ. ፱፥፲፬፡፡ እጁ የሰለለችውን ሰው በፈወሰ ጊዜም በሰንበት መፈወስ የተፈቀደ ስለመሆኑ ሲነግራቸው “ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበትም በጉ በጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ሰው ማነው? ስለዚህ በሰንበት መልካም ሥራ ተፈቅዷል አላቸው፡፡
ማቴ. ፲፪፥፲-፲፫፡፡ ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ የድካም መንፈስ ያደረባትን ሴት ከፈወሰ በኋላ የምኩራብ አለቃውን “እናንተ ግብዞች፥ ከእናንተ እያንዳንዱ በሬውን ወይስ አህያውን ከግርግሙ ፈትቶ ውኃ ሊያጠጣው ይወስደው የለምን? ይህችም የአብርሃም ልጅ ሆና ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ሰይጣን ያሠራት በሰንበት ቀን ከዚህ እሥራት ልትፈታ አይገባምን? አለው፡፡ ሉቃ. ፲፫፥፲-፲፮፡፡ በቤተ ሳይዳ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ድውይ የነበረውንም ሰው የፈወሰው በሰንበት ነበር፡፡ዮሐ. ፭፥፪--፲፩፡፡ ሆዱ የተነፋውንም ሰው የፈወሰው በሰንበት ነበር፤ሉቃ. ፲፬፥፩-፮፡፡
➤ከዚህም በላይ ደቀመዛሙርቱ እሸት ቀጥፈው በመብላታቸው የተነሣ ፈሪሳውያን በተቃወሙት ጊዜ “ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሯል እንጂ ሰው ስለሰንበት አልተፈጠረም” በማለት ሰው በሰንበት መልካም ሠርቶ መንፈሳዊ ጥቅም ሊያገኝ እንደሚገባ አስተምሯል፡፡
ማር. ፪፥፳፫፡፡ “እኔ ምሕረትን እወዳለሁ፤ መሥዋዕትንም አይደለም” በማለት በሰንበት ቀን ለድውያን የተደረገው ምሕረት ሰንበትን መሻር አለመሆኑን በሰንበትም ይህን መሰል መንፈሳዊ ተግባር መፈጸም የሚገባ መሆኑን አስረድቷል፡፡ ማቴ . ፲፪፥፯፡፡ከሁሉም በላይ ሰንበት ለመንፈሳዊ ሥራ እንዲውል እግዚአብሔር ማዘዙ በመጽሐፍ ተመዝግቧል፤ “ሰባተኛው ቀን ግን የዕረፍት ሰንበት ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንበታል፡፡ ዘሌ. ፳፫፥፫፡፡
➤ይህም በዕለተ ሰንበት መንፈሳውያን ስብሰባዎች ይደረጉበታል ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር “በየሰንበቱ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በፊቴ ይሰግድ ዘንድ ዘወትር ይመጣል” በማለት የተናገረው ሰንበት የአምልኮ መፈጸሚያ ቀን መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ኢሳ. ፷፮፥፳፫፡፡ በሌላ ምንባብ ደግሞ የሚቃጠለው መሥዋዕትና የእህሉም ቁርባን በሰንበት ቀን እንዲቀርብ አዝዞአል፡፡ ሕዝ . ፵፮፥፬፡፡
ቅዱሳት መጻሕፍትም የሚነበቡት በዕለተ ሰንበት ነው፤ “ሙሴስ ከቀደሙት ትውልድ ጀምሮ በሰንበት በሰንበት በምኩራቦች ሲያነቡ በየከተማው እርሱን የሚሰብሰኩ አሉት፡፡” እንዲል፡፡ የሐዋ. ፲፭፥፳፩፡፡
