ትምህርተ ክርስቶስ

ትምህርተ ክርስቶስ

Share

Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from ትምህርተ ክርስቶስ, Education, Addis Ababa.

05/12/2021

Krstos sinegs

10/12/2020

• ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የጾም ወቅት ከመኮነንና ከመፍረድ በመቆጠብ ይቅርታ የምናደርግበት ወቅት ነው!
• “የሰማይ አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ ርኅሩኆች ሁኑ፣ አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም፤ አትኰንኑ አትኰነኑምም። ይቅር በሉ ይቅርም ትባላላችሁ” (ሉቃስ 6፡36)

10/12/2020

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት
• ጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አሰተምህሮ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ፡ “ምስጢረ ጥመቀት የክርስትና ሕይወት መሰረት ነው”

10/12/2020

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት
ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ መጪው ጊዜ “የቅዱስ ዮሴፍ ዓመት” እንዲሆን አወጁ!
በላቲን ቋንቋ “Patris corde” በአማርኛው በግርድፉ ሲተረጎን “የአብ ልብ” በሚል አርእስት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሕዳር 29/2013 ዓ.ም ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልዕእክት ቅዱስ ዮሴፍ “የአለም አቀፋዊቷ ቤተክርስቲያን የበላይ ጠባቂ” መሆኑ የታወጀበት የ150 ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የሚያስታውስ ሐዋርያዊ መልእክት እንደ ሆነም ተገልጿል። ይህንን ቅዱስ ዮሴፍ “የአለም አቀፋዊ ቤተክርስቲያን የበላይ ጠባቂ” መሆኑ የታወጀበት የ150 ኛ ዓመት የሚዘክር በዓል ከሕዳር 29/2013-ሕዳር 29/2014 ዓ.ም ደረስ እንድከበር ቅዱስነታቸው የወሰኑ ሲሆን ጊዜውም “የቅዱስ ዮሴፍ ዓመት” ተብሎ እንዲጠራ ቅዱስነታቸው አውጀዋል።

በላቲን ቋንቋ “Patris corde” በአማርኛው በግርድፉ ሲተረጎን “የአብ ልብ” በሚል አርእስት በቅርቡ ይፋ የሆነው ሐዋርያዊ መልእክት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ ቅዱስ ዮሴፍን እንደ ተወዳጅ፣ ርህሩህ እና አፍቃሪ፣ ታዛዥ ፣ ተቀባይ የሆነ አባት እንደሆነ የሚገልጽ ሐዋርያዊ መልእክት ሲሆን በተጨማሪም የፈጠራ ችሎታ ያለው፣ ብርቱ የሆነ ጥላ ከለላ መሆን የሚችል አባት እንደ ሆነም ገልጸዋል።

ሐዋርያዊ መልእክቱ ከእዚህ ቀደም የነበሩት ብፁዕ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒየስ 9 ኛ “ቅዱስ ዮሴፍ የአለም አቀፋዊ ቤተክርስቲያን ጠባቂ” መሆኑ የታወጀበት የ 150 ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የሚዘክር ነው። ዓመቱን ለማክበር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የቅዱስ ዮሴፍ ዓመት” በማለት የጎሮጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በሕዳር 29/2013 ዓ.ም “የጽንሰታ ማርያም” አመታዊ በዓል በተከበረበት ወቅት ቅዱስነታቸው ያወጁት “የቅዱስ ዮሴፍ ዓመት” ሲሆን ይህ አመት እስከ ሚቀጥለው ሕዳር 29/2014 ዓ.ም ድረስ ለአንድ አመት ያህል የሚከበር በዓል ነው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በላቲን ቋንቋ “Patris corde” በአማርኛው በግርድፉ ሲተረጎም “የአብ ልብ” በሚል አርእስት በቅርቡ ያፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልእክት ዳራ ውስጥ “ኮቪድ -19” ወረርሽኝ የተካተተበት ሲሆን ይህንን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተመለከተ በሐዋርያዊ መልእክቱ ውስጥ እንደ ተጠቀሰው ወረርሽኙ የብርሃን እይታ ክብር ርቋቸው የነበሩ ቢሆኑም በትዕግሥት የተቀመጡ እና በየቀኑ ተስፋ የሚያደርጉ “ተራ” ተብለው የተፈረጁ ሰዎች አስፈላጊነት በበለጠ በግልጽ እንድንረዳ ረድቶናል በማለት ገልጸዋል። በዚህ ውስጥ “ብዙም ያልተሰተዋለው ሰው በዕለት ተዕለት ሕይወቱ በአስተዋይነት እና ምስጢራዊ በሆነ መልኩ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርግ” የነበረውን ቅዱስ ዮሴፍን እነዚህ “ተራ” ተብለው የፈረጁ ሰዎች በእዚህ ረገድ እርሱን እንደ ሚመስሉ የገለጹ ሲሆን ሆኖም ቅዱስ ዮሴፍ አንዳደርገው እነርሱም “በመዳን ታሪክ ውስጥ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሚና” እንደ ሚጫወቱ ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ መልእክታቸው አክለው ገልጸዋል።

የተወደደ ፣ ርህሩህ ፣ ታዛዥ አባት

ቅዱስ ዮሴፍ በእውነቱ “የእርሱን አባትነት በግልጽ አሳይቷል” ይህንንም ያሳየው ራሱን ለቤተሰቡ በፍቅር በማቅረብ “በቤቱ ውስጥ በጥበብ እያደገ ለሄደው መሲህ አገልግሎት የተሰጠ ፍቅር ነው” በማለት የቀድሞው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ስለ ቅዱስ ዮሴፍ መናገራቸውን በመጥቀስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእዚህ ሐዋርያዊ መልእክታቸው አክለው ገልጸዋል።

እናም “በብሉይ እና በአዲስ ኪዳን መካከል ባለው መንታ መንገድ” ላይ ሚና ስለነበረው ቅዱስ ዮሴፍ “በክርስቲያኖች ዘንድ ሁል ጊዜ እንደ አባት ተከብሯል” (አንቀጽ ቁ. 1) በማለት ይህ ሐዋርያዊ መልእክት ይገልጻል። በእርሱ ውስጥ “ድክመታችንን እንድንቀበል የሚረዳን ኢየሱስ እግዚአብሔርን በርህራሄ የተሞላ ፍቅር አየ” ምክንያቱም በብዙ ፍርሃቶች ፣ ድክመቶች እና ውድቀቶች ቢኖሩብንም እንኳን አብዛኞቹ በእርሱ መለኮታዊ እቅዶች ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው እርሱ አያሳፍረንም የሚል እንድምታ የያዙ አንቀጾች የሚገኙበት ሐዋርያዊ መልእክት ነው። “ከከሳሾቹ ወጥመዶች የሚያድነን ርህራሄ ፍቅር ብቻ ነው” በማለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእዚህ ሐዋርያዊ መልእክታቸው የገለጹ ሲሆን በተለይም “እውነቱን እና ርህራሄውን የምንለማመደው” የእግዚአብሔርን ምህረት የእርቅ ምስጢር በሆነው በምስጢረ ንስሃ አማካይነት ብቻ ነው-ምክንያቱም “እግዚአብሔር እውነት መሆኑን እናውቃለን አያወግዘንም ነገር ግን ይልቁኑ ይቀበለናል፣ ይቀርበናል ፣ ይደግፈናል እንዲሁም ይቅር ይለናል ”(አንቀጽ ቁ. 2) የሚሉ ጭብጦች በሐዋርያዊው መልእክቱ ውስጥ በስፋት ተገልጿል።

