የደሴ ደብረ ቤቴል ቅድስት ሥላሴና ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል የቤተ አብርሃም ሰ/ት/ቤት ገጽ

  • Home
  • Ethiopia
  • Dessie
  • የደሴ ደብረ ቤቴል ቅድስት ሥላሴና ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል የቤተ አብርሃም ሰ/ት/ቤት ገጽ

የደሴ ደብረ ቤቴል ቅድስት ሥላሴና ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል የቤተ አብርሃም ሰ/ት/ቤት ገጽ መንፈሳዊ ገጽ its a spritual page...

የእመቤታችን በዓለ ዕርገትእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያረገችበት ዕለት ነሐሴ ዐሥራ ስድስት ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ይከበራልና እኛም ስለዕርገቷ እንዲህ እንዘክራለን፤…ሐዋርያት ከእመቤ...
21/08/2026

የእመቤታችን በዓለ ዕርገት
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያረገችበት ዕለት ነሐሴ ዐሥራ ስድስት ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ይከበራልና እኛም ስለዕርገቷ እንዲህ እንዘክራለን፤…
ሐዋርያት ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ዕረፍት በኋላ ከእነርሱ በመለየቷ ባዘኑበት ወቅት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠላቸው፤ እርሷን በሥጋ ያዩ ዘንድም ተስፋ ሰጣቸው፡፡
በዚያን ጊዜ ወንጌላዊ ዮሐንስ እስያ በሚባል አገር እያስተማረ በነበረበት በነሐሴ ወር ዐሥራ ስድስተኛ ቀን ተድላ ደስታ ወደአለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቀ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ካለበት ከዕፀ ሕይወት ዘንድ ተቀምጦ አየው፡፡ የንጽሕት እናቱንም ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው፤ እነርሱም ‹‹የንጽሕት እናቱን ሥጋ ታወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል›› አሏት፡፡ ያን ጊዜም ከዕፀ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ወጣ፡፡ ጌታችንም እንዲህ እያለ አረጋጋት፤ ‹‹የተወደድሽ የወለድሽኝ እናቴ ሆይ! ዘላለማዊ ወደ ሆነ መንግሥተ ሰማያት አሳርግሽ ዘንድ ነዪ፡፡›› ከዚያም በገነት ያሉ ዕፅዋት ሁሉም አዘነበሉ፤ መላእክት፣ የመላእክት አለቆች፣ ጻድቃን ሰማዕታትም እየሰገዱላትና ፈጽሞ እያመሰገኗት አሳረጓት፡፡ ቅዱስ ዳዊትም ‹‹ንግሥት እመቤታችን! ወርቀ ዘቦ ለብሳ ደርባ ደራርባ በቀኝህ ትቀመጣለች›› እያለ በበገና አመሰገናት፡፡

ሐዋርያትም ለዓመት ከቆዩ በኋላ የነሐሴ ወር በባተ ቀን ዮሐንስ ለሐዋርያቱ እንዲህ አላቸው፤ ‹‹አምላክን የወለደች የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት የተዘጋጀን አድርጎ ያሳየን ዘንድ ኑ! ይህን ሁለት ሱባዔ በጾም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንለምነው፤ በልጅዋ በወዳጅዋ ቀኝ ተቀምጣ አይተን በእርሷ ደስ እንዲለን፡፡›› ዮሐንስም እንዳላቸው በጾም በጸሎት ሱባዔ ያዙ፤ በነሐሴ ዐሥራ ስድስትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ሐዋርያት ወደ ሰማይ አወጣቸው፡፡ በታላቅ ክብር በተወደደ ልጇ ቀኝ ተቀምጣ፣ ከሥጋዋ ተዋሕዳ፣ ተነሥታ እመቤታችን ማርያምን አዩዋት፡፡ እጆቿንም ዘርግታ የከበሩ ሐዋርያትን ባረከቻቸው፤ በልባቸውም እጅግ ደስ አላቸው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በከበረ ሥጋውና ደሙ ላይ ሠራዔ ካህን ሆነ፡፡ እስጢፋኖስም አዘጋጀ፤ ዮሐንስም በመፍራት ቁሙ አለ፡፡ ሁሉም ሐዋርያት በመሰዊያው ዙሪያ ቆሙ፤ በዚያን ጊዜ ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ ደስታ ሆነ፡፡ ጌታችንም የቅዳሴውን ሥርዓት በፈጸመ ጊዜ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው፡፡
ከዚያም በኪሩቤልና በሱራፌል ሠረገላ ተቀምጣ በምታርግ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ እመቤታችን ማርያምን እንዲህ አላት፡፡ ‹‹በዚች ቀን የሆነ የዕርገትሽን መታሰቢያ በዓለም ውስጥ እንዲሰበኩ ልጆችሽ ሐዋርያትን እዘዣቸው፡፡ መታሰቢያሽን የሚያደርገውን ሁሉ ተጠብቆም በዚች ቀን ቅዱስ ቁርባን የሚቀበለውን ኃጢአቱን እደመስስለታለሁ፡፡ የእሳትን ሥቃይ ከቶ አያያትም፤ መታሰቢያሽን ለሚያደርግ ሁሉ፣ በዚች ቀን ለድኆች በስምሽ ለሚመጸውትም ቸርነቴ ትገናኘዋለች፤ ይህም ሥጋሽ ወደ ሰማይ ያረገበት ነው፡፡›› እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ክብር ይግባውና ጌታችንን እንዲህ አለቸው ‹‹ልጄ ሆይ! እነሆ በዓይኖቻቸውም አዩ፤ በጆሮዎቻቸውም ሰሙ፤ በእጆቻቸው ያዙ፤ ሌሎችም ታላላቅ ድንቆች ሥራዎችን አዩ፡፡›› እመቤታችንም ይህን ስትናገር ጌታችን ሰላምታ ሰጥቷቸው በታላቅ ደስታ ወደ ደብረ ዘይት ተመለሱ፡፡
የክርስቲያን ወገኖች ሆይ! እኛም በፍጹም ደስታ መታሰቢያዋን እናደርግ ዘንድ ይገባናል፡፡ እርሷ ስለ እኛ ወደተወደደ ልጅዋ ሁልጊዜ ትማልዳለችና፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ይምረን ዘንድ ፈቃዱ ይሁንልን! አሜን፡፡

