29/05/2023
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን።
ግንቦት 21 አምላክን የወለደች ክብርት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በደብረ ምጥማቅ በስሟ በተሠራች ቤተ ክርስቲያን ጉልላት ላይ በብርሃን መርከብ ተቀምጣ በግልጽ የታየችበት ዕለት ነው፡፡
ደብረ ምጥማቅ
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በደብረ ምጥማቅ በስሟ በተሠራች ቤተ ክርስቲያን ጉልላት ላይ በግልጽ ስለመታየቷና ታላቅ ተአምር ስለማድረጓ፡- ጌታችን ወደ ምድረ ግብፅና ኢትዮጵያ በተሰደደ ጊዜ ከእመቤታችን፣ ከዮሴፍና ሰሎሜ ጋር ዛሬ ደብረ ምጥማቅ በሚባለው ቦታ ላይ አርፎ ነበር፡፡ ቦታውን ባርኮ ለድንግል እናቱ ‹‹ለዘለዓለም ያንቺ መገለጫ ይሁን›› ብሎ ቃልኪዳን ገብቶላት ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ደብረ ምጥማቅ ገዳም ተገድሞ የበርካታ መነኮሳት ቤት ከሆነ በኋላ እመቤታችን በልጇ ፈቃድ ግንቦት 21 ቀን አእላፍ መላእክትን ጻድቃን ሰማዕታትን አስከትላት በመሞጣት ለሕዝበ ክርስቲያኑም ለአሕዛብ ጭምር በመገለጥ ለ5 ቀናት በግልጽ ትታያቸው ነበር፡፡ ‹‹በዚህች ቀን በግብፅ አገር ደብረ ምጥማቅ በምትባል በተሰራች ቤተ ክርስቲያን ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ ያሉ ሰዎች ይሰበሰባሉ ከያገሩም ሁሉ ይመጣሉ፡፡ እነዚህም ሁሉ ሠቀላ ሠርተው ድንኳን ተክለው አጎበር ጥለው ይከትማሉ፡፡ ከ21 ቀን ጀምረው እስከ 25 ቀን ድረስ በፍጹም ደስታ በፍጹም ክብር የድንግልን በዓሏን ማክበር ይጀምራሉ፤ ድንግልም ከግንቦት 21 ቀን ጀምራ እስከ 25 ቀን ድረስ ሳታቋርጥ በነዚህ በ5ቱ ዕለታት ከመላእክት ከጻድቃን ከሰማዕታት ጋር ትገለጽላቸው ነበር፡፡ እነርሱም በፍጹም ክብር በፍጹም ደስታ በዓሏን ያከብራሉ፡፡ ክርስቲያኑም እስላሙም በገሃድ ተገልጻ ያዩዋት ነበር›› ይላል ተአምረ ማርያም፡፡
እመቤታችን በዙሪያዋ የመላእክት ሠራዊት መላእክት አለቆችም በየማዕረጋቸው ክንፋቸውን ዘርግተው ይቆማሉ፣ ይጋርዷታል፡፡ ሱራፌልም ማዕጠንታቸውን ይዘው ለንግሥናዋ ገናናነት ይሰግዳሉ፡፡ በየስግደታቸውም እንዲህ እያሉ ያመሰግኗታል፡- ‹‹አብ በሰማይ ሆኖ ተመለከተ እንደ አንቺ ያለ አላገኘም አንድ ልጁንም ልኮት እርሱም ከአንቺ ሰው ሆነ፡፡›› ሁለተኛም ሰማዕታት በየማዕረጋቸው ረቂቃን በሆኑ ፈረሶቻው ተቀምጠው እየመጡ መጀመሪያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአምባላይ ፈረሱ ወርዶ ይሰግድላታል፡፡ እንዲሁም ባልንጀሮቹ ሰማዕታት መጥተው ይሰግዱላታል፡፡ ከእርሱ በኋላ የሚመጣው በዱሪ ፈረስ የሚቀመጥ ቅዱስ መርቆሬዎስ ነው፡፡ ከዚህም በኋላ ሰማዕታት ሁሉ በመከታተል መጥተው ይሰግዱላታል፡፡ ዳግመኛም ደግሞ የጻድቃን አንድነታቸው መጥተው በፊቷ ሰግደው ይመላለሳሉ፡፡ ሄሮድስ ያስገደላቸው 144,000 ሺህ የቤተልሔም ሕጻናት ከዓለቃቸው ከቅዱስ ቂርቆስ ጋር መጥተው ይሰግዱላታል፡፡ በፊቷም እየዘለሉ አንዱ በአንዱ ላይ እየዘለለ በመተቃቀፍም ይጫወታሉ፡፡ በደብረ ምጥማቅ የተሰበሰቡትም ሁሉ ክርስቲያኑም እስላሙም ሁሉ ይህንን በግልጽ በተመለከቱ ጊዜ እጅግ ሐሴት ያደርጋሉ፡፡ እናት አባት የሞቱበት ቢኖር ወይም ከዘመዶቹም ቢሆን ወላዲተ አምላክን ‹‹እመቤቴ ሆይ ዕገሌን… አሳይኝ›› ብሎ በሚለምናት ጊዜ ቀድሞ በነበረበት መልኩ ያንጊዜ ታመጣዋለች፡፡ የብርሃን እናቱ እመቤታችን መሐመድንም ከሲኦል አውጥታ አሳይታቸዋለች፡፡ (መጨረሻ ላይ በደንብ እናየዋለን)
ደግሞም ሕዝቡ ሁሉ መሀረባቸውን ወደላይ ይወረውሩላታል እመቤታችንም የወደደችውን በእጇ ተቀብላ መልሳ ትጥልላቸዋለች፤ እነርሱም ለበረከት በየጥቂቱ ይካፈሉታል፡፡ በእንዲህም ዓይነት ሁኔታ 5 ቀን ሙሉ እስላሙም ክርስቲያኑም አረማውያኑም በገሃድ ተመለከቷት፡፡ ወደቤታቸውም ለመሄድ ሲሹ በፊቷ ሰግደው ይሰናበቷታል፤ እመቤታችንም ትባርካቸውና ሄደው እንደገና ይመለሳሉ፡፡ 5ቱ ዕለታትም ሲፈጸሙ ሕዝቡ እመቤታችንን በዕንባ ይሰናበቷታል፡፡ እመ ብርሃንም በብርሃን መስቀል ባርካቸው ከቅዱሳኑ ጋር ዐርጋለች፡፡
አምላክን የወለደች ክብርት እመቤታችን በደብረ ምጥማቅ መሐመድንም ከሲኦል አውጥታ እንዳሳየቻቸውና የአሕዛብንም የሐሰት መንፈስ እንዳጋለጠችው ተአምሯ ላይ ተጽፏል፡፡ እመቤታችን በረድኤትና በቸርነት በደብረ ምጥማቅ ተገልጻላቸው ሳለ የሚያምነው ክርስቲያኑም የማያምነው አሕዛቡም ሁሉም በገሃድ ያዩዋት ነበር፡፡ ጥያቄያቸውንም ሁሉ ታሟላላቸው ነበር፡፡ ግማሹ ዳዊትን አሳይን ሲሏት ከነበገናው አምጥታ ታሳያቸዋለች፤ ዕዝራን አሳይን ሲሏት ከነመሰንቆው አምጥታ ታሳያቸዋለች፤ጊዮርጊስን አሳይን ሲሏት ከነፀዓዳ ፈረሱ አምጥታ ታሳያቸዋለች… ሁሉንም እንደየጥያቄዎቻቸው ታስተናግዳቸው ነበር፡፡ ከመካከላቸውም አንዱ ካህን ‹‹እመቤቴ ሆይ! እነዚህ ሙስሊሞች ‹መሐመድ ነቢይ ነው› እያሉ ይዘበዝቡናልና እስቲ እርሱን አሳይን›› ይሏታል፡፡ ያን ጊዜም የብርሃን እናቱ እመቤታችን መሐመድን ከሲኦል አውጥታ አሳይታቸዋለች፡፡ እርሱም