ቅዱስ ዮሴፍ እግዚአብሔርን በሚገባ ይታዘዝ የነበረ አባት ነው - በእሽታው አማካኝነት ማርያምን እና ኢየሱስን በመንከባከብ እንዲሁም ልጁ “የአባቱን ፈቃድ እንዲፈጽም” ያስተምረው ነበር። የኢየሱስን ተልእኮ እንዲያገለግል በእግዚአብሔር የተጠራው ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደተናሩት “በእውነትም የመዳን ታሪክ አገልጋይ ነው” (አንቀጽ ቁ.3) በማለት “በደህንነት ታሪክ ታላቅ ምስጢር ውስጥ ተባባሪ” (አንቀጽ ቁ. 3) ነበር በማለት ይገልጻል።

የእግዚአብሔርን ፈቃድ መቀበል

በተመሳሳይ መልኩም ቅዱስ ዮሴፍ “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማርያምን ስለተቀበላት ተቀባይ የሆነ አባት” ነው ምክንያቱም - ዛሬም ቢሆን አስፈላጊ የሆነው ምልእክት ይህ እንደሆነ የገለጹት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእዚህ ሐዋርያዊ መልእክት ውስጥ እንደ ተናገሩት “በሴቶች ላይ የስነልቦና ፣ የቃል እና የአካል ጥቃቶች በግልጽ በሚታዩበት በዚህ ዓለም ውስጥ” የቅዱስ ዮሴፍን ታሪክ ማሳትወስ ተገቢ ነው ብለዋል። ነገር ግን የማርያም እጮኛ የነበረው ቅዱስ ዮሴፍ እንዲሁ በጌታ በመተማመን በሕይወቱ ሊኖሩ የማይገባቸውን ክስተቶች እንኳን የሚቀበል ፣ “የራሱን ሀሳብ ወደ ጎን በመተው” እና እራሱን ከራሱ ታሪክ ጋር የሚያስታርቅ ቅዱስ እንደ ነበረ በስፋት ተገልጿል።

የቅዱስ ዮሴፍ መንፈሳዊ ዳራ ወይም ጎዳና “በቃል ብቻ የሚገልፅ አይደለም፣ ነገር ግን ሁኔታዎችን የሚቀበል ነው” ይህ ማለት ደግሞ “እሱ ስልጣኑን ለቀቀ” ማለት አይደለም። ይልቁንም እሱ “በድፍረት እና በንቃት ይጠባበቅ ነበር” ምክንያቱም “በመንፈስ ቅዱስ የፅናት ስጦታ” እና በተስፋ በመሞላት በሁሉም ተቃርኖዎች ፣ ተስፋ መቁረጦች እና ብስጭቶች” ውስጥ የነበረ ቢሆንም እንኳን ህይወቱን እንዳለ ተቀብሎታል። በቅዱስ ዮሴፍ አማካይነት እግዚአብሔር በተግባር “አትፍሩ!” የሚለን ሲሆን ምክንያቱም “እምነት ለደስታ ሆነ ለሐዘን ለእያንዳንዱ ክስተት ትርጉም ይሰጣል” እንዲሁም “እግዚአብሔር ድንጋያማ ከሆነ መሬት ውስጥ አበባ እንዲበቅል ማድረግ ይችላል” እንድንል ያደርገናል የሚሉ ጭብጦች በእዚህ ሐዋርያዊ መልእክት ውስጥ ተካተዋል። ቅዱስ ዮሴፍ “አቋራጭ የሆኑ መንገዶችን አልፈለገም ነበር፣ ነገር ግን በእውነተኛ ዓይን ነገሮችን ፊት ለፊት ተጋፈጠና እሱ የግል ሀላፊነትን ተቀበለ”። በዚህ ምክንያት “ያለምንም ልዩነት ሌሎችን እንደነሱ እንድንመለከት እና እንድንቀበል እንዲሁም ለደካሞች ልዩ በሆነ መልኩ አሳቢ መሆናችንን እንድናሳይ ያበረታታናል” (አንቀጽ ቁ.4) እንደ ተጠቀሰው።

በድፍረት የተሞላ፣ የፍቅር ማስሌ የሆነ አባት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በላቲን ቋንቋ “Patris corde” በአማርኛው በግርድፉ ሲተረጎም “የአብ ልብ” በሚል አርእስት በቅርቡ ያፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልእክት የቅዱስ ዮሴፍን “በፈጠራ ችሎታ የተሞላ ድፍረትን” ጎላ አድርገው አሳይተዋል፣ “በተለይም ችግሮች በሚያጋጥሙን ወቅት ችግሮችን እንዴት መቋቋም እንደ ምንችል መንገዱን የሚገልጥልን ነው”። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በእዚህ ሐዋርያዊ መልእክታቸው አክለው እንደ ገለጹት “የናዝሬቱ አናጺ” በመለኮታዊ ጥበቃ በመተማመን አንድ ችግርን ወደ አዲስ አጋጣሚ መለወጥ ችሏል። በቤተሰቡ ውስጥ ያጋጠሙት “ተጨባጭ ችግሮች” በዓለም ላይ ያሉ ሌሎች ቤተሰቦች በተለይም ደግሞ ስደተኛ የሆኑ ቤተሰቦች ችግሮቻቸውን እንዴት መቋቋም እንደ ሚችሉ ትምህርት የሰጠ ክስተት እንደ ሆነ አክለው ገልጸዋል።

ከዚህ አንፃር ቅዱስ ዮሴፍ “በጦርነት ፣ በጥላቻ ፣ በስደት እና በድህነት ምክንያት የትውልድ አገራቸውን ለቀው እንዲወጡ የተገደዱት ሁሉ ልዩ ረዳታቸው ነው” ብለዋል። የኢየሱስ እና የማሪያም ጠባቂ እንደመሆኑ መጠን ቅዱስ ዮሴፍ የእናትነት እና የክርስቶስ አካል ምስል የሆነችው “የቤተክርስቲያኗ ጠባቂ” ካልሆነ በስተቀር ሌላ ነገር ሊሆን አይችልም። “ስለሆነም ሁሉም ድሆች ፣ ችግረኞች ፣ በመከራ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ወይም የሚሞቱ ሰዎች ፣ ሁሉም እንግዶች ፣ ሁሉም እስረኞች ፣ አቅመ ደካሞች ሁሉ ቅዱስ ዮሴፍ ጥበቃ የሚያደርግላቸው” ሰዎች ናቸው። “ከቅዱስ ዮሴፍ” አሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሐዋርያዊ መልእክታቸው “እኛ ቤተክርስቲያንን እና ድሆችን መውደድ መማር አለብን” (አንቀጽ ቁ. 5) ብለዋል።