ምንጭ፡-ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ

በዓለ ደብረ ታቦር እና ቡሄጌታችን ምሥጢረ መለኮቱን ለገለጠበት ለበዓለ ደብረ ታቦር እንኳን በሰላም አደረሰን!ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን...
19/08/2026

በዓለ ደብረ ታቦር እና ቡሄ
ጌታችን ምሥጢረ መለኮቱን ለገለጠበት ለበዓለ ደብረ ታቦር እንኳን በሰላም አደረሰን!

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን መግለጡን በማሰብ በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን በዓሉ በድምቀት ይከበራል፡፡ ይህ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ዘንድ ‹ቡሄ› በመባል ይታወቃል፡፡ ቡሄ ማለት ‹መላጣ፣ ገላጣ› ማለት ነው፡፡ በአገራችን ክረምቱ፣ ጭጋጉ፣ ደመናው ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት በዚሁ በዓል አካባቢ ስለ ኾነ በዓሉ ‹ቡሄ› ተብሎ ይጠራል፡፡ በዓለ ደብረ ታቦር ጌታችን ምሥጢረ መለኮቱን የገለጠበት፤ ብርሃን የታየበትና ድምፀ መለኮቱ የተሰማበ ዕለት ስለ ኾነ ‹የብርሃን› ወይም ‹የቡሄ› በዓል ይባላል፡፡ቡሄ ሲመጣ የክረምቱ ጨለማነት አልፎ ወደ ብርሃን፣ ወደ ጥቢ የሚያመራበት፤ ወደ መፀው የሚገባበት፤ ወገግታ የሚታይበት፤ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚሸጋገርበት ወቅት በመኾኑ ከቡሄ በኋላ የጠነከረ ክረምት አይኖርም፡፡ ‹‹ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት›› እንዲሉ፡፡ በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች የቡሄ ዕለት ማታ ምእመናን ችቦ ያበራሉ፡፡ ይህም በደብረ ታቦር ለታየው ብርሃነ መለኮት ምሳሌ ነው፡፡ ሕፃናቱ ይህ በዓል ከመድረሱ በፊት ቀደም ብለው ጅራፍ ሲገምዱና ሲያጮኹ (ሲያኖጉ) ይሰነብታሉ፡፡ እናቶችም ለዚህ በዓል የሚኾን ዳቦ ለመጋገር ስንዴያቸውን ሲያጥቡ፣ ሲፈትጉ ይሰነብታሉ፡፡ በበዓሉ ዋዜማ (ነሐሴ ፲፪ ቀን) ሕፃናት በየቤቱ እየዞሩ ‹‹ቡሄ ና በሉ፤ ቡሄ በሉ፡፡ ቡሄ መጣ፤ ያ መላጣ፤ ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ …›› እያሉ ይጫወታሉ፡፡ በዚህ ጊዜ እናቶች ካዘጋጁት ዳቦ እያነሡ ይሰጧቸዋል፡፡ ሕፃናቱ ‹ቡሄ› የሚሉትም ዳቦውን ነው፡፡ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት ዕለት እረኞች ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር፡፡ የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጥተዋል፡፡ ‹ቡሄ› ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና በበዓሉ ችቦ የሚበራውም ከዚህ ታሪክ በመነሣት ነው፡፡ ለክርስትና ልጅ፣ ለአማች፣ ለምራት፣ ለዘመድ አዝማድ ዅሉ የቡሄ ዳቦ ይሰጣል፡፡ ልጆችም ዳቧቸውን እየገመጡ ጅራፍ ሲገርፉ ይውላሉ፡፡ የጅራፉ መጮኽ የድምፀ መለኮት ምሳሌ ሲኾን፣ ጅራፉ ሲጮኽ ማስደንገጡም ነቢያትና ሐዋርያት በድምፀ መለኮት መደንገጣቸውንና መውደቃቸውን ያስታውሳል፡፡መምህረ ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱን ተማሪዎቹን ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ በደብረ ታቦር ምሥጢር መግለጡን በማስታዎስ የአብነት ተማሪዎች ከመምህራቸው ጋር በመኾን በዓለ ደብረ ታቦርን (ቡሄን) ያከብራሉ፤ ስሙን ይጠራሉ፡፡ የአብነት ተማሪዎች ‹‹ስለ ደብረ ታቦር›› እያሉ እኽል ከምእመናን በመለመንና ገንዘብ በማዋጣት ጠላውን ጠምቀው፣ ዳቦውን ጋግረው፣ ቆሎውን ቆልተው ለደብረ ታቦር ዕለት ሊያስቀድሱ የመጡትን ምእመናን በመጋበዝና እርስበርስ በመገባበዝ፣ እንደዚሁም ቅኔ በማበርከት በዓለ ደብረ ታቦርን በታላቅ ድምቀት ያከብራሉ፡፡ ይህም እስከ አሁን ድረስ በአብነት ትምህርት ቤቶች የሚሠራበት ነባር ትውፊት ነው፡፡ነገር ግን በአንድ አካባቢዎች በተለይ በከተማ ዙሪያ በዓለ ደብረ ታቦር (ቡሄ) ሃይማኖታዊ ትውፊቱን የለቀቀ ይመስላል፡፡ ለዚህም ልጆች የሚጫወቱበት መዝሙር ግጥሙና ዜማው ዓለማዊ መልእክት የሚበዛበት መኾኑ፤ በወቅቱ ችቦ ከማብራት ይልቅ ርችት መተኮሱና በየመጠጥ ቤቱ እየሰከሩ መጮኹ፤ ወዘተ. የበዓሉን መንፈሳዊ ትውፊት ከሚያደበዝዙ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም በዚህ በዓል ገንዘብ ለመሰብሰብ ብቻ የሚሽቀዳደሙ ነገር ግን የበዓሉን ታሪካዊ አመጣጥ የማያዉቁ ልጆችም ጥቂቶች አይደሉም፡፡ስለዚህ ወላጆች ለልጆቻቸው የበዓለ ደብረ ታቦርን መንፈሳዊነት፣ የመዝሙሮቹን ያሬዳዊነትና አከባበሩን ከቤተ ክርስቲያን መምህራን በመጠየቅ ማስተማር፤ ልጆችም ከወላጆች ወይም ከመምህራን በመጠየቅ የበዓሉን አከባበር መረዳትና የዚህን በዓል መንፈሳዊ ትውፊት ሳይበረዝ ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባቸዋል፡፡ ‹‹ድምፅህን ሰማና በብሩህ ደመና፤ የቡሄው ብርሃን ለእኛ በራልን …›› የሚለውንና ይህን የሚመስሉ መንፈሳውያን መዝሙራትን እየዘመሩ በየቤቱ በመዘዋወር የሚያገኙትን ዳቦና ገንዘብ ለነዳያንና ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡ ልጆችንም ማበረታታትና አርአያነታቸውን መከተል ይኖርብናል፡፡መልካም በዓል ይኹንልን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡-መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ መ/ር አፈወርቅ ተክሌ፤ ፳፻፭ ዓ.ም፣ ገጽ ፫፻፲፭-፫፻፲፯፡፡የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ፤ ፳፻፯ ዓ.ም፣ ገጽ ፻፲፩፡፡

