Ethiopia Orthodox Tewahdo

Ethiopia Orthodox Tewahdo

Share

በስመ ዓብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን!

10/02/2023

"ሕዝባችን በሕገ ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ ከአቅዋማችን እንደጸናን እንድታውቁ እንፈልጋለን:: እግዚአብሔር ጸሎታችንን ሰምቶአል:: እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው::
በጸሎት ትጉ:: ነገ ጠዋት ዝርዝር ሁኔታውን እንገልጻለን"
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ

"አባቶቻችን አንተን ተማመኑ:: ተማመኑ አንተም አዳንኻቸው" መዝ. 21:4

10/02/2023
28/11/2021

ብርሃናዊ ደጉ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል

እንኳን አደረሳችሁ የቅዱስ ገብርኤል ወዳጆች

ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱና በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው ታማኝ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ በተረዳኢነቱና በአማላጅነቱ በክርስቲያኖች ዘንድ ይወደዳል፡፡

ምክንያቱም ያዘኑትን ለማፅናናት የምስራች ለመንገር ከእግዚአብሔር ወደ ምእመናን ያላካልና፡፡

ገብርኤል ማለት የእግዚአብሔርን ልጅ የሚመስል ጌታና አገልጋይ ማለት ነው፡፡ ብርሃናዊ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ቅዱሳን ሰማዕታት ገድላቸውን እንዲፈፅሙ እሳቱንና ስለቱን ተሳቀው ወደ ኋላ እንዳይመለሱ ይረዳቸዋል፡፡

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን የቅዱሳን መላዕክትን ወርሃዊና ዓመታዊ በዓላቸውን በፀሎትና በምስጋና ታከብራለች፤ በተለይ ታህሳስ 19 ቀን የሚከበርበት ምክንያት ብርሃናዊ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ሠለስቱ ደቂቅን ከዕቶን እሳት ያዳነበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡

በጣዖት ፍቅር እጅግ ያለመጠን ልቡ ተቃጥሎ የነበረው የባቢሎን መሪ ነቡከደነፆር ቁመቱ ስድሳ ወርዱ ስድስት ክንድ የሆነውን የወርቅ ምስል አሰርቶ መኳንንቱን ሰብስቦ ሕዝቡ
በሙሉ ለጣዖቱ እንዲሰግድ አዋጅ አወጀ፡፡

ያ ዘመን ለእግዚአብሔር ወዳጆች የፈተና ዘመን ነበር፡፡ አስመሳዮች ለጣዖት ሰገዱ፤ ተረበረቡ፡፡ እውነተኛ አማኞች ግን በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት ‹‹ ንጉስ የወደደው፣ ጊዜ
የወለደው›› በሚል አስተሳስብ አይለወጥም፡፡ በዚያ ፈታኝ ዘመን ነበር ሶስት ታማኝ የእግዚአብሔር ባለሟሎች የተገኙት፡፡

ንጉሱ ላቆመው ጣኦት ያልሰገደ ወደ እቶን እሳት ተጥሎ እንደሚሞት ቁርጥ ውሳኔው መሆኑን ወጣቶቹ በሚገባ ያውቁታል ግን ይህንን አልፈሩም፡፡ ንጉስ ሆይ አምላካችንን ክደን አንተ ላቆምከው ጣዖት አንሰግድም አሉት፡፡ ሶስቱ ወጣቶች የወሰዱት ይህ አቋም ለንጉሱ ታላቅ ራስ ምታትን ፈጠረ፤ ንጉሱም አገልጋዮቹን ጠርቶ እሳቱ ሰባት እጥፍ እንዲነድ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

እሳቱም ሰባት እጥፍ ነደደ፡፡ ወዲያውኑ የንጉሱ አገልጋዮች አናንያ ፣ አዛርያን እና ሚሳኤልን እያንከበከቡ ወደ ዕቶን እሳቱ ወረወሯቸው፡፡ በእሳቱ ሀይል የተነሳ አገልጋዮቹም በእሳቱ
እየተጠለፉ እንደ ማገዶ ነደዱ፡፡ ሠልስቱ ደቂቅ ግን ከየት እንደመጣ ከማይታወቅ እንግዳ ጋር በመሆን በዕቶን እሳት ውስት ይንሸራሸሩ ጀመር፡፡

ይህ ተዓማራት ንጉሱንና መኳንንቱን አስገረመ፡፡ ንጉሱም በዚህ ወቅት ‹‹ እነሆ እኔ በእሳቱ መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ እሳቱ ምንም አላቆሰላቸውም አራተኛውም የአማልክትን ልጅ ይመስላል ፡፡ ›› አለ፡፡ ንጉስ ናብከደነፆር በግልፅ ተመልክቶ እንደመሰከረው የነደደውን እሳት በማብረድ ለሠልስቱ ደቂቅ ቤዛ የሆናቸው ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡

በግዕዙ ‹‹ ወገፁ ለራብዓይ ወልደ እግዚአብኤር ይመስል›› አራተኛውም ፊቱ የእግዚአብሔርን ልጅ ይመስላል ይላል፡፡
አዎን፤ ከዚህ በላይ እንደተገለፀው ሊቀመላዕክት ቅዱስ ገብርኤል ስለ ሀይማኖታቸው መከራ የተቀበሉትን ወጣቶች
የነደደውን እሳት አብርዶ በሃይማኖታቸው እንደአፀናቸው ተመልክተናል፡፡

የቅዱስ ገብርኤል አማላጅነት እኮ ጥንት የነበረ ብቻ ሳይሆን እስከ አለንብት ዘመን ደርሶ የመልአኩን አማላጅነት በዓይን
የተመለከትነው ተጨባጭ ድርጊት ነው፡፡

የነደደ እሳት ውስጥ ገብቶ ከመውጣት ባልተናነሰ መከራ ውስጥ ገብተው በቅዱስ ገብርኤል አማላጅነት ከሞተ ስጋ ነፍስ ድነው እውነተኛ ምስክርነታቸውን የሚሰጡ ብዙዎች ናቸው፡፡

በመልዓኩ ስም በፈለቀው ፀበል ተጠምቀው ደዌ የራቀላቸው እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ በየዓመቱ በቁልቢና በቅዱስ ገብርኤል
ስም በታነፁ አብያተ ክርስቲያናት የሚሰባሰበው ምዕመን ስዕለቱ የሰመረለት ልመናው የተሰማለት እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡

ስለዚህ ለመላዕክት አለቃ ለቅዱስ ገብርኤል የተሰጠውን ፀጋ ተረድተን መልአኩን ልናከብረውና ልናመሰግነው ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

28/11/2021

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
አሜን
ኅዳር 19-ሐዋርያው ቅዱስ በርተሎሜዎስ ዓመታዊ መታሰቢያ
በዓሉ ነው፡፡ እልዋህ በምትባልም አገር ድንቅ ተአምር
ያደረገበት ዕለት ነው፡፡ ዳግመኛም ዛሬ የእንጂፋቱ የአቡነ ዮሴፍ
ልደታቸው ነው፡፡ ዳግመኛም ዛሬ ከ5 ወር ሕፃን ልጁና ከሚስቱ
ጋር ሰማዕት የሆነው የቅዱስ ቴዎፍሎስ ዕረፍቱ ነው፡፡ ሩጻፋ
በሚባል አገር የሰማዕቱ የቅዱስ ሰርጊስ ቤተ ክርስቲያኑ
የከበረችበት ዓመታዊ መታሰቢያ በዓሉ ነው፡፡
የሰማዕቱ የቅዱስ ሰርጊስ ቤተ ክርስቲያኑ እንደከበረች፡- መ
ይህም ቅዱስ ሰርጊስ በሩጻፋ አገር በሰማዕትነት ባረፈ ጊዜ
ምእመናን ቅዱስ ሥጋውን ወስደው በክብር ገንዘው በእነርሱ
ዘንድ አኖሩት፡፡ በፊቱም መብራቶችን አኖሩ፡፡ የመከራውም ዘመን
እስኪያልፍ ድረስ በእነርሱ ዘንድ ተሰውሮ ኖረ፡፡
የመከራውም ዘመን ካለፈ በኋላ ያማረች ቤተ ክርስቲያንን
አነጹለት፡፡ 15 ኤጲስቆጶሳትንም ሰብስበው አከበሯትና የቅዱስ
ሰርጊስን ሥጋ በውስጧ አኖሩ፡፡ ከሥጋውም ድንቅ ድንቅ የሆኑ
ተአምራት ተገለጡ፡፡ ሕመምተኞችን የሚፈውሳቸው ሽታው
እጅግ ጣፋጭ የሆነ የሽቱ ቅባት ከቅዱስ ሥጋው የሚፈስ ሆነ፡፡
የቅዱስ ሰርጊስን ዜና ሕይወቱን በዕረፍቱ ዕለት ጥቅምት 10
ቀን በዝርዝር ስላየነው ገድሉን ከዚያ ላይ መመልከት ይቻላል፡፡
በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ በርተሎሜዎስ እልዋህ በምትባልም አገር
ያደረገው ድንቅ ተአምር፡- ሐዋርያው በርተሎሜዎስ ወንጌልን
ይሰብክ ዘንድ ዕጣ የደረሰው እልዋሕ በሚባል አገር ነው፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ ሊያደርሰው አብረው ወደ አልዋሕ ሄዱ፡፡ ወደ
ከተማው ለመግባት ምክንያት ፈለጉና ቅዱስ ጴጥሮስ ቅዱስ
በርተሎሜዎስን ‹‹አትክልተኛ ባለሙያ ነው›› ብሎ የወይኑን ቦታ
እንዲጠብቅለት ለአንድ ባለጸጋ መኰንን ባሪያ አድርጎ ሸጠው፡፡
ባለጸጋውም በርተሎሜዎስን በ30 እስቴታር ገዝቶት ሄደ፡፡ ቅዱስ
ጴጥሮስ ገንዘቡን ደብቆ ለቅዱስ በርተሎሜዎስ በድብቅ
ሰጥቶት እንዲመጸውተው ነግሮት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፡፡
አልዋሕ ከገባ በኋላ ቅዱስ በርተሎሜዎስ የወይን ቦታው አለቃ
ሆኖ 40 ቀን ተቀመጠ፡፡ ወንጌሉን ባለመስበኩ በሀዘን እያለቀሰ
ጌታችንን በጸሎት ጠየቀው፡፡ በገንዘቡ ገዝቶት ባሪያው ያደረገው
ባለጸጋውም የወይኑን ቦታ ያይ ዘንድ እንደመጣ መርዘኛ እባብ
ነድፎት ሞተ፡፡ ሕዝቡም ተሰብስቦ ሲያለቅስ በርተሎሜዎስ ግን
ወደ ጌታችን ከጸለየ በኋላ ሄዶ ባለጸጋውን ሰው ከሞት
አስነሣው፡፡ በዚህም ሕዝቡ ሁሉ አምነው ተጠምቀዋል፡፡ ይህም
ታላቅ ተአምር የተፈጸመው በዛሬዋ ዕለት ነው፡፡ ሐዋርያው
ቅዱስ በርተሎሜዎስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ
ይማረን፡፡
/////////////////////////////
አቡነ ዮሴፍ ዘእንጂፋት፡- ተአምረኛው ኢትዮጵያዊው ጻድቅ
አቡነ ዮሴፍ ዘእንጂፋት አባታቸው ንጉሡ ዐፄ ዳዊት እናታቸው
ዳግም ሞገሳ ይባላሉ፡፡ ትውልድ ሀገራቸው ወሎ መቄት እንጂፋ
ነው፡፡ ኅዳር 19 ቀን ሲወለዱ በርካታ ሙታን ተነሥተዋል፡፡ ጻድቁ
ያላዩት የቅዱሳን ቦታ ያልተሳለሙት ገዳም የለም፡፡ በወሎ ላስታ
ሰውንና ዝንጀሮን በቃልኪዳን ያስተሳሰሩ ታላቅ አባት ናቸው፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን ዝንጀሮዎቹ ተሰብስበው መጥተው እጅ
ነሷቸው፡፡ አቡነ ዮሴፍም ጌታችንን ‹‹ምን አበላቸዋለሁ?››
ብለው በጸሎት ጠየቁ፡፡ ጌታችንም ‹‹አንተን ያጅቡ፣ ቅጠሉን
ቃርሚያውን ይብሉ›› ብሎ አዘዛቸው፡፡ ዝንጀሮዎቹም ጻድቁን
ተከትለው ይጓዙ ጀመር፡፡ አንድ ቀን በመንገድ አብረው ሲሄዱ
ዝንጀሮዎቹ ‹‹ራበን›› ብለው ለአባታቸን ቢነግሯቸው ድንጋዩን
በጸሎታቸው ባርከው ምግባቸው አድርገው መግበዋቸዋል፡፡
አሁንም ድረስ ላስታ ውስጥ በሚገኘው በጻድቁ ገዳም አካባቢ
እህሉ በሚትረፈረፍበት ቦታ ዝንጀሮዎች በብዛት ይገኛሉ፡፡
ዝንጀሮዎቹ የሰውን እህል እንዳይበሉ፣ ገበሬውም ቃርሚያውን
እንዳያነሳ በአቡነ ዮሴፍ ቃልኪዳንና ግዝት ተይዘዋል፡፡ በዚህም
መሠረት አሁንም ድረስ ዝንጀሮዎቹም የሰውን እህል አይበሉም፣
ገበሬውም ቃርሚያውን አያነሳም፡፡ ገበሬው ቃርሚያውን ቢያነሳ
ግን ዝንጀሮዎቹ የእሱን እህል ብቻ ለይተው ይበሉበታል፡፡
በአካባቢው አደገኛና መርዛማ እባቦች በብዛት ቢኖሩም በጻድቁ
የገዳሙ ክልል ውስጥ ግን በፍጹም ሰውን አይነኩም፡፡ አቡነ
ዮሴፍ ለ40 ቀን ከሰው ጋር ሳይገናኙ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም
