10/09/2025
እንኳን አደረሰን አደረሳችሁ!
የ ፳፻፲፰ (2018) ዓ.ም በዓላትና አጽዋማት
አድኅነኒ ፡ እግዚኦ ፡ እስመ ፡ ኅልቀ ፡ ኄር ፤ ወውሕደ ፡ ሀይ?
ይህች ፔጅ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን እምነት፥ ሥርዓትና ትውፊት ለማስተማር የተዘጋጀች ስትሆን ሁላችሁም ሃሳብና አስተያየታችሁን እንድትለግሱንና ለሌላውም እንድትደርስ ሼር በማድረግ እንድትተባበሩን በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን።
10/09/2025
እንኳን አደረሰን አደረሳችሁ!
የ ፳፻፲፰ (2018) ዓ.ም በዓላትና አጽዋማት
06/04/2025
ታላቅ የገቢ ማሰባሰቢያ
አረቋቴ (ኤፍራታ ) ደብረ መዊዕ ቅዱስ ቂርቆስና ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አንድነት ገዳም
06/01/2025
«በጎል ሰከበ፣ በአፅርቅት ተጠብለለ፣ ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ።» በበረት ተኛ፣ በጨርቅም ተጠቀለለ፣ የዓለም መድኃኒት ዛሬ ተወለደ። እንኳን አደረሳችሁ!
26/09/2024
"ዛሬም የመስቀሉ ቃል ማለት ሰዎች በነፍሳቸውም ሆነ በሥጋቸው የተሟላ ደኅንነት ያግኙ ማለት ነው፤ የመስቀሉ ቃል ማለት የሰዎች ሃይማኖታዊ ነጻነት ይከበር፤ በሕይወት የመኖር ሰብአዊ መብታቸውም ይጠበቅ ማለት ነው፤ የመስቀሉ ቃል ማለት ሰዎች በዚች ምድር በእኩልነት በአንድነት በመተጋገዝ በመረዳዳት በፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል በሰላም በፍቅር በስምምነት በመተባበር ይኑሩ ማለት ነው፤"
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
በ2017 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል ከተናገሩት
10/09/2024
እንኳን ከዘመነ ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ቅዱስ ማቴዎስ በሰላም አደረሳችሁ!!!
በኢትዮጵያ የወራት ሁሉ መጀመሪያ መስከረም ነው፡፡ ይህ ወር ዘመን መለወጫ፣ ዕንቁጣጣሽ፣ ቅዱስ ዮሐንስ እየተባለ ይጠራል፡፡
የዘመን መለወጫ በመስከረም ወር የሆነበትን ምክንያት ሊቃውንቱ ሲያትቱ ብርሃናት ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ክዋክብት የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ “ለዘመን መታወቂያው ይሆን ዘንድ ፀሐይና ጨረቃ ከዋክብትንም ፈጠረ” ይላልና /ሄኖክ 21፥49/፡፡ በሌላ በኩልም በዘመነ ኖኅ በፍል ውኃ አጥለቅልቆ በኃጢአት ሕይወት ይኖሩ የነበሩት የኖኅ ዘመን ሰዎች ቀጥቶ ካጠፋ በኋላ ከንፍር ውኃ ምድር የተገለጠችበት ወር ነው /ኩፋሌ 7፥1/፡፡
“በመጀመሪያው ወር ምድር ታየች የንፍር ውኃም ከምድር ደረቀ” የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል መሠረት አድርገው የአቡሻኸር ሊቃውንት የዘመን መለወጫን ታሪካዊ አመጣጥ ያስቀምጣሉ፡፡ እንግዲህ መስከረም አንድ ቀን የዘመን መለወጫ፥ አሮጌውን ዘመን ጨርሰን መጪውን አዲሱን ዓመት የምንቀበልበት ቀን ናት። በልዩ ስም ቅዱስ ዮሐንስ ተብላ የተሰየመች ሲሆን ፍጹም መንፈሳዊ በሆነ ሁኔታ ትከበራለች።