የሥራ ዋጋን ፣ ክብርን እና ደስታን የሚያስተምር አባት

ቅዱስ ዮሴፍም “ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ለማሟላት በሐቀኝነት የሠራ አናጺ” የነበረ ሰው ሲሆን እርሱም “ደግሞም የራሳችን ድካም ፍሬ የሆነውን እንጀራ መብላት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው፣ ክብርና ደስታ እንደ ሚሰጥ” ያስተምረናል በማለት የሚገልጹ ጭብጦች ተካተውበታል። ይህ የቅዱስ ዮሴፍ የባህርይ ገጽታ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እንዳሉት በተወሰነ ደረጃ ደህንነታቸው በተጠበቀ ሀገሮች ውስጥ እንኳን “አስቸኳይ ማህበራዊ ጉዳይ” የሆነው ሥራን የሚደግፍ አቤቱታ ለማቅረብ እድል ይሰጣቸዋል በማለት የገለጹ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አክለው እንደ ገለጹት “የተከበረ ሥራን አስፈላጊነት የማድነቅ አዲስ ፍላጎት አለ ፣ ከእነዚህም ውስጥ ቅዱስ ዮሴፍ አርአያ የሚሆን ረዳታችን ነው” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሥራ “በደህንነት ምስጢር ውስጥ ለመሳተፍ ፣ የመንግሥቱን መምጣት ለማፋጠን ፣ ችሎታዎቻችንን እና ክህሎቶቻችንን ለማዳበር እና በህብረተሰብ እና በወንድማማች ኅብረት ውስጥ ለማገልገል የሚያስችል አጋጣሚ ነው” እንደ ሆነ ገልጸዋል። የሚሰሩ ሰዎች “ከእራሱ ከእግዚአብሄር ጋር በመተባበር እና በሆነ መንገድ በዙሪያችን ያለው ዓለም ፈጣሪዎች ይሆናሉ” ሲል ገልጸዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ገለጹት አዲስ መደበኛ ሁኔታዎችን መልሶ ለማምጣት ይችላ ዘንድ “ሁሉም ሰው የሥራን ዋጋ ፣ አስፈላጊነት እና ጠቃሚነት እንደገና እንዲያሳውቁ” በእዚህ ሐዋርያዊ መልእክት ያበረታታሉ። በተለይም በኮቪ -19 በተስፋፋው ወረርሽኝ ምክንያት እየሰፋ ከመጣው የሥራ አጥነት አንጻር ሊቃነ ጳጳሳቱ ሁሉም ሰዎች “ቅድሚያ የምሰጧቸውን ነገሮች መልሰው እንዲገመግሙ” እንዲሁም ማንም ወጣት ፣ ማንም ሰው ፣ ቤተሰብ ያለ ሥራ መቆየት እንደሌለባቸው ጽኑ እምነታቸውን እንዲገልጹ ጥሪ አቅርበዋል! (አንቀጽ ቁ. 6)

እንደ አባት በማርያምና ​​በኢየሱስ ላይ ያተኮረ ነበር

ከአባትነቱ ጥላ ፍንጭ በመውሰድ የፖላንዳዊው ጸሐፊ ጃን ዶብራኪንስኪ መጽሐፉ ውስጥ የጠቀሰውን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዋቢነት የገለጹ ሲሆን ቅዱስ ዮሴፍ የኢየሱስ አባት መሆኑን “የሰማያዊ አባት ምድራዊ ጥላ” በማለት ገልፀዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ አክለው በሐዋርያዊ መልእክታቸው እንደ ገለጹት “አባቶች አልተወለዱም ፣ ነገር ግን የተፈጠሩ ናቸው” ብለዋል። አንድ ሰው ልጁን ወደ ዓለም በማምጣቱ ብቻ አባት ሊሆን አይችልም፣ ነገር ግን ያንን ልጅ የመንከባከብ ኃላፊነት በመወጣት ጭምር ነው አባትነቱን ሊያረጋግጥ የሚችለው ብለዋል። እንደ አለመታደል ሆኖ በዛሬው ህብረተሰብ ውስጥ ልጆች “ብዙውን ጊዜ ሕይወትን እና እውነታን የሚያስተምሯቸው ወላጆችን በማጣታቸው የተነሳ ወላጅ አልባ ሆነው ሲኖር ይታያሉ። ልጆች አሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ልጆች እንደሚሉት እነሱን ለመቆጣጠር የማይሞክሩ አባቶችን ይፈልጋሉ፣ ይልቁንም “እራሳቸውን የመወሰን ፣ ነፃነትን የማጣጣም እና አዳዲስ ዕድሎችን የመፈለግ ችሎታ” እንዲኖራቸው አሳዳጊ ወላጆች ያስፈልጓቸዋል ብለዋል።

ይህ ቅዱስ ዮሴፍ “በጣም ንፁህ” አባት ተብሎ የተገለጸበት ስሜት ሲሆን” ይህም የበላይ ሆኖ መግዛት ከሚለው ሐሳብ በተቃራኒ ጎራ የሚገኝ ነው። ቅዱስ ዮሴፍ አሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ልዩ በሆነ ነፃነት እንዴት መውደድ እንደሚቻል ያውቅ ነበር። እሱ ራሱን የነገሮች ማዕከል በጭራሽ አላደረገም። እሱ ስለራሱ አላሰበም፣ ይልቁንም በማርያምና ​​በኢየሱስ ሕይወት ላይ አተኩሯል” የሚሉ አንቀጾች ይንጸባረቁበታል።

ቅዱስ ዮሴፍ የነበረው ደስታ እውነተኛ በሆነ መልኩ ራስን ስጦታ አድርጎ ማቅረብን ያካተተ ነበር፤ “በእርሱ ውስጥ መቼም ቢሆን ብስጭትን አናይም፣ ነገር ግን መተማመንን ብቻ ነው የምንመለከተው” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእዚህ ሐዋርያዊ መልእክታቸው ገልጸዋል። በትዕግሥት ያሳየው ዝምታ ተጨባጭ የመተማመን መግለጫዎች ቅድመ ዝግጅት ነበር። ስለሆነም ቅዱስ ዮሴፍ “አባቶችን በሚፈልግ” በዛሬው የአባገነንነት መንፈስ በሚታይበት አለማችን ውስጥ በተለይም በእኛ ጊዜ አርአያ የሆነ ምሳሌ ሆኖ ጎልቶ ይታያል፣ “ስልጣን ከአምባገነንነት፣ አገልግሎት ከአገልጋይነት ፣ መወያየት ከጭቆና ጋር ማያያዝ ፣ በጎ አድራጎትን ከድህነት አስተሳሰብ ጋር፣ ኃይልን ከጥፋት ጋር በማዝመድ ግራ የሚጋቡትን የማህበረሰብ” ክፍሎች የቅዱስ ዮሴፍ ሕይወት ምሳሌ ይሰጣቸዋል።

እውነተኛ አባቶች በምትኩ “ስለ ልጆቻቸው ሲሉ የራሳቸውን ሕይወት ለመኖር እምቢ ይላሉ” ይልቁንም ነፃነታቸውን ያከብራሉ። በዚህ አባባል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እንደ ገለጹት አንድ አባት “ልጆቹ በእርሱ ላይ ጠግኛ መሆናቸውን እና ማንም ሰው ሳያጅባቸው በሕይወት ጎዳናዎች ላይ መጓዝ የማችሉ መሆናቸውን የሚረዳ ከሆነ እርሱ ትክክለኛ አባት ነው በማለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በአጽንኦት ገልጸዋል፣ አባት መሆን ማለት “ከንብረት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ፣ ይልቁንም ወደ ታላቅ አባትነት “የሰማይ አባት” የሚጠቁም‘ ምልክት ’ነው” (አንቀጽ ቁ.7) ብለዋል።