በደመና እየተመላለሱ ጸሎት ያደርጉ ነበር፡፡ አባታችን የተለያዩ
ተአምራትን እያደረጉ ባሕር ከፍለው እየተሻገሩ ሙታንን እያስነሱ
ወንጌልን ዞረው አስተምረዋል፡፡ ወደ ሰማይም ተነጥቀው
እመቤታችን ዕጣን ሰጥታቸው ከ24ቱ ካህናት ጋር አጥነዋል፡፡
ጻድቁ ያመነኮሷቸው መነኮሳት በጣም በርካታ ናቸው፡፡ አቡነ
ዮሴፍ ከብዙ ተጋድሏቸው በኋላ ቃልኪዳን ተቀብለው በመጨረሻ
ግንቦት 19 ቀን በክብር ዐርፈው በዚያው በገዳማቸው
ተቀብረዋል፡፡ ዛሬ ኅዳር 19 ዓመታዊ የልደት በዓላቸው ነው፡፡
በረከታቸው ይደርብን በጸሎታቸው ይማረን፡፡
//////////////////////////////////
ቅዱስ ቴዎፍሎስ ከ5 ወር ሕፃን ልጁና ከሚስቱ ጋር ሰማዕት
እንደሆነ፡- ይህም ቅዱስ እግዚአብሔርን መፍራትና ሥርዓተ
ቤተ ክርስቲያንን እየተማረ አደገ፡፡ ምግባር ሃይማኖቱ የቀና ሆኖ
ቢያገኙት ክፉዎች ሄደው ‹‹ቴዎፍሎስ የሚባል ክርስቲያን ከዚህ
አለ›› ብለው ለከሃዲው መኮንን ወነጀሉት፡፡ መኮንኑ
አንቲጳጦስም ወደ እርሱ ካስመጣው በኋለ እምነቱን
መረመረው፡፡ ቅዱስ ቴዎፍሎስም ‹‹የክብርን ባለቤት ጌታዬን
ኢየሱስ ክርስቶስን የማምን ክርስቲያን ነኝ›› አለው፡፡ መኮንኑም
‹‹በክፉ አሟሟት እንዳትሞት ለአማልክት ሠዋ›› አለው፡፡ ቅዱስ
ቴዎፍሎስም ‹‹ከጌታዬ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ለረከሱ
አማላክት ፈጽሞ አልሠዋም›› አለው፡፡
ከዚህም በኋላ መኮንኑ በቁጣ ቅዱስ ቴዎፍሎስን የሆድ ዕቃው
እስኪታይ ድረስ ሰውነቱን በመሰነጣጠቅ አሠቃየው፡፡ ቅዱሱም
በጌታችን ኃይል ጤነኛ ሆነ፡፡ ዳግመኛም መኮንኑ እሳት አስነድዶ
በውስጡ እንዲጨምሩት አዘዘ፡፡ እንዳዘዘውም በእሳት ውስጥ
በጨመሩት ጊዜ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ከእሳቱ ውስጥ ሆኖ ቢጸልይ
ምንም ሳይቃጠል ቀረ፡፡ በደህናም ከእሳቱ ውስጥ ወጣ፡፡
በዚህም ጊዜ ብዙዎች በእርሱ አምላክ አመኑ፡፡
መኮንኑም ቅዱስ ቴዎፍሎስን በረሃብ ተሠቃይቶ ይሙት በማለት
በእሥር ቤት ዘጋበትና ምንም የሚበላው ነገር እንዳይሰጡት
ጠባቂዎቹን አስጠነቀቃቸው፡፡ ከ8 ቀን በኋላ ሚስቱ ያለበትን
አፈላጋ መጥታ አጽናናችው፣ በጌታችንም ስም ሰማዕት ይሆን
ዘንድ አበረታችው፡፡ መኮንኑም ለቅዱስ ቴዎፍሎስ ምግብ
የሰጠው ሰው እንዳለ ሊመረምር በመጣ ጊዜ የእሥር ቤቱን
ደጅ ሲፍት መዓዛው የሚያውድ የዕጣን ሽታ ሸተተው፡፡ ቅዱስ
ቴዎፍሎስንም ሦስት ቅዱሳን መላእክት ማርና ወተት ሲመግቡት
ተመለከተ፡፡ ይህንንም በተመለከተ ጊዜ ደንግጦ ወደኋላው
ተመለሰ፡፡
በማግሥቱም ቅዱስ ቴዎፍሎስን ወደ አደባባይ አውጥቶ
በሕዝቡ ፊት ‹‹ለአማልክት ሠዋ›› አለው፡፡ ቅዱሱም ‹‹እኔ
ዓለምን ሁሉ ለያዘው ለእውነተኛው አምላክ ለጌታዬ ለኢየሱስ
ክርስቶስ በቀር አልሠዋም›› አለው፡፡ የቅዱስ ቴዎፍሎስ
ሚስቱም የ5 ወር ሕፃን ልጃቸውን ይዛ ባሏን ተከትላው
እስከመጨረሻው እንዲጸና እና ሰማዕተነቱን እንዲፈጽም
ታበረታው ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ መነኮንኑ ቅዱስ ቴዎፍሎስን
ለተራበ አንበሳ ሰጠው ነገር ግን አንበሳው ሄዶ ሰግዶ እግሮቹን
ሳመው፡፡ ጌታችንን እነ አባ በብኑዳን፣ እነ አባ ኤጲፋንዮስን፣
መቃነ መቃብራቸውን የአንበሳ ሆድ እንዳደረገላቸው ሁሉ
የዚህንም ቅዱስና የቤተሰቡን መቃብራቸውን የአንበሳ ሆድ
አደረገላቸው፡፡ አንበሳውም ለቅዱስ ቴዎፍሎስ ከሰገደለትና
እግሮቹን ከሳመ በኋላ ሥጋውን አቆሰለውና ነፍሱም በዚያው
አለፈች፡፡ ሚስቱ ቅድስት ጰጥሪቃም ሥጋውን አንሥታ ከሣጥን
በጨመረች ጊዜ መኮንኑ እርሷንም ለአንበሳው አሳልፎ ሰጣትና
ነፍሷን ለእግዚብሔር ሰጠች፡፡ የ5 ወር ዕድሜ ብቻ ያለው
ልጃቸው ቅዱስ ደማሊስም አንበሳውን ባየጊዜ ሳቀና አንደበቱን
ፈቶ ‹‹አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ
ስም አምናለሁ›› ብሎ ተናገረ፡፡ ይህንንም ብሎ በአንበሳው አፍ
ከእናቱ ጋር ተበላ፡፡ የቅዱስ ቴዎፍሎስና የቅድስት ጰጥሪቃ
የልጃቸውም የቅዱስ ደማሊስ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን
በጸሎታቸው ይማረን፡፡
ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! እኛንም በአማላጅነታቸው
የምንታመን የተዋሕዶ ልጆች የሆንን ሁላችንን ዛሬ ኅዳር 19
ቀን በዓመታዊ በዓላቸው አስበናቸው የምንውለውን
የሐዋርያውን የቅዱስ በርተሎሜዎስን፣ የአቡነ ዮሴፍን፣
የሰማዕቱ የቅዱስ ሰርጊስን፣ የቅዱስ ቴዎፍሎስንና የቅድስት
ጰጥሪቃን የልጃቸውም የቅዱስ ደማሊስን ረድኤት በረከታቸውን
ያሳድርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡
(ምንጭ፡- የመስከረምና የኅዳር ወር ስንክሳር፣ መዝገበ
ቅዱሳን)

Photos from Ethiopia Orthodox Tewahdo's post 27/11/2021

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ጥቅምት 17-ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ የተሾመበት ዓመታዊ በዓሉ ነው፡፡
+ ቅዱስ ፊልያስ በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡
+ አቡነ ዲዮስቆሮስ 2ኛ በዓለ ዕረፍታቸው ነው፡፡
+ የነቢዩ ሳሙኤል እናት ቅድስት ሐና ልደቷ ነው፡፡
+ የቅዱስ ባስልዮስ ወንድም ቅዱስ ጎርጎርዮስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡
ሰማዕቱ ቅዱስ ፊልያስ፡- እኚህም ቅዱስ የሀገረ ቀምስ ኤጲስቆጶስ ናቸው፡፡ በዘመናቸው ቍልቍልያኖስ የተባለ ከሃዲ መኮንን ነበረና አባታችንን ወደ ፍርድ አደባባይ አቀረባቸውና ‹‹ለአማልክቶቼ ሠዋ›› አላቸው፡፡ አቡነ ፊልያስም ‹‹እኔ ሰማይንና ምድርን ፈጥሮ ለሚገዛ ለልዑል እግዚአብሔር ብቻ ነው የምሠዋው›› አሉት፡፡ መኮንኑ ቍልቍልያኖስም ‹‹እግዚአብሔር ምን ዓይነት መሥዋዕት ይሻል?›› አላቸው፡፡ አባታችንም ‹‹ቅን ትሑት የሆነ ንጹሕ ልቡናን፣ ዕውነተኛ ፍርድን፣ ቁም ነገርንና እንዲህ የመሰለውን መሥዋዕት እግዚአብሔር ይወዳል›› አሉት፡፡
ቍልቍልያኖስም አቡነ ፊልያስን ‹‹የምትጋደለው ስለ ነፍስህ ነው ወይስ ስለ ሥጋህ?›› ሲላቸው ‹‹ስለ ነፍስና ስለ ሥጋ ነው፣ እነርሱ በአንድነት ይነሣሉና›› አሉት፡፡ ከዚህም በኋላ ቍልቍልያኖስ ‹‹የምትወዳት ሚስትና የምትወዳቸው ልጆች ወይም ዘመድ አለህን?›› አላቸው፡፡ አቡነ ፊልያስም ‹‹ከሁሉም የእግዚአብሔር ፍቅር ይበልጣል›› አሉት፡፡ ከሃዲውም መኮንን ‹‹እግዚአብሔር ከበጎ ሥራ የሠራው ምንድነው?›› አላቸው፡፡ አቡነ ፊልያስም እንዲህ አሉት፡- ‹‹እግዚአብሔር ያደረገልን ይህ ነው፡- ሰማይንን ምድርን በውስጣቸው ያሉትን ሁሉ ፈጠረልን፡፡ ዳግመኛም ከጠላታችን ከሰይጣን እጅ ያድነን ዘንድ ከሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆኖ ተወለደ፤ የሕይወትንም መንገድ በዓለም ውስጥ ተመላልሶ አስተማረ፣ መከራንም በሥጋው ተቀብሎ ተሰቅሎ ሞተ፣ በሦስተኛውም ቀን ከሞት ተነሥቶ በ40 ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ፣ ዳግመኛም ለፍርድ ይመጣል፡፡ ይህንንም ሁሉ ስለእኛ አደረገ›› አሉት፡፡ ቍልቍልያኖስም ይህን በሰማ ጊዜ ‹‹አምላክ ይሰቀላልን?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ አባታችንም ‹‹አዎን የዘላለም ሕይወትን ይሰጠን ዘንድ ስለእኛ ፍቅር ሞተ›› አሉት፡፡
ከዚህም በኋላ ከሃዲው መኮንን ቍልቍልያኖስ አባታችንን ‹‹አንተ የከበርክ እንደሆንህ ዐውቃለሁና እኔ እንዳከበርኩህ ልጣላህም እንዳልፈለግሁ ዕወቅ፡፡ አሁን ለአማለክቶቼ ሠዋ፣ እምቢ ካልክ ግን በክፉ አሟሟት ትሞታለህ›› አላቸው፡፡ አቡነ ፊልያስም ‹‹እኔንስ ደስ ማሰኘት ከወደድህ እንዲያሠቃዩኝና እንዲገድሉኝ እዘዝ›› አሉት፡፡ ቍልቍልያኖስም በዚህ ንግግራቸው በጣም ተቆጥቶ የአባታችንን ራሳቸውን በሰይፍ ይቆርጧቸው ዘንድ አዘዘ፡፡
አባታችንንም ሊገድሏቸው ሲወስዷቸው ዘመዶቻቸውና የሀገሩ ታላላቅ ወገኖች ወደ እርሳቸው መጥተው ለመኮንኑ በመታዘዝ ለአማልክቶቹ እንዲሠው አባታችንን እጃቸውንና እግራቸውን እየሳሙ ለመኗቸው፡፡ አባታችንም ይህን ጊዜ ‹‹የጌታዬን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ መስቀል ልሸከም እሄዳለሁና እናንተ አሳሳቾች ከእኔ ወግዱ›› ብለው ገሠጹዋቸው፡፡ ከመገደያቸውም ቦታ በደረሱ ጊዜ ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ መልሰው በመጸለይ ምእመናንንም ለጌታችንን በአደራ አስጠብቀውና ተሰናብተዋቸው አንገታቸውን ለሰያፊዎቹ አሳልፈው ሰጧቸው፡፡ ሰያፊዎቹም የአባታችንን ራስ ቆረጡትና የሰማዕትነትን አክሊልን ተቀዳጁ፡፡
የቅዱስ ፊልያስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!
+ + +
ቅዱስ ዲዮስቆሮስ 2ኛ፡- ይህም ቅዱስ አባት በዘመኑ ካሉ ትውልድ እርሱን የሚመስል ያልተገኘ በጠባዩ ቅን፣ የዋሕ፣ በዕውቀቱም አስተዋይ በበጎ ሥራው ሁሉ ፍጹም የሆነ ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ 31ኛው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ሆኖ በማርቆስ መንበር ላይ ተሾመ፡፡ ከሹመቱም በኋላ መልእክትን ጽፎ ለአንጾኪያው ሊቀ ጳጳሳት ለአቡነ ሳዊሮስ ላከለት፡፡ መልአክቱም ስለ ሥሉስ ቅዱስ አንድነትና ሦስትነት የሚያስረዳ ነው፡፡ እንዲሁም ስለ ምሥጢረ ሥጋዌና ስለ እመቤታችን ንጽሕና ጽፎ ለአቡነ ሳዊሮስ ላከለት፡፡ አቡነ ሳዊሮስም መልእክቱን ተቀብሎ ባነበባት ጊዜ ፈጽሞ ደስ ተሰኘባትና ለአንጾኪያ ሕዝቦች አስተማረባት፡፡ ሁሉም በዚህ ደስ አላቸው፡፡
አቡነ ሳዊሮስም በመልሱ መልእክት ጻፈለትና ‹‹በኒቅያ ከተማ ተሰብስበው ሃይማኖታቸው የቀና 318 ቅዱሳን አባቶቻችን በቀናች ሃይማኖት አጽንተው የሠሯትን ቤተ ክርስቲያን እንድትጠብቅ ለዚህች ለከበረች አገልግሎት የመረጠህ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ›› በማለት በሃይማኖት እስከመጨረሻው ጸንቶ ምእመናንንም እንዲያጸና አስገነዘበው፡፡ ብዙ ድርሳናትንም ጨምሮ ላከለት፡፡ አቡነ ዲዮስቆሮስ ሁለተኛም መልአክቱን ተቀብሎ ለሕዝቡ አስተማረባት፡፡ ሁልጊዜም ቅዱሳት መጻሕፍትን በማስተማር ምእመናንን በሃይማኖት እንዲጸኑ በማስተማር ብዙ ካገለገለ በኋላ መልካም አገልግሎቱን ፈጽሞ በሰላም ዐረፈ፡፡ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!
+ + +
ዳግመኛም ይህች ዕለት ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ የተሾመባት ዕለት ናት፡፡ እስጢፋኖስ ማለት ‹‹መደብ›› ማለት ሲሆን በግሪክ ቋንቋ ‹‹አክሊል›› ማለት ነው፡፡ በግብሩ የቀን ሃሩር የሌሊት ቁር የማይለውጠው፣ መብራት ማለት ነው፡፡ ትውልዱ ከነገደ ብንያም ሲሆን አባቱ ስምዖን እናቱ ሐና ይባላሉ፡፡ እነርሱም እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ከነቢያትና ከጻድቃን ወገን ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ሁለት ወንድ ልጆችን ወለዱ፡፡ አንዱ ይሁዳ ሲባል ሁለተኛውም ቅዱስ እስጢፋኖስ (አስተፓኖስ) ነው፡፡ እስጢፋኖስ የተወለደው ጥር 1 ቀን በእስራኤል ሃገር ውስጥ ልዩ ስሟ ሐኖስ በተባለች ቦት ነው፡፡ የተወለደውም በስለት ነው፡፡ እርሱም ከመጥምቁ ዮሐንስ እግር ሥር በመሆን ተምሯል፡፡ በኋላም ወደ ቅዱሳን ሐዋርያት በመሄድ ይላላካቸውና ያገለግላቸው ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ከተሾሙት ከ7ቱ ዲያቆናት አንዱ ሲሆን የዲያቆናት አለቃ እርሱ ነው፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ወንጌልን በማስተማሩና ብዙዎችን ክርስቶስን ወደማመን ስለመለሳቸው ክፉዎች አይሁድ በጠላልትነት ተነስተውበት ጥር 1 ቀን በ34 ዓ.ም ከጌታችን ቀጥሎ ከምእመናን ወገን የመከራውን ገፈት ስለተቀበለ (በድንጋይ ተወግሮ በሰማዕትነት ስላረፈ) ‹‹ቀዳሜ ሰማዕት›› ተሰኘ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስ›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ይኸውም የከበሩ ቅዱሳን ሐዋርያት በሰባቱ ዲያቆናት ላይ አለቃ አድርገው በሾሙት ጊዜ የተሰጠው ስያሜ ነው፡፡
