07/08/2026
ፍልሰታ ለማርያም፡ ሰአ(ዐ)ሊ ለነ ቅድስት
መ/ር ጌታቸው በቀለ
በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዐት መሠረት ሁሉ እንዲጾማቸው መጀመሪያቸውና መጨረሻቸው ተቀምሮ ጊዜና ወቅት ተወስኖላቸው የተደነገጉ ሰባት የዐዋጅ አጽዋማት አሉ፡፡ እነዚህንም በሐዋርያት ሲጾሙ የቆዩና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በቀኖና ያጸኗቸው ዲድስቅልያና ሌሎች የቀኖና መጻሕፍት ሥርዐታቸውን የሠሩላቸው ናቸው፡፡ ከእነዚህም አንዱ “ጾመ ፍልሰታ ለማርያም” ሲሆን ከሕጻናት እስከ አረጋውያን የሚጾም ታላቅ ጾም ነው፡፡
ፍልሰታ ማለት ምን ማለት ነው?
“ፍልሰታ” የሚለው ቃል ፈለሰ፣ ተሰደደ (ተገለጠ)፣መከፈት፣ መገለጥ፣ የመዝጊያ የመጋረጃ ከሚለው የግእዝ ሥርወ ቃል የተገኘ ሲሆን፤ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ትንሣኤ ይመለከታል፡፡ “ፍልሰት” የሚለው ቃል ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር መሔድን ያመለክታል፡፡ “ፍልሰታ ለማርያም” ሲባልም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካረፈች በኋላ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መወሰዷን (ማረጓን)፣ በኋላም ሥጋዋ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ነው፡፡
ጾመ ፍልሰታ ለማርያም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን ያለው ሁለት ሱባዔ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ኾኖ በምእመናን ዘንድ መጾም እንደሚገባው ሥርዓት ሠርተውልናል (ፍትሐ ነገሥት አንቀት ፲፭)፡፡ ይህ ጾምም ‹‹ጾመ ማርያም (የማርያም ጾም)›› ወይም ‹‹ጾመ ፍልሰታ ለማርያም (የማርያም የፍልሰቷ ጾም)›› እየተባለ ይጠራል፡፡ በጾሙም መጨረሻ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ ይከበራል፡፡
የሚነበቡ መጻሕፍት
በጾመ ፍልሰታ በቤተክርስቲያናችን በየቀኑ በማኅሌቱ፣ በሰዓታቱና በቅዳሴው በሚደርሰው ቃለ እግዚአብሔር ነገረ ማርያም ማለትም የእመቤታችን ከመፀነሷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ድረስ ያለው ታሪኳ፣ ለአምላክ ማደሪያነት መመረጧ፣ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ክብሯ፣ ርኅርራኄዋ፣ ደግነቷ፣ አማላጅነቷ፣ ሰውን ወዳድነቷ በስፋት ይነገራል፡፡ እመቤታችንን ከሚያወድሱ ድርሳናት መካከልም በተለይ ቅዳሴ ማርያም፤ ውዳሴ ማርያምም በስፋት ይጸለያል፤ ይቀደሳል፤ ይተረጐማል፡፡ በሰንበታት የሚዘመሩ መዝሙራት፤ በየዕለቱ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ለተዋሕዶ መመረጧን፣ ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን፣ ክብሯን፣ ቅድስናዋን፣ ንጽሕናዋን የሚያወሱ ናቸው፡፡ የእመቤታችን ንጽሕና የነገረ ድህነት፣ የጌታችን ቤዛነት መነሻ፣ መሠረት ነውና፡፡
ሱባኤ በጾመ ፍልሰታ
በጾመ ፍልሰታ በርካታ ምእመናን፣ ካህናት እና ገዳማውያን በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በየገዳማቱና በየአብያተ ክርስቲያናቱ በዓት አዘጋጅተው፣ ሱባኤ ገብተው፣ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፡፡ እንደዚሁም ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ ይህ ጾም ለእመቤታችን ያለንን ፍቅርም የምንገልጽበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ ኦርቶዶክሳውያን ሕፃናት በአብዛኛው ትምህርተ ወንጌል የሚማሩት፤ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የሚቀበሉት በዚህ በጾመ ፍልሰታ ነው፡፡ ሁላችንም በጾመ ፍልሰታ ሳምንታት በጌታችን፣ በእመቤታችንና በቅዱሳን ሐዋርያት ስም በቤተ ክርስቲያን ተሰባስበን ቅዱሳት መጻሕፍትን ከመማር ባሻገር ብንጾም፣ ብንጸልይ፣ ብናስቀድስ፤ እንደዚሁም ሥጋውን ደሙን ብንቀበል በበረከት ላይ በረከትን፤ በጸጋ ላይ ጸጋን እናገኛለን፡፡
ሰአ(ዐ)ሊ ለነ ቅድስት
በቤተክርስቲያናችን በጾመ ፍልሰታ በተለየ መልኩ ከሚነበቡ፣ ከሚተረጎሙ ቅዱሳት መጻሕፍት አንዱ “ውዳሴ ማርያም” ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ከደግነቱ የተነሳ እመቤታችን ተገልጣለት ውዳሴ ማርያምን ደርሶ አመስግኗታል፡፡ ምስጋናውም በሰባቱ ዕለታት የተከፈለ ፷፬ ምዕራፎች ያሉት ነው፡፡ ፷፬ መሆኑም እመቤታችን በዚህ ምድር በሥጋ የኖረችበትን ዘመን ያጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ደግሞ በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ “ሰአ(ዐ)ሊ ለነ ቅድስት” (ቅድስት ሆይ ለምኝልን) የሚለውን ጨምሮበታል፡፡ ሰዐሊ ለነ ቅድስት ተብሎ በዐይኑ ‘ዐ’ ሲጻፍ አዕምሮውን ለብዎውን (ማስተዋሉን) ሳይብን አሳድሪብን ማለት ነው፡፡ ሰአሊ ለነ ቅድስት ተብሎ በአልፋው ‘አ’ ሲጻፍ ለምኝልን ማለት ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቅድስት ቤተክርስቲያን “ሰአ(ዐ)ሊ ለነ ቅድስት” እያለች እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ትለምንልን ዘንድ በጸሎትና በምልጃ ታሳስባለች፡፡
እንደማጠቃለያ
ኦርቶዶክሳውያን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ዕረፍትና ትንሣኤ በማሰብ ከልጇ ከወዳጇ ጸጋና በረከት ለማግኘት በየዓመቱ ጾመ ፍልሰታን እንጾማለን፤ የምንችል ደግሞ ንስሐ ገብተን አስቀድሰን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እንቀበላለን፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር “ሥጋዬን የሚበላ፤ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው” በማለት እንደተናገረ በጾመ ፍልሰታ አረጋውያንና ሕፃናት ብቻ ሳይኾኑ፤ መላው ኦርቶዶክሳውያን ንስሐ ገብተን፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል መንግሥቱን ለመውረስ መዘጋጀት ይኖርብናል /ዮሐ. ፮፥፶፬/፡፡
የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣
የቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋና በረከት አይለየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ዋቤ መጻሕፍት
✍️ ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ
✍️ ነገረ ማርያም ትርጓሜ
✍️ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ፣
✍️ መልክአ ማርያም