17/07/2026
ሰዎች ለምን ሁለት ዓይነት (የሕፃናት ማለት የወተት እና የአዋቂ) ጥርስ ይኖራቸዋል?
የልጅ የራስ ቅል (የጭንቅላት አጥንት) አብዛኞቹ ወላጆች መቼም የማይመለከቱትን ምስጢር ይዟል።
የሕፃናት መንጋጋ የአዋቂ ጥርሶች ብዛትን ሊይዝ ስለማይችል የሰው ልጆች ሁለት ዓይነት ጥርስ ይኖራቸዋል። ከዚህም በላይ ሁለተኛው የአዋቂ ጥርስ አደጋዎች እና ደካማ የጥርስ ንፅህና አጠባበቅ በረጅም ጊዜ ውስጥ የሚያስከትሏቸው መዘዞች ን መቋቋም የሚችሉ እንዲሆኑ ይረዳል። ጥርስ መፈጠር የሚጀምረው ከተፀነሰ በሰባተኛው ሳምንት ውስጥ ነው። ከተፀነሰ ዘጠኝ ሳምንት አካባቢ እያንዳንዱ እምቡጥ (bud) ወደ ቋሚ ጥርስ ወደሚያድግ ትንሽ እና ተኝቶ ወደ ሚቆይ የጥርስ እምቡጥ፣ እንዲሁም ወደ ሕፃን ጥርስ ወደሚያድግ ትልቅ ደወል-መሳይ ጥርስ ይከፈላል። በመቀጠልም መንጋጋው አጥንት በሕፃኑ እና በቋሚ ጥርሱ ዙሪያ በመፈጠር በቦታቸው ያቆያቸዋል። ከዚያም በጥርስ ውስጥ የዴንቲን (dentin) ንብርብሮችን በመጨመር እና በጥርስ ውጫዊ ክፍል ላይ ኤናሜል (enamel) በመጨመር ጥርሱ ያድጋል። በመጨረሻም የሕፃናት ጥርሶች ከተወለዱ በግምት ስድስት ወራት ጀምሮ ከድድ ውስጥ ብቅ ማለት ይጀምራሉ።
የወተት ጥርሶች ስር፣ ሙሉ ሌላ ሁለተኛ የጥርስ ስብስብ በመንጋጋ አጥንት ውስጥ በዝምታ ቅርፅ እየያዘ ይገኛል። እነዚህ ቋሚ ጥርሶች ከድድ ውስጥ ፈልቀው ከመውጣታቸው ከዓመታት በፊት አክሊላቸውን (የላይኛውን ክፍላቸውን) መገንባት ይጀምራሉ፤ ይህም ተራቸውን እንደሚጠብቅ ድብቅ ንብርብር በላይኛውና በታችኛው መንጋጋ አጥንት ውስጥ ተሸጉጠው ይቆያሉ።
አብዛኛዎቹ ሕፃናት በ2 ዓመታቸው 20 የሆኑትን የሕፃናት ጥርሶቻቸውን ያሟላሉ። ቋሚ ጥርሶች በመንጋጋው አጥንት ውስጥ በመጀመሪያው የልጅነት ጊዜ ውስጥ ይመሰረታሉ። ሕፃናት የወተት ጥርሳቸውን ሲለውጡ (ሲነቅሉ) የሚወድቀው አክሊሉ (crown) እና የስሩ የላይኛው ክፍል ብቻ ነው። ቋሚ ጥርሶች የሕፃናት ጥርሶች ይጠቀሙበት የነበረውን ተመሳሳይ የደም ቧንቧ እና የአጥንት ቀዳዳ (socket) ይጠቀማሉ።
አንድ ልጅ ከስድስት እስከ አስራ ሁለት ዓመት ዕድሜ ላይ ሲደርስ፣ የኤክስሬይ (X-ray) ምስሎች እና የአካል መዋቅር ሞዴሎች አንድ አስደናቂ እይታን ይፋ ያደርጋሉ፡ እሱም በአንድ ትንሽ የጭንቅላት አጥንት ውስጥ በአንድ ጊዜ ተፋፍገው የሚገኙ ሁለት ሙሉ የጥርስ ስብስቦችን ነው። የአዋቂ ጥርሶች አክሊሎች ቀድመው የተገነቡ ቢሆኑም፣ ስሮቻቸው ግን አሁንም በመፈጠር ላይ ናቸው፤ ይህ ሂደት ጥርሱ በመጨረሻ ፈንድቶ ወደ አፍ ውስጥ ከወጣ በኋላም እንኳ ይቀጥላል።ይህ በሰው ልጅ እድገት ውስጥ ካሉ በጣም አስደናቂ ክስተቶች አንዱ ነው። ተፈጥሮ የሚቀጥለውን ትውልድ ጥርስ መገንባት ለመጀመር የወተት ጥርሶች እስኪረግፉ ድረስ አትጠብቅም። ምትኮቹን አስቀድማ፣ በደረጃ በደረጃ፣ እኛ ፈጽሞ ማየት በማንችለው አጥንት ውስጥ ትገነባቸዋለች።በሚቀጥለው ጊዜ ልጅዎ ጥርስ ሲያወልቅ ይህንን ያስታውሱ፡ እሱን የሚተካው ጥርስ ለዓመታት ተደብቆ ውስጥ ሲያድግ የቆየ ነው።
Sources
Sadler, Thomas W. Medical Embyrology. 14th ed., 2019.
Moore, Keith, TVN Persaud, and Mark G. Torchia. The Developing Human, Clinically Oriented Embryology. 10th ed. Philadelphia: Elsevier, 2016.