26/01/2023
ከ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ጋር በተያያዘ ምን አዲስ ነገር አለ ?
እጅግ በጣም በርካታ ወላጆች እና ተማሪዎች " የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ጉዳይ ከምን ደረሰ ? ይፋ የሚደረግበት ቀን ታውቋል ወይ ? " የሚሉ ጥያቄዎችን ካለፈው ሰኞ / ጥር 15 ጀምሮ በቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መልዕክት መቀበያ ላይ እያስቀመጡ ይገኛሉ።
የተቀመጡት የወላጆች እና ተማሪዎች ጥያቄ ብዙ መሆናቸውን ተከትሎ እና ተማሪዎችም ያለመደበኛ ትምህርት እያሳለፉ ያሉት ቀናት እጨመረ በመሆኑ ከትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ለማግኘት ጥረት አድርገናል።
ባለፈው ሳምንት ላይ የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራር " የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መቼ ይፋ ይደረጋል ? " ብለን ጠይቀናቸው ፤ ከጥር 15 ጀምሮ ባሉት ቀናት የሚል ምላሽ ሰጥተውን ነበር።
ዛሬ ይህንኑ ጥያቄ በድጋሚ ለትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራር አቅርበን ውጤት ይፋ ማድረጊያ ቀኑ " ከነገ እንደማያልፍ " በዚገይ ደግሞ እስከ ቅዳሜ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመውናል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የተሰጠውን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከ930 ሺ በላይ ተማሪዎች መውሰዳቸው መገለፁ የሚዘነጋ አይደለም።