23/05/2026
#ለትውልድ #ብርሃን #የሆኑት #የሙያ #አባት #የአንጋፋው #መምህር #ሲልማ #ተመስገን #ደማቅና #ታሪካዊ #የክብር #ሽኝት
የሰው ልጅ በምድር ላይ ሊያሳካቸው ከሚችላቸው ታላላቅ ስኬቶች መካከል አንዱና ዋነኛው ትውልድን በእውቀትና በሥነ-ምግባር አንጾ ለሀገር የሚበቃ ፍሬ ማፍራት ነው።
ይህንን ታላቅና ቅዱስ ተልዕኮ የሙያቸው መመሪያ አድርገው፣ ዕውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ ለ37 ዓመታት ሙሉ ለትውልድ ግንባታ የገበሩት አንጋፋው መምህርና ርዕሰ-መምህር ሲልማ ተመስገን በደማቅ ሁኔታና በታላቅ ክብር በጡረታ ተሸኝተዋል።
ይህ የሽኝትና የእውቅና ፕሮግራም መምህርነት ተራ ስራ ሳይሆን የሀገርን እጣ ፈንታ የሚወስን የክብር ማማ መሆኑን በተግባር ያሳየ ደማቅ ኩነት ነበር።
#በትጋትና #በቅንነት #የተገነባው #የ37 #ዓመታት #የብርሃን #ጉዞ
የመምህር ሲልማ ተመስገን የ37 ዓመት ከ9 ወር የቅንነት፣ የልፋትና የስኬት የጉዞ መስመር የተጀመረው በሀምሌ 1 ቀን 1980 ዓ.ም ነበር።
በደቡብ ወሎ ዞን ጃማ ወረዳ 02 ቀበሌ አቢዮት ፍሬ አጠቃላይ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመድበው የመጀመሪያ አሻራቸውን ያኖሩት መምህሩ፣ ከዚያ በኋላ ባሉት ዘመናት ሁሉ ለትምህርት ጥራትና ለተቋማት ለውጥ የከፈሉት መስዋዕትነት ታሪክ የማይረሳው ሆኗል።
#የአገልግሎትና #የሥራ #ታሪክ
📌 ከ1981 - 1992 ዓ.ም፦ በከታሪ አጠቃላይ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት (11 ዓመታት በትጋት ያገለገሉበት)።
📌 ከ1992 - 1995 ዓ.ም፦ በጉራጫሌ አጠቃላይ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በርዕሰ-መምህርነት። (የዚህን ትምህርት ቤት ዲዛይን በራሳቸው በመስራት አዲስ ግንባታ እንዲካሄድ አድርገዋል)።
📌 ከ1996 - 2004 ዓ.ም፦ በሲልማ አጠቃላይ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በርዕሰ መምህርነት። (ከ4 ሄክታር በላይ መሬት ለተቋሙ እንዲከለልና የ017 ቀበሌ የባህርዛፍ ልማት ለትምህርት ቤቱ ገቢ እንዲሆን በማድረግ ታላቅ ተቋማዊ ለውጥ አምጥተዋል)።
📌 ከ2005 - የካቲት 30/2018 ዓ.ም፦ በሲልማ አጠቃላይ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርነት በትጋትና በታማኝነት አገልግለው በክብር አጠናቀዋል።
#ታሪክ #የማይረሳው #ትውልድ #ተሻጋሪ #አሻራ
እንደ ሲልማ አጠቃላይ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ስንታየሁ እሸቴ ገለጻ፣ መምህር ሲልማን የሀገርና የወገን ልዩ ባለውለታ ያደረጋቸው በትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሳዩት ልዩ የመሪነት ጥበብ ነው።
በወረዳው ውስጥ ህብረተሰቡን፣ መንግስትንና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላትን በከፍተኛ ሁኔታ በማስተባበር፣ የትምህርት ቤቱን ፕላን በራሳቸው አዘጋጅተው በመስራት፣ በወረዳው በስማቸው ብቸኛ የሆነውን ትምህርት ቤት በደጎሎ ከተማ ዐ2 ቀበሌ እንዲመሰረት አስችለዋል።
ይህ ለሙያ ያላቸው ፍቅርና ቁርጠኝነት ከመምህርነት አልፎ ለትውልድ የሚተርፍ ቅርስ እንዲተክሉ አድርጓቸዋል።
"ለደከሙለት ልፋት ፍሬ ማየት" ፦ የእውቅናና የሽልማት መርሃ-ግብር
ለሀገርና ለወገን የዋሉትን ውለታና ታሪክ የማይረሳውን ተጋድሎ ለመዘከር የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የመምህራንን ክብር ከፍ የሚያደርጉ ሽልማቶችን አበርክተውላቸዋል።
አንጋፋው መምህር ሲልማ ተመስገን በተደረገላቸው የክብር ሽኝት የተሰማቸውን ጥልቅ ደስታ ገልጸው፣ በሙያቸው ያሳለፏቸው 37 ዓመታት ሙሉ የደስታና የኩራት መሆናቸውን ተናግረዋል።
አክለውም፦ "ተቋማቱና ማህበረሰቡ ይህንን ታላቅ እውቅናና ክብር ሲሰጡኝ ማየቴ፣ ለሀገርና ለትውልድ የደከምኩት ልፋት ሁሉ ፍሬ ማፍራቱን አሳይቶኛል" በማለት በምሬት ሳይሆን በኩራትና በደስታ የተሞላ ስንብት አድርገዋል።
መምህር ሲልማ ተመስገን ለተቋሙ እድገት፣ ለተማሪዎች መጻኢ እድልና ለወረዳው የትምህርት ተደራሽነት የከፈሉት መስዋዕትነት የትኛውንም መሰናክል በቅንነትና በትጋት ማሸነፍ እንደሚቻል ማረጋገጫ ነው።
