22/08/2026
በአርቲስት ኡስማዮ ሙሳ ህይወት ታሪክ ዙሪያ የተፃፈ መፅሐፍ ዛሬ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተመረቀ
የታዋቂውን አርቲስት ኡስማዮ ሙሳን የህይወት ታሪክ የሚያስቃኝ እና በአርቲስቱ የመጀመሪያ ልጅ አርቲስት ሳርቱ ኡስማዮ የተፃፈ መጽሐፍ የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራር እና ጥሪ የተደረገላቸው ታዋቂ አርቲስቶች በተገኙበት ተመርቋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ክቡር አቶ አብዲ ሙክታር በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ አርቲስት ኡስማዮ ለኦሮሞ የሙዚቃ እና ስነ ጥበብ እድገት ካበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ባልተናነሰ መልኩ ለህዝቦች እኩልነት፣ ነፃነት እና አንድነት ታሪክ የሚዘክረው አሻራ ያኖረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለህዝብ እኩለነት ዋጋ የከፈሉ ጀግኖች እንዲታወሱ የሚያደርገውን ጥረት ያደነቁት ክቡር አቶ አብዲ ሙክታር፣ ታላላቅ የማህበረሰቡ መሪዎች እና ፋና ወጊ የነፃነት ታጋዮች እንዲታወሱ ፣ አበርክቷቸው ለትውልድ አንዲተላለፍ ታሪካቸው በመፅሐፍ መልክ ተሰንዶ ለአንባቢወ መድረስ አለበት ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በበኩላቸው፣ በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ለትውልድ የሚተላለፉ ታሪኮችን በመፅሐፍ መልክ አዘጋጅቶ የማቅረብ ልምድ ያልዳበረ መሆኑን ገልፀው በአርቲስት ኡስማዮ ታሪክ ዙሪያ የተዘጋጀው መፅሐፍ በብዙ መልኩ አስተማሪ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡ መፅሐፉ በአርቲስቱ ሴት ልጅ መዘጋጀቱ ሴት ፀሐፊያንን ከማበረታታት ባሻገር የህዝብ ታሪክ፣ ባህል እና ቋንቋ እድገት ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የአርቲስት ኡስማዮ ሙሳ ልጅ እና የመፅሐፉ ፀሐፊ አርቲስት ሳርቱ ኡስማዮ በበኩሏ በመፅሐፉ መመረቅ የተሰማት ደስታ እና የወላጅ አባቷ በህይወት ኖሮ ይህንን የህዝብ ፍቅር ያለማየቱ የተደበላለቀ ስሜት እንደፈጠረባት ገልፃ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በዚህ ልክ ያማረ እና የወላጅ አባቷን ክብር የሚመጥን ታላቅ ዝግጅት በማዘጋጀቱ ምስጋና አቅርባለች፡፡
በመርሃ ግብሩ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ም/አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ከሪማ አሊ፣ የትምህርት ቢሮ ሀላፊ ሱልጣን አሊዩ፣ የገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር አብዱሰላም መሀመድ እና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡ በመድረኩ አርቲስት ጂሬኛ ሽፍራው እና ኬኦል ነጋሳ ተወዳጅ የሙዚቃ ስራዎቻቸውን ለታዳሚው አቅርበዋል፡፡
ድሬዳዋ፣ ነሐሴ 16፣ 2018 (የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት)
ለበለጠ መረጃ
👉 ድረ ገጽ: http://www.ddu.edu.et/
👉 ፌስቡክ: https://www.facebook.com/DDUniv/
👉 ቴሌግራም: https://t.me/DDUniv/
👉 ትዊተር፡ https://twitter.com/DDUniv/”