ለቅዱስ ዮሴፍ የሚደረግ ዕለታዊ ጸሎት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሐዋርያዊ መልእክታቸው መደምደሚያ ላይ እንደ ገለጹት “ከአርባ ዓመት በላይ በየቀኑ የጠዋት ጸሎት በሚያደርጉበት ወቅት ለቅዱስ ዮሴፍ የሚደረገው እና በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የነበረው በፈረንሳይኛ ቋንቋ የተጻፈ የፀሎት መጽሐፍ የተወሰደ የኢየሱስ እና የማርያም ማሕበር አባላት ጸሎት ይጸልዩ” እንደ ነበረ ተናግረዋል። ይህ ጸሎት አሉ ቅዱስነታቸው አምልኮ እና መተማመንን ይገልጻል፣ አልፎ ተርፎም ቅዱስ ዮሴፍ የገጠመውን ፈታኝ ሁኔታ ይገልጻል፣ በማጠቃለያ ቃላቱ ጸሎቱ እንድህ ይላል “የምወድህ አባቴ ፣ መተማመኔ ሁሉ በአንተ ላይ ነው። እያንዳንዱን ነገር ማድረግ ስለቻልኩኝ አንተን በከንቱ ጠርቼሃለሁ አይባልም፣ እናም ሁሉንም ነገር በኢየሱስ እና በማሪያም ማድረግ ስለምትችል፣ መልካምነትህ እንደ ኃይልህ ታላቅ መሆንህን ያሳየኝ” የሚለውን ጸሎት ለባለፉት 40 አመታት ያህል በእየቀኑ መድገማቸውን ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ መልእክታቸው ገልጸዋል።

በሐዋርያዊ መልእክታቸው ማጠቃለያ ላይ ለቅዱስ ዮሴፍ ሌላ አዲስ ጸሎት አክለዋል፣ ሁላችንም አብረን እንድንጸልይ ቅዱስነታቸው ያበረቱናል። እንዲህም ይላል . . .

የአዳኙ ጠባቂ ፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም እጮኛ።

እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ለአንተ በአደራ ሰጠ፣

ማርያም በአንተ ላይ መተማመኗን አደረገች፣

ከእናንተ ጋር ክርስቶስ ሰው ሆነ።

የተባረክ ቅዱስ ዮሴፍ ሆይ ለእኛም ራስህን እንደ አባት አድርገህ አሳየን፣

በሕይወት ጎዳና ላይ ምራን።

እኛ ጸጋን ፣ ምህረትን እና ብርታትን እንድናገኝ አድርገን ከክፉም ሁሉ ጠብቀን።

አሜን!

17/05/2020

የፖምፔይ እመቤታችን ማርያም ቤተመቅደስ - በጣልያን

17/05/2020

በዓለም አቀፍ የጥሪ ቀን፥ “ለእግዚአብሔር እውነተኛ መልስ እንድንሰጥ ተጠርተናል”።

16/05/2020

ቤተሰባችን” ወረርሽኙ ያመጣው የጸጥታ ጊዜ የመለወጥ እንጂ የጭንቀት መሆን የለበትም!

ክቡራት እና ክቡራን የ“ቤተሰባችን” ዝግጅት ተከታታዮቻችን እንደምን ሰንብታችኋል። በዛሬው ሳምንታዊ የ“ቤተሰባችን” ዝግጅት ዓለማችንን በማስጨነቅ ላይ በሚገኝ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ የተሰጡ አንዳንድ አስተያየቶችን እናካፍላችኋለን።

በማኅበራዊ መገናኛዎች ስለ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መወራት ከጀመረ ወራት አልፈዋል። ስለ ቫይረሱ እና የመተላለፊያ መንገዶች በሚገባ አውቀን ራሳችንን እና ሌሎችን ከሞት ማትረፍ የእያንዳንዳችን ግዴታ ነው። ወረርሽኙ በቅርብ ወራት በመቶ ሽህዎች የሚቆጠር የሰው ሕይወት ለሞት መዳረጉ አደገኛነቱን እጅግ አጉልቶታል።

ስለ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ብዙ ተብሏል። በተለይ ፈዋሽ መድኃኒት እሳካሁን አለመገኘቱ መላውን ዓለም ጭንቀት ውስጥ ከቶታል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጤና ተቋም የቫይረሱን መዛመት ለመቆጣጠር የሚያግዙ ምክሮችን በየጊዜው ለአገራቱ እያዳረሰ ይገኛል። ይህ መረጃ በሁሉም የዓለማችን አካባቢዎች መልካም ውጤት እያስገኘ ነው ባይባልም ጥንቃቄዎችን በተግባር በሚያውሉ አካባቢዎች የቫይረሱ መዛመት ከመቀነሱ በላይ የሟቾች ቁጥርም ዝቅ ማለቱ የሚያስመሰግን ነው። የቫይረሱ መዛመት በመላው ዓለም በቁጥጥር ካልዋለ መልካም ውጤት ተገኘ ማለት አይቻልም። ምክንያቱም ተመልሶ ማጥቃቱ አይቀርምና። ለዚህም ነው ወረርሽኙ ዓለም አቀፍ ትብብርን እና ጥረትን ይጠይቃል የሚባለው።

የቫይረሱን መዛመት ለመቀነስ ሲባል መንግሥታት የተለያዩ እርምጃዎች ወስደዋል። መሥሪያ ቤቶች እና የትምህርት ተቋማትእንዲዘጉ፣ የስፖርት ማዕከላት፣ የአምልኮ ሥፍራዎች፣ ባጠቃላይ ሰው በብዛት የሚገኙባቸው ቦታዎች ለጊዜው እንዲዘጉ ተደርገዋል። በተለያዩ ምክንያቶች ተለያይተው የቆዩ የቤተሰብ አባላት ወደ ቤታቸው ተመልሰው በአንድነት የሚሆኑበት አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋል። ይህን አጋጣሚ በመልካም ጎኑ ስንመለከተው ቤተሰባዊ ግንኙነት እና የእርስ በእርስ መረዳዳት ማደጉን እንገነዘባለን። ባሁኑ ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የቤተሰብ አባላትን ብቻ ሳይሆን ጎረቤትን፣ ቀበሌዎችን፣ ወረዳዎችን፣ አውራጃዎችን፣ ክፍላተ ሃገራትን፣ ሃገራትን ወይም መንግሥታትን በማቀራረብ አንዱ ለሌላው እንዲጨነቅ እና በመካከላቸው መረዳዳት እንዲኖር አድርጓል። ዜጎች ስለ ሕዝባቸው በመጨነቅ ከወረርሽኙ የሚተርፉበትን የገንዘብ፣ የእውቀት እና የጉልበት እርዳታ በማስተባበር አለኝታነትን እና ፍቅርን በማሳየት ላይ ይገኛሉ። ወረርሽኙ በባሕሪው የመንግሥታትን፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን እና የግለሰቦችን ትብብር የሚጠይቅ መሆኑ ግልጽ ነው።

የሐይማኖት ተቋማት ተቀራርበው ይቅርታን በመደራረግ፣ ከዚህ አስከፊ ወረርሽኝ እግዚአብሔር እንዲታደጋቸው በማለት ምዕመናኖቻቸውን በማስተባበር ተንበርክከው ምሕረቱን በመለመን ላይ ይገኛሉ። ሁላችንም እንደምንረዳው አሁን የምንገኝበት ወቅት አንዴ ቆም ብለን ብዙ ነገሮችን እንድናስብ፣ ህሊናችንን እንድንመረምር ይጋብዘናል። የተጓዘንባቸው የሕይውት መንገዶቻችን ምን እንደሚመስሉ፣ ወደ ፊት ሕይወታችንን እንዴት መምራት እንዳለብን ለማሰብ ጥሩ አጋጣሚን ፈጥሮልናል ማለት ይቻላል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሚያዝያ 13/2012 ዓ. ም. “የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያመጣውን የጸጥታ ጊዜ በመጠቀም ከእግዚአብሔርን እና ከራሳችን ጋር መነጋገር የምንችልበትን አቅም ለማግኘት በርትተን መጸለይ ያስፈልጋል” ማለታቸው ይታወሳል። አሁን የምንገኝበት ጊዜ በሕይወታችን መሠረታዊ ለውጥን ለማምጣት ምቹ አጋጣሚ፣ የምሕረት እና የጸጥታም ጊዜ መሆኑን አንድ የፍራንችስካዊያን ካፑቺን ታናናሽ ወንድሞች ማኅበር አባል የሆኑት አባ ኤሚሊያኖ አንተኑቺ አስረድተዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሰው ሕይወት ላይ እያስከተለ ያለውን የሞት አደጋ ብቻ ተመልክተን በፍርሃት እና በጭንቀት ከመኖር ይልቅ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በጸሎት የምንቀርብበት መልካም አጋጣሚ መሆኑን መጠቀም እርስ በእርስ መጽናናትን፣ ከወረርሽኙ አስቀድሞ ይሁን በኋላ፣ በተለያዩ ችግር ውስጥ ለሚገኙት ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እርዳታችንን፣ በሕዝቦች፣ በመንግሥታት እና በሐይማኖት ተቋማት መካከል ያመጣውን ኅብረት መመልከት እና ማስታወሱ መልካም ይሆናል።