ይህ ታሪካዊ ሽኝት መምህራን የህብረተሰብ ቁልፍ መሪዎች መሆናቸውን ያስመሰከረና ለቀጣዩ ትውልድ መምህራን ታላቅ መነሳሳትንና አርአያነትን ያሳረፈ ደማቅ አሻራ ሆኖ ይኖራል።
ክብርና ሞገስ ለሀገር ባለውለታው መምህር #ሲልማ #ተመስገን!
21/05/2026
💼 #ለአዲስ #ምሩቃን #የወጣ #የቅጥር #ማስታወቂያ!
የደቡብ ወሎ ዞን ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ በኢኮኖሚክስ ወይም በዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ መጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው እና 0 ዓመት የስራ ልምድ የሆኑ ባለሙያዎችን አወዳድሮ መቅጠር ይፈልጋል።
📅 የምዝገባ ጊዜ፡ ከ10/09/2018 ዓ.ም እስከ 18/09/2018 ዓ.ም (በስራ ሰዓት)
📍 የምዝገባ ቦታ፡ የደቡብ ወሎ ዞን ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ (ቢሮ ቁጥር 106)
መስፈርቱን የምታሟሉ መወዳደር የምትችሉ ሲሆን፣ ለወዳጅ ዘመድዎም እንዲደርስ በማድረግ ያጋሩት!
19/05/2026
የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ለመስጠት 667 የፈተና ማዕከላት ተዘጋጁ።
------------------------ // -----------------------------
(ግንቦት 11/2018 ዓ.ም) የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና በ667 የፈተና ማዕከላት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነመሆኑን ገልጿል ።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) እንደገለጹት፥ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናን በ97 ዩኒቨርሲቲዎች እና በ570 የክልል ማዕከላት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 17 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚሰጠው ፈተና መደበኛ ተማሪዎችን ጨምሮ በሁሉም ፕሮግራሞች በተፈጥሮ ሳይንስ 306 ሺህ 964 እንዲሁም በማህበራዊ ሳይንስ 257 ሺህ 255 በድምሩ 564 ሺህ 219 ተማሪዎች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡
ፈተናውን በሙሉ አቅም በበይነ መረብ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ በወረቀት የሚፈተኑ ተማሪዎች እንደሚኖሩም ጠቁመዋል።
በየክልሎች እና የፈተና ማዕከላት ያለው አቅም የተለያየ ቢሆንም በርካታ ኮምፒዩተሮች ለፈተና ዝግጁ እየተደረጉ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
ከባለፈው አርብ ጀምሮ ለተፈታኞች የበይነ መረብ የሙከራ ፈተና መሰጠት መጀመሩን አንስተዋል።
ፈተናው በ6 ዙር እንደሚሰጥና በማህበራዊ ሳይንስ በሶስት ዙር በተመሳሳይ በተፈጥሮ ሳይንስ ደግሞ በሶስት ዙር በመሆኑ አንድ ኮምፒዩተር ስድስት ተማሪን ያስተናግዳል ብለዋል።
ተማሪዎች የፈተና ስርዓቱን እንዲለማመዱና ትምህርት ቤቶች እና ወላጆች ለተፈታኝ ተማሪዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን በሚከተሉት ማስፈንጠሪያዎች ያግኙ፡-
በፌስቡክ -https://www.facebook.com/fdremoe/
በቴሌግራም -https://t.me/ethio_moe
በትዊተር - http://twitter.com/fdremoe
ዩቱዩብ- https://www.youtube.com/-of-education-ethiopia
በሊንክዲን - https://www.linkedin.com/.../ministry-of-education-ethiopia
በዌብሳይት - www.moe.gov.et ይከታተሉ
18/05/2026
በለገሂዳ ወረዳ በህብረተሰቡና በአልማ የተገነቡ አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ተመረቁ
ግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም — በለገሂዳ ወረዳ በሚገኘው የወይን አምባ አጠቃላይ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበረውን ከፍተኛ የመማሪያ ክፍሎች እጥረትና የህንጻዎች መፍረስ አደጋ ለመቅረፍ የተገነቡ አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ዛሬ በይፋ ተመርቀዋል። የክልል፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የምረቃ ስነ-ስርዓቱ ተከናውኗል።
