20/04/2023
ዘካተል ፊጥር በገንዘብ
ነቢዩ ﷺ ዘካተል ፊጥርን አንድ ቁና ተምር ወይም ገብስ ይሰጡ ነበር።
(ቡኻሪይ 1503)
ዘካተል ፊጥርን በገንዘብ መስጠት ይቻላል? የሚለውን በተመለከተ 3 ዓይነት አስተያየቶች አሉ።
♦️ አብዛኛው ዑለማዎች ነቢዩ ﷺ በእህል ስለሰጡ በእህል እንጅ በገንዘብ መሰጠት አይፈቀድም። መከተል ያለብን የነቢዩን ﷺ ተግባር እንጅ የሰዎችን አስተያየት አይደለም ይላሉ።
ከእነሱም መካከል ኢማም ማሊክ፣ ኢማም አሽ-ሻፊዒይ፣ ኢማም አህመድና ኢብን ሐዝም ይጠቀሳሉ።
♦️ ታላላቅ የታቢዒይ ዑለማዎች ደግሞ በገንዘብ ለውጦ መስጠት ይቻላል ብለዋል።
ከእነሱም መካከል ሐሰን አል-በስሪ፣ አጣዕ ኢብን አቢ-ረባህ፣ ዑመር ኢብን አብዱልአዚዝ፣ ኢማም ሱፍያን አስ-ሰውሪ፣ ኢማም አቡ-ሐኒፋ እና ኢማም ቡኻሪይ ይጠቀሳሉ።
(ሙስነፍ 4/37)
♦️ ሶስተኛው ለተቀባዩ ሰው በሚጠቅመው ሁኔታ በእህል ወይም በገንዘብ መስጠት ይቻላል የሚለው ነው።
ኢብን ተይሚያህ ስለዚህ ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ፦
«ዘካተል ፊጥርን ተቀባዩ በገንዘብ ቢሰጠው የሚፈልግና የሚጠቅመው ከሆነ በገንዘብ ተምኖ መስጠት ይቻላል። ለምሳሌ 5 ግመሎች ያሉት ሰው አንድ በግ ዘካ እንዲያወጣ ተጥሎበታል። ነገርግን በአካባቢው በግ ከሌለ በገንዘብ ተምኖ መስጠት ይችላል። ሙዓዝ ኢብን ጀበል የየመን ሰዎችን ዘካ ሲቀበል ‹ከእህል ይልቅ በልብስ ቀይራችሁ ብትሰጡኝ ትችላላችሁ። ይሄ በመዲና ለሚገኙ ሙሐጅሮችና አንሷሮች የበለጠ ጠቃሚ ነው።› ብሏቸዋል። ይህም ዘካተል ፊጥርንም የበለጠ ጠቃሚ በሆነው መስጠት እንደሚቻል ያሳያል።»
(ፈታዋ ኢብን ተይሚያህ 25/82)
ይህንን ሃሳብ የደገፉ ዑለማዎች ነቢዩ ﷺ ዘሃተል ፊጥርን በእህል የሰጡበት ምክንያት አንደኛ በወቅቱ በአረቦች ዘንድ የገንዘብ ዝውውር አነስተኛ በመሆኑ፤ ሁለተኛ የገንዘብ አቅም በየጊዜው ስለሚለዋወጥ ዘካውን በስፍር ተምኖ ለማስቀመጥ እንዲረዳ ነው ይላሉ።
(አል-ሙግኒ 3/60)
♦️ ከዘመናችን ዑለማዎች መካከል ሸይኽ ሸልቱት እና አል-ቀርዷዊ በገንዘብ መስጠቱ የደገፉ ሲሆን፡-
👉 የዘካተል ፊጥር ዋና ዓላማው ሰዎች በዓሉን ተደስተው እንዲውሉ ለማድረግ በመሆኑ ሰውየው የበለጠ በሚደሰትበት መንገድ መስጠቱ እንደሚበልጥ
👉 በዘመናችን የገንዘብ ዝውውር የበዛበትና በገንዘብ ቢከፈል ለሰጭውም ለተቀባዩም ስለሚቀል
👉 እንዲሁም እህል ቢሰጣቸው እንኳን እነሱ መልሰው ሽጠው ወደ ገንዘብ መቀየራቸው ስለማይቀር ቀጥታ በገንዘብ ቢሰጥ ይበልጣል ይላሉ።
(ፊቅህ ወ ሂሳብ ዘካት አል-ፊጥር 15)
አላህ የበለጠ ያውቃል!
©ሰል ማን