16/05/2020

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሰላም እንዲነግሥ፣ ወረርሽኙም እንዲቆም የማርያምን እርዳታ እንጠይቅ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ግንቦት 5/2012 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው፣ ሰላም እንዲወርድ እንዲሁም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዲቆም የእመቤታችን ቅድስት ማርያም እርዳታን በጸሎት እንጠይቅ ብለዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ እንደገለጹት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር ግንቦት 13/1917 ዓ. ም. በፖርቱጋል አገር፣ ፋጢማ በምትባል መንደር ውስጥ ብጽዕት ድንግል ማርያም ለሦስቱ እረኞች የታየችበት ዕለት መሆኑን አስታውሰዋል። ግንቦት 5/2012 ዓ. ም. በብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ አውጉስቶ ዶስ ሳንቶስ የተመራው የመስዋዕተ ቅድሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት እና የፋጢማ እመቤታችን ድንግል ማሪያም ካቴድራል መሪ ካህን የሆኑት ክቡር አባ ካርሎስ ካቤቺናስ መልዕክ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት የተነሳ በቪዲዮ ምስል አማካይነት ለምዕመናን በቀጥታ የተሰራጨ መሆኑ ታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

በፖርቱጋል፣ ፋጢማ በምትባል መንደር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለመጀመሪያ ጊዜ ለሦስት እረኞቹ የታየችው እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ግንቦት 13/1917 ዓ. ም. መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውሰው በማከልም ለእግዚአብሔር እና ለባልንጀራ የማያቋርጥ ፍቅር ሊኖረን ይገባል ብለዋል።

ለወጥ የሚገኝበት መንገድ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ግንቦት 5/2012 ዓ.ም. ሳምንታዊውን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ካቀረቡ በኋላ ለፖርቱጋል ቋንቋ ተናጋሪዎች ሰላምታቸውን ካቀረቡ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥያቄ እና ቤተክርስቲያንም እንደምትመክረን በያዝነው የግንቦት ወር ምዕመናን በየቀኑ የመቁጠሪያ ጸሎት በመድገም ጸሎታቸውን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲያቀርቡ አደራ ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም በእመቤታችን ጥበቃ ሥር ከሆንን፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት የምንከተል ከሆነ የሚደርስብንን ስቃይ እና መከራ በትዕግስ መሻገር እንችላለን ብለው፣ ዘወትር ከእመቤታችን ጋር በጸሎት የምንተባበር ከሆነ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመድረስ በምናደርገው የለውጥ ጉዞ ቅድስት ማርያም ታግዘናለች ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እና የፋጢማው ቅድስት ማርያም፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ግልጸት በማስታወስ ለፖላንድ ምዕመናን ባቀረቡበት የሰላምታ መልዕክታቸው፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ለመላው ዓለም ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር ግንቦት 13/1981 ዓ. ም. የተቃጣባቸውን የግድያ ሙከራ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እናታዊ ጥበቃ ለመትረፍ እንደቻሉ መናገራቸውን አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም ወደ እግዚአብሔር አብ በምናቀርበው ጸሎት፣ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ በዓለማችን ሰላም እንዲወርድ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዲቆም፣ የንስሐ እና የመለወጥ መንፈስ እንጠይቅ ብለዋል።

የብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ አጉስቶ ሰላምታ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት ለመላው ዓለም ምዕመናን ልባዊ ሰላምታቸውን ማስተላለፋቸው ታውቋል። በተመሳሳይ መልኩ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዳይስፋፋ በሚል ስጋት በፖርቱጋል ዋና ከተማ ሊዝቦን ግንቦት 5/2012 ዓ. ም. የተፈጸመው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት በቪዲዮ ምስል በኩል ለምዕመናን የተሰራጨ መሆኑ ታውቋል። በፖርቱጋል በዕለቱ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው እና በልበ ኢየሱስ እና በልበ ማርያም ስም የሚካሄድ ዓለም አቀፍ ንግደት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት መሰረዙ ታውቋል። ትናንት ግንቦት 5/2012 ዓ. ም. በፖርቱጋል ዋና ከተማ ሊዝቦን የቀረበውን ዓለም አቀፍ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የመሩት የሊዬሪያ-ፋጢማ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል አንቶንዮ አጉስቶ ዶስ ሳንቶስ ማርቶ ሲሆኑ፣ መስዋዕተ ቅዳሴው በሚካሄድበት ሰዓት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ሐዋርያዊ ሰላምታቸውን ልከውላቸዋል። ብጹዕ ካርዲናል አንቶንዮ አጉስቶ ዶስ ሳንቶስ ማርቶ በበኩላቸው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት ላልቻሉት የጣሊያን ምዕመናን በሙሉ በቫቲካን ሬዲዮ በኩል ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

የፋጢማ እመቤታችን ድንግል ማሪያም ካቴድራል መሪ ካህን መልዕክት፣

የፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ካቴድራል መሪ ካህን የሆኑት ክቡር አባ ካርሎስ ካቤቺናስ በቪዲዮ ምስል አማካይነት ለመላው ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት፣ በግንቦት 5/2012 ዓ. ም. በፋጢማ እመቤታችን መቅደስ በተካሄደው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ የመላው ዓለም ምዕመና በመንፈስ መተባበራቸውን ገልጸው፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር በ1917 ዓ. ም. አካባቢው በወረርሽኝ መጠቃቱን አስታውሰዋል። “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ፋጢማ የተስፋ መልዕክትን ይዛ መጥታለች” ያሉት ክቡር አባ ካርሎስ፣ ያን ጊዜም ቢሆን ዓለማችን በከባድ ችግር የወደቀ መሆኑን አስታውሰዋል። የእመቤታችን ቅድስት ማርያም የተስፋ መልዕክት ለመላው የዓለም ሕዝብ ነው ብለው፣ ዘንድሮ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የቀረበው ጸሎትም በፋጢማ ወደሚገኝ የእመቤታችን ማርያም ቤተ መቅደስ ተመልሰን ለመምጣት ብርታትን እና ተስፋን የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ተስፋ በመታገዝ ሁላችን በድጋሚ ተገናኝተን አብረን እምነታችንን ለማክበር እንሰበሰባለን በማለት ክቡር አባ ካርሎስ ምኞታቸውን ገልጸዋል።

11/02/2020

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “ቤተክርስቲያን የድሆችን ጩኸት ልታዳምጥ ይገባል”።