ነሐሴ ፯ቁጽረታ (ጽንሰታ) ለማርያም ይህችን ዕለት አበው ሊቃውንት "ጥንተ መድኃኒት፤ የድኅነት መነሻ ቀን" ሲሉ ይጠሯታል። ስለ ምን ነው ቢሉ ለዓለም ድኅነት ምክንያት የሆነች የአምላክ እናቱ...
12/08/2026

ነሐሴ ፯

ቁጽረታ (ጽንሰታ) ለማርያም

ይህችን ዕለት አበው ሊቃውንት "ጥንተ መድኃኒት፤ የድኅነት መነሻ ቀን" ሲሉ ይጠሯታል።

ስለ ምን ነው ቢሉ ለዓለም ድኅነት ምክንያት የሆነች የአምላክ እናቱ የተጸነሰችበት ዕለት በመሆኑ ነው። አንድም ከአዳም ስሕተት በኋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተጸነሰች የመጀመሪያ ሰው እርሷ ናትና እንዲህ ይላሉ።

"ለጽንሰትኪ በከርሥ: እንበለ አበሳ ወርኩስ: ወለልደትኪ እማኅጸን ቅዱስ።" "ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው: የተወለድሽበት ማኅጸንም ቅዱስ ነው።" (መጽሐፈ ሰዓታት፣ ኢሳ. ፩÷፱ ፣ መኃ. ፬)

ይሕች ዕለት ለኢያቄምና ለሐና ብቻ ሳይሆን ለፍጥረት ሁሉ የተስፋ ድኅነት ቀን ናትና ሐሴትን ልናደርግ ይገባል።

የእመቤታችን መጸነስስ እንደ ምን ነው ቢሉ ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ (አሮን) የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ በሕጉ ጸንተው በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር። ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች "ልጅ የላችሁም።" በሚል ይናቁ ነበር።

ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር። ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ። እነሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም።

የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው። አንድ ቀን ርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች። "እንስሳትና አራዊትን ዕጽዋትን በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች።

ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ። ለአርባ ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ። በአርባኛው ቀን ሁለቱም ሕልምን ያልማሉ:: እርሱ:- ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ: በሐና ቀኝ ጆሮ ገብታ በማኅጸኗ ስትደርስ አየ።

እርሷ ደግሞ የኢያቄም በትር አብቦ አፍርቶ ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች። ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን።" አሉ። ለሰባት ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ።

በሰባተኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ ፯) መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ:: "ዓለም የሚድንባት የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ" ብሏቸው ተሠወራቸው። እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

እንደ ሥርዓቱም በዚህች ቀን አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች።
"ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ።" "ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም።" እንዳለ ሊቁ። (ቅዳሴ ማርያም)

ከእመቤታችን ረድኤት በረከት ያሳትፈን።
መልካም በዓል።

ምንጭ:- ዝማሬ ዳዊት የቴሌግራም ገጽ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።‎"ድንግል ሆይ! የብርሃን እናቱ፣ ከተመረጡት የተመረጥሽ፣ ከተከበሩት የከበርሽ ነሽ። የለመኑሽን የማታሳፍሪ፣ ለአማላጅነትሽ የምንተጋበት...
06/08/2026

