07/01/2024
ብጣሿ ወረቀት
ለንደን ከተማ ውስጥ ጥሩ ኑሮ የሚኖሩና አላህን እጅግ ፈሪ የሚባሉ እናትና ልጅ ነበሩ፤ ልጁ በመንግስታዊ ድርጅት ውስጥ የሚሰራ ሲሆን፤ እናቱም አብራው ትኖራለች፤ በዲኑ ላይም እጅግ ጠንካራና መስጂዶችም ውስጥ በጀመዓ ሰላት በስፋት የሚታወቅ ልጅ ነው።
አጋጣሚ ሆኖ ከሚሰራበት መስሪያ ቤት ለአንድ ዓመት ያህል ወደ ሌላ ሃገር ነፃ የትምህርት እድል ( scholarship ) ደረሰው። ልጁም ለጉዞ የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ ካዘጋጀ በኋላ ለእናቱ ለወር ወጪ የሚሆን ያህል ገንዘብ አስቀመጠላትና ተሳፈረ።
ቀናትና ሳምንታት ተፈራርቀው ወር ደረሰ፤ እናትም የተቀመጠላትን ገንዘብ ለወጪ እየተጠቀመች ቢሆንም ገንዘቡ በመገባደድ ላይ ነው፤ ቀናትና ወራት እየተቆጠሩ በሄዱ ቁጥር እናት ችግሯና ረሃቧ ከምትቋቋመው በላይ እጅግ እየበረታባት መጣ። ልጁ ከተሳፈረ ስምንት ወር ሞላው፤ እናትም ማንነቷን ለመለየት በሚከብድ ያህል ተጎሳቆለች።
ይህቺ ሚስኪን እናት ችግሯ ቢጠናባት አንዲት ብጣሽ ጨርቅ መስጂድ በር አንጥፋ ከመስጂድ ከሚወጡ ሰዎች መለመን ጀመረች። ከመስጂድ ለሚወጣውም ጀመዓ ይህቺ እናት ፈፅሞ አዲስ አልሆነችባቸውም። የሆነ ቦታ እንደሚያውቋት ተረድተዋል፤ ነገር ግን ማን ናት? የሁሉም ጥያቄ ነበር። የተጎሳቆለው ሰውነቷ ማንነቷን ቀይሮታል። ነገር ግን እሷ ከመስጂድ ዘውትር የማይጠፋው የአኺራ ወንድማቸው እናት ነበረች።
ከመስጅዱ መጨረሻ የወጡት ኢማሙ ሆኑና እንዳዩዋት የዚያ ሙዕሚን ልጅ እናት መሆኗን አወቁ፤ ግራ በመጋባትም ጠጋ ብለው ምን እንደገጠማት ጠየቋት፤ እሷም የልጁን ወደ ሌላ ሃገር መጓዝና የስምንት ወር ችግርና ስቃይዋን ነገረቻቸው።
ኢማሙም እጅግ በመገረም " ልጅሽ ከሄደ በኋላ ለወጪሽ የሚሆን ገንዘብ አይልክልሽም? " ብለው ጠየቋት። እናትም " ምንም አይነት ገንዘብ ልኮልኝ አያውቅም፤ ነገር ግን በየወሩ አንዲት ብጣሽ ወረቀት በፖስታ ቤት በኩል ይልክልኛል፤ እኔም ከልጄ የተላከልኝ ወረቀት እንደደረሰኝ መልዕክቱን ሳላነብ " የውዱ ልጄ ደብዳቤ " እያልኩ እየሳምኩ መሳብያ ውስጥ አስቀምጣለሁ፤ ምክንያቱም እንግሊዝኛ ማንበብ አልችልም " ብላ ለኢማሙ መለሰች።
ኢማሙም ወደ ቤቷ ይዘዋት ሄደው ለስምንት ወራት የተላከላትን ደብዳቤ እንድታመጣ ጠየቋት። እናትም ካስቀመጠችበት መሳብያ አውጥታ ሰጠቻቸው። ኢማሙ እጅግ ተገረሙ፤ ወደሷ ዞረውም " አንቺ እናት ሆይ፦ ይህ ልጅሽ በየወሩ የሚልክልሽ ብጣሽ ወረቀት እያንዳንዱ እኮ የአንድ ሺህ ዩሮ ቼክ ነው፤ ይህ ወረቀት ማለት ባንክ ቤት ሄደሽ በገንዘብ የምትቀይሪው ነው " በማለት ገንዘቡን ከባንክ እንዴት እንደምትቀበል አስረድተው ካለችበት ችግር አወጧት።
ይህቺ እናት ስለ ቼክ ባለማወቋና ማንበብ ባለመቻሏ፤ እንዲሁም ከቼኩ ጋር ባለመግባባቷ ምክንያት ወራትን በችግርና እንግልት አሳለፈች።
አላህም ተባረከ ወተዓላ የዱንያ ሃያታችንን ሊያሳምርልን የሚችልና፤ በአኺራም ድልን ሊያጎናፅፈን የሚችል ቼክ ለእያንዳንዳችን ሰጥቶናል። የቼኩን አጠቃቀም ነቢ አለይሂ ሰላም አበብራርተው ነግረውናል።
ነገር ግን እንደዚያች እናት ከቼኩ ጋር ባለመግባባታችን ምክንያት ቼኩን ቤት አስቀምጠን ችግርና ያልተረጋጋ ህይወት እየተፈራረቀብን ነው። ይህም ከአላህ ዘንድ የተሰጠንና፥ ሃያታችንን ሊያሳምርልን የሚችለውና ሳንግባባው ቀርተን ቤት ያስቀመጥነውም ቼክ ቁርዓን ነው።
አላህ ያግባባን።
Haji Ahmedin