ቤተክርስቲያን የድሆችን ጩኸት በማዳመጥ ብርሃኗንም በዓለም ሁሉ ልታበራ ይገባል ብለዋል።

30/12/2019

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት
የሕይወት ፈተና ለማሸነፍ “የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን መመልከት” ይኖርብናል

የጎርጎስሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ-ክርክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት የገና በዓል በታኅሳስ 15/2012 ዓ.ም በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ከተከበረበት የገና በዓል በመቀጠል ባለው እለት የቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው ሰማዕት ተብሎ የሚጠራው የቅዱስ እስጢፋኖስ ዓመታዊ በዓል እንደ ሚከበር ይታወቃል። የእዚህ የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን ሰማዕት በመባል የሚታወቀው የቅዱስ እስጢፋኖስ ዓመታዊ በዓል በታኅሳስ 16/2012 ዓ.ም. በተከበረበት ወቅት በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ይህንን የቅዱስ እስጢፋኖስ በዓል ለማክበር ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎብኝዎች ባሰሙት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ገለጹት “በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች መጋፈጥ እንድንችል “የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን መመልከት” ይኖርብናል ማለታቸው ተገልጹዋል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው እለት ማለትም በታኅሳስ 16/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን የቅዱስ እስጢፋኖስን ዓመታዊ በዓል አስመልክተው ያሰሙትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ!

የመጀመሪያው ሰማዕት የቅዱስ እስጢፋኖስ በዓል ዛሬ ይከበራል። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ከምዕራፍ (6-7) ውስጥ ስለሱ የሚያወሳ ሲሆን እናም በዛሬው የስረዓተ አምልኮ በእርሱ ማለትም በቅዱስ እስጢፋኖስ በሕይወቱ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ የገጠመውን ስቃይ እና መወገር ለእኛ ገልጦልናል (የሐዋ. 6,12; 7,54- 60 ይመልከቱ)። በገና በዓል አስደሳች ወቅት ለእምነቱ የተገደለው የመጀመሪያው ክርስቲያን መታሰቢያ በዓል ብቅ ማለቱ ያለቦታው የተከሰተ በዓል ሊመስል ይችል ይሆናል። ሆኖም በትክክል በእምነት እይታ፣ የዛሬው በዓል ከገና ትክክለኛ ትርጉም ጋር የሚስማማ ነው። በቅዱስ እስጢፋኖስ ሰማዕትነት፣ በእውነቱ አመጽ በፍቅር ፣ በሞት በህይወት መሸነፉን ያሳያል፣ እርሱ በታላቅ ስቃይ ውስጥ እምነቱን በመሰከረበት ወቅት የተከፈተ ሰማይ ይመለከታል፣ ለአሳዳጆቹም ይቅርታ ያደርግላቸዋል።

በመንፈስ ቅዱስ የተሞላው ይህ ወጣት የወንጌል አገልጋይ ኢየሱስን በቃላት እና ከሁሉም በላይ በሕይወቱ ውስጥ ለመተረክ ችሏል። የእርሱን ሕይወት ስንመለከት “በምትያዙበትም ጊዜ ምን እንናገራለን፣ ምንስ እንመልሳለን ብላችሁ አትጨነቁ፤ በዚያን ጊዜ የምትናገሩት ይሰጣችኋል፤ በእናንተ የሚናገረው የሰማዩ አባታችሁ መንፈስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና” (ማቴ 10፡19-20) በማለት ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ የሰጠው ተስፋ ሲፈጸም እናያለን። በሕይወትም ሆነ በሞቱ ውስጥ ከጌታው ጋር በተመሳሰለ የቅዱስ እስጢፋኖስ አስተምህሮ ውስጥ፣ እኛም በአብ የታመነ እውነተኛ የኢየሱስ ምስክርነት ላይ ማተኮር እንደ ሚገባን እንማራለን። ለዘለአለም ህይወት እና ለሰማይ ክብር የሚያበቃን ሀብት እና ስልጣን ሳይሆን ነገር ግን ፍቅር እና ራስን በመስጠት እንደ ሆነ እንማራለን።

በእለታዊ ሕይወታችን ውስጥ የሚያግጥሙን ፈተናዎች እና ተግዳሮቶች በተገቢው ሁኔታ ለመጋፈጥ እና በተስፋ የተሞላ ምላሽ ለመስጠት ያስችለን ዘንድ ትኩረታችንን “የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን መመልከት” (ዕብ 12፡2) ይገባናል። ለእኛ ክርስቲያኖች ፣ ሰማይ ከእንግዲህ ወዲህ ከምድር እጅግ የተለየ ሩቅ አይደለም፣ በኢየሱስ አማካይነት ሰማይ ወደ ምድር ወረደ። ለእርሱ ምስጋና ይግባውና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መላውን የሰው ልጅ መገናኘት እና ወደ መንግስተ ሰማይ መምራት እንችላለን። የመጀመሪያው ምስክርነት ትክክለኛ ሰው የመሆን ባሕሪይ ሲሆን በኢየሱስ መሠረቱን ያደረገ የአኗኗር ዘይቤ የሆኑትን ገርነት እና ብርታት፣ ትሑት እና ክቡር ፣ ዓመፀኛ ያልሆነ ነገር ግን ጠንካራ ባሕሪይ መላበስ ይኖርብናል።

እስጢፋኖስ ከቤተክርስቲያኗ የመጀመሪያዎቹ ሰባት ዲያቆናት መካከል አንዱ ነበር (ሐዋ. 6: 1-6)። እርሱ በወንድማማችነት መንፈስ እና በቅዱስ ወንጌል የተቀባ ፍቅር አማካይነት ክርስቶስን እንድናውጅ አስተምሮናል። የእርሱ ምስክርነት በሰማዕትነት የሚጠናቅቅ ሲሆን፣ ለእኛ የክርስቲያን ማህበረሰባች እድሳት የመነሻ ምንጭ ነው። እነሱ የበለጠ የወንጌል ተልዕኮ እንዲያፋፍሙ የተጠሩ ሲሆን ሁሉም ቅዱስ ወንጌልን ለማብሰር የሚጥሩ በየተኛውም የመልካምድር አቀማመጥ ውስጥ ለሚገኙትን ሰዎች ቅዱስ ወንጌልን ለማዳረስ እና የመዳን ጥማት ያላቸውን ሰዎች ጥም ለማርካት ተጠርተዋል። ዓለማዊ አመክንዮን የማይከተሉ ማህበረሰቦች ራሳቸውን ማዕከል ያላደረጉ፣ የራሳቸውን ምስል የማይከተሉ ሲሆን ነገር ግን ለየት ባለ መልኩ የእግዚአብሔር ክብር እና የሰዎችን መልካምነት፣ በተለይም አቅመ ደካማ እና ድሃ ለሆኑ ሰዎች ትኩረት ይሰጣሉ።

የመጀመሪያው ሰማዕት የቅዱስ እስጢፋኖስ በዓል ትናንት እና ዛሬ ያሉትን ሰማዕታት ሁሉ እንድናስታውስ ፣ ከእነሱ ጋር ህብረት እንዳለን እንዲሰማን፣ በልባችን እና በከንፈሮቻችን የኢየሱስን ስም በማኖር እንድንኖር ኣና እንድንሞት ጸጋ እንዲያሰጡን ልንማጸናቸው የገባል። የአዳኙ እናት የሆነቺው ማርያም እይታችንን በኢየሱስ ላይ በማደረግ በየቀኑ ከእርሱ ጋር የተመሳሰለ ሕይወት በዚህ የገና ወቅት እንድንኖር እንድትረዳን ልንማጸናት የገባል።