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

‎"ድንግል ሆይ! የብርሃን እናቱ፣ ከተመረጡት የተመረጥሽ፣ ከተከበሩት የከበርሽ ነሽ። የለመኑሽን የማታሳፍሪ፣ ለአማላጅነትሽ የምንተጋበትን የሱባዔ ወራት የተባረከ አድርጊልን።"

‎የደሴ ደብረ ቤቴል ቅድስት ሥላሴና ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል የቤተ አብርሃም ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት በሙሉ፤ እንዲሁም ለመላው የሀገራችንና የዓለም ሕዝበ ክርስቲያን፦ ለ፳፻፲፰ ዓ.ም. የፍልሰታ ለማርያም ጾም (የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤና ዕርገት መታሰቢያ) በሰላም፣ በጤና እና በሕይወት አደረሳችሁ፤ አደረሰን።
‎የፍልሰታ ጾም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባረፈችበት ወቅት ቅዱሳን ሐዋርያት የእመቤታችንን ሥጋ ዐይተው ለመቅበርና በረከቷን ለመቀበል በሱባዔና በጾም የለመኑበት፣ በጸሎታቸውም የእመቤታችንን ትንሣኤና ዕርገት ለማየት የበቁበት ታላቅ የጸጋና የበረከት ወቅት ነው።
‎የቤተ አብርሃም ሰንበት ትምህርት ቤትም በዚህ በተቀደሰ የሱባዔ ወቅት ሁላችንም ወደ እግዚአብሔር ቤት እንድንገሰግስና የበረከቱ ተሳታፊ እንድንሆን ጥሪዋን እያስተላለፈች፤ በጾሙ ወራት በሚከተሉት መንፈሳዊ መርሐ ግብሮች ላይ እንድትሳተፉ በፍቅር ትጋብዛለች፦
‎👉 በሌሊት በሰዓታት ምስጋና ላይ በመገኘት፣
‎👉 ኪዳኑን በማድረስ፣
‎👉 የውዳሴዋን ትርጉም በማዳመጥ፣
‎👉 በዕለታዊው የቅዳሴ ጸሎት ላይ በመካፈል፣
‎👉 በሰንበት ትምህርት ቤቱ በሚዘጋጀው የጸሎት መርሐ ግብር ላይ በመሳተፍ ሁላችንም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት በትሕትና፣ በፍቅርና በምጽዋት በመመላለስ ወደ እመቤታችን አማላጅነትና ወደ ልጇ ቸርነት በመጠጋት የበረከትና የፍሬ መከር የምንሰበስብበት ሱባዔ ይሁንልን። ጾሙን የሰላም፣ የፍቅር፣ የንሥሐ፣ የበረከትና የፈውስ ጾም ያድርግልን።

‎የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅድስት ሥላሴ ቸርነት፣ የቅዱስ ገብርኤል ጥበቃና ተራዳኢነት ከሁላችን ጋር ይሁን።

ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በልዕልና ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ልምኝልን።

‎ ወስብሐት ለእግዚአብሔር! አሜን።
‎የቤተ አብርሃም ሰንበት ትምህርት ቤት

ዜና ቤተ አብርሃም‎✨ የቤተ አብርሃም ሰንበት ትምህርት ቤት ፵፱ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከበረ።✨ #ደሴ|ኢትዮጵያ፳፰/፲፩/፳፻፲ ዓ.ም.ቤ.አ.ሚ‎"ይህ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆ...
04/08/2026

ዜና ቤተ አብርሃም
‎✨ የቤተ አብርሃም ሰንበት ትምህርት ቤት ፵፱ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከበረ።✨

#ደሴ|ኢትዮጵያ
፳፰/፲፩/፳፻፲ ዓ.ም.
ቤ.አ.ሚ

‎"ይህ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ ነው፤ በዓይናችንም ድንቅ ነው።" (መዝሙር ፻፲፯፥፳፫)
‎በእግዚአብሔር ቸርነትና በቅዱሳኑ ረድኤት የደሴ ደብረ ቤቴል ቅድስት ሥላሴና ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል የቤተ አብርሃም ሰንበት ትምህርት ቤት ፵፱ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል፣ በኮምቦልቻ ርዕሰ አድባራት ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ሐመረ ኖህ ሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ በታላቅ ድምቀትና በመንፈሳዊ ክብር ሐምሌ ፳፮ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም. ተከበረ ።

‎ይህ ታላቅ መርሐ ግብር በጸሎት ተጀምሮ በኢንጅነር ሚክያስ አወቀ እና በእህት ቤተልሄም አሞኜ መሪነት መርሐ ግብሩ የተከወነ ሲሆን፣ በመቀጠልም በሰንበት ትምህርት ቤቱ ሰብሳቢ ኢንጂነር ስንታየሁ ዘመነ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ቀርቧል።

‎በዕለቱ የተከናወኑ ዋና ዋና መርሐ ግብሮች፦

‎✥ በአባላት የሕብረትና የግል መዝሙራት ቀርበዋል።

‎✥ በመምህር መንክር ተስፋዬ እና በመምህር ዲያቆን ሮቤል አማረ በጧት እና ከሰዓት በነበረው የትምህርት መርሐ ግብር ሰጥተዋል።

‎✥ የ፶ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ ኮሚቴ የመጪውን የወርቅ ኢዮቤልዩ ዕቅድና ፕሮጀክቶች በማቅረብ ከአባላት ጋር ሰፊ ውይይት አካሂዷል።

