08/03/2023
ዩዴሞኒያ 28-ዶ/ር ሌሊ ሌንሳሞ
====================
ሌሊ በትምህርቷ በጣም ጎበዝ ናት። አባቷ ደግሞ ዶክተር ነው። ስለዚህ 12ኛ ክፍል ጨርሳ ዩኒቨርሲቲ ስትገባ ምን እንደምትማር ግልፅ ነበር። ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህክምና ትምህርት ቤት ገባች። እነዛ እንኳን ተነበው ተቀደው የማያልቁ መፅሀፎችን አነበበች። እጅግ ብዙ እንቅልፍ የለሽ ዲውቲዎችን ህክምና እየሰራች አሳለፋ ዶክተር ሆና ተመረቀች። እኔ ሳይካትሪ ስፔሻላይዝ እያደረግሁ እሷ ደግሞ አምስተኛ አመት ህክምና ተማሪ ሆና የሳይካትሪ ሴሚናር ስታቀርብ አይቼያት አውቃለሁ። "ምናለ ሳይካትሪ በተማረች!" ብዬ ተመኝቼ ነበር።
ከምረቃ በኋላ ግን ሼክስፒራዊ ጥያቄው አፍጥጦ መጣ። መሆን ወይም አለመሆን። ዶ/ር ሌሊ ከልጅነቷ ጀምሮ ሙዚቃ ትወዳለች። ደግሞ ተስጥኦም አላት። ህክምናን ትወዳለች። ሙዚቃን ደግሞ የበለጠ ትወዳለች። ኑረታዊ ጭንቀት (Existential anxiety) ግራ አጋባት። በመጨረሻ ከባዱን ውሳኔ ወስና ልቧን ተከተለች። She flirted with medicine and married music.😂 የስራ አቅጣጫዋን መቶ ሰማኒያ ዲግሪ ቀየረች። ምክኒያቷን ስትጠየቅ "ውስጥህ የሚንቦለቦል ፍላጎት ካለህ ከመቀየር ውጭ አማራጭ የለም!" ትላለች።
ለውጡ ቀላል አልነበረም። ሆኖም ጠንክራ በመስራት እንዲሁም በውስጧ ላለው ተስጥኦ ብዙ ነገሮችን መስእዋት በማድረግ አሁን መስመር እየያዘላት ነው። የJulian Marley ጊታሪስት ከሆነው Jamie Hinckson ጋር አብራ መስራት ጀምራለች። ነገ የት እንደምትደርስ መገመት ያስቸግራል።
ዶ/ር ሌሊ እውነተኛ ማንነቷን ስታወጣ ይቅርታ አትጠይቅም። She is unapologetically authentic. በየትኛውም ዘርፍ ቢሰማሩ የከፍተኛ ትምህርት መማርና መጨረስ መልካም ነው። ተስጥኦና ፍላጎት ሲገጣጠሙ ደግሞ ልብን መከተል የተሻለ ጥሩ ነው።
'ባሉ ዳንቻሆ' የሚለው ሙዚቃዋ በሲዳምኛ "ሁሉ መልካም" ማለት ነው። Way to go Leli.
ዩዴሞኒያ ለሁላችን!!!! ባሉ ዳንቻሆ!!!!!!
ዶ/ር ዮናስ ላቀው።
የአፕል ካምፓኒ መስራችና ፈጣሪ የነበረው ስቲቭ ጆብስ ከመሞቱ በፊት በስታንፎርድ ዩንቨርስቲ የ2005 ዓ.ም. ተመራቂ ተማሪዎችን ለመመረቅ ተገኝቶ ነበር፡፡ በዚህ የምርቃት መድረክ ላይ የተናገረው ነገር የብዙ ሰዎችን ልብ ያነሳሳ ነበር፡፡ በዛን ሰሞን ጆብስ የPancreatic ካንሰር ሕመምተኛ የነበረ በመሆኑ በሕይወት ሊቆይ የሚችለው ከሶስት እስከ ስድስት ወር ብቻ እንደነበር ሐኪሞቹ ነግረውት ነበር፡፡ ሞት አፋፍ ላይ ሆኖ ተመራቂ ተማሪዎቹ ሶስት ጥያቄዎችን ለራሳቸው ይጠይቁ ዘንድ መክሮአቸዋል፡፡ ጥያቄዎቹም፡-
1ኛ፡- ‹‹መኖር የምፈልገውን ሕይወት ነው እየኖርኩ ያለሁት? የምፈልገውንስ ነው እየሰራሁ የምገኘው? (Am I living the life that I want and doing the work that I want to do?)››
ጆብስ በሕይወታችን ደስተኛ የሚያደርገን የምንፈልገውን ሕይወት በመኖርና የሚያስደስተንን ስራ በመስራት ነው ሲል ይገልፃል፡፡ ብዙዎቻችን በተኮረጀ ሕይወት ዕድሜአችንን እያቃጠልን እንገኛለን፡፡ ሰው እንዴት የሌላ ሰውን ሕይወት ይኮርጃል? ሰው መነሻ ሃሳብ ሊኮርጅ ይችላል፤ የሌላ ሰው ህይወት ግን አይኮረጅም!
2ኛ፡- ‹‹ዛሬ የሕይወቴ የመጨረሻ ቀን ቢሆን ኖሮ ልሰራ የምፈልገውን ለመስራት እችላለሁን?›› (If today were the last day of my life, would I want to do what I am about to do today?)››
ለዚህ ጥያቄ መልሳችን ‹‹አይደለም›› ከሆነ ልንለውጣቸው የሚገቡን ብዙ ነገሮች አሉ ማለት ነው፡፡ መልሳችን ‹‹አዎ›› እስከሚሆን ድረስ ጥያቄአችንን ማቋረጥ እንደሌለብን ይመክረናል፡፡ ይሄን ጥያቄ ለመመለስ ከራሳችን ጋር ግብግብ ልናደርግ ይገባናል ሲል ያሳስባል፡፡
3ኛ፡- ‹‹እየሰራሁ ያለሁት የምወደውን ነው? (Am I doing what I love?)››
በነገራች ላይ የምንፈልገው ሁሉ የምንወደው ላይሆን ይችላል፡፡ አንዳንዶቻችን የፍላጎታችን ምንጭ የሌሎች ፍላጎት ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ፍላጎታችን የራሳችን መሆኑን ማረጋገጥ አለብን፡፡ ሁለተኛ የምንፈልገው ነገር የምንወደው መሆኑን መፈተሽ ይገባናል፡፡ ሶስተኛ የወደድነውን ካገኘነው በኋላ የሚያስደስተን መሆኑን ቀድመን ልንረዳው ያስፈልጋል፡፡ የወደድነው ሁሉ ካላስደሰተን ትክክለኛ ውዴታችን አይደለም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እውነተኛ መውደዳችን ምን ላይ እንደሆነ ቀድሞ መመርመር ይገባናል ማለት ነው፡፡ አለበለዚያ ትርጉም የሌለው የቅብዝብዝ ሕይወት ነው የምናሳልፈው፡፡
ለዚህ ነው እህቴ ስቲቭ ጆብስ ‹‹Your time is limited, so do not waste it living someone else’s life‹‹ የሚለን፡፡ አዎ ዕድሜያችን ውስን ነው! የሌላ ሰውን ኑሮ በመኖር የህይወት ዘመናችንን አናባክነው፡፡