እንደከሰል ጠቁሮ በግመል ላይ ተቀምጦ ነበር፡፡ የመሐመድ ብልት ከግመል አንገት ጋር በእሳት ሰንሰለት ታስሮ እርሱም ከሰል መስሎ በግመሏ ላይ ተቀምጦ አጋንንት ከፊት ከኋላ፣ ከቀኝ ከግራ በእሳት አለንጋ እየገረፉትና እያዳፉት ከሲኦል አውጥተው የተሰበሰበው ሕዝብ ሁሉ እንዲመለከተው አደረጉት፡፡ የተሰበሰበው ሕዝበ ክርስቲያንም እመቤታችን ባሳየቻቸው ተአምር እጅግ ተደንቀው ለክብሯ እየሰገዱ በእንባ አመሰገኗት፡፡ በቦታው የነበሩ ሙስሊሞችም ወዲያው በክርስቶስና በድንግል እናቱ እንዳመኑ ተአምረ ማርያም ላይ በሰፊው ተጽፏል፡፡
አምላክን የወለደች ክብርት እመቤታችን ለ3 ቀናት ማለትም ከግንቦት 21-23 ድረስ በእንደዚህ ዓይነት መልኩ በደብረ ምጥማቅ በገሃድ ተገልጻ ታላቅ ተአምር ያደረገችበት ዕለት ነው፡፡ ለተሰበሰቡ ምእመናን ሁሉ በግልጽ በመታየት ትነጋገራቸው እንደነበረ ሁሉ ዛሬም በረድኤት በቸርነቷ ልጆቿ ትጎበኘን ዘንድ መልካም ፈቃዷ ይሁንልን። ልጇ አምላካችን በአማላጅነቷ ይማረን፡፡
* ሌሎች በዕለቱ የሚታሰቡ ቅዱሳን
ዳግመኛም በዚኽች ዕለት እንግዶች መጥተውባቸው ሳለ ርግቦችን አብስለው ምግብ ሠርተው ቢያቀረቡላቸው እንግዶቹ እምቢ ቢሏቸው የርግቦቹ ሥጋ ላይ አማትበው እፍ ብለው ርግቦቹን ክንፍ አውጥተው እንዲበሩ ያደረጓቸው ሶርያዊው አቡነ አሮን ዕረፍታቸው ነው፡፡
ገሃነመ እሳት በማሰብ በዝሙትም ላለመውደቅ ብለው ሰውነታቸውን የሚነድ እሳት ውስጥ በመጨመር ዘማዊቷን ሴት ለንስሓ ያበቋት አቡነ መርትያኖስ ዕረፍታቸው ነው፡፡
* ነቢዩ ቅዱስ አሞጽ መታሰቢያ በዓሉ ነው፡፡
* አቡነ አሮን ሶርያዊ
በዚችም ዕለት ከልጅነቱ ጀምሮ ተጋዳይ የሆነ አባ አሮን ሶርያዊ አረፈ።
ፈውስ የመስጠትና ታላላቅ ተአምራትን የማድረግ ሀብት የተሰጣቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ እንግዶች የሆኑ መነኮሳት ወደ እሳቸው በመጡ ሰዓት ርግቦችን አብስለው ይመግቡ ነበርና አንድ ቀን እንዲሁ አድርገው ርግቦችን አብስለው ለእንግዶቹ መነኮሳት ቢያቀርቡላቸው መነኮሳቱ ግን "ሥጋ አንበላም" አሏቸው፡፡ አቡነ አሮንም አብስለው ሠርተው ባቀረቡት የርግቦቹ ሥጋ ላይ አማትበው እፍ ብለው ርግቦቹን ክንፍ አውጥተው እንዲበሩ አድርገዋቸዋል፡፡