‎✥ በሕይወት የሌሉ የቀድሞ እህትና ወንድሞች መታሰቢያ የሕሊና ጸሎት ተደርጓል፤ በአንጋፋ አባላትም "ለዘብ (አብርሂ)" መርሐ ግብር ቀርቧል።

‎✥ ፵፱ኛውን ዓመት ለማድመቅ ሻማ በማብራትና ኬክ በመቁረስ የደስታ መርሐ ግብር ተከናውኗል። ከተለያዩ ቦታዎች የተላኩ የተንቀሳቃሽ ምስል (የቪዲዮ) መልእክቶችም ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ሰጥተዋል።

‎✥ ለረጅም ዓመታት በታማኝነት ላገለገሉ አባላት የምስጋናና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

‎በመጨረሻም መርሐ ግብሩ በአባቶች ቃለ ምእዳንና ጸሎት ተጠናቆ፣ በጋራ የማስታወሻ ምስል (ፎቶ) በመነሳት በደስታ ተፈጽሟል።
‎"ወንድሞች በአንድነት በሚኖሩበት እንዴት መልካምና እንዴትስ ደስ የሚያሰኝ ነው!" (መዝሙር ፻፴፪፥፩)
‎፵፱ ዓመታት የአገልግሎት ጉዞን በምስጋና እያሰብን፣ ወደ ፶ኛው የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል በአንድነት፣ በፍቅር፣ በእምነትና በቁርጠኝነት እንጓዛለን።
‎"ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባዋል፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና።" (መዝሙር ፻፴፭)

‎የቤተ አብርሃም ሰንበት ትምህርት ቤት
‎የሚዲያና ሕዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ

"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።" ‹‹ዑራኤል የተባለ መልአክ ሊረዳኝ መጣ፡፡›› መጽሐፈ ዕዝራ ፪፡፩፡፡ እንኳን ለተራዳኢው ለብርሃናት መሪ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራ...
28/07/2026

"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።"

‹‹ዑራኤል የተባለ መልአክ ሊረዳኝ መጣ፡፡›› መጽሐፈ ዕዝራ ፪፡፩፡፡
እንኳን ለተራዳኢው ለብርሃናት መሪ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳችሁ።
ሐምሌ ፳፩ እና ፳፪ ቀን
በእነዚህም ዕለታት ለካህኑና ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል የዕውቀትን ጽዋ ያጠጣበት ቀን እና ቅዳሴ ቤቱ የሚከበርበት በዓላት ናቸው ።
አስቀድሞ ምሥጢረ ሰማይን ለሄኖክ ያሳየዉ ዕዉቀትን የገለጠለት (ሄኖክ ፳፰፡፲፫)፣ የብርሃናት ሁሉ መሪ ቅዱስ ዑራኤል ለነብዩ ለዕዝራ ሱቱኤልም ጽዋዓ ልቦና አጠጥቶ ምሥጢራትን፣ የጠፉና የተሰወሩ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ተርጉሞ ይጽፍ ዘንድ የዕውቀትን ብርሃን ገልጦለታል። (ዕዝ ሱቱ.፪ )።
የሚያጽናና የሚፈውስ ፣ የሚያረጋጋ ለኃጢያተኞች ምሕረት የሚለምን ፈጥኖ ደራሽ የሆነው የብርሃናት ሁሉ መሪ ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ረድኤቱ በረከቱ ፍጹም አማላጅነቱ ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡

ዜና ቤተ አብርሃም‎የደሴ ደብረ ቤቴል ቅድስት ሥላሴና ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል የቤተ አብርሃም ሰንበት ትምህርት ቤት የ፶ኛ ዓመት የወርቅ ኢዩቤልዩ የምሥረታ በዓል ምክንያት በማድረግ፣ “ቤተ ...
27/07/2026

ዜና ቤተ አብርሃም

‎የደሴ ደብረ ቤቴል ቅድስት ሥላሴና ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል የቤተ አብርሃም ሰንበት ትምህርት ቤት የ፶ኛ ዓመት የወርቅ ኢዩቤልዩ የምሥረታ በዓል ምክንያት በማድረግ፣ “ቤተ አብርሃም በልጆቿ” በሚል መሪ ርዕስ የተዘጋጀው ልዩ የሦስት ቀን መንፈሳዊ ጉባዔ በታላቅ ድምቀትና መንፈሳዊ በረከት ተከናወነ።

‎ሰንበት ትምህርት ቤቱ ላለፉት አምስት አሥርት ዓመታት የወለዳቸውና ለአገልግሎት ያበቃቸው ዕውቅ ሰባክያነ ወንጌል እና ዘማርያን ተሰባስበው ያገለገሉበት ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ጉባዔ አባላቱን ያነቃቃ ታላቅ አውድ ሆኖ አልፏል። ይህ ታላቅ የወርቅ ኢዩቤልዩ በዓል ለአንድ ዓመት ሙሉ በተለያዩ መንፈሳዊ መርሐ ግብራት እና ልዩ ልዩ ዘላቂ የልማት ሥራዎች በደመቀ ሁኔታ የሚከበር ሲሆን፣ በዚህ ወቅት ለአንድ ሳምንት ሙሉ በሚቆዩ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች የሚታሰበውን የ፵፱ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በታላቅ ድምቀት ማክበር ጀምሯል። ‎በዚህ ሳምንት በሚከበረው የ፵፱ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል መርሐ ግብር ላይ:-
‎✝️ የሀገር ፍቅርና የሃይማኖት ምልክት የሆኑት የሰማዕተ ጽድቅ አቡነ ጴጥሮስ መታሰቢያ ሐምሌ ፳፪ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም. በታላቅ ክብር በቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል በዝማሬና በትምህርተ ወንጌል የሚታሰብ ሲሆን
‎✝️ የነገይቱ ቤተክርስቲያን ተረካቢዎችን የምናይበት የሕጻናትና ታዳጊዎች ልዩ መርሐ ግብርም ሐምሌ ፳፭ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም. በሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ ይከናወናል።
‎ለአንድ ሳምንት የሚቆየው ይህ ታላቅ በዓል ፍጻሜውን የሚያገኘውና የሚቋጨው ደግሞ መላው የሰንበት ትምህርት ቤቱ አባላት በሚሳተፉበት ልዩ ዓመታዊ መንፈሳዊ ጉዞ ሐምሌ ፳፮ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም. አማካኝነት ይሆናል።

