Dilla University

Dilla University

Share

It is an academic institution in Ethiopia.

01/06/2026

በስራ ፈጠራ ክህሎት ዙሪያ ለቤተመጻሕፍት ሰራተኞች ስልጠና ተሰጠ
============*************============

ዲ.ዩ: ግንቦት 21/2018 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)

የዲላ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ከስነ ውጤት ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር በስራ ፈጠራ ክህሎት ዙሪያ ለቤተ-መጻሕፍት ሰራተኞች ስልጠና ሰጥቷል።

በስልጠናው መክፈቻ ላይ የዲላ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ታምራት በየነ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ መንግስት በሀገር ደረጃ እያካሄደ ያለው መጠነ ሰፊ ለውጥ ስራዎች በትምህርት፣ በምርምርና በሌሎች ዘርፎች ላይ የተለያዩ ስራዎች እንዲከናወኑ እያስቻለ መሆኑን ገልጸው፣ በዩኒቨርሲቲውም በርካታ የልማትና የፈጠራ ስራዎች እየተካሄዱ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በቤተመጻሕፍት ሰራተኞች የተጀመረው የስራ ፈጠራ ክህሎት ስልጠና በቀጣይ ለሁሉም የአስተዳደር ሰራተኞችና ለመምህራን እንደሚሰጥ የገለጹት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፣ ስልጠናው ሰራተኞች በስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑና ራሳቸውን እንዲያበረታቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቁመው፣ ይህም ለሰራተኛውና ለተቋሙ ውጤታማነት ትልቅ ፋይዳ ያለው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

ምክትል ፕሬዘደንቱ በተጨማሪ እንደተናገሩት ሰራተኞች የወሰዱትን ስልጠና በተግባር ላይ እንዲያውሉ ለማስቻል ከዞን፣ ከከተማ፣ ከክልልና ከፌዴራል ተቋማት ጋር በመተባበር የንግድ ፈጠራ ስራዎችን የሚደግፉ አሰራሮች እንደሚመቻቹ ገልፀው፣ ይህም ሰራተኞች የራሳቸውን ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ የተቋሙንም ውጤታማነት ለማሳደግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ የስነ ውጤት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መምህር አብይ ረጋሳ በበኩላቸው፣ ስልጠናው ተማሪዎችንና የተቋሙን ሰራተኞች በፈጠራ አስተሳሰብ ለማበረታታት ያለመ መሆኑን ገልጸው፣ ሰራተኞች ከመደበኛ የስራ ተግባራቸው በተጨማሪ አዳዲስ የንግድ እድሎችን በመለየት የግል ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ የሚያስችል እውቀትና ክህሎት ለማስጨበጥ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ አያይዘውም ስልጠናው ለሁሉም የተቋሙ ማህበረሰብ፣ ለተማሪዎች፣ ለአካዳሚክ እና ለአስተዳደር ዘርፍ ሰራተኞች በተለያዩ ይዘቶችና ጊዜያት ላይ እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ የቤተ መጻሕፍትና ኢንፎርሜሽን አገልግሎት ዳይሬክተር አስናቀ ሙሉዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ስልጠናው ለሁሉም ሰራተኞች የተዘጋጀና በስራ ፈጠራ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ገልጸው፣ ሁሉም ስልጠናውን በተገቢው ሁኔታ ተግባራዊ ካደረጉ ምርታማ እንደሚሆኑና ኢኮኖሚያቸውን እንደሚያሻሽሉ ተናግረዋል። በተጨማሪም ለሌሎችም የስራ እድል የሚፈጥር በመሆኑ ሰራተኞች ራሳቸውን አነሳስተው ወደ ስራ እንዲገቡ ያበረታታል ብለዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል ወ/ሮ በለጠች ወረታው በሰጡት አስተያየት፣ ስልጠናው ከውድቀት በኋላ ስኬት እንዳለ ግንዛቤ እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ገልጸው፣ ችግሮችን በጽናት በመቋቋም ወደ ስኬት መድረስ እንደሚቻል ጥሩ ግንዛቤ እንዳገኙ ተናግረዋል።

