AY Bible Club የወጣቶች መጽሐፍ ቅዱስ ማሕበር

AY Bible Club የወጣቶች መጽሐፍ ቅዱስ ማሕበር የዘመን መጨረሻ ቀርቧል። ክፋት ምድርን እንደሰደድ እሳት እየወረሰ ነው። በመልካምና በክፉ መካከል የሚደረገው ተጋድሎ በቅርቡ ይደመደማል! ተዘጋጅተዋል?

18/08/2026

በአሕዛብ መካከል ሥራውን አስታውቁ
============================

📖“በዚያም ቀን እንዲህ ትላላችሁ፦ እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ስሙንም ጥሩ፤ በአሕዛብ መካከል ሥራውን አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ያለ እንደ ሆነ ተናገሩ።”

— ኢሳይያስ 12፥4

በተራራ ላይ የተለኮሰ እሳት አድማሱ የተገደበ አይደለም። ይልቁን በየአቅጣጫው ብርሃኑን ይረጫል። ይህም ብርሃን ለሁሉም የሚታይ ይሆናል።

“እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም።” (ማቴ 5፥13-14) በማለት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ "የመውጣትን" አስፈላጊነት ሲናገር እንመለከታለን። ብርሃናችን የሚገኘው "የዓለም ብርሃን" ከሆነው ከእርሱ መሆኑ ደግሞ ብርታትንና ድፍረትን ይሰጠናል (ዮሐ 8፥12)።

ምስክርነት የሌለው ህይወት እውነተኛ የክርስቲያን ልምምድ አይደለም። ቃላትን አውጥተን ለሌሎች የእግዚአብሔርን ስራ የማውራት ስጦታው ባይኖረን እንኳን ምንም ሳንናገር በህይወታችን ብቻ መመስከር እንችላለን።

“በዚያም ቀን እንዲህ ትላላችሁ፦ እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ስሙንም ጥሩ፤ በአሕዛብ መካከል ሥራውን አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ያለ እንደ ሆነ ተናገሩ።” (ኢሳ 12፥4) ይህ ትዕዛዝ ዛሬ ለእኛ ነው። እግዚአብሔርን ላላወቁ፣ ግራ ለተጋቡ፣ ለሚቅበዘበዙ፣ ሰላምን ላጡና የመኖር ትርጉም ለጠፋባቸው ሰዎች "የምስራች" የተባለውን ወንጌል በማወጅ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ልናፈልሳቸው ይገባል።

🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ በህይወቴ ስለሰራኸው ድንቅ ስራ አመሰግንሃለሁ። አቤቱ፣ የአንተን መልካምነትና አዳኝነት ደግሞ ለሌሎች በማካፈል የከበረ ኃላፊነቴን መወጣት እንድችል በፀጋህ እርዳኝ። አሜን።

17/08/2026

መድኃኒቴ፣ ኃይሌና ዝማሬዬ
============================

📖“እነሆ፥ አምላክ መድኃኒቴ ነው፤ ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌና ዝማሬዬ ነውና፥ መድኃኒቴም ሆኖአልና በእርሱ ታምኜ አልፈራም ትላለህ።”

— ኢሳይያስ 12፥2

የእግዚአብሔር ልጆች ተብሎ መጠራት እንዴት መታደል ነው። በነገር ሁሉ አብሮን የሚሆን መልካም አባት አለን። እርሱ ቢመኩበት የሚያስመካ፣ ቢደገፉበት የማይጥል ፅኑ አምላክ ነው።

ኢሳይያስ ይህን አምላክ እንደዚህ በማለት ያወድሰዋል፦ “እነሆ፥ አምላክ መድኃኒቴ ነው፤ ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌና ዝማሬዬ ነውና፥ መድኃኒቴም ሆኖአልና በእርሱ ታምኜ አልፈራም ትላለህ።” (ኢሳ 12፥2) ከዚህ የውዳሴ መዝሙር ዕንቁ የሆኑ ትምህርቶችን መቅሰም እንችላለን።

አንደኛ፣ መድኃኒቴ

በበሽታ የተያዘ ሰው ከደዌው የሚያላቅቀውን ፈዋሽ መድኃኒት ይፈልጋል። ይህን ማግኘት ካልቻለ ህይወቱን ማስቀጠል ስለሚሳነው ለሞት እጅ ይሰጣል። የኃጢአት በሽታም እንዲሁ ነው። ፈጥነን ወደ ፀጋው ዙፋን በእምነት ካልቀረብንና የኃጢአትን ይቅርታ ካላገኘን ከዘላለማዊ ህይወት በመጉደል ወደ ዘላለማዊ ሞት እንሄዳለን። “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።” (ሮሜ 6፥23) እንደ 'ሚል ቅዱስ ቃሉ "መድኃኒት" ወደ ሆነው አምላክ ፈጥነን ልንመጣ ያስፈልጋል። እርሱም በመስቀል ላይ በተከፈለው ቤዛነት የኃጢአት ቀንበራችንን ከላያችን ላይ ያንከባልልልናል።

ሁለተኛ፣ ኃይሌ

ሁልጊዜ እንደ በረታን ላንዘልቅ እንችላለን። የሆነ ወቅት ላይ ደንቀፍቀፍ ማለት ያጋጥመን ይሆናል። ይህም አቅማችንን አሟጦት ደካሞች ያደርገናል። ግና መጨረሻችን በዚህ አያበቃም። እንደ ተፍረከረክን ከቶ አንቀርም። ኃያሉ አምላክ ኃይሉን ይሞላብናል። በድካም የሰለሉትን ጉልበቶቻችንን እንደ ብሆር እግሮች ያፀናቸዋል።