25/12/2019

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ዛሬ ምሽት የእግዚኣብሔር የፍቅር ብርሃን ተገልጾልናል” አሉ።
የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል እየተከበረ እንደ ሚገኝ ይታወቃል። የእዚህ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የዋዜማ መስዋዕተ ቅዳሴ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመሩት እና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት መስዋዕተ ቅዳሴ በታኅሳስ 14/2012 ዓ.ም መካሄዱ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት “ዛሬ ምሽት የእግዚኣብሔር የፍቅር ብርሃን ተገልጾልናል” ማለታቸው ተዘግቡዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በታኅሳስ 14/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያሰሙትን ስብከት ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

“ነገር ግን ተጨንቀው የነበሩ ከእንግዲህ ተስፋ ቢስ አይሆኑም!” (ኢሳያስ 9:1)። ይህ በመጀመሪያው ንባብ ውስጥ የሰማነው ትንቢት በወንጌ ውስጥ ፍጻሜውን አግኝቱዋል - እረኞች በሌሊት መንጎቻቸውን ሲጠብቁ ፣ “የእግዚአብሔር ክብር በዙሪያቸው አበራ” (ሉቃስ 2፡9)። በምድራዊ ጨለማ ውስጥ ፣ ከሰማይ ብርሃን ተገለጠ ፡፡ በጨለማ ውስጥ የሚያበራ የዚህ ብርሃን ትርጉም ምንድን ነው? ቅዱስ ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ጸጋ ታየ” ሲል ይናገራል። ለሁሉም “ድነትን የሚያመጣ የእግዚአብሔር ጸጋ (ቲቶ 2፡ 11) ፣ በዚህ ምሽት በአለማችን ላይ ብቅ ብሏል።

ነገር ግን ይህ ጸጋ ምንድነው? ህይወትን የሚቀይር ፣ ታሪክን የሚያድስ ፣ ከክፉ ነገር ነፃ የሚያወጣ፣ መለኮታዊ ፍቅር ነው፣ በሰላምና በደስታ ይሞላናል። በዛሬ ምሽት የእግዚአብሔር ፍቅር ተገለጠልን እርሱም ኢየሱስ ነው። በጣም ታላቅ እና ልዑል የነበረው ኢየሱስ እንወደው ዘንድ ራሱን ትንሽ እጅግ ትንሽ አድርጎ አቀረበ። ነገር ግን አሁንም እራሳችንን መጠየቅ እንችላለን - ቅዱስ ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ወደ ዓለም የመጣበትን ሁኔታ ሲገልጽ “ጸጋ” በማለት የገለፀው ለምንድነው? ሙሉ በሙሉ ነፃ መሆኑን ለእኛ ለመናገር አስቦ ነው። በምድር ላይ ሁሉም ነገር የሚገኘው በመስጠት ሲሆን ነገር ግን እግዚአብሔር በነጻ ወደ እኛ ይወርዳል። ፍቅሩ ለድርድር የሚቀርብ ነገር አይደለም፣ እኛም ለእርሱ የሚገባውን ነገር አላደረግንም ውለታውን ሙሉ በሙሉ ለመክፈል በጭራሽ አንችልም።

የእግዚአብሔር ጸጋ ታየ ፡፡ ዛሬ እኛ ይህንን የእግዚኣብሔር ጸጋ መለካት ባቃተን ጊዜ እግዚአብሔር ለእኛ ሲል ትንሽ ሆኖ እንደ መጣ እንገነዘባለን፣ እኛ ወደራሳችን ሥራ በምንሄድበት በአሁኑ ጊዜ እርሱ በመኃላችን ገባ። የገና በዓል እግዚኣብሔር ሁላችንንም መውደዱን እንደሚቀጥል ያስታውሰናል። ለእኔ፣ ለሁላችንም፣ ለእያንዳንዳችን ሳይቀር ዛሬ “እወድሃለሁ፣ ሁሌም ቢሆን እወድሃለው፣ አንተ በዐይኔ እይታ ውስጥ ውድ ነህና” በማለት ይናገራል።

እግዚኣብሔር የሚወድህ በትክክለኛ ሁኔታ ስላስብክ እና በትክክለኛው መንገድ ላይ ስልተጓዝክ አይደለም። እርሱ ይወድሃል፣ ይህም ግልፅ እና ቀላል ነገር ነው። ፍቅሩ በመስፈሮች ላይ የተመሰረተ አይደለም፣ የሚወድህ በአንተ ስለተመካም አይደለም። የተሳሳቱ ሀሳቦች ሊኖሩህ ይችሉ ይሆናል ፣ ብዙ ስህተቶችን የሰራህ ሰው ልትሆን ትችል ይሆናል፣ ነገር ግን ጌታ አንተን መውደዱን ይቀጥላል። እኛ ጥሩ ሰው በምንሆንበት ወቅት እግዚኣብሔር ለእኛ መልካም፣ መጥፎ ሰዎች ስንሆን ደግሞ እግዚኣብሔር እንደ ሚቀጣን ሆኖ የሚሰማን ምን ያህል ጊዜ ነው? ነገር ግን እሱ እንደዚያ አይደለም ። ከነኃጢያታችን ሁሉ እርሱ እኛን መውደዱን ይቀጥላል። ፍቅሩ አይለወጥም። እሱ ተለዋዋጭ አይደለም; ታማኝ ነው፣ ታጋሽ ነው። በገና በዓል ላይ የምናገኘው ስጦታ ይህ ነው። ጌታ በነጻ የሚሰጠን ፍጹማዊ በሆነ ፍቅር የሚወደን መሆኑን አስገራሚ በሆነ ሁኔታ እንረዳለን። የእርሱ ክብር አያሸብረንም የእርሱ ከእኛ ጋር መሆን አያስፈራንም። በጣም አስቸጋሪ በሆነ ድህነት ውስጥ የተወለደው በከፈተኛ ፍቅር ልባችንን ለማሸነፍ ነው።

የእግዚአብሔር ጸጋ ታየ። ጸጋ የውበት ተመሳሳይ ቃል ነው። ዛሬ ማታ በእግዚአብሔር ፍቅር ውስጥ እኛ የራሳችንን ውበት እንመለከታለን፣ ምክንያቱም እኛ በእግዚአብሔር የተወደድን በመሆናችን የተነሳ። በመልካም ወይም በክፉ፣ በበሽታ እና በጤና፣ በደስታ ሆነ በሐዘን፣ በእሱ ፊት ቆንጆዎች ነን፣ ይህም የሆነበት ምክንያት እኛ በሰራነው መልካም ነገር ሳይሆን፣ እኛ የእርሱ በመሆናችን የተነሳ ነው። በውስጣችን ጥልቅ ፣ የማይታይ እና የማይዳሰስ ውበት፣ ልናልመው ከምንችለው በላይ የሆነ ውበት አለ፣ ይህም የእኛነታችን ዋና አካል ነው ፡፡ ዛሬ እግዚአብሔር ይህንን ያስታውሰናል ፡፡ እሱ በፍቅር ተነሳስተን ሰብአዊነታችንን እራሱን ወስዶ የእሱ እንዲሆን ያደርገዋል ፣ እናም ለዘላለም የእርሱ ያደርገዋል።