=== # # #===


30/05/2026

የ2018 ዓ/ም የአቅም ማሻሻያ ፈተና መስጫ የጊዜ ሰሌዳ

Photos from Dilla University's post 27/05/2026

የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ለፍሬሽማን እና ሪሜድያል ተማሪዎች ገለፃ አደረገ
============*************============

ዲ.ዩ: ግንቦት 19/2018ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ፍሬሽማን እና ሪሜድያል ፕሮግራም እየተከታተሉ ለሚገኙ ተማሪዎች አጠቃላይ ገለፃ አድርጓል።

በኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ልማት እንስቲትዩት ዳይሬክተር የሆኑት ኮለኔል በርሱፈቃድ ነጋሽ (ዶ/ር) እና በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ጉዳይ ዳይሬክተር የሆኑት ኮለኔል አድናን ከማል ለተማሪዎቹ ገለፃ አድርገዋል።

በመድረኩ ላይ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች እና ተማሪዎች በመሳተፍ የጋራ ውይይት አድርገዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ይመኑ ዳካ፣ በመድረኩ ላይ በመገኘት ገለፃ ያደረጉ የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችን አመስግነው፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲም በተለያዩ ዘርፎች ላይ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ ስለመሆኑ አንስተዋል።

መሠል የልምድ ልውውጥ ስራዎች ወደፊትም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የጠቆሙት አቶ ይመኑ፣ በተቋማት ላይ የሚሰሩ የምርምር ስራዎች ለሀገር ልማትና እድገት ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ፣ ልምዶችን መለዋወጥ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። በቴክኖሎጂው ላይ የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ የሚሰራቸው ስራዎች ለዲላ ዩኒቨርሲቲም ልምድ የሚሆኑ ስለመሆናቸውም አንስተዋል።

በኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ልማት እንስቲትዩት ዳይሬክተር የሆኑት ኮለኔል በርሱፈቃድ ነጋሽ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት፣ ዩኒቨርሲቲው ከምስረታው ጀምሮ ላለፉት በርካታ ዓመታት ለሀገር ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ዜጎችን ማፍራቱን ጠቁመው፣ አሁን ላይ ተቋሙን ከአፍሪካ ምርጥ 5 የመከላከያ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ለማድረግ ዓላማ ተይዞ መጠነ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የታጠቀ፣ ለተግባር ትምህርት ስርዓቱም የተሟሉ ላብራቶሪዎችን የያዘ ተቋም መሆኑን የገለፁት ኮሎኔል በርሱፍቃድ (ዶ/ር)፣ ብቃት ባላቸው አሰልጣኞች፣ ሀገር ወዳድ እና መልካም ስነ ምግባር የተላበሱ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ለተማሪዎች ገለፃ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ጉዳይ ዳይሬክተር የሆኑት ኮለኔል አድናን ከማል በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ በቁጥር ውስን የሆኑ ነገር ግን ልዩ ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን በትምህርት ሚኒስቴር መስፈርት መሠረት የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያመጡና የተቋሙን መስፈርቶች የሚያሟሉ ተማሪዎችን እንደሚቀበል ገልፀው፣ በዩኒቨርሲቲው የሚማሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ተከታትለው እንደጨረሱ በተለያዩ የተቋሙ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የስራ እድል እንደሚያገኙ አብራርተዋል።

የፈጠራ ችሎታ እና ክህሎት ያላቸው ተማሪዎች አስፈላጊውን ሁሉ ግብዓት በማግኘት ለሀገር የሚተርፍ የፈጠራ ውጤታቸው ግቡን እንዲመታ ብሎም መሬት ላይ እንዲወርድ አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው የገለፁት ኮሎኔል አድናን፣ አሁን ላይ በዩኒቨርሲቲው በርካታ የፈጠራ ውጤቶች በመሰራት ላይ እንደሚገኙና የተሰሩ የፈጠራ ስራዎችም ገበያውን እንዲቀላቀሉ እየተደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በዩኒቨርሲቲው ገብተው ህልማቸውን ማሳካት የሚፈልጉ ተማሪዎችም እድሉን እንዲጠቀሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በመድረኩ ከተማሪዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን፣ ተሳታፊ ተማሪዎች የተደረገላቸው ገለፃ እጅግ ግልጽ እንነበርና ዩኒቨርሲቲውን ለመቀላቀል ፍላጎት እንዳሳደረባቸው ገልፀዋል።

