20/09/2026
ርእሰ ገዳማት ወአድባራት ጣና ቅዱስ ቂርቆስ አንድነት ገዳም የ3,000 ዓመት የታሪክ በዓልን አከበረ።
ርእሰ ገዳማት ወአድባራት ጣና ቅዱስ ቂርቆስ አንድነት ገዳም በኢትዮጵያ የተመሠረተበትን የሦስት ሺህ (፴፻) ዓመት ታሪካዊ ዘመን በማሰብ አከበረ። ይህ ታላቅ የታሪክና የእምነት ክብረ በዓል የገዳሙን ታሪካዊ እሴት፣ መንፈሳዊ አገልግሎትና የትውፊት ቅርስ በማስታወስ ተከብሯል።
በክብረ በዓሉ ላይ ብፁዓን አባቶች፣ የቤተ ክህነት ኃላፊዎች፣ መምህራን፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳደሪዎች፣ የተጋበዙ እንግዶችና በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ፣ የሊቃውንት ጉባኤ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል፣ የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ቀሲስ ግርማ ባቱ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ፤ መምህር አባ ገብረሥላሴ፣ የገዳሙ አበምኔት፤ መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ የጥናትና ምርምር መምሪያ ኃላፊ፤ መጋቤ ሐዲስ ኃይለእግዚእ አሰፋ፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ፤ ርዕሰ ሊቃውንት አባ ገብረኪዳን ግርማ፣ የገዳሙ የአራቱ ጉባኤያት መምህር፤ ሊቀ ሊቃውንት ሰመዐከነ መልአክ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ኃላፊዎችና ሌሎችም ተገኝተዋል።
በተጨማሪም የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች፣ የታላላቅ ገዳማትና አድባራት አስተዳደሪዎችና አበምኔቶች፣ የተጋበዙ እንግዶችና በርካታ ምእመናን በክብረ በዓሉ ተሳትፈዋል።
የሦስት ሺህ ዓመት የታሪክ በዓሉ የገዳሙን ታሪካዊና መንፈሳዊ አስተዋጽኦ ለማስታወስ፣ የእምነት ትውፊትን ለማጠናከርና ቅርሱን ለትውልድ ለማስተላለፍ ያለውን ጠቀሜታ በማጉላት ተከብሯል።
ፈለገ ገነት ሚዲያ