አቡነ አሮን በተራራ ላይ ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ውኃው ከተራራው ይርቅ ነበርና አባታችን በመስቀል ምልክት አማትበው ውኃውን ስበው ከተራራው ላይ አውጥተውታል፡፡ ሰይጣን ወደ በዓታቸው ተመሳስሎ ገብቶ በላያቸው ላይ ‹‹እጅግ ትልቅ ድንጋይ ጥዬ እገድላቸዋለሁ›› ብሎ አስቦ በዓታቸው ውስጥ ገባ፡፡ እርሳቸውም አስቀድመው ዐውቀውት ሳለ ግን እንዳላወቁ ሆነው ‹‹እንግዳ ነህን ና ወደ ውስጥ ግባ›› ብለው ካስገቡት በኋላ በእሳቸው ላይ እጥላዋለሁ ብሎ ያሰበውን እጅግ ትልቅ ድንጋይ በላዩ ላይ ጫኑበትና ዙሪያን ደፍነው እንዳይወጣ በመስቀል አማትበው ዘግተውበት ገድለውታል፡፡ አባታችን አገረ ገዥው መሞቱን ሰምተው ሄደው በጸሎታቸው ከሞት አስነሥተውታል፡፡ ውኃ የሚቀዱባቸው አራት ትላልቅ እንስራዎችን በአንበሳ እየጫኑ 10 ዓመት ገዳማትን አገልግለዋል፡፡ ጻድቁ በመጨረሻ ከጌታችን ታላቅ ቃልኪዳን ተቀብለው ግንቦት 21 በታላቅ ክብር ዐርፈዋል፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበረች ጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
* ቅዱስ አባ መርትያኖስ
ይህም ታላቅ ጻዲቅ ከልጅነቱ ጀምሮ በቅድስና ሕይወት ያጌጠ ነበር፡፡ መንኩሶ ሐመረ ኖኅ ወደምትባል ገዳም ገብቶ በታላቅ ተጋድሎ እየተጋደለ 67 ዓመት ኖረ፡፡ ምግባር ሃይማኖቱ፣ ገድሉና ትሩፋቱ በቦታው ሁሉ በተሰማ ጊዜ እነሆ አንዲት በክፉ ሥራዋና በዝሙቷ የታወቀች ኃጢአተኛ አመንዝራ ሴት ቅድስናውን ሰማች፡፡ እርሷም መልኳ እጅግ ያማረ ነበር፡፡ ጽድቁንና ቅድስናውን በመናገር የሚያመሰግኑትን ሰዎችም እንዲህ አለቻቸው፡- ‹‹እናንተ ታመሰግኑታላችሁ እርሱ የሚኖረው በዱር ነው የሴት ፊት አይቶ አያውቅም እኔን ቢያይ ግን ድንግልናውን አጥፍቼ ቅድስናውን አረክስበታለሁ›› አለቻቸው፡፡ ቅድስናውን የሚያውቁት ሰዎችም በፍጹም እርሱን በፈተና መጣል እንደማትችል ነገሯት፡፡ በእነርሱና በዚህች ዘማ ሴት መካከል ክርክር በሆነ ጊዜ አባ መርትያኖስን ፈትናው በኃጢአት ከጣለችው ከፍተኛ ገንዘብ ሊሰጧት ተስማሙ፡፡
ከዚህም በኋላ ያች ዘማ ሴት የምንዝር ጌጦቿን ሰብስባ ተጋጊጣ ልብሶቿንና ሽቱዎቿን ይዛ እጅግ የሚያምረውን መልኳን ይበልጥ አስውባ ተከናንባ ወደ አባ መርትያኖስ በዓት አጠገብ ሄዳ ቆየች፡፡ ሲመሽላትም የበዓቱን ደጃፍ አንኳኩታ ‹‹አራዊት እንዲበሉኝ በውጭ አትተወኝ እኔ መጻተኛ ነኝና መንገድንም ተሳስቼ ወደዚህ ደረስኩ›› አለችው፡፡ አባ መርትያኖስም በልቡ አሰበ፡፡ ‹‹በውጭ ብተዋት አራዊት ይበሏታል ባስገባትም ስለእርሷ ጦር በእኔ ላይ ይነሳብኛል›› ብሎ አሰበ፡፡ ‹‹በአውሬ ከምትበላ አስገብቻት ፈተናውን ብቋቋም ይሻላል›› ብሎ አስገብቷት እርሱ ትቷት ፈቀቅ አለ፡፡ ከዚህም በኋላ እርሷ አብሯት እንዲተኛ ለማድረግ ስትል ‹‹ከዚህ ማንም