ገለፃው በዩኒቨርሲቲው ኦዳያኣ እና ሀሴዴላ ጊቢዎች ላይ የተደረገ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ሪሜድያል እና ፍሬሽማን ተማሪዎች ተሳትፈዋል።

=== # # #===


Photos from Dilla University's post 27/05/2026

እንኳን ለ1447ኛው የዒድ አል-ዓድሃ በዓል በሰላም አደረሳችሁ
===========**********===========

ዲ.ዩ: ግንቦት 18/2018ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ቶሎሳ ዳዲ እንኳን ለ1447ኛው የዒድ አል-ዓድሃ (አረፋ) በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን ገለፁ።

ፕሬዝዳንቱ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እና ለመላው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ የአስተዳደር ሰራተኞች እንዲሁም መምህራንና የአከባቢው ነዋሪዎች እንኳን አደረሳችሁ በማለት፣ በዓሉ የሠላም፣ የፍቅር እና የአንድነት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

ፕሬዝዳንቱ በመልዕክታቸው በዓሉን ስናከብር፣ ያለንን በማካፈል፣ አቅመ ደካማ ወገኖቻችንን በመርዳት እና ማዕድ በማጋራት ሊሆን ይገባል ያሉ ሲሆን፣ በዓሉን ያለ አንዳች ልዩነት በህብረት እና በፍቅር በማክበር ኢትዮጵያ አንድነታችንን የበለጠ የምናጠናክርበት እንዲሆንልን እመኛለሁ ብለዋል።

ዒድ ሙባረክ፣ መልካም በዓል!

=== # # #===


Photos from Dilla University's post 26/05/2026

ለዲላ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ እና ረዳት ፕሮፌሰሮች ስልጠና ተሰጠ
============***********=============

ዲ.ዩ፡ ግንቦት 18/2018 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)

በሶስተኛ ዲግሪ ፕሮግራም የምርምር ስራ ሱፐርቪዥን፣ ክትትልና ድጋፍ ዙሪያ ለዲላ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ እና ረዳት ፕሮፌሰሮች ስልጠና ተሰጠ።

በስልጠናው መክፈቻ ላይ የዲላ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ታምራት በየነ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ዓመታት በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ በርካታ ምሁራንን ማፍራት ችሏል። እንደ ሀገርና እንደ ተቋም እየተተገበሩ ያሉ ሪፎርሞችን ለማሳካት የምርምር ስራዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ገልጸው፣ ዩኒቨርሲቲው የተግባር ሳይንስ ተልዕኮውን የሚያሳኩ ብቁ ምሁራንን ለማፍራት የሚያግዝ እና ተጨማሪ እውቀትና ልምድ እንዲያገኙ በማሰብ ስልጠናው መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ትዝአለኝ ተስፋዬ እንደገለጹት፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች በዘርፉ ከፍተኛ እውቀትና ልምድ ያላቸውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህርንና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ካሳሁን አለሙን በመጋበዝ ለዲላ ዩኒቨርሲቲ ረዳትና ተባባሪ ፕሮፌሰሮች በምርምር ስራዎች ሱፐርቪዥን፣ ክትትልና ድጋፍ፣ የምርምር ፋይናንስ አፈላለግ፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነትና የትብብር ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ዙሪያ ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።

ስልጠናውን የሰጡት ፕሮፌሰር ካሳሁን አለሙ በበኩላቸው፣ የሶስተኛ ዲግሪ ፕሮግራም ምርምር ስራዎች ረዥም ጊዜ የሚወስዱና የማህበረሰብ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ ሚና ያላቸው በመሆናቸው ተከታታይ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸው፣ በዘርፉ ያላቸውን እውቀትና ተሞክሮ ለዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ማካፈላቸውን አስታውቀዋል።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ተባባሪ ፕሮፌሰር ግርማ ተንኮሉ በሰጡት አስተያየት፣ ስልጠናው በሶስተኛ ዲግሪ ፕሮግራም የሚማሩ ተማሪዎችን በምርምር ስራ ለመደገፍና ለመከታተል ተጨማሪ እውቀትና ልምድ ያገኙበት ጠቃሚ መድረክ መሆኑን ገልፀዋል።