➤ ሰንበት የአምልኮ መፈጸሚያ ብቻም ሳይሆን የማስተማሪያ ዕለት ጭምር ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰንበት ያስተምር እንደነበር ሁሉ ደቀ መዛሙርቱ ሐዋርያትም እንደእርሱ እንደመምህራቸው በሰንበት ያስተምሩ እንደነበር ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡
ማር. ፮፥፪፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በየሰንበቱም ሁሉ በምኩራብ ይነጋገር ነበር፤ አይሁድንና የግሪክን ሰዎች /ስለ ወንጌል/ ያስረዳ ነበር፡፡ የሐዋ. ፲፬፥፬፡፡በተሰሎንቄም እንዲሁ “የአይሁድ ምኩራብ ነበረ፡፡ ጳውሎስም እንደልማዱ ወደ እነርሱ ገባ፥ ሦስት ሰንበትም ያህል ከእነርሱ ጋር ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ይነጋገር ነበር የሐዋ. ፲፯፥፩-፪፡፡
➤በሐዲስ ኪዳን ሰንበት ሁለት ነው፡፡
➛ዕለት ቅዳሚት እና
➛እሁድ ናቸው፡፡እነዚህም ማክበር እንደሚገባና ሥራ እንዳይሰራባቸው ሐዋሪያት በሲኖዶስ
አዘዋል፡፡ (አንቀጽ 65፤2)
🤳🤳🤳🤳 🤳🤳🤳🤳
➤ቅዳሜ የሚከበርበት ምክንያት እግዚአብሔር ስድስት ቀን ሰርቶ በእርሷስላረፈና በኦሪት በእግዚአብሔር የታዘዘ በእግዚአብሔር ተባርኮና ተቀድሶ የተሰጠ ስለሆነ ነው።
ዘጸ.20፤8 ሆኖም ግን በዘመነ ሐዲስ የክርስቲያኖች
የቀዳሚት ሰንበት አከባበር እንደ አይሁድ ለሰው የሚከብድ እንዳይሆን በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 19 ላይ ተገልጿል፡፡
🤳🤳🤳🤳 🤳🤳🤳🤳
➤እሑድ ማለት ‹‹አሐደ›› ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም የመጀመሪያ ማለት ነው፡፡ ይህቺ ዕለት በመጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ከሳምንቱ በፊተኛው ቀን›› በመባል ትታወቃለች፡፡ ዮሐንስም በራዕዩ ‹‹የጌታ ቀን›› ያላት ናት
ራእይ 1፤10 ቅዱስ ያሬድም በድጓው ላይ ‹‹ዕለተ እግዚአብሔር› የሚላት ዕለተ እሑድ ናት፡፡ዕለተ እሑድ እንደ ሰንበት የሚከበርበት ምክንያቶች፡--እግዚአብሔር ሥራውን የጀመረባት ለሥነፍጥረት መጀመሪያ ዕለተ (ጥንተዕለት) ናትና
➛-ዕለተ ሥጋዌ ናት፡፡ ጌታ የተፀነሰባትና እርቅ የተወጠነባት የፍሰሐ ቀን፡፡
➛ዕለተ ትንሣኤ ናት፡፡ ጌታ ከሙታን ተለይቶ የተነሳባት ዕለት
➛-የቤተ/ክ የልደት ቅን ናት፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋሪያት የወረደባት ኃይልና ፅናትን ያኙባት ዕለት
➛ጌታ በክበበ ትስብእት በግርማ መለኮት ዳግም በቅዱሳን መላእክቱ ታጅቦ በጌትነቱ ለፍርድ የሚመጣባት ታላቅ የፍርድ ቀን ናትና።
➛የተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች የሚካሄዱባት ዕለት ናት
1ኛ ቆሮ 16÷1የሐዋሪያት ዘመንም በጤሮዓዳ ያሉ ክርስቲያኖች እሑድ ቀን ይሰበሰቡ ነበር። የሐዋ 20÷7
🤳🤳 ?🤳🤳