‎ለዚህ ታላቅ የኢዩቤልዩ በዓል የተመረጠውና “በዚች ኢዩቤልዩ በዓል ሰው ሁሉ ወደ ርስቱ ይመለስ።” የሚለው መሪ ቃል መለኮታዊ መሠረቱ በኦሪት ዘሌዋውያን ምዕራፍ ፳፭ ቁጥር ፲ ላይ የሚገኘው “አምሳኛውንም ዓመት ቀድሱ፥ በምድርም ለሚኖሩባት ሁሉ አርነትን አውጁ፤ እርሱ ኢዩቤልዩ ይሆንላችኋል፤ ከእናንተም እያንዳንዱ ወደ ርስቱ ይመለስ፥ እያንዳንዱም ወደ ወገኑ ይመለስ።” የሚለው የእግዚአብሔር ቃል ነው። ይህ ቅዱስ ቃል እንደሚያስተምረን የአምሳኛው ዓመት የወርቅ ኢዩቤልዩ የነጻነት፣ የይቅርታ እና የዕርቅ ዘመን እንደመሆኑ መጠን፣ የቤተ አብርሃም ሰንበት ትምህርት ቤት በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የሰንበት ትምህርት ቤቱ ፍሬዎች በሙሉ “እንኳን ለ፶ኛ ዓመት የወርቅ ኢዩቤልዩ የዝግጅት ምዕራፍ እና ለ፵፱ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን።” በማለት የመልካም ምኞት መልዕክቱን ያስተላለፈ ሲሆን በዓሉ የታሪክ ማስታወሻ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ክርስቲያን ሕይወቱን መርምሮ ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመለስበትና መንፈሳዊ ርስቱን የሚያጸናበት የተቀደሰ ወቅት እንዲሆን ጥሪውን አቅርቧል።

ዘገባው:- የሚዲያና ሕዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ ነው።

የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ተራዳቸው።መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ ለቅዱስ ቂርቆስና ለቅድስት ኢየሉጣ ተረዳኢ የሆነበት ሐምሌ ፲፱ ቀን ታላቅ በዓል በመሆኑ ቅድ...
25/07/2026

የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ተራዳቸው።

መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ ለቅዱስ ቂርቆስና ለቅድስት ኢየሉጣ ተረዳኢ የሆነበት ሐምሌ ፲፱ ቀን ታላቅ በዓል በመሆኑ ቅድስት ቤተ ከርስቲያናችንም ታከብረዋለች፡፡ የእነዚህም ቅዱሳን ታሪክ በስንክሳር እንደተመዘገበው እንዲህ ይተረካል፡፡

