Dassenech woreda education office የዳ/ወ/ት/ጽ/ቤት

Dassenech woreda education office  የዳ/ወ/ት/ጽ/ቤት

Share

Education

Photos from Dassenech woreda education office  የዳ/ወ/ት/ጽ/ቤት's post 18/06/2026

በዳሰነች ወረዳ 163 የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች የክልል አቀፍ ምዘና እየወሰዱ ነው!

​ኦሞራቴ | ሰኔ 11/2018 ዓ.ም

​በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ፣ የዘንድሮው የ8ኛ ክፍል የክልል አቀፍ ምዘና በታላቅ ድምቀት በኦሞራቴ አዳሪ ትምህርት ቤት ተጀምሯል።

​በዛሬው ዕለት ጠዋት በአማርኛ ፈተና የተጀመረው የዚህ ዓመት ምዘና፣ በወረዳው በተቋቋመው የፈተና ማዕከል፣ በአጠቃላይ 163 ተማሪዎች ፈተናውን በልበ ሙሉነት እየወሰዱ ይገኛሉ።በዚህም መሠረት

​መደበኛ ተማሪዎች፡ 96 ወንዶች እና 40 ሴቶች (በድምሩ 136)

​የግል ተፈታኞች፡ 16 ወንዶች እና 11 ሴቶች (በድምሩ 27)

​ ፈተናው በ1 ማዕከል፣ በ8 አስፈታኝ ትምህርት ቤቶች እና በ10 ባለሙያዎች (የጣቢያ ኃላፊ፣ አስተባባሪዎች እና ፈታኞች) በመታገዝ በስኬት እየተካሄደ ይገኛል።

ለተፈታኞች የተረጋጋ እና ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር፣ በአንድ ክፍል ውስጥ ከ30 ተማሪዎች በታች ብቻ እንዲፈተኑ ተደርጓል።

Photos from Dassenech woreda education office  የዳ/ወ/ት/ጽ/ቤት's post 17/06/2026

የዳሰነች ወረዳ ተማሪዎች ለፈተና ዝግጁ ሆኑ
! 📝​ነገ ሰኔ11/2018ዓ.ም ለሚጀምረው የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች የትምህርት ጉዟቸውን ወሳኝ ምዕራፍ ለመጀመር በአካል እና በስነ-ልቦና ተዘጋጅተዋል።

ዛሬ 9:00 ​ተማሪዎቹ በተመደቡበት የፈተና ጣቢያ በመገኘት ወንበራቸውን ለይተው ተቀምጠዋል::
ይህ ድርጊት ለፈተናው ያላቸውን ከፍተኛ ዝግጁነት በግልጽ የሚያሳይ ተግባር ነው።

Photos from Dassenech woreda education office  የዳ/ወ/ት/ጽ/ቤት's post 17/06/2026

ለ2018 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች የተሰጠ የኦሬንቴሽን መርሃ-ግብር በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ

​ቀን፡ ሰኔ 10/2018 ዓ.ም

ቦታ፡ ኦሞራቴ

​የዳሰነች ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት፣ የዘንድሮውን የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በከፍተኛ ዝግጅት እና ጥንቃቄ ለማካሄድ አስፈላጊውን ሁሉ እያከናወነ ይገኛል። የዚህ ዝግጅት አካል የሆነው የኦሬንቴሽን መርሃ-ግብር ዛሬ ተካሂዷል።

​የዳሰነች ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምንብየው ታምራት፣ ኦሬንቴሽን ለመውሰድ በተገኙት ተማሪዎች ፊት በመገኘት ባስተላለፉት መልዕክት፡ "የ8ኛ ክፍል ፈተና የብዙ ዓመታት ጥረታችሁ የሚለካበት፣ የትምህርት ህይወታችሁን መሰረት የሚጥል ወሳኝ ምዕራፍ ነው፤ ስለዚህም በታላቅ መረጋጋት እና ትኩረት እንድትፈተኑ አደራ እላለሁ" ብለዋል። አያይዘውም ተማሪዎች በፈተና አሞላል ሂደቱ ላይ ማናቸውም ጥያቄ ካላቸው፣ በግልጽ በመጠየቅ ክፍተታቸውን እንዲሞሉ አሳስበዋል።

