30/03/2025
አርዮ አካዳሚ በተሻለ ርምጃ ላይ ነው
ት/ቤቱ አርብ መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓም የተማሪ ወላጆችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት የ2017 ት/ዘመን የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምና የተማሪዎች ውጤት ሪፖርት አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በግማሽ ዓመት ትምህርት ውጤት ከየክፍልና ከአጠቃላይ ብልጫ በማምጣት ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ለወጡ ተማሪዎች ማበረታቻ ምስክር ወረቀት ተሠጥቷቸዋል። እንድሁም በህፃናት ክትትል፣ ድጋፍና፣ የወላጅ ግዴታ በመፈፀም ግምባር ቀደም ለሆኑ ወላጆች የምስጋና ምስክር ወረቀት ተሠጥቷቸዋል። በዕለቱ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ የተማሪዎች ወላጆች በመገኘታቸው የትምህርት ቤቱ ሥራ አመራር ቦርድ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርቧል።
በዕለቱ የተገኙት ተጋባዥ እንግዳ የነበሩት የማሻ ከተማ ት/ጽ/ቤት ተወካይ አቶ ግርማ አቾሞ በት/ቤቱ አሠራርና ውጤታማ ተማሪ ለመፍጠር እየተደረገ ባለው ትጋት ተደንቀው ሰፊ የማበረታቻ አሰተያየት በመስጠት አሁን ት/ቤቱ የደረሰበት ደረጃ ከሌሎች አንፃር የተሻለ ስለሆነ የበለጠ በማሻሻል ከደረጃ 2 ወደ ደረጃ 3 ለመሸጋገር ተግቶ እንዲሠራ የሥራ መመሪያ ሠጥቷል። አቶ ግርማ አቾሞ ከተደነቁባቸው ሥራዎች
1ኛ) ት/ቤቱ የቤት ኪራይና የመ/ራን ደመወዝ ለመክፈል ከፍተኛ የገንዘብ እጥረትና የዕዳ ጫና እያለበት ለመክፈል አቅም የሌላቸው የደሃ ቤተሰብ ልጆች የሆኑ 3 በላይ ተማሪዎችን በየዓመቱ በነፃ እያስተማረ መቆየቱን በማየታቸው ለትርፍ ንግድ ሳይሆን አከባቢውን ለማገዝ ያለመ ት/ቤት ነው ብለዋል። ሌሎች ት/ቤቶችም መልካም አርአያነቱን ማስፋት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
2ኛ) ት/ቤቱ የገንዘብና የግብኣት(የመጽሐፍ) እጥረት እያለበት በተማሪ ውጤትና ትምህርት ጥራት ላይ በየዓመቱ ጎልቶ የሚታይ ዕድገት ማስመዝገብ ላይ መሆኑ በሱፔርቪዥንና እንስፔክሽን የተረጋገጠ ቢሆንም ዛሬ ተግባራዊ ሁኔታ ያሳዩ ተማሪዎች ድንቅ ብቃት ስመለከት ት/ቤቱ በገንዘብና በግብኣቶች ቢደገፍ ለአከባቢው ድንቅ ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን እንደሚፈጥር እምነት ይጣልበታል ብለዋል። ለዚህም የተማሪው ወላጆችና የአከባቢው መንግሥት ድርሻ የጎላ መሆኑን አስገንዝበዋል።
3ኛ) የመምህራኑን ብቃት ለማሻሻልና ተነሳሽነት ለመጨመር ተከታታይነት ያለው ስልጠና ለሁሉም መ/ራን ከመሠጠቱ በላይ ለኬጂ(ቅድመ መደበኛ ተማሪዎች) ልዩ ስልጠና መሠጠቱ የሙያ ክፍተት በመሙላት ለተሻለ አፈፃፀም ይረዳል
4ኛ) የተማሪዎች ውጤት በብቃት ደረጃቸው የተተነተነበት (ትወራ) አሳማኝና ተማሪዎችን ብቃት ለይቶ ለመደገፍ ምቹ መሆኑ
5ኛ) የተማሪዎች ውጤት በየትምህርት ዓይነት ተለይቶ የየክፍሉ አማካይ መለየቱ ለወደፊቱ ጉድለቶችን ለይቶ ለመደገፍ ጠቃሚ በመሆኑ ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል በአቶ ግርማ አቾሞ አጽንኦት ተሰጥቶበታል።
በዕለቱ የተገኙ የተማሪ ወላጆችም ከ2012 ዓም ጀምሮ በኪራይ ቤት ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ፣ ትርፍ ሳይሆን ወጪውን ሳይሸፍን በከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ ሆኖ እየሠራ በየጊዜው በተማሪዎች ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ያለ ት/ቤት መሆኑን መስክረው ት/ቤቱ ለወደፊቱ የራሱ ግቢና መማሪያ ክፍሎች እንዲኖሩት አሳስበዋል። ባጠቃላይ ወላጆች ት/ቤቱ የልጆቻችን የወደፊት ተስፋ መሆኑን ዛሬ ከቀረበው በዓይን የሚታይ ተጨባጭ ሪፖርት፣ ግልጽ ውይይትና ከተማሪዎች ተግባራዊ ብቃት ስለተረዳንና በትምህርት ቤቱ ቀጣይነት ላይ ስላመንንበት በሚንችለው መልኩ ት/ቤቱን እንደግፋለን ብለዋል። አንዳንድ ወላጆችም ከወራዊ ክፍያ በተጨማሪ በግል ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
የት/ቤቱ ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ጀመረ ቆጭቶ ከመጋቢት 16 ቀን 2017 ዓም ጀምሮ የት/ቤቱን አጠቃላይ ሁኔታና የሪፖርቱን ተዓማኒነት በመገምገም በግልፀኝነት ለወላጆችና ባለድረሻ አካላት እንዲቀርብ አድርገዋል። የቦርድ ሰብሳቢው በሠጡት ማጠቃለያ ሀሳብ መጨረሻ ላይ ከወላጆችና ከባለድርሻ አካላት ከተነሱ ሀሳቦችን የተገነዘብነው በአወንታዊነት በጋራ ት/ቤቱን ወደፊት እናሸጋግራለን፣ የሚያስፈልገውን መስዋዕትነት በጋራ እንከፍላለን የሚል ቃል ኪዳን ሲሆን ከ2012 ዓም እስካሁን የመጣንበት ሁኔታ እጅግ ፈታኝና ት/ቤቱን የሚያስዘጉ ቢሆንም በይሉኝታ ተሸብበን መከራችንን በውስጣችን ይዘን መልካም ውጤት ብቻ አሳይተን ዞር ለማለት ያሰብን ሲሆን ዛሬ ግን ድንገት ወላጆች የገቡት ቃል ኪዳን ሳናስበው ያንን ሁሉ የመከራና የኪሳራ ጊዜ ረስተን ከሕዝቡ ጋር የወደፊቱን ተስፋ አሻግሬን እንዲናይ ያደረገ ነው ካሉ በኋላ አርዮ አካዳሚ በትውልዶች ቅብብሎሽ ለዘላለም ይቀጥላል በማለት ቃል በመግባት ይህንን ተረድተው በዋናነት የማሻ ከተማ አስተዳደር ኬንቲባና ማዘጋጃ ቤት ፈጣን መልስ በተግባር እንደሚሠጡ እምነታችን የፀና ነው ብለዋል።
በዕውቀትና በመልካም ሥነምግባር የታነፀ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ የመቅረጽ ራዕያችን በጋራ ጥረት ይሳካል።
አርዮ አካዳሚ
መጋቢት 19 ቀን 2017 ዓም
ማሻ