ስልጠናው ለሶስት ተከታታይ ቀናት የተሰጠ ሲሆን፣ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል።

=== # # #===


Photos from Dilla University's post 26/05/2026

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ከመንግስት የሚሰጥ የበጀት ድጋፍ አፈጻጸም ረቂቅ ደንብን አጸደቀ።

(ግንቦት 18/2018 ዓ.ም) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 55ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ ለራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ከመንግስት የሚሰጥ የበጀት ድጋፍ አፈጻጸምን ለመደንገግ በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ በስፋት ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህም ምክር ቤቱ በረቂቅ ደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ፣ አስፈላጊ ግብአቶችን በማከል ደንቡ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል።

ደንቡ ለራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠውን የመንግስት የበጀት ድጋፍ በታወቀ የጥቅል በጀት ስርዓት ላይ በመመስረት፣ የፋይናንስ ተጠያቂነትን፣ ፍትሃዊነትን እና ውጤታማነትን ለማረጋገጥ ያለመ ሲሆን፣ ዩኒቨርሲቲዎች የራሳቸውን ወጪ በራሳቸው የመሸፈን አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲያሳድጉ ያግዛል።

በተጨማሪም፣ በተቋማቱ መካከል ተመጣጣኝ የመማርና ማስተማር ጥራት፣ የአገልግሎት ፍትሃዊነት እና ኃላፊነት የተሞላበት አሰራር እንዲጠናከር ያስችላል።
ምንጭ: Ministry Of Education

24/05/2026

መደመር አንቀጽ

ኢትዮጵያ በብዙ ማዕድናት የታደለች ብትሆንም፤ አብዛኛው የማዕድን ሀብት ገና ወደ ልማት አልተሸጋገረም። እንደ ታንታለም ያሉ የከበሩ ማዕድናት የምርት ጅማሬዎች አሉ። እንደ ወርቅ ባሉት ላይ ደግሞ በተወሰነ ደረጃ ጥሩ እንቅስቃሴ ጀምረናል። ሰፋፊ ሽፋን ያለባቸው እንደ ነዳጅና ፖታሽ ያሉ ሀብቶቻችን ገና ብዙ መሥራት የሚጠበቁብን ናቸው።

ሀገራችን ለነዳጅ ዘይት ግዢ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ታወጣለች። ለማዳበሪያ ዋነኛው ግብአት የሆነውን ፖታሽን በከፍተኛ ደረጃ ታቅፋ፣ ለማዳበሪያ ቢልዮን ዶላሮች ትከሰክሳለች። የተፈጥሮ ሀብታም፣ የልማት ድኻ መሆናችን ያስቆጫል። ተገድደን ሳይሆን ወደን ፈቅደን ድኻ የሆንን ይመስላል።

ሌላው የሀገራችንን የመልማት ዕምቅ ዐቅም የሚወስነው የኃይል ሀብታችን ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ትልቅ ኃይል የማመንጨት ዕምቅ ዐቅም አላት። ከዚህ ዕምቅ ዐቅም ውስጥ ከታዳሽ የኃይል ምንጮች ብቻ ከፍተኛ ኃይል ማመንጨት ትችላለች፤ ይህም ሀገራችንን በዚህ ረገድ ተመራጭ ያደርጋታል። ከዚህም ባለፈ ከነዳጅና ከጋዝ ተጨማሪ ኃይል የማመንጨት ዕድሎች አሏት።

የመደመር መንግሥት
ገጽ 51

Photos from Dilla University's post 23/05/2026

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ቶሎሳ ዳዲ (ዶ/ር) አዲሱ ሆስፒታል ላይ ጉብኝት አደረጉ
==========************==========