ቅድስት ኢየሉጣ በሮም ግዛት በሚገኝ አንጌቤን በሚባል አገር በፈሪሃ እግዚአብሔር፣ በክርስትና ሃይማኖት እና በበጎ ምግባር ጸንታ ትኖር የነበረች ደግ ሴት ናት፡፡ በሥርዓት ያሳደገችው ቂርቆስ የሚባል ሕፃን ልጅም ነበራት፡፡ ይህቺ ቅድስት የዘመኑን አረማዊ መኰንን እለእስክንድሮስን በመፍራቷ ከልጇ ጋር ከሮም ወደ ጠርሴስ በተሰደደች ጊዜ መኰንኑ እነርሱ ከሚገኙበት አገር ገብቶ ክርስቲያኖችን እያሳደደ መግደል ጀመረ፡፡ የንጉሡ ወታደሮችም እግዚአብሔርን እንዲክዱ፤ ለጣዖት እንዲሰግዱ ቅድስት ኢየሉጣንና ቅዱስ ቂርቆስን አስፈራሯቸው፡፡ ቅዱሳኑ ግን ሃይማኖታቸውን ለመለወጥ ፈቃደኛ አልሆኑም ነበር፡፡ በዚህም መኰንኑ ተቈጥቶ በዓይንና በአፍንጫቸው ውስጥ ጨውና ሰናፍጭ በመጨመር፤ በጋሉ የብረት ችንካሮች በመቸንከርና መላ ሰውነታቸውን በመብሳት በብዙ ዓይነት መሣሪያ አሠቃያቸው፡፡ እግዚአብሔርም የጋሉ ብረቶችን እንደ ውኀ ያቀዘቅዝላቸው፤ ሥቃያቸውንም ያቀልላቸው ነበር፡፡
በሌላ ጊዜም በገመድ አሳሥሮ ንጉሡ ሲያስጨንቃቸው ከቆየ በኋላ ራሳቸውን ከቆዳቸው ጋር አስላጭቶ እሳት አነደደባቸው፡፡ ዳግመኛም ከትከሻቸው እስከ እግራቸው ድረስ በሚደርሱ ችንካሮች ቸነከራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ ከሥቃያቸው አድኗቸዋል፡፡ አሁንም ቀኑን ሙሉ በልዩ ልዩ የሥቃይ መሣሪያዎች ቢያስጨንቃቸውም የእግዚአብሔር ኃይልና የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት አልተለያቸውም ነበርና ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰባቸውም፡፡ እንደ ገናም በመጋዝ ሰንጥቀው በብረት ምጣድ በቆሏቸው ጊዜ ጌታችን ከሞት አነሣቸውና በመኰንኑ ፊት ድንቅ ተአምራትን አደረጉ፡፡ ከተአምራቱ መካከልም ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ የመኰንኑን ጫማ በጸሎት ወደ በሬነት እንዲቀየር ማድረጉ ተጠቃሽ ሲሆን፣ መኰንኑ በተአምራቱ ተቈጥቶ የቅዱስ ቂርቆስን ምላስ አስቈርጦታል፤ ጌታችንም ምላሱን አድኖለታል፡፡
ዳግመኛም በፈላ የጋን ውኀ ውስጥ ቅዱሳን ቂርቆስና ኢየሉጣን ሊጨምሯቸው ሲሉ ቅድስት ኢየሉጣ በፈራች ጊዜ ቅዱስ ቂርቆስ ‹‹እናቴ ሆይ አትፍሪ፤ አናንያ፣ ዓዛርያና ሚሳኤልን ከእሳት ነበልባል ያዳናቸው እግዚአብሔር እኛንም ከዚህ የፈላ ውኀ ያድነናል›› እያለ ያረጋጋት በተጋድሎዋ እንድትጸና ወደ እግዚአብሔር ይጸልይላት ነበር፡፡
ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደ ጋኑ ውስጥ ገቡ፡፡ ያ ውኀም እንደ ውርጭ ቀዘቀዘ፡፡ ደግሞም ወታደሮቹ መንኰራኵር ባለበት የብረት ምጣድ ውስጥ አስገብተው ሥጋቸው እስኪቈራረጥ ድረስ በጎተቷቸው ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል አድኗቸዋል፡፡ በመጨረሻም ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተቀብለው በመንፈቀ ሌሊት አንገታቸውን ተቈርጠው በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ እስከ ሞት ድረስ በታመኑበት ተጋድሏቸውም ከእግዚአብሔር ዘንድ የሕይወትን አክሊል ተቀብለዋል፡፡
በአጠቃላይ ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ የዚህን ዓለም ጣዕም በመናቅ ‹‹ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ ግዛትም ቢሆን፣ ያለውም ቢሆን፣ የሚመጣውም ቢሆን፣ ኃይላትም ቢሆኑ፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ›› በማለት ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ቃል በተግባር በማሳየት ለክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ራሳቸውን ለመከራና ለሞት አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ቅዱሳኑ ተጋድሏቸውን እስኪፈጽሙ ድረስም ቅዱስ ገብርኤል አልተለያቸውም፡፡ በቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት ቅድስት ኢየሉጣና ቅዱስ ቂርቆስ ብቻ ሳይሆኑ ብዙ ምእመናንም ተጠቅመዋል፡፡ ስሙ በሚጠራባቸው ገዳማትና አድባራት መልአኩ የሚያደርጋቸው ድንቅ ድንቅ ተአምራት ለዚህ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ይህም ቅዱሳን መላእክት በእግዚአብሔር ስም መከራ የሚቀበሉ ምእመናንን እንደሚጠብቁና ከልዩ ልዩ ደዌ እንደሚፈውሱ የሚያስረዳ ታሪክ ነው፡፡ (ሮሜ. ፰፥፴፰-፴፱)
እኛም በሃይማኖታችን ምክንያት መከራ ባጋጠመን ጊዜ ቈራጥ ልብ ያለው ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ‹‹እናቴ ሆይ አትፍሪ›› እያለ በእሳት ውስጥ ሊጣሉ ባሉበት ወቅት እናቱን እንድትጸናና ለሰማዕትነት እንድትበቃ እንዳደረጋት ሁሉ፣ ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት በአንድነት ለመውረስ እንድንችል ‹‹አይዞህ! አይዞሽ! አትፍራ! አትፍሪ›› በመባባል በዚህ ዓለም የሚገጥመንን መከራ ታግሠን፣ እስከ ሞት ድረስ በሃይማኖታችን ጸንተን መኖር ይገባናል፡፡ ክርስትና ለብቻ የሚጸደቅበት መንገድ ሳይሆን በጋራ ዋጋ የሚያገኙበት የድኅነት በር ነውና፡፡ ከዚሁ ሁሉ ጋርም ቅዱስ ቂርቆስንና ቅድስት ኢየሉጣን የተራዳው የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል በአማላጅነቱ እንዲጠብቀን ‹‹በተአምኖ ንሴፎ ትንባሌ ዚአከ መዓልተ ወሌሊተ፤ በእግዚአብሔር ታምነን በቀንም በሌሊትም የአንተን ልመና ተስፋ እናደርጋለን›› እያልን ዘወትር ልንማጸነው ያስፈልጋል፡፡ እርሱ ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር በተሰጠው ቃል ኪዳን መሠረት ከሚደርስብን ልዩ ልዩ መከራና ሥቃይ ያድነናልና፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙርያ ይሠፍራል፤ ያድናቸውማል›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (መዝ. ፴፬፥፯)፡፡ ይህን እንድናደርግም የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን፡፡ የቅዱስ ገብርኤል፣ ቅድስት ኢየሉጣ እና ቅዱስ ቂርቆስ ጸሎታቸው፣ ምልጃቸው ይጠብቀን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኃ ሐምሌ