​የፈተናና ምዘና ቡድን መሪ ተወካይ አቶ ምንዋጋው ደሳለኝ፣ ተማሪዎች የፈተና ውጤታቸው እንዳይበላሽ እና በራስ መተማመን እንዲፈተኑ የሚከተሉትን ወሳኝ ኦሬንቴሽን ሰጥተዋል

✅​ትክክለኛ መረጃ፡ ተማሪዎች መለያ ቁጥራቸውን (Registration Number) እንዲሁም የትምህርት ዓይነት ኮዶችን በመልስ ቅጹ ላይ በትክክል ማጥቆር እንዳለባቸው።
✅​የአሞላል ጥንቃቄ፡ ቀደም ሲል ከተሰጠው ሞዴል ፈተና በመነሳት፣ የመልስ ቅጽ አሞላል ላይ ግራ መጋባት እንዳይኖር በቂ ማብራሪያ ተሰጥቷል
✅የተሳትፎ ሁኔታ፡ ኦሬንቴሽኑን መውሰድ ከነበረባቸው 140 መደበኛ ተማሪዎች መካከል 126 ተማሪዎች ተገኝተው ኦሬንቴሽኑን ወስደዋል። ያልተገኙ ተማሪዎችን በተመለከተም አስፈላጊው ክትትል እንደሚደረግ እና ዛሬ 9:00 ኦሬንቴሽን እንዲወስዱ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
​በዚህ አስፈላጊ የኦሬንቴሽን መድረክ ላይ የተገኝተው
✅የወረዳው ኮማንድ ፖስት አባላት
✅የዞን ደጋፊ ባለሙያ
✅​የፈተና ጣቢያ ኃላፊዎች
✅​የፈተና ጣቢያ ሱፐርቫይዘሮች
✅​ፈታኝ መምህራን
ለተማሪዎቹ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል

​ማሳሰቢያ፡ ሁሉም ተማሪዎች ዛሬ ከሰዓት በ9፡00 ሰዓት በመገኘት፣ የራሳቸውን የመፈተኛ ወንበር እና ክፍል እንዲያዩ እና። ያልተገኙ ተማሪዎችም በዚህ ሰዓት ተገኝተው ኦሬንቴሽኑን እንዲወስዱ እናሳስባለን።

​ለፈተናው ለሚዘጋጁ ተማሪዎቻችን በሙሉ መልካም ዕድል እንመኛለን!

Photos from Dassenech woreda education office  የዳ/ወ/ት/ጽ/ቤት's post 16/06/2026

የ6ኛ ክፍል የክልል ምዘና፡ የፈተና ሰነዶች ከሁሉም የፈተና ጣቢያዎች ወደ ወረዳ ማዕከል በሰላም ገቡ

​በ4ቱም የፈተና ጣቢያዎች ሲካሄድ የነበረው የ6ኛ ክፍል የክልል ምዘና መጠናቀቁን ተከትሎ፣ የፈተና ሰነዶቹ ከየፈተና ጣቢያ ኮማንድ ፖስቶች ተነስተው ወደ ወረዳ ማዕከል ኮማንድ ፖስት በሰላም መግባታቸውን በደስታ እንገልጻለን።

አቶ ምንዋጋው ደሳለኝ ​የዳሰነች ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት የፈተናና ምዘና ቡድን ተወካይ አቶ ምንዋጋው ደሳለኝ እንደገለጹት፣ ዛሬ ከጠዋቱ 5:30 ሰዓት ጀምሮ የትኩረት ማዕከላችን "የሰነዶች ደህንነት እና ርክክብ" ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር። በዚህም መሰረት በአራቱም የፈተና ጣቢያዎች የነበሩ የፈተና ሰነዶች በሙሉ፣ ምንም አይነት እንከን ሳይገኝባቸው ወደ ወረዳ ማዕከል ኮማንድ ፖስት መድረሳቸውን አረጋግጠዋል።

​አቶ ምንዋጋው አያይዘውም፣ ይህ ሂደት የፈተናውን ሂደት ትክክለኛነትና ክብደት የሚያሳይ ቁልፍ ምዕራፍ መሆኑን አስገንዝበዋል። "የተማሪዎቻችን የጥረት ውጤት በታሸገበት ሰነድ ውስጥ በጥንቃቄ ተይዟል። ከየፈተና ጣቢያዎቹ ወደ ወረዳ ማዕከል የተከናወነው የሰነዶች ርክክብ በአስተማማኝ የደህንነት ሰንሰለት የታጀበና የተሳካ ነበር" ብለዋል።