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ቶሎሳ ዳዲ አዲሱ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያ እና ሪፈራል ሆስፒታል እና በሀሴዴላ ጊቢ የሚገኙ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ጎብኝተዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር በፍቃዱ መኩሪያ አጠቃላይ ገለፃ አድርገውላቸዋል። የፍኒሽንግ ስራዎች በአብዛኛው መጠናቀቃቸውን በመግለጽ ቀሪ ውስን ስራዎችን ለማገባደድ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

አሁን ላይ ግንባታው 95 በመቶ መጠናቀቁን በመግለጽ ሆስፒታሉ የያዛቸውን አገልግሎቶች ተዘዋውረው አስጎብኝቷቸዋል።

የዩኒቨርሲቲው ማስተማሪያ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ትዝአለኝ ተስፋዬ ፕሮጀክቱ ማህበረሰቡም ጭምር በጉጉት የሚጠበቀው በመሆኑ ቀሪ ስራዎችን አጠናቆ ወደ ስራ ማስገባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ሆስፒታሉን ማስጨረስ ብቻ ሳይሆን የህክምና መሳሪያዎችን እና አስፈላጊ ግብዓቶችን በሚመለከት፣ የተለያዩ ተቋማትን በማስተባበር ማሟላት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ቶሎሳ ዳዲ በምልከታው ወቅት እንደተናገሩት፣ ሆስፒታሉ ያለበት ደረጃ እና የተሰራበት መንገድ ይበል የሚያሰኝ ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ ለአከባቢው ማህበረሰብም ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ በመሆኑ ይህንን አሻራ ያኖራችሁ፣ በዚህ ስራ ላይ የተሳተፋችሁ ወገኖች ልትኮሩ ይገባል ብለዋል።

በሀሴዴላ ጊቢ በግንባታ ላይ ያሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችንም የጎበኙት ፕሬዝዳንቱ፣ እጅግ በጣም በርካታ ሀብት እንዳለ ተገንዝበያለው ሲሉ ባዩት ነገር መደሰታቸውን ገልፀዋል። እዚያም እዚህም ያሉንን ሀብቶች በአግባቡ ከተጠቀምን የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት የማንችልበት ምክንያት አይኖርም ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ የተጀመሩትን ጅምር ስራዎች ለማስቀጠል እንደሚተጉ ገልፀዋል።

በምልከታው ላይ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት አባላት እንዲሁም የትምህርት ሚኒስቴር ተወካዮች ተሳትፈዋል።

=== # # #===


Photos from Dilla University's post 23/05/2026

በትምህርት ሚኒስቴር ለዩኒቨርሲቲው አዲስ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት መመደቡን ተከትሎ የስራ ርክክብ ተደረገ
============**************=============

ዲ.ዩ: ግንቦት 15/2018ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)

የቀድሞው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኤልያስ አለሙ እና አዲሱ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ቶሎሳ ዳዲ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት አባላት እና የትምህርት ሚኒስቴር ተወካዮች በተገኙበት የስራ ርክክብ አደርገዋል።

ከትምህርት ሚኒስቴር የርክክብ ስነ ስርዓቱን ለማከናወን የመጡት አቶ አብዶ ናስር የሪፎርም ስራዎች በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለፉት ጊዜያት ላይ ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል። የትምህርት ጥራት ችግርን ለመቅረፍ፣ ብሎም ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮች እንዲሰሩ ወደ ማህበረሰቡም እንዲሸጋገሩ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት።

ባለፉት ዓመታት ተቋማት ላይ የተሰሩ የሪፎርም ስራዎች ውጤት ስያመጡ መቆየታቸውን ያነሱት አቶ አብዶ፣ የቀድሞው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንትም በዩኒቨርሲቲው በርካታ አመርቂ ውጤቶችን ማምጣታቸውን እና በዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እውቅና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

አመራርነት የዱላ ቅብብሎሽ እንደመሆኑ፣ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት እና ሰራተኞች የተቋምን ቀጣይነት ከግምት በማስገባት በአንድነትና በትብብር መንፈስ መስራት ይኖርባቸዋል ሲሉ አቶ አብዶ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የቀድሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኤልያስ አለሙ በበኩላቸው፣ በነበራቸው የስራ ወቅቶች ላይ ከትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሰራተኞች ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