የመጀመሪያ ክርስቲያኖች የአማኞች ቊጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በሄደ ጊዜ የማኅበራዊው ኑሮ አስተዳደር ማለትም የምግብንና የመሳሰሉትን ቁሳቁሶች (ገንዘብም ጭምሮ) በትክክልና በእኩልነት የማከፋፈሉ ሥራ በሐዋርያት ዘንድ አስቸጋሪ ሆኖ ተገኘ፡፡ እነርሱም ደግሞ ዋና ተግባር አድርገው በትጋት ለመያዝ የፈለጉት ማስተማርን ነበር፡፡ ስለዚህም አማኞችን ሁሉ ሰብስበው ከመካከላቸው በመልካም ጠባያቸው የተመሰገኑ በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ ሰባት ሰዎችን እንዲመርጡ አሳስቧቸው፡፡ አማኞችንም ነገሩ አስደስቷቸው ሰባት ሰዎችን መረጡ፡፡ እነርሱም፡- ቅዱስ እስጢፋኖስ (ዕረፍቱ ጥር 1)፣ ቅዱስ ጵሮኮሮስ (ሰኔ 8)፣ ቅዱስ ጢሞና (ሚያዝያ 16)፣ ቅዱስ ፊልጶስ (ጥቅምት 14)፣ ቅዱስ ጰርሜና (መስከረም 1)፣ ቅዱስ ኒቃሮና (3 ጊዜ ሞቶ የተነሣ)፣ ቅዱስ ኒቆላዎስ (ሚያዝያ 15) ናቸው፡፡ ሐዋ 6፡5፡፡
እነዚህንም ቅዱሳን በከበሩ ሐዋርያት ፊት ባቆሟአቸው ጊዜ ጸልየው እጃቸውን በራሳቸው ላይ ጭነው ሾሟቸው፡፡ በከበሩ ሐዋርያት ጫንቃ ላይ ተጭኖ የነበረው ከባድ ሸክም ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶችና ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ደሀ አደጎች በመርዳት ችግሮቻቸውን አቃለሉላቸው፡፡ በከበሩ ሐዋርያት ከተመረጡት ሰባቱ ዲያቆናት መካከል ሊቀ ዲያቆናት ተደረጎ የተመረጠው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲሆን ሌሎቹም ዲያቆናት እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ወንጌልን በማስተማርና የመጀመሪያ ክርስቲያኖች በማስተዳደር በጽናት ተጋድለዋል፡፡
እነዚህም ሰባቱ ዲያቆናት ከአባቶቻቸው ከከበሩ ሐዋርያት አይተው የእነርሱንም መንፈስ ተቀብለው ያልተማሩ አህዛብን ልቡናቸውን ለመስበርና የእግዚአብሔርን ኃይልነት ተረድተው እንዲገነዘቡ በማሰብ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን ያደርጉ ነበር፡፡ ከእነርሱም ውስጥ በዋነኛነት ቅዱስ እስጢፋኖስ በአህዛብ ፊት ያደረጋቸው ተአምራት እጅግ ድንቅ ናቸው፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ በአህዛብ መካከል ቆሞ ሲያስተምር ከቆየ በኋላ አንድ አንደበቱ ዲዳ የሆነ ሰው አጠገቡ ቢመጣ በጆሮው የሕይወት እስትንፋስ እፍ ቢልበት መስማት የማይችለው መስማት ቻለ፡፡ በዚህም ጣኦት አምላኪው ናኦስ እና ተከታዮቹ ሁሉ ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ተመለሱ፡፡ ጣኦት አምላኪው ናኦስ በድርጊቱ በጣም ከመናደዱ የተነሣ በአጠገቡ የቆመውን በሬ ጠንቋዩ ናኦስ በጆሮው እፍ ብሎ ቢተነፍስበት በሬው በምትሃት ለሁለት ተሰንጥቆ በመሞቱ ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ የተመለሱት በናኦስ ምትሃታዊ ድርጊት በመሳባቸው እንደገና ወደ ናኦስ ተመለሱ፡፡
ቅዱስ እስጢፋኖስም በዚህ ጊዜ የአህዛብ ልቡና ወላዋይ እንዳይሆንና እንዳይጠፉም በማሰብ ናኦስ እፍ ብሎ ለሁለት ሰንጥቆ የገደለውን በሬ መልሶ በሕይወት እንዲያስነሣው ናኦስን ጠየቀው፡፡ ነገር ግን ናኦስ ያንን ማድረግ አልቻለም፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዱስ እስጢፋኖስ ‹‹ናኦስ ዳግመኛ ሕይወት ዘርቶ ማስነሣት ካልቻለ እኔ ነገሩ ሀሰተኛ ነው ማለት ነው፣ እኔ ግን በእግዚአብሔር ኃይልና ድንቅ ሥራ ይህን ለሁለት ተሰንጥቆ የሞተውን በሬ ዳግመኛ ሕይወት ዘርቶ እንዲነሣ አደርገዋለሁ›› በማለት ወደ እግዚአብሔር ከጸለየ በኋላ በሬውን አስነሣው፡፡ ይህንንም ተአምር አድርጎ በማስተማር ልቦናቸው ወላውሎ ወደ ናኦስ የተመለሱትን አህዛብ ገንዘቡ እንዲሆኑ በእግዚአብሔር ኃይልነት እንዲያምኑ አድርጓል፡፡ ናኦስ በአልሸነፍ ባይነትና በአጋንንት ረዳትነት ራሱን ወደ ላይ እንዲንሣፈፍ አድርጎ በአየር ላይ ቢወጣ ቅዱስ እስጢፋኖስ የእግዚአብሔርን ተአምር በማሳየት በትዕግስት ጠብቆ በአጋንንት ረዳትነት ወደ ላይ የተነሳውን ናኦስ በትምዕርተ መስቀል ቢያማትብበት ይዘውት የነበሩት አጋንንት ሁሉ ለቀውት ሲበተኑ ናኦስም ምድር ደርሶ ተንኮታኩቶ በመውደቁ በጣኦት አምላኪነት የነበሩ ሁሉ ዳግም ወደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ተመልሰዋል፡፡
የሰማዕታት መጀመሪያ የሆነው ቅዱስ እስጢፋኖስ በትምህርቱና በተአምራቱ ብዙዎችን ወደቀናች ሃይማኖት ስለመለሰ ክፉዎች አይሁድ ቀኑበትና የሐሰት ምስክር አዘጋጁበት፡፡ ‹‹በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ የስድብን ቃል ሲናገር ሰምተነዋል›› ብለው በሐሰት ከሰሱትና በሸንጎአቸው አቆሙት፡፡ ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስም ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ጌታችን ያለውን ሁሉንም እየጠቀሰ የሃይማኖትን ነገር አስተማራቸው፡፡ ነቢያትን ስለማሳደዳቸውና ስለመግደላቸው እየወቀሰ ሲናገራቸው በትምህርቱ ተናደው ጆሮአቸውን ይዘው በመጮህ በድንጋይ ወግረው ይገድሉት ዘንድ እየጎተቱ ከከተማው ውጭ አወጡት፡፡ ቅዱሱም በድንጋይ ወግረው ሲገድሉት ከጌታችን የተማረውን ‹‹አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው›› እያለ ስለገዳዮቹ ምሕረትን ይለምን ነበር፡፡ ሰማይም ተከፍቶ የእግዚአብሔርን ክብር ተመለከተ፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ይኸውም የቀድሞው ሳውል ቅዱስ እስጢፋኖስን በድንጋይ ሲወግሩት የገዳዮቹን ልብስ ይጠብቅና ድንጋይ ያቀብል ነበር፡፡ ‹‹የሰማዕትህንም የእስጢፋኖስን ደም ባፈሰሱ ጊዜ፥ ራሴ ደግሞ በአጠገባቸው ስቆም ተስማምቼ የገዳዮችን ልብስ እጠብቅ ነበር አልሁ›› ብሎ ራሱ ቅዱስ ጳውሎስ መስክሯል፡፡ ሐዋ 22፡20፡፡ የቅዱስ እስጢፋኖስ መምህር የነበረው ምሑረ ኦሪቱ ገማልያልና ልጁ አቢብ በእስጢፋኖስ ትምህርትና የሞቱ ሰዎች የሰጡትን ምስክርነት አይተው ከይሁዲነት ተመልሰው በክርስቶስ አምነው ተጠምቀዋል፡፡ ስለ ሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲህ ተብሎ ነው የተጻፈው፡- ‹‹እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር፡፡ የነፃ ወጪዎች ከተባለችው ምኵራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያም ሰዎች ከኪልቅያና ከእስያም ከነበሩት አንዳንዶቹ ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር፤ ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም፡፡ በዚያን ጊዜ በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል የሚሉ ሰዎችን አስነሡ፡፡ ቀርበውም ያዙት ወደ ሸንጎም አመጡትና ‹ይህ ሰው በዚህ በተቀደሰው ስፍራ በሕግም ላይ የስድብን ነገር ለመናገር አይተውም፤ ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ ያፈርሰዋል ሙሴም ያስተላለፈልንን ሥርዓት ይለውጣል ሲል ሰምተነዋልና› የሚሉ የሐሰት ምስክሮችን አቆሙ፡፡ በሸንጎም የተቀመጡት ሁሉ ትኵር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት፡፡›› 6:8-15፡፡