Photos from Dassenech woreda education office  የዳ/ወ/ት/ጽ/ቤት's post 16/06/2026

የ6ኛ ክፍል የክልል ምዘና በድል ተጠናቀቀ!
ሰኔ 09/2018ኦሞራቴ

​ከሰኔ 08 እስከ ሰኔ 09 /2018 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ምዘና፣ በታላቅ ስኬት እና በሰላም ተጠናቋል።

​በአራቱም የፈተና ጣቢያዎች (አዳሪ፣ ሸራ፣ ሀዶ እና ኦቾሎ) የተሰጠውን ፈተና በድምሩ 295 ብርቱ ተማሪዎች ተሳትፈውበታል።

አቶ ምንብየው ታምራት ​የዳሰነች ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፣ ይህንን ስኬት እውን ላደረጉ ሁሉ ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል:፡

​"በወባ ወረርሽኝ መሀል ሳይበገሩ፣ ልጆቻችንን ለትምህርት እንክብካቤ ያደረጋችሁ የጤና ባለሙያዎች፣ በየደረጃው የለፋችሁ የፈተና ጣቢያ ኃላፊዎች፣ ሱፐርቫይዘሮችና ፈታኝ መምህራን፣ እንዲሁም ልጆቻችሁን በሰዓቱ ለፈተና ያደረሳችሁ የተከበራችሁ ወላጆች እና መላው ህብረተሰብ፤ ለሰጣችሁት ድጋፍ ከልብ እናመሰግናለን!"

አቶ ምንዋጋው ደሳለኝ ​የፈተናና ምዘና ቡድን መሪ ተወካይ እንደገለጹት፣ አሁን የፈተናው የሁለተኛ ቀን መጠናቀቅን ተከትሎ የፖሊስ ጣቢያ ቅንጅት ስራዎች በጥብቅ ዲሲፕሊን እየተከናወኑ ይገኛሉ፦
​✅ የፈተና ወረቀቶች ማሰባሰብና ማሸግ፦ ሁሉም የፈተና ወረቀቶች በዝርዝር ተጣርተው በደህና ሁኔታ ታሽገዋል።
✅ የሰነዶች ርክክብ፦ የታሸጉ የፈተና ሰነዶች በኃላፊነት ለወረዳው ኮማንድ ፖስት ማስረከብ ተጀምሯል።
✅ የጣቢያዎች ቁጥጥር፦ ፈተናው የተሰጠባቸው ክፍሎች ከማንኛውም የፈተና ሰነድ የፀዱ መሆናቸው ተረጋግጦ፣ የክፍል ቁልፎች ለርዕሰ መምህራን ተረክበዋል።
❤❤​ለተማሪዎቻችን በሙሉ መልካም ውጤት እንመኛለን! ❤❤

Photos from Dassenech woreda education office  የዳ/ወ/ት/ጽ/ቤት's post 16/06/2026

የዳሰነች ወረዳ የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ምዘና የሁለተኛ ቀን የፈተና መርሐ ግብር ጀመረ

ኦሞራቴ ሰኔ09​/2018 ዓ.ም
​ሰኔ08/2018ዓ.ም የጀመረው የ2018ዓ.ም የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ የትምህርት ምዘና፣ የሁለተኛ እና የመጨረሻ ቀን ፈተና በዛሬው ዕለትም በወረዳው በሚገኙ አራቱም የፈተና ጣቢያዎች የሁለተኛው ቀን የፈተና መርሐ ግብር ተጀምሯል። በዛሬው ዕለትም 295 ተማሪዎች (አዳሪ ት/ቤት ፈተና ጣቢያ 153፣ ሸራ ፈተና ጣቢያ56፣ ሀዶ ፈተና ጣቢያ43፣ ኦቾሎ ፈተና ጣቢያ43) በመገኘት ምዘናውን እየወሰዱ ይገኛሉ።

