27/12/2025
ወንቅሸት ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳም
= = = =
ወንቅሸት ገብርኤል በደቡብ ጎንደር አስተዳደር ዞን ደራ ወረዳ የሚገኝ ታሪካዊ ገዳም ነው፡፡ ወደ ገዳሙ በተለያዩ መስመሮች መሄድ የሚቻል ሲሆን ብዙዎች የሚመርጡት ከጢስ ዓባይ ከተማ ምስራቅ አቅጣጫ በሚገኘው ጥንታዊ የአለታ ድልድይ የዓባይን ወንዝ ተሻግሮ በአማካኝ የአንድ ሰዓት የእግር መንገድ የሚወስደውን መስመር ነው፡፡
በዚህ መስመር መጓዝ ከመንገዱ አቋራጭነት ባሻገር አስደማሚውን የጢስ ዓባይ ፏፏቴ፣ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዓባይ ወንዝ ላይ የተሰራውን የመጀመሪያ ድልድይ/አለታ/፣ የአለታ ተንጠልጣይ ድልድይ እንዲሁም ሌሎችን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መስህቦችን ለመጎብኘት የሚያስችል ነው፡፡
ወንቅሸት በሰንሰለታማ ተራሮች የተከበበ፣ በተፈጥሮ ደን የተሸፈነ፣ ፍልና ቀዝቃዛ የተፈጥሮ ፀበሎች የሚፈሱበት፣ በርካታ የዱር እንሰሳትና አእዋፍት የሚቦርቁበትና ዘወትር ልምላሜ የማይለየው ጥንታዊ ገዳም ነው፡፡
ገዳሙ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከንግሥት ሳባና ከንጉሥ ሰለሞን የተወለደው ቀዳማዊ ምኒልክ ከእስራኤል ታቦተ ጽዮንን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ አብረውት የመጡ እስራኤላውያንን ካህናት በህገ ልቦና ይመራ ለነበረው ነባር ህዝብ ሕገ ኦሪትን ይሰብኩበትና መስዋዕተ ኦሪት ይሰውበት እንደነበረ የገዳሙ አስተዳዳሪ ይናገራሉ፡፡
ለሃይማኖታዊና ለሌላም አገልግሎት ይውሉ እንደነበር የሚገመቱ የተለያየ ቅርጽ ያላቸው ጥንታዊ ሸክላዎች፣ መስቀሎች እንዲሁም የንግሥት አዜብ ቤተመንግስት እንደነበር የሚነገርለት አሁን የንግሥት አዜብ ካብ እየተባለ የሚጠራ እና ጥንታዊ ዋሻዎች በገዳሙ ከሚገኙ መስህቦች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ዛሬ ሐምሌ 19 የቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ የንግሥ በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው ቦታዎች መካከል ወንቅሸት ቅዱስ ገብርኤል አንድነት ገዳም ዋናው ነው፡፡ በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ምዕመናን በክብረ በዓሉ ከቀናት ቀደም ብለው በመታደም በዓሉን እያከበሩ ነው፡፡
እንኳን አደረሳችሁ!!!