22/05/2026
የክልላዊ እና ብሔራዊ ፈተናዎች ዝግጅት ተጠናቀቀ፤ የተማሪዎች መረጃ እና የፈተና ጣቢያዎች ይፋ መሆን
ጋምቤላ — በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የሚሰጡትን የ6ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና እና የ8ኛ ብሄራዊ ፈተና በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ የሚያስችሉ የቅድመ-ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። ከፈተናው የጊዜ ሰሌዳ፣ ከተማሪዎች ምዝገባ እና ከፈተና ጣቢያዎች ጋር የተያያዙ ዝርዝር መረጃዎችም ይፋ ሆነዋል።
1. የፈተና ጊዜ ሰሌዳ (Schedule)
ፈተናዎቹ በአገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ በተቀመጠው ወጥ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የሚሰጡ ሲሆን፣ ተማሪዎች ካሁኑ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ጥሪ ቀርቧል።
የ6ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና: ከሰኔ 08 እስከ ሰኔ 09 ቀን 2018 ዓ.ም ባሉት 2 ተከታታይ ቀናት ውስጥ ይሰጣል።
የ8ኛ ክፍል ፈተና: ከሰኔ 11 እስከ ሰኔ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ባሉት ቀናት ውስጥ የሚሰጥ ይሆናል።
ማሳሰቢያ: ተማሪዎች በፈተናው እለት ጠዋት በ2:30 ሰዓት ላይ በየፈተና ክፍሎቻቸው መገኘት እንዳለባቸውና ፈተናው በ3:00 ሰዓት በይፋ እንደሚጀምር ተገልጿል።
2. የተማሪዎች መረጃ እና ዲጂታል ምዝገባ
በዘንድሮው የፈተና ዝግጅት ላይ የተማሪዎችን መረጃ ጥራት ለመጠበቅ እና ማጭበርበሮችን ለመከላከል ዘመናዊ የዲጂታል የመረጃ ሥርዓት ጥቅም ላይ ውሏል።
የተማሪዎች ብዛት: ተፈታኝ የ6ኛ ክፍል ወንድ: 9,351
ሴት: 7,473 ድምር: 16,824 ሲሆኑ
የ8ኛ ክፍል ፈተናውን ለመውሰድ ወንድ: 11,093
ሴት: 8,327 ድምር: 19,420 የሚቆጠሩ ተማሪዎች መሆናቸው ታውቋል።
የመለያ ቁጥር (Admission Card): እያንዳንዱ ተማሪ ፎቶግራፉን እና ሙሉ መረጃውን የያዘ ዲጂታል የፈተና መግቢያ ካርድ ለሁሉም ወረዳዎች በሲስተም መተግበሪያው ለተማሪዎች እንዲደርስ ተደርጓል።
የመረጃ ማጣራት: የተማሪዎች ስም፣ እድሜ እና የትምህርት ክፍል ስህተቶች እንዳይኖሩ የወረዳ ፈተና ክፍል ከትምህርት ቤቶች ጋር በመቀናጀት አስቀድሞ የማጣራት ስራ ተከናውኗል።
3. የፈተና ጣቢያዎች
ፈተናው ሙሉ በሙሉ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ታማኝ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ የ6ኛ ክፍል 270 እና የ8ኛ ክፍል
217 የፈተና ጣቢያዎች ተዘጋጅተዋል
መልዕክት
ክልል ትምህርት ቢሮም በስተመጨረሻ ባስተላለፈው መልዕክት፣ ወላጆች ለልጆቻቸው ምቹ የንባብ አካባቢ እንዲፈጥሩላቸው፣ ተማሪዎችም በተረበሸ ስሜት ሳይሆን በራስ መተማመን ለፈተናው እንዲዘጋጁ እና ከማንኛውም የፈተና ኩረጃ ድርጊት እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
ለሁሉም ተማሪዎች መልካም የፈተና ጊዜ እንዲሆን እንመኛለን!