​በዛሬው ዕለት የሚሰጠው ፈተና ግብረ ገብ እና አካባቢ ሳይንስ ትምህርቶችን ያካተተ ሲሆን፣ ይህ የዘንድሮው የ6ኛ ክፍል የመጨረሻ ምዘና በመሆኑ ​ፈተናው ሲጠናቀቅ በየጣቢያው መከናወን ያለባቸው ተግባራት፡ ​ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።

​የጤና እና የህክምና ድጋፍ አሰጣጥ
​በወረዳው በተከሰተው የወባ ወረርሽኝ ምክንያት፣ ተማሪዎች ፈተናቸውን በሰላም እንዲያጠናቅቁ የትምህርት ጽህፈት ቤቱ ከጤና ዘርፍ ጋር በመቀናጀት ልዩ የህክምና ድጋፍ በማዘጋጀት በየፈተና ጣቢያው በተግባር እየተከናወነ ይገኛል። በየፈተና ጣቢያው የተመደቡ አንድ የጤና ባለሙያ (HO) እና አንድ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኛ ተማሪዎችን በቅርበት እየተከታተሉ ይገኛሉ።
​ቅድመ-ምርመራ እና ክትትል፦ ፈተና ከመጀመሩ በፊት እና በቆይታው ወቅት የተማሪዎች የጤና ሁኔታ ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን፣ የወባ ምልክቶች የታዩባቸው ተማሪዎች ፈጣን ምርመራ እንዲያደርጉ እየተደረገ ይገኛል።
​አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት፦ በፈተና ወቅት ህመም የተሰማቸው ወይም የጤና እክል የገጠማቸው ተማሪዎች፣ በጣቢያው በተዘጋጀው የህክምና ክፍል አስቸኳይ እርዳታ እና አስፈላጊው የህክምና ክትትል እንዲያገኙ እየተደረገ ነው።
​የመድኃኒት አቅርቦት፦ ለወባ ህመም እና ለተለመዱ የጤና እክሎች የሚሆኑ መሰረታዊ መድኃኒቶች በየጣቢያው ተደራጅተው ለህክምናው እየዋሉ ይገኛሉ።

​የፈተናና ምዘና ቡድን መሪ ተወካይ አቶ ምንዋጋው ደሳለኝ፤ "ምዘናው በሰላም መጠናቀቁ ብቻ ሳይሆን፣ ከፈተና በኋላ ያለው የአሰራር ሂደትም በታቀደው መሰረት በታማኝነት እንዲፈጸም ሁሉም የፈተና ጣቢያ ኃላፊዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ" ጥሪ አቅርበዋል።

Photos from Dassenech woreda education office  የዳ/ወ/ት/ጽ/ቤት's post 15/06/2026

የዳሰነች ወረዳ የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ምዘና የመጀመሪያ ቀን ፈተና በሰላም ተጠናቀቀ
ኦሞራቴ | ሰኔ 08/2018 ዓ.ም

​በዳሰነች ወረዳ የተካሄደው የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ምዘና የመጀመሪያ ቀን (8/10/2018 ዓ.ም) ፈተና በጠዋት እና በከሰዓት መርሐ ግብር በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።

በሂደቱ የነበረውን የተማሪዎች ተሳትፎ እና የጤና ድጋፍ አሰጣጥ ስንመለከት፣ በአራቱም የፈተና ጣቢያዎች በድምሩ 295 ተማሪዎች ፈተናውን ወስደዋል።
​የተማሪዎች ክፍፍል በየጣቢያው እንደሚከተለው ነው፦
​✅ አዳሪ ትምህርት ቤት የፈተና ጣቢያ፡ 153 ተማሪዎች (88 ወንድ እና 65 ሴት)።
​✅ ሸራ የፈተና ጣቢያ፡ 56 ተማሪዎች (39 ወንድ እና 17 ሴት)።
​✅ ሀዶ የፈተና ጣቢያ፡ 43 ተማሪዎች (26 ወንድ እና 17 ሴት)።
​✅ ኦቾሎ የፈተና ጣቢያ፡ 43 ተማሪዎች (33 ወንድ እና 10 ሴት)።

​የፈተናና ምዘና ቡድን መሪ ተወካይ አቶ ምንዋጋው ደሳለኝ እንደገለጹት፤ ምዘናው ከማንኛውም እንከን የፀዳ እንዲሆን ጥብቅ የደህንነት እና የዲስፕሊን ቁጥጥር ተደርጓል።