➤ቀደም ባሉ ዘመናት በተለይም በኢትዮጵያ ይህን በተመለከተ ብዙ ክርክሮች ተደርገው እንደነበር መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ ፍትሐ ነገስት እንደ እሑድ ቀዳሚትን አትጠናቀቁ ቢልም በአገራችን በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን‹‹ቀዳሚት እንደ እሑድ ይከበር›› በሚሉና ‹‹እሑድ ብቻ ይከበር›› በሚሉ
በቤተ ተክለሃይማኖትና በቤተ ኤውስጣቴዎስ ሊቃውንት መካከል ውዝግብ ተነስቶ ነበር፡፡በመጨረሻም በወቅቱ የነበሩት የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ተከራክረው በመተማመን መንፈስ ቅዱስ በገለጠላቸው መጠን ባስቀመጡት መሠረት
በቤተክርስቲያን ሁለቱን ቀናት ሳምንታዊ በዓላት በመሆን እንደ አንድ ቀን አድርገንና አስተካክለን እናከብራቸዋለን፡፡
✍️ቅዳሜ ተሽሯል በምትኩ እሑድ ተሰጠን የሚሉትን ቤተክርስቲያን አትቀበላቸውም፡፡ ‹‹እኔ ሕግንና ነቢያትን
ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ ልፈጽም እንጂ ለመሻር
አልመጣሁም››ማቴ 5፤7 ይላልና ጌታችን በኦሪት ላይ ወንጌልን እንደሠራ ሁሉ በቅዳሜ ላይም እሑድን ሰራ፡፡
ይህን ክርክር በተመለከተ በ1442 ዓ.ም ልዩ ስሙ ደብረ ምጥማቅ በተባለ ቦታ በአባ ሚካኤልና በአባ ገብርኤል መሪነት ጉባኤ ተደርጐ ቅዳሜና እሑድ እኩል እንዲከበሩ ወስነዋል። ይህም በመጽሐፈ ብርሃን ሁለቱም ሰንበታት
አንድ ሆነው እንዲከበሩ በጉባኤው መስማማታቸውን ይገልፃል፡፡
➤ታላቁ የቤተክርስቲያን አባት ቅዱስ አትናቴዎስም በሰንበተ ክርስቲያን እንዲቀደስ በደረሰው ቅዳሴ ቁጥር 60-64 ‹‹በነቢዩ በዳዊት መዝሙር
በታወቀች በበዓላችን ቀን በእውነት ሃሌሉያ እንበል፡፡ እግዚአብሔር ሥራውን ይሠራ ዘንድ የጀመራት በእውነት የታወቀች ናት በእርሷም ደስ ይበለን፡፡በእርሷም ሐሴት እናድርግ፡ ትከብሩባት ዘንድ አክብሯት፡ዘመን ወር ለመባል በእርሷ የታወቃችሁ ሌሎች ዕለታት ሆይ የበዓላትን በኩር ኑ አመስግኗት ይህችውም የከበረች ሰንበተ ክርስትያን ናት›› በማለት የሰንበተ ክርስቲያንን ታላቅነት ተናግሯል፡፡የሮም ቄሳሮች ዕለተ እሑድ እንዳይከበር ከልክለው የነበሩ ሲሆን ተመልሶ እንዲከበር በአዋጅ የተደነገገው በንግሥት ዕሌኒ ልጅ በንጉሥ ቆስጠንጢኖስዘመን ነው፡፡
➤ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ሥልጣን በያዘ ጊዜ ክርስቲያኖች የእምነት ነፃነታቸውን በማግኘታቸው ለቤተክርስቲያን ከሰጣቸው መብቶች ውስጥ አንዱ ከጌታ ትንሣኤ ጀምሮ ክርስቲያኖች ያከብሯት በነበረችው ዕለተ እሑድ ሥራ እንዳይሰራባትና የክርስቲያኖች የበዓል ቀን እንድትሆን በ321 ዓ/ም የታወጀው አዋጅ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን በሕገ መንግሥቱ አፅድቆ አወጀው እንጂ በክርስቲያኖች ዘንድ ዕለተ እሑድ ቀደም ሲልም የታወቀችና የተከበረች ዕለት ናት፡፡
በሰንበት የወደድነውን ሁሉ ልንፈጽምበት አልተሰጠንም፡፡
የሰንበት ውሎአችንን ለሰንበት ጌታ ለእግዚአብሔር ሰጥተን በዚህ ቀንም እርሱ ያደረገልንን ቸርነት እያሰብን በማመስገን፣ መንፈሳዊ ዋጋ የሚገኝባቸውን ቅዱሳት ተግባራት መፈጸም ይኖርብናል፡፡
👉👉👉👉 ።👉👉👉👉