አያየንም›› በማለት የዝሙትን ሀሳብ አቀረበችለት፡፡ አባ መርትያኖስም የሰይጣን ማጥመጃው እንደሆነች ዐውቆ ‹‹ትንሽ ታገሺኝ›› አላትና እንጨት ሰብስቦ ታላቅ እሳት አነደደና እያየችው እግሩን ከእሳቱ ውስጥ ጨመረው፡፡ ነፍሱንም ‹‹የሲኦልን እሳት የምትችይ ከሆንሽ እነሆ ኃጢአትን ሥሪ›› አላት፡፡ ያችም ዘማ ሴት ይህንን በተመለከተች ጊዜ እጅግ ደነገጠች፡፡ አባ መርትያኖስንም ከእሳቱ ውስጥ ጎትታ አወጣችው፡፡ ልቧም ወደ ንስሓ ተመለሰ፡፡ የምንዝር ጌጦቿንና ልብሶቿን ከላይዋ ላይ አውልቃ ጣለችና ለአባ መርትያኖስ ሰግዳ የነፍሷን መንገድ እንዲመራት ለመነችው፡፡ እርሱም የዓለም ፍላጎት ሁሉ ኃላፊ እንደሆነ ሲያስተምራት አደረ፡፡ በቅዱስ ወንጌል ላይ ‹‹ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንደሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኗል፡፡›› የሚለውን እየጠቀሰ አስተማራት፡፡ ያዕ 2፡4፡፡ የእግዚአብሔር ወዳጅ አለመሆን በሥጋም ሆነ በነፍስ እጅግ ትልቁ የሕይወት ኪሳራ ነው፤ የእግዚአብሔር ጠላት መሆን ግን ምንኛ የሚያስጨንቅ ነገር ነው! ዳግመኛም ጌታችንም ‹‹…ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም፡፡ ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል፡፡›› ያለውን እየጠቀሰ አስተማራት፡፡ ማር 8፡34-36፣ ማቴ 10፡39፣ 1ኛ ዮሐ 2፡16፡፡
ከዚህም በኋላ እርሷም ወደ ዓለም ላለመመለስ በፍጹም ልቡናዋ ቆርጣ ንስሓ ገባችና አባ መርትያኖስ ወደ ሴቶች ገዳም ወሰዳትና ለእመ ምኔቷ አደራ ሰጣት፡፡ ከዚህ በኋላ እርሷ በገድል ተጠምዳ እግዚአብሔርን እያገለገለች ደስ አሰኘችው፡፡ የመፈወስ ሀብትም አድሮባት ብዙ ሕመምተኞችን በጌታችን ስም የምትፈውስ ሆነች፡፡ እስከ ሽምግልናዋም ዕድሜ ድረስ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ስታገለግል ኖረች፡፡
አባ መርትያኖስም ሌላ ሴት እንዳትመጣበት ፈርቶ በባሕር መካከል ወዳለች ደሴት ገብቶ በዚያ ቢኖር በአንድ ወቅት መርከብ ተሰብራ አንዲት ሴት በመርከቧ ስባሪ ተንጠላጥላ ማዕበሉ እያናወጠ አባ መርትያኖስ ያለበት በዓት ድረስ ፈቃደ እግዚአብሔር አደረሳት፡፡ እርሱም እጅግ ደንግጦ እርሷንም እንዲሁ አስተምሮ አመንኩሶ ደሴቲቱን ለእርሷ ጥሎላት ወደ ሌላ ሀገር ሄደ፡፡ ከዚህም በኋላ በአንድ ቦታ እንዳይቀመጥ አስቦ በ108 የተለያዩ ሀገሮች እየዞረ በታላቅ ተጋድሎ የሚኖር ሆነ፡፡ የዕረፍቱም ጊዜ እንደቀረበ ዐውቆ በበዓቱ ውስጥ ራሱን እስረኛ አደረገ፡፡ ኤጲስቆጶሱንም አስጠርቶ ገድሉን ሁሉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ነገረው፡፡ ኤጲስቆጶሱንም ከጸጋው ገናናነት የተነሣ አደነቀ፡፡ ወደ እርሱ ከመምጣቱ በፊት የታዘዘ መልአክ ለኤጲስቆጶሱ ተገልጦለት ስለ አባ መርትያኖስ ሥጋ እንዲያስብ ነግሮት ነበርና፡፡ ጌታችንም ለአባ መርትያኖስ ቃልኪዳን ከገባለት በኋላ በሰላም ዐርፎ ኤጲስቆጶሱ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን ሰብስቦ በክብር ገንዞ ቀበረው፡፡ ከሥጋውም ታላላቅ ተአምራት ተፈጽመው ታዩ፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበረች ጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
ቅዱስ አሞጽ ነቢይ
በዚችም ቀን ከዐሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ አሞጽ ነቢይ መታሰቢያው ነው። አሞጽ ማለት "እግዚአብሔር ጽኑዓ ባሕርይ ነው: አንድም እግዚአብሔር ያጸናል::" ማለት ነው:: "ተወዳጅ ሰው" ተብሎም ይተረጐማል:: የነበረውም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በስምንት መቶ ዓመት ሲሆን አባቱ ቴና እናቱ ሜስታ ይባላሉ:: ትውልዱም ከነገደ ስምዖን ነው:: በትውፊት ይህ ነቢይ የነቢዩ ኢሳይያስ አባት ነው የሚሉ ቢኖሩም ሁለቱ አሞጾች የተለያዩ መሆናቸውን ሊቃውንት ይናገራሉ::
ይህ ዕውነተኛ ነቢይ በእስራኤል ነገሥታት በኢዮአስና በኦዝያ ዘመን አስተማረ የእስራኤልንም ልጆች የእስራኤልንና የይሁዳንም ነገሥታት ይገሥጻቸው ነበር።
ስለ ክብር ባለቤት ስለ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ ስለመቀበሉ በዚያችም ቀን ስለ ፀሐይ መጨለም ከዚያም በኋላ እስራኤልን ስለሚደርስባቸው መከራ፣ ኀዘን፣ ልቅሶ፣ ረድኤትም እንደሚአጡ፣ የእግዚአብሔርንም ቃል መስማትን ከማጣት የተነሣ እንደሚራቡና እንደሚጠሙ። በሀገሩ ሁሉ በአሕዛብም መካከል እንደሚበተኑ አሕዛብም እንደ አጃ ሸክሽከው እንደሚአጓልቧቸው ትንቢትን ተናገረ ትንቢቱም በላያቸው ተፈጸመ።
ቅዱሱ ነቢይ ወገኖቹን አብዝቶ ይገስጻቸው ነበር፤ ስለኃጢአታቸውና ስለ ክፉ ሥራቸው፣ ስለ ዘለፋቸው እነርሱ እንደ ገደሉት ተነገረ። የትንቢቱም ዘመን ከጌታችን ሥጋዌ በፊት በስምንት መቶ ዓመት ነው ። በረከቱ በሁላችንም ይደር።
ምንጭ፦ የግንቦት ❷❶ ስንክሳር