በፈተና ጣቢያዎች አካባቢ በተከሰተው የወባ ወረርሽኝ ምክንያት ህመም የተሰማቸው ተማሪዎች ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ፣ አንድ የጤና ባለሙያ (HO) እና አንድ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኛ ተመድበው አስቸኳይ የህክምና ድጋፍ ሲሰጡ ቆይተዋል።

Photos from Dassenech woreda education office  የዳ/ወ/ት/ጽ/ቤት's post 15/06/2026

የ2018 ዓ.ም የ6ኛ ክፍል የሒሳብ ክልላዊ ፈተና መሰጠት ጀመረ

የ2018 ዓ.ም የ6ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና፣ በወረዳችን በተቋቋሙ 4 የፈተና ጣቢያዎች በተሳካ ሁኔታ እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን​በኦሞራቴ አዳሪ ትምህርት ቤት የፈተና ጣቢያ በተካሄደው ይፋዊ የማስጀመሪያ መድረክ ላይ፦
👉​የክልሉ ትምህርት ቢሮ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ተዋጋ አሰፋ፣
👉​ከደቡብ ኦሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ የተወከሉት ኢንስፔክተር ስንታየሁ ታመነ፣​እንዲሁም ከዞኑትምህርት መምሪያ (ወተመህ) ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ታምሩ ተገኝተው፣ የከሰዓት የሒሳብ ፈተናውን በይፋ አስጀምረዋል።

​የከሰዓት የሒሳብ ፈተናም በየጣቢያው መሰጠት ተጀምሯል። የፈተናው ሂደት በታቀደለት ስነ-ምግባር እና ጥብቅ የክትትል ስርዓት እየተከናወነ ይገኛል።

​ከፈተና ሂደቱ ጎን ለጎን የተማሪዎቻችንን ጤንነት በቅርበት እየተከታተልን እንገኛለን። በኦሞራቴ አዳሪ ትምህርት ቤት የፈተና ጣቢያ በጠዋቱ መርሃ ግብር፣ ጥቂት ተማሪዎች ላይ የታየውን የጤና መታወክ ተከትሎ ፈጣንና ውጤታማ እርምጃ ተወስዷል።
​በጣቢያው በተደረገ የህክምና ምርመራ፣ የጤና እክል ከታየባቸው 5 ተማሪዎች መካከል በ3ቱ ላይ የወባ በሽታ መኖሩ ተረጋግጧል። በዚህም መሰረት፣ የጤና ባለሙያው ህዝቅኤል ተክሌ (HO) እና ሲስተር ማስረሻ ማሞ በፈተና ጣቢያው በአካል በመገኘት፣ አስፈላጊውን የህክምና ክትትል እና ድጋፍ ለተማሪዎቹ እያደረጉ ይገኛሉ።

Photos from Dassenech woreda education office  የዳ/ወ/ት/ጽ/ቤት's post 15/06/2026

295 ተማሪዎች ፈተናውን መውሰዳቸውን አቶ ምንዋጋው ደሳለኝ ገለፁ።በአራቱም የፈተና ጣቢያዎች በተከናወነው የጠዋቱ የፈተና መርሐ ግብር፣ 295(186 ወንድ እና 109 ሴት )የወሰዱ ሲሆን​በዘንድሮው የፈተና ወቅት፣ በተለይም በፈተና ጣቢያዎቻችን አካባቢ የተከሰተው የወባ ወረርሽኝ በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ የጤና እክል ፈጥሯል። አብዛኛዎቹ ተማሪዎች በወባ ህመም በመያዛቸው፣ በተደጋጋሚ በሚከሰት የሰውነት መንቀጥቀጥ ምክንያት ፈተናውን በትኩረት ለማንበብ፣ ጥያቄዎችን ለመረዳት እና መልሶችን በትክክል ለማጥቆር ተቸግረዋል።