የአይሁድ በቅዱስ እስጢፋኖስ ላይ ያቀረቡት የክሳቸው ምክንያት ጌታችንን ከከሰሱት ክስ ጋር በሁለት ነጥቦች ይመሳሰላል፡፡ የመጀመሪያው ክሳቸው ‹‹የሙሴን ሕግ ሽሯል›› የሚል ነው፡፡ ‹‹የሙሴን ሕግ በመሻር ኦሪት አትጠቅምም አትመግብም አታድንም፤ ሐዲስ ኪዳን (ወንጌል) ግን ትመግባለች ታድናለች›› ብሏል ብለው ከሰሱት፡፡ ሐዋ 6፡13፡፡ ሁለተኛው ክሳቸው ‹‹እግዚአብሔርንም ይሰድባል›› የሚል ነው፡፡ ሐዋ 7፡50፡፡ አይሁድም የቅዱስ እስጢፋኖስን የወንጌል ቃል ንግግሮች በእግዚአብሔር ላይ እንደተሰነዘሩ ስድቦች በመቁጠር ነበር የወነጀሉት፡፡ የኦሪት የካህናት አለቃውም ቅዱስ እስጢፋኖስ ለተከሰሰበት መልስ ይሰጥ ዘንድ ሲጠይቀው እርሱ ግን ለተከሰሰበት መልስ ከመስጠት ይልቅ ከአብርሃም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ በዝርዝር በሚገባ ተረከላቸው፡፡
ቅዱስ እስጢፋኖስም እንዲህ አላቸው፡- ‹‹ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁንም መምጣት አስቀድሞ የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ በመላእክት ሥርዓት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ገደላችሁትም፡፡ ይህንም በሰሙ ጊዜ በልባቸው በጣም ተቈጡ ጥርሳቸውንም አፋጩበት፡፡ መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፡፡ እነሆ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ አለ፡፡ በታላቅ ድምፅም እየጮኹ ጆሮአቸውን ደፈኑ፣ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ ሮጡ፤ ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት፡፡ ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎበዝ እግር አጠገብ አኖሩ፡፡ እስጢፋኖስም ‹ጌታ ኢየሱስ ሆይ ነፍሴን ተቀበል› ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር፡፡ ተንበርክኮም ‹ጌታ ሆይ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው› ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፡፡ ይህንም ብሎ አንቀላፋ፡፡ ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር፡፡ 7:52-60፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ ስለንጽሕናው ስለድንግልናው፣ ስለሰማዕትነቱ ስለተጋድሎው እና ስለስብከቱ ስለተአምራቱ ሦስቱ አክሊላት ተቀዳጅቷል፡፡
ቅዱስ እስጢፋኖስ አምላኩን ክርስቶስን በብዙ ነገር መስሏል፡፡ በመጨረሻዋ የመሞቻው ሰዓት ላይ እንኳን ሆኖ አምላኩን አብነት አድርጎ ተገኝቷል፡፡ ጌታችን ‹‹ነፍሴን ተቀበላት›› እንዳለ ሁሉ ቅዱስ እስጢፋኖስም ‹‹አቤቱ ጌታ ሆይ ነፍሴን ተቀበላት›› ብሏል፡፡ ጌታችን ‹‹አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው›› እንዳለ እስጢፋኖስም ‹‹ጌታ ሆይ ይህን ኃጥአት አትቁጠርባቸው የሚያደርጉትን አያውቁምና›› በማለት ለገዳዩቹ ምሕረትን ለምኗል፡፡ በጌታችን ጸሎት እነ ፊያታዊ ዘየማንን ጨምሮ እልፍ ነፍሳት ወደ ንስሐ ተመልሰው ገነት መንግስተ ሰማያትን እንደወረሱ ሁሉ በቅዱስ እስጢፋኖስም ጸሎት ብዙ ነፍሳት ድነው ገነት መንግስተ ሰማያትን ወርሰዋል፡፡ የጌታችን ቅዱስ መስቀል እልፍ ሙታንን ያስነሣ ድውያንን ይፈውስ እንደነበር ሁሉ የቅዱስ እስጢፋኖስም ዐፅም ሙታንን ያስነሣ ድውያንን ይፈውስ ነበር፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ የተወገረበት ድንጋይ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ታንጸውበታል፡፡
የቅዱስ እስጢፋኖስ ልደቱና ዕረፍቱ ጥር 1 ቀን ነው፡፡ መእመናንም ሥጋውን ወስደው በክብር ቀበሩት፡፡ ጥቅምት 17 የተሾመበት ነው፡፡ መስከረም 15 ቀን ፍልሰተ ሥጋው ነው፡፡ የቅዱስ እስጢፋኖስ ቅዱስ ዐፅሙ ሙትን ያስነሣ ድውይን ይፈውስ ነበርና አይሁድ በቅናት ተነሥተው እንደ ጌታችን ቅዱስ መስቀል የቅዱስ እስጢፋኖስን ዐፅም አርቀው በመቆፈር ቀብረው በላዩም ቆሻሻ በመጣል ለ300 ዓመት ያህል ተቀብሮ ኖሮ በመጨረሻ በፈቃደ እግዚአብሔር እንደ ቅዱስ መስቀሉ ተቆፍሮ በመውጣት መስከረም 15 ቀን ቅዱስ ዐፅሙ ወጥቶ በክብር በስሙ በታነጸው ቤተ ክርስቲያን በክብር ተቀምጧል፡፡ ይኸውም የሆነው እንዲህ ነው፡- ሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ ካረፈ ከ300 ዓመት በላይ በሆነ ጊዜ ጻድቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ሲነገሥና ሃይማኖትን በመላው ዓለም አቀና፡፡ ተዘግተው የነበሩ ገዳማትና አብያተ ክርስያናት ተከፈቱ፡፡ በዚህም ወቅት የቅዱስ እስጢፋኖስ ሥጋው በሚገኝበት በኢየሩሳሌም አካባቢ ሉክያኖስ ለሚባል ሰው ቅዱስ እስጢፋኖስ በራእይ ተገለጠለትና ‹‹እኔ እስጢፋኖስ ነኝ፣ ሥጋዬ በዚህ ቦታ ተቀብሯል›› በማለት ሥጋውን ያወጡ ዘንድ አዘዘው፡፡ ሉክያኖስም ለኢየሩሳሌሙ ኤጰስ ቆጶስ ሄዶ ነገረውና ወደ ቦታው ሄደው ሲቆፍሩ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነና ሳጥኑ ተገኘ፡፡ ከሳጥኑ እጅግ ደስ የሚል በዓዛ ወጣ፡፡ በዚያ ቦታም ቅዱሳን መላእክት ሲያመሰግኑ ተሰሙ፡፡ ኤጲስ ቆጶሳቱና ካህናቱም የቅዱስ እስጢፋኖስን ሥጋ በክብር በታላቅ ዝማሬ ወስደው አስቀመጡት፡፡
ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፡- በኢየሩሳሌም የሚኖር የቁስጥንጥንያ ተወላጅ የሆነ ስሙ እለእስክንድሮስ የሚባል ሰው ነበር፡፡ እርሱም ለቅዱስ እስጢፋኖስ ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ሠርቶለት ሥጋውን አፍልሰው በዚያ በክብር አኖሩት፡፡ ከ5 ዓመት በኋላም እለእስክንድሮስ ዐረፈና ሚስቱ በቅዱስ እስጢፋኖስ አስክሬን ጎን ቀበረችው፡፡ ከሌሎች ከ5 ዓመቶችም በኋላ ሚስቱ የባሏን አስክሬን ወደ ቁስጥንጥንያ አገር ይዛ ልትሄድ አስባ ወደ መቃብሩ ስትሄድ የባሏን አስክሬን የወሰደች መስሏት በእግዚአብሔር ፈቃድ የቅዱስ እስጢፋኖስን ሣጥን ወስዳ እስከ አስቃላን ከተማ ድረስ ተሸከመችውና በመርከብ ተሳፍራ ወደ ቁስጥንጥንያ ሄደች፡፡
የእለእስክንድሮስም ሚስት በመርከብ ስትጓዝ ጣዕም ያለው የመላእክትን ዝማሬ ሰማች፡፡ ልታየውም በተነሣች ጊዜ ሣጥኑ የቅዱስ እስጢፋኖስ ሥጋ ያለበት መሆኑን ዐወቀቸ፡፡ ወደ ኢየሩሳሌምም ለመመለስ አልተቻላትም ይልቁንም ይህ እንዲሆን የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ዐውቃ ለዚህ ክብር ስላበቃት አመሰገነች፡፡ ቁስጥንጥንያም እንደደረሰች ለሊቀ ጳጳሱ በእግዚአብሔር ፈቃድ የቅዱስ እስጢፋኖስብ ሥጋ ይዛ እንደመጣች ላከችበት፡፡ ካህናቱና ሕዝቡም ሁሉ በታላቅ ደስታ ወጥተው በክብር ተቀበሏት፡፡ ከሥጋውም ብዙ ተአምራት ተገልጠው ታዩ፡፡ ከዚህም በኋላ ሥጋውን በበቅሎ ጭነው ሲጎትቱ ቁስጣንጢኖስ ከሚባል ቦታ ሲደርሱ የቅዱስ እስጢፋኖስን ሥጋ የያዘችው በቅሎ አልንቀሳቀስ አለች፡፡ እግዚአብሔር የቅዱስ እስጢፋኖስ ሥጋው በዚህ ቦታ እንዲኖር የፈቀደ መሆኑን ዐወቁ፡፡ ሥጋውን የተጫነው በቅሎም በሰው አንደበት ‹‹የቅዱስ እስጢፋኖስን ሥጋ በዚህ ሊያኖሩ ይገባል›› ብሎ ተናገረ፡፡ ይህንንም ያዩና የሰሙ ሁሉ እጅግ አደነቁ፡፡ የበለዓምን አህያ ያናገረ አምላክ አሁንም የቅዱስ እስጢፋኖስን ሥጋ የተሸከመችውን በቅሎ እንዳናገራት ዐውቀው ደስ አላቸው፡፡ የሀገሪቱም ንጉሥ በቦታው ላይ ውብ ቤተ ክርስቲያን ሠርተውለት ሥጋውን በውስጧ በክብር አኖሩ፡፡ ከሥጋውም ብዙ አስገራሚ ተአምራት ተፈጽመው ታዩ፡፡
የቅዱስ እስጢፋኖስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፣ በጸሎቱ ይማረን!