የተወደዳችሁ የደሴ ርዕሰ አድባራት ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ወልድ ዋሕድ ሰንበት ትምህርት ቤት አመራሮችና አባላት «የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።» (መዝሙር...
19/07/2026

የተወደዳችሁ የደሴ ርዕሰ አድባራት ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ወልድ ዋሕድ ሰንበት ትምህርት ቤት አመራሮችና አባላት «የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።» (መዝሙር ፻፲፮፥፲፭)
‎የሰንበት ትምህርት ቤታችሁ ነባር አባል የእህታችን የልዩወርቅ አረጋ ወደ ዘለዓለም ቤት መግባት (ዕረፍት) በደሴ ደብረ ቤቴል ቅድስት ሥላሴና ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል የቤተ አብርሃም ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ዘንድ ታላቅ ሐዘንን ፈጥሯል። እህታችን ልዩወርቅ አረጋ በቅንነትና በታማኝነት ያገለገለች የቤተክርስቲያን ፍሬ ነበረች።
‎በመሆኑም እኛ ክርስቲያኖች ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች አይደለንምና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል።» (ዮሐንስ ፲፩፥፳፭) በማለት የትንሣኤ ተስፋ ሰጥቶናል። በሐዘናችን ሰዓት ሁልጊዜ ከጎናችን የማትጠፋው፣ የሐዘንተኞች መጽናኛና የቅዱሳን እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በደጇ የለመነችውንና ያገለገለችውን የእህታችንን ነፍስ በልጇ መንግሥት እንድታማልድልን እንማጸናለን። ለእህታችን ልዩወርቅ አረጋ ዕረፍተ ነፍስን፤ ለቤተሰቦቿና ለወልድ ዋሕድ ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ወንድምና እህቶቿ በሙሉ ልዑል እግዚአብሔር መጽናናትና እንዲሰጥልን የእመቤታችንን አማላጅነት እንመኛለን። የእህታችን ነፍስ በአጸደ ገነት ትረፍ።

‎የደሴ ደብረ ቤቴል ቅድስት ሥላሴና ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል የቤተ አብርሃም ሰንበት ትምህርት ቤት

ዜና ቤተ አብርሃም"የደሴ ደብረ ቤቴል ቅድስት ሥላሴና ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል የቤተ አብርሃም ሰንበት ትምህርት ቤት የ፳፻፲፰ ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የሁለተኛ ወሠነ ዓመት ማጠቃለያ ፈተናን...
19/07/2026

ዜና ቤተ አብርሃም

"የደሴ ደብረ ቤቴል ቅድስት ሥላሴና ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል የቤተ አብርሃም ሰንበት ትምህርት ቤት የ፳፻፲፰ ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የሁለተኛ ወሠነ ዓመት ማጠቃለያ ፈተናን በስኬት አጠናቀቀች።"

ሐምሌ ፲፪ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም.
#ደሴ|ኢትዮጵያ
ቤ.አ.ሚ.

የደሴ ደብረ ቤቴል ቅድስት ሥላሴና ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል የቤተ አብርሃም ሰንበት ትምህርት ቤት የ፳፻፲፰ ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የሁለተኛ ወሠነ ዓመት ማጠቃለያ ፈተናን በስኬት አጠናቀቀች። ታላቁ የቤተክርስቲያን አባት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ልጆቻችሁን በእግዚአብሔር ቃል ኮትኩታችሁ አሳድጉ፤ የቀረውን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ይጨምርላቸዋል።” እንዳለው፣ የሰንበት ትምህርት ቤቱ ዕቅበተ እምነት ማስተባበሪያ የ፳፻፲፰ ዓ.ም. የትውልድ ግንባታ ተልዕኮውን በድል ተወጥቷል። ይህ ማጠቃለያ ፈተና የተሰጠው በቅድስት ሥላሴ እና በቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ቅጥር ግቢ በመገኘት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ለነበሩት የቅዳሜና እሑድ የሥርዓተ ትምህርት ተማሪዎች ነው። በዚህም መሠረት ሰኔ ፲፩ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም. ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ክፍል እንዲሁም የአምስተኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተናቸውን በአግባቡ የወሰዱ ሲሆን፣ በቀጣዩ ቀን ሰኔ ፲፪ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም. ደግሞ የሰባተኛ ክፍል ተማሪዎች የወሠነ ዓመቱን ማጠቃለያ ፈተና በመፈተን የዓመቱን ትምህርት በሰላም አጠናቀዋል። ሰንበት ትምህርት ቤቱ የነገን ኦርቶዶክሳዊ ትውልድ በዕውቀትና በግብረ ገብነት የመኮትኮት መንፈሳዊ ተልዕኮውን ይበልጥ በማስፋት፣ በበጀት ዓመቱ ያሳየውን ጠንካራ አፈጻጸም መሠረት በማድረግ በ፳፻፲፱ ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ እስከ ዘጠነኛ ክፍል ድረስ ያለውን መንፈሳዊ ትምህርት በበለጠ ጥራትና ዝግጅት አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን እያበሰረ፣ ወላጆችም ልጆቻቸውን በቤተ እግዚአብሔር አደባባይ እንዲያሳድጉ ጥሪውን ያስተላልፋል።

ዘገባው:- የሚዲያና ሕዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ ነው።

Address

Dessie

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when የደሴ ደብረ ቤቴል ቅድስት ሥላሴና ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል የቤተ አብርሃም ሰ/ት/ቤት ገጽ posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Shortcuts

Share