06/10/2026
አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተቋማዊ ባህል በማዳበርና ያለውን አቅም በአግባቡ በመጠቀም ለለውጥ ጉዞ እንዲተጋ ጥሪ ቀረበ
መስከረም 26/2019 ዓ.ም
+++++++++++++++++++++++++++++++++++++
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሥራት ዓፀደወይን ከአካዳሚክ እና ከአስተዳደር ሠራተኞች እንዲሁም ከተማሪዎች ሕብረት ተወካዮች ጋር በመሆን የበዓለ ሲመታቸውን የመጀመሪያ መድረክ ንግግር አድርገዋል። በመድረኩም የተቋሙን ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች እና የለውጥ እቅዶች ይፋ አድርገዋል።
ዶ/ር አሥራት በንግግራቸው አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አራተኛ ቤታቸው መሆኑን ገልጸው ተቋሙ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በአዎንታዊ መልኩ የሚለይባቸው በርካታ ጥንካሬዎች እንዳሉት አንስተዋል። ሆኖም አሁን ያሉትን ጠንካራ ጎኖች ይበልጥ በማጠናከር የታዩ ክፍተቶችን በአጭርና በረጅም ጊዜ ዕቅዶች በመሙላት እንዲሁም ከኢንዱስትሪዎች እና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመሥራት ዩኒቨርሲቲውን በምርምር፣ በፈጠራና በኢኖቬሽን የላቀ የልህቀት ማዕከል ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል::
ዩኒቨርሲቲው የISO 9001:2015 የጥራት እውቅና የምስክር ወረቀት ያገኘ ብቸኛ ተቋም እና የ6 አካዳሚክ ፕሮግራሞች ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኙ፣ 54 በመቶ የ3ኛ ዲግሪ ባለቤቶችን ያካተተ ብቁ መምህራን ማኅበረሰብ ያለበት እና ከተልዕኮ ልየታ አንፃር ቀዳሚ ተቋም መሆኑ ተገልጿል።
በመሆኑም የለውጥ ጉዞውን ለማሳካት ተስማሚ ማሻሻያዎች እና የስትራቴጂክ ዕቅድ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ እንደሚሠራ ተመላክቷል።
በመጨረሻም ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና ገንቢ አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን ዶ/ር አሥራት ከአካዳሚክ ሠራተኞች፣ ከተማሪዎች ሕብረት እና ከአስተዳደር ሠራተኞች በተዋረድ ለተነሱ በርካታ ገንቢ ሐሳቦችና ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽና መፍትሔ እንደሚሰጡ ገልጸዋል።
______________________________________________________________________
ስለ ዩኒቨርሲቲያችን ዝርዝር መረጃ ለማግኘት የሚከተሉትን አማራጮች ይጠቀሙ::
ድረ-ገፅ: https://www.aastu.edu.et
ፌስቡክ: http://facebook.com/aastu.edu.et
ቴሌግራም: t.me/pir2011
ኢሜይል:[email protected]/[email protected]
ዩቲዩብ :youtube.com/
ኤክስ (ትዊተር): x.com/aastu_addis
ሊንክድኢን: https://bit.ly/aastu_officialin
______________________________________________________________________