27/11/2021

በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሀይማኖት ዓመታዊ እና ወርሃዊ መታሰቢያ በዓላት
--------
”በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ።” (ኢሳ.56:5)
“የቅዱሳን መታሰቢያ ለበረከት ነው።” (ምሳ 10፤7)
እግዚአብሄር ለቅዱሳን በቸርነቱ ከሰጣቸው በረከት ለመሳተፍ መታሰቢያቸውን ማድረግ የግድ ነው “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል። ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።” (ማቴ 10፤40-46) ይላልና ይህም የተባለው በነብያት፣ በጻድቃንና በሌሎችም ቅዱሳን ስም መታሰቢያ ማድረግ እንደሚገባ ለመግለጽ ነው።

ዓበይት በዓላትን እና ንዑስ በዓላትን ሙሉ በሙሉ ሳናካትት በከፊል ዓመታዊ በዓላትን እና ወርሃዊ በዓላትን ነው፡፡

ዓመታዊ በዓላት

#መስከረም
መስከረም 1 ቅዱስ ራጉኤል (ርእስ አውደ ዓመት/
መስከረም 2 ቅዱስ ዮሀንስ /አንገቱ የተቆረጠበት ቀን/
መስከረም 10 ፀደኒያ ማርያም
መስከረም 15 ቅዱስ እስጢፋኖስ(የተሾመበት) (ይህ በዓል ከመስቀል በዓል ጋር የሚታሰብ ነው)
መስከረም 17 ቅዱስ እስጢፋኖስ /በዓለ መስቀል/
መስከረም 21 መናገሻ ማርያም ፣ ግሼን ማርያም ፣ እንጦጦ ማርያም
መስከረም 29 ቅድስት አርሴማ

#ጥቅምት
ጥቅምት 5. አቡነ ገብረመንፈስ
ጥቅምት 9. አባ አትናስዮስ(እረፍቱ)
ጥቅምት 12.አባ ዲሜጥሮስ(እረፍቱ)
ጥቅምት 13.አባ ዘካርያስ(እረፍቱ)
ጥቅምት 14. አቡነ አረጋዊ (የተሰወሩበት)፡ በገብረክርስቶስ(እረፍቱ)፡ ኢትዮጰያዊውን ጀንደረባ ያጠመቀውን ዲያቆኑ ፊሊጶስ (እረፍቱ)
ጥቅምት 17. ቅዱስ እስጢፋኖስ(የተሸመበት)
ጥቅምት 20. ዮሐንስ ሐፂር(እረፍቱ)
ጥቅምት 21.ነቢየ እግዚአብሔር ኢዩኤል (እረፍቱ)
ጥቅምት 22. ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ (እረፍቱ)
ጥቅምት 25 አቡነ ሀቢብ አረፈ
ጥቅምት 27. መድሐኔአለም፣ አባ መብዓ ፅዮን (እረፍታቸው)
ጥቅምት 8. ቅዱስ አማኑኤል
ጥቅምት 30. ቅዱስ ማርቆስ /ልደቱ/

#ህዳር
ህዳር 6. ቁስቋም ማርያም እመቤታችን ስደቷን ጨርሳ የገባችበት
ህዳር 7. ሕንጻ ቤቱ ለጊዮርጊስ/ አጥንቱ ተሰብስቦ መቃብር ቤት የገባበት/
ህዳር 8. በዓል አርባዕቱ እንስሳ /ክሩቤል ሱራፌል/አባኪሮስ
ህዳር 11. ዕረፍተ ቅድስት ሀና
ህዳር 12. ቅዱስ ሚካኤል
ህዳር 13. እግዚአብሔር አብ/የአእላፍ መላእክት ቀን
ህዳር 14. አባ ዳንኤል እረፍቱ
ህዳር 15. ቅዱስ ሚናስ እረፍቱ
ህዳር 18. ሐዋርያው ቅዱስ ፊሊጶስ እረፍቱ ከ12ተ ሐዋርያት አንዱ
ህዳር 21. ፅዮን ማርያም/የእመቤታችን በዓል/
ህዳር 24. ሀያአራቱ ካህናተ ሰማይ /ደብረ ሊባኖስ/
ህዳር 25. ቅዱስ መርቆሪዎስ ሰማዕቱ /እረፍቱ/
ህዳር 26. አቡነ ሀብተማርያም /ደብረሊባኖስ/፣ አባ ኢየሱስ ሞአ(እረፍቱ)
ህዳር 27. አባ ተክለሃዋርያት፣ ሐዋርው ቅዱስ ያዕቆብ በሰማዕትነት አረፈ
ህዳር 29. ተፈፃሚ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ(እረፍቱ)

#ታህሳስ
ታህሳስ 1.ነቢዩ ኤልያስ የተወለደበት ቀን
ታህሳስ 3. በአታ ለማርያም እመቤታችን በሶስት አመቷ ቤተመቅደስ የገባችበት፡ አቡነ ዜና ማርቂስ(እረፍቱ)
ታህሳስ 4. ሐዋርያው እንድርያስ በሰማዕትነት ያረፈበት
ታህሳስ 6. ቅድስት አርሴማ (ቅዳሴ ቤቷ)
ታህሳስ 12. አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ
ታህሳስ 13. ቅዱስ ሩፋኤል
ታህሳስ 15. አባ ጎርጎርዮስ (እረፍቱ) ዘሀገረ አርማንያ
ታህሳስ 19. በዓለ ቅዱስ ገብርኤል
ታህሳስ 22. ብስራተ ገብርኤል /እመቤታችን ክርስቶስን እንደምትወልድ ያበሰረበት/
ታህሳስ 24. አቡነ ተክለሀይማኖት /ልደታቸው/
ታህሳስ 28. ቅዱስ አማኑኤል በዓለ ልደት ለእግዚእነ ገና
ታህሳስ 29. ቅዱስ በዓለ ወለድ /ተዘከረ ልደቱ ለእግዚነ/ገና/

#ጥር
ጥር 1. ቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሚ ሰማእት (እረፍቱ)
ጥር 4. ቅዱስ ዮሐንስ /ወንጌላዊ/ወልደ ነጎድጓድ
ጥር 6. ኢየሱስ/ግዝረቱ ለእግዚእነ /እየሱስ ገዳም/ ነቢዩ ኤልያስ የተሰወረበት ቀን
ጥር 7. ቅድስት ሥላሴ
ጥር 11. በዓለ ጥምቀት
ጥር 12. በዓለ ቅዱስ ሚካኤል /ቃና ዘገሊላ/
ጥር 13. ቅዱስ ሩፋኤል /የቃና ዘገሊላ በዓል መታሰብያ/
ጥር 14 አቡነ አረጋዊ
ጥር 15. ቅዱስ ቂርቆስ እየሉጣ
ጥር 18. ቅዱስ ጊዮርጊስ /ዝርዎተ አጽሙ/
ጥር 21. የእመቤታችን በዓለ እረፍት
ጥር 22. ቅዱስ ኡራኤል ቃል ኪዳን የተቀበለበትና የተሸመበት ቀን
ጥር 23. ሐዋርያው ጢሞቲዋስ (እረፍቱ)
ጥር 24. አቡነ ተክለሃይማኖት
ጥር 28. ቅዱስ አማኑኤል ለ5000 ሰዎች ጌታችን ህብስቱን ያበረከተበት

#የካቲት
የካቲት 3. አባ ያዕቆብ (እረፍቱ)
የካቲት 8. ጌታችን አምላካችን መድሀኒታችን ወደ ምኩራብ የገባበት ቀን(የአረጋዊው የስምዖን ታሪክ ልብ የበሉ)
የካቲት 9. አባ በርሱማ (እረፍቱ)
የካቲት 15. ነቢዩ ዘካርያስ (እረፍቱ)
የካቲት 16. ኪዳነምህረት /እመቤታችን ቃልኪዳን የተቀበለችበት/
የካቲት 20. ቅዱስ ፊልጶስ
የካቲት 23. ቅዱስ ጊዮርጊስ
የካቲት 26. ነቢዩ ሆሴዕ (እረፍቱ)
የካቲት 28. ሮማዊው ቅዱስ ቴዌድሮስ(እረፍቱ)

#መጋቢት
መጋቢት 4. ቅዱስ ጊዮርጊስ /ደብረዘይት/
መጋቢት 3. ተዝካረ ልደቱ ለአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ
መጋቢት 10. መስቀሉን ንግስት እሌኒ ቆፍሬ ያገኘችበት ቀን መድሐኔአለም
መጋቢት 15. ቅድስት ሳራ(እረፍቷ)
መጋቢት 22. ጥንተ ሆሳእና
መጋቢት 27. ቸሩ መድሃኒአለም (የጌታችን ጥንተ ስቅለቱ መታሰቢያ)
መጋቢት 29. የበዓለ ወልድ /የጌታችን ጽንሰት/

#ሚያዝያ
ሚያዝያ 22. አባ ይስሀቅ(እረፍቱ)
ሚያዝያ 23. የቅዱስ ጊዮርጊስ በዓለ እረፍት
ሚያዝያ 27. ምስካየ ሕዙናን /ስደተኛው መድሀኒአለም/
ሚያዝያ 30. ቅዱስ ማርቆስ በሰማዕትነት ያረፈበት ቀን ነው

#ግንቦት
ግንቦት 1. ልደታ እመቤታችን የተወለደችበት ቀን ነው
ግንቦት 7. ሊቁ አቡነ አትናቲዎስ (እረፍቱ)
ግንቦት 11. ቅዱስ ያሬድ(የተሰወረበት)
ግንቦት 12. አቡነ ተክለሃይማኖት /አፅማቸው የፈለሰበት /ክርስቶስ ሳምራ
ግንቦት 14. አቡነ አረጋዊ ቅዱስ ገብረክርስቶስ
ግንቦት 17. አባ ኤጲፋንዮስ(እረፍቱ)
ግንቦት 21 . እመቤታችን ማርያም /እመቤታችን በድብረ ምጥማቅ በምትባል ቦታ ወርቅ ወንበር ላይ ተቀምጣ ለአራት ቀን የታየችበት ነው
ግንቦት 24. ቁስቋም ማርያም /የስደቷ መነሻ/
ግንቦት 28. ቅዱስ አማኑኤል፣ ቅድስት አመተ ክርስቶስ (እረፍቷ)