የተማሪዎችን የመማሪያ አካባቢ ለማሻሻል የተከናወኑት እነዚህ ግንባታዎች፡-
በትምህርት ቤቱ የነበረውን አሳሳቢ የክፍል እጥረት ለመቅረፍ ባለ 1 ወለል (G+1) ህንጻ ግንባታ በ2015 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ተጀምሮ የነበረውና 10 የመማሪያ ክፍሎችን የያዘው ይህ ህንጻ በአጠቃላይ 21 ሚሊየን 851 ሺህ 548 ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን፣ በአንድ ፈረቃ ለበርካታ ተማሪዎች አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዳለው ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪ የአካባቢው ማህበረሰብ ባደረገው ንቁ ተሳትፎና የገንዘብ ማሰባሰብ ሂደት ከ 4.9 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ተጨማሪ 4 የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተው ሙሉ በሙሉ ተጠናቀዋል።
ይህ የትምህርት ተቋማት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ቀደም ሲል በትምህርት ቤቱ ይስተዋል የነበረውን የህንጻዎች መፍረስ አደጋ በዘላቂነት ከመቅረፉም በላይ፣ ህጻናት ንጹህ፣ አስተማማኝና ምቹ በሆነ የመማሪያ ክፍል ውስጥ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ትልቅ እድል ይፈጥራል።
ፕሮጀክቱ የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (ልማት ማህበራት) እና የአካባቢው ማህበረሰብ በጋራ ሲረባረቡ በትምህርት ዘርፍ ላይ ሊመጣ የሚችለውን አዎንታዊ ለውጥ የሚያሳይ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
18/05/2026
በወረኢሉ ወረዳ የተገነቡ ሁለት የቅድመ-አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተመረቁ
በደቡብ ወሎ ዞን ወረኢሉ ወረዳ በአማራ ልማት ማህበር (አልማ) ድጋፍ የተገነቡት የሰኞ ገበያ እና የካቤ ቅድመ-አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
በትምህርት ቤቶቹ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የወረዳው የአልማ ቦርድ ሰብሳቢ እና የአልማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪን ጨምሮ የማኅበረሰብ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የትምህርት ቤቶቹ አመራሮች፣ መምህራንና ተማሪዎች ተገኝተዋል።
በምረቃው ወቅት የቅድመ-አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶቹ በጥራት መገንባታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በቀጣይም የሚቀሩ አጋዥ ሥራዎችን ወረዳው በቅርበት እየተከታተለ እንደሚያከናውን ተመላክቷል። የክልሉንና የሀገሪቱን የነገ ተስፋ የሆኑ ሕፃናትን በዕውቀት ለመቅረጽና ብቁ ትውልድ ለማፍራት እንዲህ ያሉ የትምህርት ተቋማትን በጥራት መገንባትና ማስፋፋት ወሳኝ መሆኑ በዕለቱ ተጠቅሷል።
የወረኢሉ ወረዳ አመራሮች እንደገለጹት፣ የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) ከሕዝብ የሰበሰበውን ሀብትና ገንዘብ መልሶ ለሕዝብ ጠቃሚ በሆኑ የልማት ሥራዎች ላይ በማዋል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከተ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም በወረዳው በርካታ መሰረተ-ልማቶችን በተለይም የትምህርት ተደራሽነትን የሚያረጋግጡ ሞዴል ግንባታዎችን አጠናቆ ለሕዝብ ጥቅም ማብቃት መቻሉ ተገልጿል።
ይህ አዲስ የተመረቁት የቅድመ-አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም የአካባቢውን ሕፃናት የትምህርት ተጠቃሚነት በተግባር የሚያረጋግጡ መሆናቸው ተመልክቷል።