የቤተ ክርስቲያን ቀኖናዊ ሥርዓት ያጠኑ ሊቃውንት ደግሞ አዲስ ዓመት መስከረም አንድ ቀን መሆኑን አስመልክተው በክታባቸው እንዳስቀመጡት በዐራቱ ወንጌላውያን ዘመኑን ይከፍሉታል፡፡ ምክንያቱም ጌታችን በዘመነ ዮሐንስ ተፀንሶ በዘመነ ማቴዎስ ተወልዶአል፡፡ በዘመነ ማርቆስ ተጠምቋል፡፡ በዘመነ ሉቃስ ተሰቅሎ ዓለምን ከፍዳና ከመርገም ነጻ አውጥቷል፤ እያሉ ያስረዳሉ፡፡ ከእነርሱም ማቴዎስና ዮሐንስ ከዐስራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል ሲሆኑ ማርቆስና ሉቃስ ደግሞ ከሰባ ሁለቱ አርድዕት ናቸው፡፡
እግዚአብሔር አምላክ አዳምን “በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ” (ዘፍ 3፥17) እንዳለው ይህ የእግዚአብሔር ቃል ሕገ ተፈጥሮአዊ ሆኖ የሰው ልጅ ወጥቶና ወርዶ፣ አርሶና ቆፍሮ በወዙና በድካሙ እንጀራውን የሚበላ ሆኗል። በዚህም መሠረት የምሕረትህን ዓመት አክሊል ትባርካለህ ፥ ምድረ በዳውም ጠልን ይጠግባል (መዝ 64፥11) እንዳለ፤ ዘር ተዘርቶ እሸት አፍርቶ ምድርም በልምላሜ ተጊጣ እንስሳትም ለምለም ሣርን ግጠው ፅሩውን ውሃ ጠጥተው ጠግበውና ወፍረው የሚታይበት ጊዜ ነው የመስከረም ወር።
አዲስ ዓመት በተለያየ ስም የመጠራቱ ታሪካዊ አመጣጥና ስያሜ መነሻ ሐሳቡ እንደሚከተለው ነው፡፡
ዘመን መለወጫ
ዘመን መለወጫ መስከረም ወር የሆነበት ምክንያት “ብርሃናት /ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት/ የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ወር ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ነው፡፡ ሌሊቱ ከቀኑ ጋር ይተካከላል፡፡ ዓመቱን ጠንቅቀው ቢቆጥሩ 364 ቀናት ይሆናል፡፡ “ሌሊቱም ከቀኑ ጋራ ይተካከላል፡፡ ዓመቱም ጠንቅቆ ቢቆጥሩት ሦስት መቶ ስልሳ አራት ቀን ይሆናል፡፡ /ሄኖክ.26፥44/ “ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ” /ሰ.ኤር.5፥21/ እንዲል፡፡
በዘመነ ኖኅ ዓለምን ንፍር ውኃ አጥለቅልቆት ከቆየ በኋላ ዳግመኛ ውኃው የጎደለበት በመሆኑ /ኩፋሌ 7፥1/ “በመጀመሪያው ወር መባቻም ምድር ታየች” እንዲል፡፡
ዕንቁጣጣሽ
ዕንቁጣጣሽ የተባለበት ምክንያት አንደኛ “ዕንቁ – ዕፅ አወጣሽ” ብሎ የአበባውን መፈንዳት ያመለክታል፡፡ ሁለተኛ ኖኅ ለሦስቱ ልጆቹ አህጉራትን በእጣ ሲያካፍላቸው አፍሪካ ለካም ደረሰችው፡፡ በአፍሪካ ምድርም ሲገባ በመጀመሪያ ያረፈው በኢትዮጵያ ነበር፡፡ ሀገሪቱም በአደይ አበባ አሸብርቃ ነበር፡፡ ወሩ ወርኀ መስከረም በመሆኑ ደስ ብሎት ዕንቁ ዕጣ ወጣሽልኝ ይህችን ወቅት ዕንቁጣጣሽ ብሏታል፡፡
ሦስተኛው /1ኛ ነገ.10፥1-10/ ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሳባ /አዜብ የንጉሡን ጥበብ ከመስማት ማየትን መርጣ ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ከብዙ ሠራዊቶቿ ጋር የእጅ መንሻ በመያዝ ሄደች፡፡ ንጉሡም በደስታ ተቀብሎ እርሱም “ዕንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንሽ” በማለት አራት አይነት ቀለም የሚታይበት በቀንና በሌሊት የምታበራ ቀለበት ሰጥቷታል፡፡ ወሩም ወርኀ መስከረም ነበር፡፡ ከዚህ በመነሣት ዕንቁጣጣሽ የሚለው ስያሜ ወጥቷል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ
ሦስተኛው የአዲስ ዘመን ስያሜ ቅዱስ ዮሐንስ ነው፡፡ የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ተግባር ለዘመነ ወንጌል በር ወይም መነሻ እንዲሆን ለኢትዮጵያ ዐውደ ዓመት መስከረም አንድ ቀን እንዲከበር አባቶች ወስነዋል፡፡
/ድርሳነ ዮሐንስ አፈወርቅ ገጽ 1-3/ መጽሐፈ ስንክሳር “የመስከረም ወር የተባረከ ነው፡፡ እርሱም የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመቶች መጀመሪያ ነው፡፡ የዚህ ወር ቀኑና ሌሊቱ እኩል 12 ሰዓት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ቀኑ እየጎደለ ይሄዳል” እንዲል፡፡
መስከረም ሰማዩ፣ ወንዙ፣ ጅረቱ፣ የደፈረሰውና የጠቆረው ሁሉ የሚጠራበት ጊዜ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ ከብልየት እንዲታደሱ፤ በመንፈስ እንዲጎለምሱ፤ ከርኩሰት፣ ከጣዖታት፣ ከቂም ከበቀል እንዲርቁ፣ እንዲጠሩና እንዲነጹ፤ በ1ኛ ጴጥ 4፥3 “የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና።”
በአዲስ ዓመት እኛ ክርስቲያኖች በተሰማራንባቸው ሥራዎች ሁሉ ከሁሉ የተሻልን አርአያነትና ምሳሌነት ያለን መሆን ይጠበቅብናል። በአጠቃላይ ንስሐ ገብተን ዘወትር በጸሎትና በጾም፣ በስግደትና በምጽዋት ተግተን አዲሱን ዓመት አካሄዳችንን ከእግዚአብሔር ጋር አድርገን በአዲስ ሕይወት እንኖር ዘንድ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን።
እግዚአብሔር አምላካችን ሀገራችንን ኢትዮጵያንና ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ይጠብቅልን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
ምንጭ- eotcmk.org
- eotcnor.no
29/08/2024
መዝሙር 12
1፤ አቤቱ አድነኝ፤ ደግ ሰው አልቋልና ከሰው ልጆችም መተማመን ጐድሏልና።
2፤ ርስ በርሳቸው ከንቱ ነገርን ይናገራሉ፤ በሽንገላ ከንፈር ኹለት ልብ ኾነው ይናገራሉ።
3፤ የሽንገላን ከንፈሮች ዅሉ እግዚአብሔር ያጠፋቸዋል ታላቅ ነገርን የምትናገረውን ምላስ፤
4፤ ምላሳችንን እናበረታለን፤ ከንፈራችን የእኛ ነው ጌታችን ማን ነው? የሚሉትን።
5፤ ስለድኻዎች መከራ ስለችግረኛዎች ጩኸት እግዚአብሔር፦ አኹን እነሣለኹ ይላል፤ መድኀኒትን አደርጋለኹ በላዩም እገልጣለኹ።
6፤ በምድር ላይ እንደ ተፈተነ ሰባት ጊዜ እንደ ተጣራ ብር። የእግዚአብሔር ቃላት የነጹ ቃላት ናቸው።
7፤ አቤቱ አንተ ጠብቀን ከዚችም ትውልድ ለዘለዓለም ታደገን።
8፤ በሰው ልጆች ዘንድጨምናምንቴጨከፍ ከፍ ባለ ጊዜ ክፉዎች በዙሪያው ዅሉ ይመላለሳሉ።
06/02/2024
ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች እንደፃፈላቸው እርሱ ላይ ቢጽ ሐሳዊያን፤ የእግዚአብሔር ጠላቶች ከአገልግሎት ሊያስቀሩት ክልከላ የፈፀሙበት ታሪክ ነበር። «ስለዚህ ደግሞ ወደ እናንተ እንዳልመጣ ብዙ ጊዜ ተከለከልኹ።» (ሮሜ 15፥22፣ሮሜ 1፥13)።