#ሰኔ
ሰኔ 8. ከደረቅ ዓለት ላይ ውሃን ያፈለቀበት ከ33ቱ ከእመቤታችን በዓል አንዱ
ሰኔ 9. ታላቁ ነብይ ሳሙኤል (እረፍቱ) (የሐና ልጅ)
ሰኔ 11.ሰማዕቱ ቅዱስ ገላውድዮስ (እረፍቱ)
ሰኔ 12. ቅዱስ ሚካኤል ባሕራንን ከውሃ ያወጣበት ቀን ነው (አፎምያን ከሰይጣን ያዳነበት)፣ ቅዱስ ላሊበላ(እረፍቱ)
ሰኔ 20.ሕንፀተ ቤተ ክርስቲያን
ሰኔ 21. ጌታችን /የእመቤታችንን ቤት ያነጸበት ቀን ነው፡፡ ግሽን ማርያም በጎልጎታ በጌታችን መቃብር የጸለየችበት
ሰኔ 23.ጠቢቡ ሰሎሞን እረፍቱ
ሰኔ 24. አባ ሙሴ ፀሊም (እረፍቱ)
ሰኔ 25. የዮሴፍ ልጅ ሐዋርው ይሁዳ እረፍቱ
ሰኔ 26. ኢያሱ እረፍቱ
ሰኔ 27. እረፍቱ ለሐናንያ ሐዋርያ
ሰኔ 30. ልደተ ዮሐንስ መጥምቅ

#ሐምሌ
ሐምሌ 2. ሐዋርያው ታዴዎስ (እረፍቱ)
ሐምሌ 3. አባ ቄርሎስ (እረፍቱ)
ሐምሌ 4. ነቢዩ ሶፎንያስ እረፍቱ
ሐምሌ 5. ጴጥሮስና ጳውሎስ እረፍታቸው
ሐምሌ 7. አጋእዝተ ዓለም ስላሴ በአብርሃም ቤት፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እረፍቱ
ሐምሌ 8. አባ ኪሮስ
ሐምሌ 10.ሓዋርያው ናትናኤል እረፍቱ
ሐምሌ 15. ኤፍሬም ሶርያዊው እረፍቱ
ሐምሌ 16. ወንጌላዊው ዮሐንስ እረፍቱ
ሐምሌ 18. የጻድቁ የዮሴፍ ልጅ ሐዋርያው ያዕቆብ እረፍቱ
ሐምሌ 19. በዓለ ቅዱስ ገብርኤል ቂርቆስና እየሉጣን ከእሳት ያዳነበት ቀን ነው/ቁልቢ ገብርኤል/
ሐምሌ 22. ቅዱስ ኡራኤል ፣ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት የተቀበሉበት
ሐምሌ 23. ቅዱስ ጊዮርጊስ
ሐምሌ 26. ቅዱስ ዮሴፍ (እረፍቱ) ፣ አቡነ ሀብተማርያም ዘደብረሊባኖስ
ሐምሌ 28.ቅድስት መስቀል ክብራ (እረፍቷ) (የቅዱስ ላሊበላ የትዳሩ አጋር)
ሐምሌ 30.ቅድስት ማርያም ክብራ (እረፍቷ)

#ነሐሴ
ነሐሴ 7.ፅንሰታ ለማርያም
ነሐሴ 13. እግዚአብሔር አብ በደብረታቦር ተራራ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱ ለእነ ሙሴና ኤልያስ የገለጸበት ቀን ነው/የቡሄ በዓል/
ነሐሴ 15. ቅድስት እነባመሪና(እረፍቷ)
ነሐሴ 16. ኪዳነምህረት
ነሐሴ 19. አባ መቃርስ የስጋው ፈልሰት
ነሐሴ 21. ጌቴ ሴማኒ ገዳም እመቤታችን (ሰበታ)
ነሐሴ 24. አቡነ ተክለሃይማት እረፍታቸው ፤ ክርስቶስ ሳምረ
ነሐሴ 27 ቅዱስ ሱርያል (4 ሊቀ መላእክት)
ነሐሴ 28.አበው አብርሃም ይህሳቅ ያዕቆብ (እረፍታቸው)
ጳጉሜ
ጳጉሜ 2.ሐዋርያው ቲቶ (እረፍቱ)
ጳጉሜ 3. ቅዱስ ሩፋኤል
ጳጉሜ 4.አባ ባይሞን(እረፍቱ)

ወርሃዊ በዓላት:-

1. ልደታ፣ ዮሐንስ፣ ራጉኤል፣ እዮብ፣ ኤልያስ፣ ሶስና
2. በርቶሎሚዎስ፣ ጴጥሮስ፣ አባ ጉባ፣ መሪና
3. በአታ ማርያም ፣ ፋኑኤል ፣ ዜና ማርቆስ
4. ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ፣ አባ መቃርዎስ፣ አባ አብርሐ
5. ጴጥሮስና ጳውሎስ ፣ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
6. ቁስቋም ፣ ኢየሱስ ፣ ቅድስት አርሴማ ፣ እያሱ
7. አጋዕዝተ አለም ስላሴ ፣ ዲዎስቆሮስ
8. ኪሮስ፣ ማቲዮስ፣ ኪሩቤል አርባእቱ እንስሳ፣ ዘካርያስ
9. ሰልስቱ ምዕት፣ ቶማስ፣ እስትንፋሰ ክርስቶስ፣ አትናትዮስ
10. መስቀለ ክርስቶስ ፣ ናትናኤል ሐዋርያ ፣ ፀደንያ ማርያም
11. ሐና እና ኢያቄም ፣ አቡነ ሐራ
12. ቅዱስ ሚካኤል፣ አባ ሳሙኤልና፣ ናትናኤል ሐዋርያ
13. ፀጋ ኢየሱስ/ ዘርአ ብሩክ/ ፣ ሩፋኤል ፣ እግዚአብሔር አብ
14. አቡነ አረጋዊ፣ ገብረ ክርስቶስ/ገብረ መርአዊ/ ዘሚካኤል፣ ሙሴ ፀሊም
15. ቂርቆስና እየሉጣ ፣ ሚናስ
16. ኪዳነ ምህረት ፣ ኤልሳቤጥ
17. እስጢፋኖስ ፣ ገሪማ ፣ ወለተ ጴጥሮስ ፣ አቡነ በትረ ማርያም ፣ ያዕቆብ ወልደ ዘብዲዮስ ፣ ሙሴ
18. ማዕቀብ አልፋ ፣ ኢዩስጣቲዮስ ፣ ፊሊጶስ
19. ቅዱስ ገብርኤል ፣ ስልስቱ ደቂቅ ፣ ይመርሐነ ክርስቶስ
20. ዮሐንስ ሀፂር ፣ ሕንፀተ ቤተ ክርስቲያን
21. ቅድስት ድንግል ማርያም
22. ሉቃስ ፣ ደቅስዮስ ፣ ኡራኤል ፣ ብስራተ ገብርኤል
23. ቅዱስ ማር ጊዮርጊስ
24. አቡነ ተክለ ሐይማኖት ፣ ጎርጎርዮስ ፣ 24ቱ ካህናተ ሰማይ ፣ ክርስረቶስ ሰምራ
25. ቅዱስ መርቆሬዎስ ፣ አቡነ ሀቢብ
26. ዮሴፍ፣ ቶማስ ዘህንደኬ፣ አቡነ ሀብተ ማርያም
27. መድሐኔአለም ፣ አቡነ መባዓ ፅዮን ተክለ አልፋማርያም
28. አማኑኤል ፣ አበው አብርሃም ይህሳቅ ያዕቆብ
29. በዓለ እግዚአብሔር (በዓለወልድ)፣ ቅዱስ ላሊበላ
30. ቅዱስ ማርቆስ፣ ዮሐንስ መጥምቅ

“እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ።” ዘሌ 19፤2 በተባለው መሰረት ቅዱስ የሚለው ስያሜ በምግባር በቱርፋት ለጽኑ የሚታየውን አለም ለለወጡ ከዚህ አለም ደስታ ተድላ ይልቅ ዘላለማዊውን ለመረጡ ፤ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ እራሳቸውን ለኃላፊው ነገር ላላስገዙ የሚሰጥ ስያሜ ነው።
የቅዱሳን አምላክ ከሁሉ ነገር ይጠብቀን አሜን!

Want your school to be the top-listed School/college in Addis Ababa?

Click here to claim your Sponsored Listing.

Location

Category

Website

Address


Addis Ababa