በመድረኩ ላይ የቀድሞው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት በዩኒቨርሲቲው ያሉ ዋና ዋና ተግባራትና ቀሪ ስራዎችን እንዲሁም ተግዳሮቶችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በተደረጉ የመምህራን እና አጠቃላይ ሰራተኞች ስብሰባ ላይ ከተነሱ ነጥቦች መካከል የሰራተኞች ድልድል፣ ውዝፍ የትርፍ ሰዓት ክፍያዎች፣ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን ጨምሮ በርካታ ስንቅ የሚሆኑ ግብዓቶች መገኘታቸውን ገልፀዋል። የሆስፒታል የአስተዳደር ሰራተኞች ድልድል እየተሰራበት ያለ ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል።

ከስርዓተ ትምህርት ክለሳ ስራ ጋር ተያይዞ ተቋሙ ግንባር ቀደም የሆነበት ደረጃ ላይ መድረሱንና የተማሪዎች ምደባ በትኩረት መስኩ አማካኝነት እየተደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ሌሎች የተጀመሩ ስራዎችን በተመለከተ የመውጫ ስትራቴጂ ሰነድን መጨረስ፣ ዓለም አቀፍ ትስስር እና ትብብሮችን ማጠናከር፣ አዲሱ ሆስፒታልን ማስመረቅና ወደ ስራ ማስገባት፣ የመምህራን መኖሪያ ቤት ችግርን መፍታት እና ሌሎችም በቀጣይ ትኩረት ተደርጎባቸው ቢሰሩ መልካም ናቸው በሚል አንስተዋል። አክለውም የኦዲት እና ሪፎርም ስራዎች፣ የራስ ገዝነት እና ገቢ ማመንጫ ጉዳዮች አዲሱ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት በትኩረት ቢሰሩባቸው በሚል ዶ/ር ኤልያስ አንስተዋል።

ከትምህርት ሚኒስቴር የመጡ አቶ በሱፍቃድ ሀይለማሪያም፣ በቀድሞው አመራር የተሰሩ በርካታ መልካም ስራዎች መኖራቸውንና መልካም ስራዎችን የማስቀጠል እንዲሁም ቀሪ ስራዎች የተባሉትን ደግሞ የቤት ስራ አርጎ በመውሰድ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በመጨረሻም አዲሱ የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት እና የቀድሞው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኤልያስ አለሙ መካከል የስራ ርክክብ ተደርጓል።

=== # # #===

Photos from Dilla University's post 23/05/2026

የዲላ ዩኒቨርሲቲ አዲሱ ፕሬዝዳንት ከዩኒቨርሲቲው ካውንስል ጋር የትውውቅ መርሃ ግብር አካሄዱ
============***********=============

ዲ.ዩ: ግንቦት 15/2018ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)

በትምህርት ሚኒስቴር ወደ ዲላ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡት አዲሱ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ቶሎሳ ዳዲ (ዶ/ር)፣ በዛሬው እለት የስራ ርክክብ በማድረግ ከዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት ጋርም ትውውቅ አድርገዋል።

በትውውቅ መርሃ ግብሩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የዲላ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ታምራት በየነ (ዶ/ር)፣ ወደ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ተቋማዊ የሽግግር ስርዓት ለመስራት ለመጡ የትምህርት ሚኒስቴር ልዑካን እና ለአዲሱ ፕሬዝዳንት እንኳን ወደ ዩኒቨርሲቲው በሰላም መጡ ብለዋል። የቀድሞ ፕሬዝዳንት ለሰሯቸው በርካታ ስራዎች ምስጋና አቅርበው፣ የተሳካ የስራ ዘመንን በመመኘት፣ ዲላ ዩኒቨርሲቲ የጀመራቸውን በጎ ተግባራት ከአዲሱ ፕሬዝዳንት ጋር አጠናክረው ለማስቀጠል ዝግጁ ስለመሆናቸውም ተናግረዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር ልዑክ አባል የሆኑት አቶ አብዶ ናስር በበኩላቸው፣ ትምህርት ሚኒስቴር ላለፉት አራት እና አምስት ዓመታት ዘረፈ ብዙ የሪፎርም ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፣ በዚህም መሰረት ዶ/ር ቶሎሳ ዳዲ አዲሱ የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ተደርገው መመደባቸውን ተናግረዋል።