ጠላት ዲያብሎስ ምን ጊዜም ቅዱሳኑን ለማዘግየት እንደሚጥር ሁሉ፤ ሐሳዊው ንጉሥም ይሄን ይሞክራል። ነገር ግን የአቡኑን ክብር ሊጨምርላቸው ካልሆነ በቀር ፈጽሞ ከአገልግሎታቸው ሊያስቀራቸው አይሆንለትም።
06/01/2024
«ወኮነ ሰማይ ዓለመ ወዓለምሂ ሰማየ፤ ወኮነ እግዚአብሔር ሰብአ በታሕቱ፤ ወረሰዮ ለሰብእ ውስተ አርያም በላዕሉ። ወስብሐተኒ ዘውስተ ሰማይ ኮነ ዲበ ምድር፤ ዘሃሎ በሕጽነ አቡሁ ኮነ በሕጽነ ማርያም፤ ወለዘወለዶ እግዚአብሔር አብ በምሥጢር ዘኢይትረከብ እንበለ መንጸፈ አንስት፤ ወለደቶ ማርያም በሥጋ በምሥጢር ዘኢይትረከብ እንበለ ሩካቤ ተባዕት።»
(ሰማይ ዓለም ሆነ ዓለምም ሰማይን ሆነ፤ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ በዚህ ዓለም ተገኘ፤ ሰውንም በላይ በአርያም አደረገው፤ በሰማይ የሚቀርበው ምስጋና በዚህ ዓለም ተደረገ (መላእክትና ደቂቀ አዳም በአንድ ቦታ ተገልጠው አመሰገኑ) በአብ እሪና ያለ እርሱ በእመቤታችን ክንድ ተይዞ ታየ። እግዚአብሔር አብ በማይመረመር ምሥጢር ያለ እናት የወለደውን ማርያም በማይመረመር ምሥጢር ያለ ዘርዐ ብእሲ በሥጋ ወለደችው።) (ሃ.አበው ዘሳዊሮስ 85፥37)
ሆ ሣ ዕ ና
እንቋዕ አብጽሐክሙ አብጽሐክን ለበዓለ ልደተ ክርስቶስ በሰላም ወበፍቅር ሠናይ በዓል ይኩን ለኲሎሙ ሕዝበ ክርስቲያን።
የማቴዎስ ወንጌል (ምዕራፍ 25)
1፤ በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ ዐሥር ቈነዣዥትን ትመስላለች።
2፤ ከነርሱም ዐምስቱ ሰነፎች ዐምስቱም ልባሞች ነበሩ።
3፤ ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከነርሱ ጋራ ዘይት አልያዙምና፤
4፤ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋራ በማሰሯቸው ዘይት ያዙ።
5፤ ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ዅሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና*ተኙ።
6፤ እኩል ሌሊትም ሲኾን፦ እንሆ ሙሽራው ይመጣል ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ኾነ።
7፤ በዚያን ጊዜ እነዚያ ቈነዣዥት ዅሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ።
8፤ ሰነፎቹም ልባሞቹን፦ መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችኹ ስጡን አሏቸው።
9፤ ልባሞቹ ግን መልሰው፦ ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ኼዳችኹ ለራሳችኹ ግዙ አሏቸው።
10፤ ሊገዙም በኼዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከርሱ ጋራ ወደ ሰርግ ገቡ ደጁም ተዘጋ።
11፤ በዃላም ደግሞ የቀሩቱ ቈነዣዥት መጡና፦ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ ክፈትልን? አሉ።
12፤ ርሱ ግን መልሶ፦ እውነት እላችዃለኹ አላውቃችኹም አለ።
13፤ ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።
16/04/2023
የጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ
እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላምና በጤና አደረሰዎ!