ዛሬ ማታ ለእረኞቹ የተነገረው “ታላቅ ደስታ” “ለመላው ህዝብ የተነገረ ነው። እኛ ሁላችንም ከነድክመቶቻችን እና ከእነውድቀቶቻችን ሁሉ በእውነቱ ቅዱሳን ካልነበሩ ከእረኞች መካከል እንመደባለን። እግዚአብሔር እረኞችን እንደጠራ ሁሉ እርሱ እኛን ሰለሚወደን እኛንም ይጠራናል። እርሱ ይወደናልና። በጨለማ ውስጥ በነበሩበት ሕይወት እረኞቹን “አትፍሩ!” (ሉቃ 2 10) ብሎ እንደ ተናገረው ሁሉ እኛንም አትፍሩ ይለናል። አይዞህ፣ በርታ፣ ተስፋ አትቁረጥ ፣ መውደድ ጊዜ ማባከን ማለት አይደለም ይለናል። ዛሬ ማታ ፍቅር ፍርሃትን አሸንፉል ፣ አዲስ ተስፋም ፍንጥቋል፣ የእግዚአብሔር ደግ ብርሃን በእብሪት የተሞላውን የሰውን ጨለማ አሸንፉዋል። የሰው ልጅ ሆይ!፣ እግዚአብሔር ይወድሃል! በአንተ ምክንያት ሰው የሆነው እርሱ ይወድሃል። ከእንግዲህ ብቸኛ አይደለህም!

ውድ ወንድሞች እና እህቶች ፣ ይህንን ጸጋ ምን እናድርግ? አንድ ነገር ብቻ ማድረግ ይጠበቅብናል፣ ይህም ይህንን የጸጋ ስጦታ መቀበል ነው። እግዚአብሔርን ለመፈለግ ከመሄዳችን በፊት እርሱ እንዲፈልገን እራሳችንን ለእርሱ እናስገዛ። በራሳችን ችሎታዎች አንጀምር ፣ ነገር ግን በእርሱ ጸጋ ፣ እርሱ ኢየሱስ እርሱ አዳኝ ነውና። በልጁ ላይ እናሰላስል እና በእርሱ ኃይለኛ ፍቅር እንያዝ። ያኔ እራሱ በእርሱ እንዳንወደድ ላለመፍቀድ ምንም ተጨማሪ ሰበብ አይኖረንም። በሕይወታችን ውስጥ ስሕተት ያለ ከሆነ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ ችግሮች የሚታዩ ከሆነ፣ በዓለም ላይ የትኛውም ችግር ቢኖር፣ እንደ ሰበብ ከእንግዲህ አያገለግልም። ከኢየሱስ ድንገተኛ ፍቅር ፣ የየዋህነት እና የጠበቀ ቅርበት ፍቅር ጋር እነዚህ ነገሮች ፊት ለፊት ሲታዩ ሁለተኛ ነገር ይሆናሉ፣ ስለዚህ ሰበብ የለንም። በገና በዓል ላይ ጥያቄው “እግዚአብሔር እንዲወደኝ እፈቅድለታለሁ ወይ? እኔን ለማዳን በመጣው ፍቅር እታመናለሁ ወይ? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባናል።

ስለዚህ ለእዚህ ታላቅ ስጦታ ታላቅ ምስጋና ይገባዋል። ይህንን ጸጋ መቀበል ማለት በምላሹ ለማመስገን ዝግጁ መሆን ማለት ነው። ብዙውን ጊዜ ህይወታችንን በእንደዚህ ባልይ ትናንሽ ምስጋና በማቅረብ መኖር ይኖርብናል። ወደ ማደሪያው ድንኳን ወደ ከብቶች በረት ወደ ግርግሙ ለመቅረብ እና ለማመስገን ዛሬ ትክክለኛ ቀን ነው። ስጦታ የሆነውን ኢየሱስን እንቀበል፣ እንደ ኢየሱስ ሆነን እንኖር ዘንድ ኢየሱስ የሆነውን ስጦታ እንቀበል ፡፡ ስጦታ መሆን ለሕይወት ትርጉም መስጠት ማለት ነው። እናም ዓለምን ለመለወጥ ምርጡ መንገድ ነው ፣ እኛ እንቀየራለን ፣ ቤተ-ክርስቲያን ትለወጣለች ፣ ታሪክ ይለወጣል ፣ ሌሎችን ለመለወጥ ከመሞከር ይልቅ በቅድሚያ ራሳችንን ብንለውጥ ራሳችንን እና ሕይወታችንን ስጦታ አድርገን እናቀርባለን ማለት ነው።

ዛሬ ማታ ኢየሱስ ይህንን ያሳያል። እሱ በህይወቱ ስጦታ ሆኖ መጣ እንጂ ማንንም በማስገደድ እና ብዙ ቃላትን በመናገር አለወጠም። እርሱ እኛን ከመወደዱ በፊት ጥሩ እስክንሆን ድረስ አልጠበቀንም፣ ነገር ግን እራሱን ለእኛ ሰጠን። ጎረቤቶቻችን መልካም እስኪሆኑ ድረስ ጠብቀን ለእነርሱ መልካም ማደረግ የለብንም፣ ቤተክርስቲያንን ለመወደድ የግድ ቤተክርስቲያን ፍጹም እስክትሆን ድረስ መጠበቅ የለብንም፣ ሌልቾ ሰዎች እስኪያከብሩን ድረስ ጠብቀን እነርሱን መውደድ የለብንም። በመጀመሪያ በራሳችን እንጀምር ፡፡ የፀጋ ስጦታን በነፃነት መቀበል ማለት ይህ ነው ፡፡ ቅድስና ይህንን ነፃነት ከመጠበቅ የበለጠ የተሻለ ትርጉም የለውም።

አስደሳች በሆነ መልኩ የኢየሱስ ልደት ታሪክ የተነገራቸው እረኞች ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ይዘው ወደ ከብቶች በረት ግርግም በፍጥነት ሮጠው ሄዱ። እያንዳንዳቸው ያለቸውን አመጡ; ጥቂቶች የጉልበታቸውን ፍሬ፣ ሌሎቹ ደግሞ ጥቂት ውድ ነገሮችን አመጡ ፡፡ ነገር ግን ሁሉም ስጦታቸውን ያቀረቡት በጣም ብዙ ነገር አላቸው ተብለው የማይታሰቡት እረኞች ነበሩ። እነርሱ በጣም ድሃ ሰዎች ነበሩ። ነገር ግን እነርሱ የነበራቸውን ነገር ለመስጠት በመሽቀዳደም ላይ በነበሩበት ወቅት አንድ ምንም መስጠት የማይችል ሰው ከእነሩስ ጋር ነበር። እርሱም በሁኔታው እጅግ አፍሮ ነበር፣ ጉዳዩም ተስምቶት ነበር። በአንድ ወቅት ቅዱስ ዮሴፌ እና እመቤታችን ማርያም የመጣላቸውን ስጦታ ለመቀበል እስከሚያዳግታቸው ድረስ ከባድ ሆኖባቸው ነበር።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እጆቻችሁ ባዶ ሆኖው የሚሰማችሁ ከሆነ፣ ልባችሁ ፍቅር የሚጎለው መስሎ የሚሰማችሁ ከሆነ፣ በእዚህ ምሽት የእግዚአብሔር ጸጋ በሕይወታችሁ ውስጥ እንዲገለጥ፣ ይህንን ብርሃን ተቀበሉ፣ የገና በዓል ብርሃን በውስጣችሁ ያበራልና።

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የገና ዋዜማ መስዋዕተ ቅዳሴ ባሳረጉበት ወቅት

Want your school to be the top-listed School/college in Addis Ababa?

Click here to claim your Sponsored Listing.

Location

Category

Telephone

Website

Address


Addis Ababa