ዶ/ር ቶሎሳ በስራ ልምዳቸው በጅማ ዩኒቨርሲቲ በፕላን ዳይሬክተርነት እንዲሁም በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ከምስረታው ጀምሮ በቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት እና በአስተዳደር ልማት ምክትል ፕሬዝዳትነት በሳል አመራርነትን በመስጠት በተቋሙ ለውጥ እንዲመጣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ መሪ እንደመሆናቸው፣ ባላቸው ልምድ በመታገዝ ዲላ ዩኒቨርሲቲን ወደተሻለ ደረጃ እንደሚያሻግሩ እምነታቸው መሆኑን በመግለፅ የተጀመሩ ሥራዎችን በቁርጠኝነት እንዲያስቀጥሉ አሳስበዋል።

አቶ አብዶ አያይዘውም፣ መላው የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ሰራተኞች ከአዲሱ ፕሬዝዳንት ጋር በመሆን ተቋሙን የበለጠ ተወዳዳሪ እንደምያደርጉ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኤልያስ አለሙም በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በተጨባጭ የሚታዩ በርካታ ለውጦችን ያመጡ መሪ እንደነበሩ ገልፀው፣ ለዚህም በተቋሙ ለሰጡት መልካም አመራር እንደ ትምህርት ሚኒስቴር የላቀ ምስጋናና አክብሮት እንዳላቸው አቶ አብዶ አያይዘው ተናግረዋል።

አዲሱ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ቶሎሳ ዳዲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በዩኒቨርሲቲው፣ በከተማ እና ዞን አስተዳደር ለተደረገላቸው ልዩ አቀባበል ምስጋና አቅርበው፣ በቀድሞ ፕሬዝዳንት የተከናወኑ ሥራዎችን ለማስቀጠል ብሎ በተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ከመላው ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እንዲሁም የአከባቢው አመራሮች ጋር በመሆን የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

ለዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላትም በአንድነት ተሰልፈን ተቋሙን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር በጋራ እንስራ ሲሉም አዲሱ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ቶሎሳ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከትምህርት ሚኒስቴር የመጡት አቶ በሱፍቃድ ሀይለማርያም በአንፃሩ፣ የዩኒቨርቲዎች የአመራርነት ምድባን በውድድር ለማድረግ ስነዶች ጭምር ተዘጋጅተው ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ አውስተው፣ በቀጣይ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ከአዲሱ ፕሬዝዳንት ጋር በመሆን ዩኒቨርሲቲው የሚታወቅበትን ጥራት ያለው የመማር ማስተማር ስራ በመስራት፣ ማህበረሰቡ የሚሻገርባቸውን የምርምር ስራዎችንም ወደፊት በማምጣት ጠንክረው እንዲሰሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኤልያስ አለሙ (ዶ/ር) በትውውቅ መርሃ ግብሩ እንደገለጹት፣ እንደ አንድ የዩኒቨርሲቲው አልሙናይ በዩኒቨርሲቲው ከተማሪነት አንስቶ እስከ አመራርነት ደረጃ ድረስ ማገልገል መቻል መታደል እንደሆነ ገልጸው፣ በዩኒቨርሲቲው በነበራቸው ቆይታ ከካውንስል አባላቱ ጋር አብረው በመስራታቸው ክብር እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።

በቀጣይ አዲሱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንትም ከዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ጋር በመሆን የተጀመሩ ስኬቶችን በማስቀጠል ተቋሙን የላቀ ደረጃ ደርሶ ማየት እንደሚመኙ ገልጸዋል።

በትውውቅ መርሃ ግብሩ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ካውንስል አባላት ለቀድሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኤልያስ አለሙ ላበረከቱት አስተዋጽዖ ምስጋና በማቅረብ ለአዲሱ ፕሬዝዳንት መልካሙ የስራ ጊዜን ተመኝተዋል።

=== # # #===


Want your school to be the top-listed School/college in Dilla?

Click here to claim your Sponsored Listing.

Location

Telephone

Address


Dilla