እግዚአብሔር አምላክ ሰው ስሙን በመቀደስ መለኮታዊ ክብሩን እንዲወርስ ከፈጠረው ፍጥረት ሁሉ በላይ በጸጋ ሸልሞ በልጅነት አክብሮ በራሱ አርአያና አምሳል ፈጥሮ የተድላና የደስታ ቦታ በምትሆን በገነት አኑሯት ነበር። ከሰማይ በታች ባሉ ፍጥረታትም ላይ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን አምላክ ዘበጸጋ አድርጎ ሁሉን እንዲገዛና እንዲነዳ ሥልጣንን ሰጥቶት ነበር። ከዚህ ሁሉ ጋር ፍጡርነቱን እዲረዳና ሁሉን ያስገዛለት ገዢ የባሕርይ አምላክ የሆነ ፈጣሪ እንዳለው እንዲያውቅ ምልክት እንዲሆነው “ዕፀ በለስን አትብላ” የሚል የጾምን ሕግ ሰጥቶት ነበር። አዳም ግን በምክረ ከይሲ ተታሎ የእግዚአብሔርን ሕግ በማፍረስ በደለ። ያልተሰጠውን በመመኘት እራሱን ከፈጣሪው ጋር በማስተካከሉ ከአምላኩ ጋር ተጣላ። ርስት ሆና ከተሰጠችው ከደስታ ቦታ ከገነትም ወጣ። የሞት ሞት ተፈርዶበት በሥጋው ወደ መቃብር በነፍሱ ወደ ሲዖል ወረደ። ያ ክቡር ፍጥረት ሰው ተዋረደ - የእግዚአብሔር ልጅነቱን አጥቶ የዲያብሎስ ባሪያ ተባለ፤ ያ የጸጋ ባለቤት ጸጋውን ሁሉ ተገፈፈ፤ ያ የእግዚአብሔር ምሳሌ ሕያው ፍጥረት የሰው ልጅ ባሕርይው ጎስቁሎ ሰላሙንና ነጻነቱን አጥቶ የሞት ተገዥ ሆነ።
እንዲህ በበደሉ ከቀደመ ክብሩ ተዋርዶ በፍዳና በመርገም ተይዞ የዲያብሎስ ተገዥ የሆነውን የሰውን ልጅ ሊቤዥ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ በሥጋ ማርያም ተገልጦ ወደ ዓለም መጣ። የመጀመሪያው አዳም በጥንተ ተፈጥሮ ያገኘውንና በበደል ምክንያት ያጣውን ጸጋውን ሊመልስለት ባሕርይውንም ሊያድስለት ሁለተኛው አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ በተገዥው በሰው ባሕርይ ተገለጸ። ሰው ሆኖም ሕማምና መከራን ተቀብሎ በዕለተ አርብ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ የማይሞተው አንድ ጊዜ ሞቶ ለአዳምና ለዘሩ ካሣን ከፍሎ ከራሱ ጋራ ከባሕርይ አባቱ ከአብና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሰውን ሁሉ አስታረቀ። (ኢሳ 53፥4-)
ክብር ይግባውና ፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ በዕለተ አርብ በፈጸመው የማዳን ሥራው ሰውን ሁሉ በዘር ይቆራኝ የነበረውን ኃጢአት (ጥንተ አብሶን) አጠፋ። በዚያም ምክንያት ወደ ዓለም የገባውን የሞት እርግማንንም አነሣ። አርብ በሠርክ ነፍሱን በፈቃዱ ለሁላችን ቤዛ አሳልፎ ከሰጠ በኋላ በሥጋው ወደ መቃብር ወርዶ ሙስና መቃብርን (ፈርሶ በስብሶ መቅረትን) አስወገደ፤ በነፍሱ ወደ ሲዖል ወርዶ በመከራ ተይዘው ዲያብሎስ ሰልጥኖባቸው ለነበሩ ነፍሳት ነጻነትን ሰብኮ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከዋዕየ ሲዖል (ከሲዖል ቃጠሎ) ወደ ልምላሜ ገነት፣ ከጨለማ ወደሚደንቅ ብርሃን መለሰ።
ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን መካከል ሙታንን ቀድሞ ተነሣ። (መዝ 77፥85)
ጠላት ዲያብሎስን ድል አድርጎ ሞትን በትንሣኤው ኃይል ሻረ፤ በክቡር ትንሣኤው ዘላለማዊ ዋጋን በተስፋ ለሚጠባበቁና በስሙ ለተጠሩ፣ ሠርቶ ያሳያትን ሕገ ወንጌልን አምነው ለፈጸሙ፣ በመጨረሻዋ የፍርድ ቀን ትንሣኤ ዘለክብር (የክብር ትንሣኤ) እንዳላቸው አረጋገጠ። (1ኛ ቆሮ 15፥20)
ስለሆነም ይህን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤውን ስናከብር እርሱ በመስቀል ላይ ለገደለው ኃጢአት ዳግመኛ ባሪያዎች እንዳልሆንን ራሳችንን ልንመረምር ይገባል።
ለዚህም የአምላካችን ቸርነት፣ የእመቤታችን የንጽሕተ ንጹሐን የቅድስተ ቅዱሳን የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳኑ ሁሉ በረከት ከእኛ ጋር ይሁን አሜን።