​ይህንን የጤና ችግር ለመቀነስ እና ተማሪዎች ፈተናቸውን በተገቢው ሁኔታ እንዲወስዱ ለማስቻል፣ አንድ የጤና ባለሙያ (HO) እና አንድ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኛ በየፈተና ጣቢያው በመገኘት አስቸኳይ የህክምና ድጋፍ እየሰጡ ይገኛሉ።
​ይህ የጤና ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በጠዋቱ የፈተና መርሐ ግብር በአራቱም የፈተና ጣቢያዎች የተማሪዎች ተሳትፎ
👉👉​በሀዶ የፈተና ጣቢያ፡ 26 ወንድ እና 17 ሴት በድምሩ 43 ተማሪዎች፣

👉👉​በኦቾሎ የፈተና ጣቢያ፡ 33 ወንድ እና 10 ሴት በድምሩ 43 ተማሪዎች፣

👉👉​በሸራ የፈተና ጣቢያ፡ 39 ወንድ እና 17 ሴት በድምሩ 56 ተማሪዎች፣

👉👉​በአዳሪ ትምህርት ቤት የፈተና ጣቢያ፡ 88 ወንድ እና 65 ሴት በድምሩ 153 ተማሪዎች ተፈትነዋል።

Photos from Dassenech woreda education office  የዳ/ወ/ት/ጽ/ቤት's post 15/06/2026

የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ምዘና በዳሰነች ወረዳ በድምቀት ተጀመረ
​ኦሞራቴ | ሰኔ 08/2018 ዓ.ም
​የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ምዘና በዳሰነች ወረዳ፣ በኦሞራቴ አዳሪ ትምህርት ቤት በይፋ ተጀምሯል። በጠዋቱ የፈተና መርሃ ግብር በወረዳው በድምሩ 294 ተማሪዎች የተገኙ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 185 ወንዶች እና 109 ሴቶች ይገኙበታል።

​የፈተናና ምዘና ቡድን መሪ ተወካይ አቶ ምንዋጋው ደሳለኝ፣ በፈተና አሰጣጥ ሂደቱ ላይ እንደገለጹት፤ ምዘናው ፍትሐዊ እና ከማንኛውም እንከን የፀዳ እንዲሆን የተሟላ ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠዋል። አቶ ምንዋጋው አክለውም የፈተና አሰጣጡን አስመልክቶ የሚከተለውን ገለጻ ሰጥተዋል፦
​"በአራቱም የፈተና ጣቢያዎች ጥብቅ የደህንነት እና የዲስፕሊን ቁጥጥር እየተደረገ ነው። በአንድ ክፍል ውስጥ በአንድ ፈታኝ መምህር አማካኝነት ቢበዛ 30 ተማሪዎች ብቻ እንዲፈተኑ በማድረግ ለተማሪዎች ምቹ እና የተረጋጋ አካባቢ ተፈጥሯል።"

​የደቡብ ኦሞ ዞን ደጋፊ ባለሙያ አቶ አስረስ አዲሱ በበኩላቸው፣ የዳሰነች ወረዳ የፈተና አሰጣጥ ሂደት ለሌሎች አካባቢዎች አርአያ የሚሆን መሆኑን ጠቁመዋል። አቶ አስረስ አክለውም፣ ወረዳው ለፈተናው የሰጠው ትኩረት የባለድርሻ አካላትን የተቀናጀ ጥረት ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

​የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ሎሲያ እርጉዶ ተማሪዎቹን ሲያበረታቱ፦ "ይህ ፈተና የወደፊት ህልማችሁ መነሻ ነውና በልበ ሙሉነት ተፈተኑ" በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

​የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምንብየው ታምራት በበኩላቸው ተማሪዎችን ሲያበረታቱ እንዲህ ብለዋል፦ "በእጃችሁ ያለው የመልስ ወረቀት ብቻ ሳይሆን፣ የወደፊት ከፍታ የምታነጥፉበት የዕድል ካርታ ነው።" አያይዘውም ተማሪዎች ይህንን የፈተና ወቅት የረጅም ጊዜ ዝግጅታቸው መደምደሚያ እና ለቀጣይ የክልልና የሀገር አቀፍ ፈተናዎች መነሻ እንዲያደርጉት አደራ ብለዋል።
​የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ምዘና እስከ ሰኔ 09/2018 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።

Want your school to be the top-listed School/college in Awassa?

Click here to claim your Sponsored Listing.

Location

Category

Telephone

Address


Omorate
Awassa