ሶስተኛ፣ ዝማሬዬ

ከኃጢአት በሽታ የተፈወሰና ድካሙ በብርታት የተለወጠለት ሰው እንዴት ዝም ማለት ይቻለዋል። ይልቁን የምስጋናን መስዋዕት ያቀርባል እንጂ። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ያደረገልንን ነገር ሁሉ በማሰብ በምስጋና እፊቱ ልንቀርብ ይገባል።

ይህን ስንረዳ ታዲያ እንደዚህ በማለት እናውጃለን፦

“ጕልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፥ መድኃኒቴም ሆነልኝ፤ ይህ አምላኬ ነው አመሰግነውማለሁ፥ የአባቴ አምላክ ነው ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ።” (ዘጸ 15፥2)

“ኃይሌም ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፥ እርሱም መድኃኒት ሆነልኝ።” (መዝ 118፥14)

🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ ከኃጢአት በሽታ የምፈወስብህ መድኃኒቴ፣ ስደክም የምበረታብህ ኃይሌና የምስጋናዬ ምንጭ ዝማሬዬ ስለሆንከኝ እጅግ አድርጌ አመሰግንሃለሁ። አቤቱ፣ ዘውትር ደግሞ በአንተ መታመን እንድችል በፀጋህ እርዳኝ። አሜን።

15/08/2026

አጽናንተኸኛል
============================

📖“በዚያም ቀን፦ አቤቱ፥ ተቈጥተኸኛልና፥ ቍጣህንም ከእኔ መልሰሃልና፥ አጽናንተኸኛልምና አመሰግንሃለሁ።”

— ኢሳይያስ 12፥1

አንዳንድ ጊዜ አባቴ ከእኔ መለየቱ "እውነት እውነት" አልመስልህ ይለኛል። ዓይኑን አፍጥጦ የመጣን ሀቅ ለመካድ እሞክራለሁ። ለአፍታ እንኳን ከሀሳቤ ተለይቶ አያውቅም። አይደለም ስኬቴን ውድቀቴን ላጋራሁ እናፍቃለሁ። ከእርሱ ጋር ብዙ ህልም፣ ብዙ ጉዞ ነበረን። አብረን ቁጭ ብለን "ስለ ነገ" ያወራንባቸው ጊዜያቶች ምኞቶቼ ቅዠት እንደ ሆኑ ሹክ ይሉኛል።

የናፈቀኝ አባቴ ነገ ላይ መድረስ ተስኖት ትላንት ጥሎኝ ሄደ። ዛሬዬ ባለፈው ዘመን ፍቅር ለመኖር ይሞክራል። ከተስፋ ይልቅ ትዝታው ፀንቶበት የኃሊት ይጓዛል። የቀደመውን ጊዜ በመናፈቅ ራሱን በእርሱ ውስጥ ደብቆ አሁንን ይፈራል።

ግና "እንደ ክርስቲያን" ለመጠንከር እሞክራለሁ። ከእንቅልፉ ነቅቶ ዳግም የምንገናኝበት ጊዜ ሩቅ እንደ 'ማይሆን ሳስብ ለመፅናናት ራሴን አዘጋጃለሁ። ሁሉም ነገር በእግዚአብሔር ቁጥጥር ውስጥ መሆኑ በሀዘን ለደቀቀች ነፍሴ ሰላምን ይሰጣታል። ማፅናናቱ በውስጤ ጠልቆ ዛሬን ሳይ "ተመስገን!" እላለሁ። “በዚያም ቀን፦ አቤቱ፥ ተቈጥተኸኛልና፥ ቍጣህንም ከእኔ መልሰሃልና፥ አጽናንተኸኛልምና አመሰግንሃለሁ።” (ኢሳ 12፥1)

🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ ሁኔታዎችን በሙላት መረዳት ባልችል እንኳን አምንሃለሁ። ልቤን ደግፈህ ስለያዝከው ደግሞ አመሰግንሃለሁ። አሜን።

14/08/2026

እግዚአብሔርን በማወቅ
============================

📖“በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጐዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና።”

— ኢሳይያስ 11፥9

በህይወቴ ውስጥ ስላወኳቸው ሰዎች የማልፀፀትባቸው ወገኖች አሉ። እነርሱን ማወቄ እጅግ ጠቅሞኛል። አሁን ላለውም ማንነቴ የተወሰነ ድርሻ አላቸው። በተቃራኒው ደግሞ "ምነው እነዚህን ሰዎች ባላወኳቸው" ያልኩባቸው ወቅቶች ነበሩ።

እውቀት ትልቅ የሆነ ኃይል አለው። ለዚህ ነው የእውቀታችን መሰረት ሊፈተሽ የሚገባው። ማወቅ እንዲሁ ዝም ብሎ መረጃ ከመሰብሰብ በእጅጉ ይለያል። እንኪያስ ከሆነ ግን ያወቅነው የመሰለን ነገር ያጠፋናል።

ከላይ መግቢያ ላይ ለመጥቀስ እንደ ተሞከረው ብዙ ነገር አውቀን በውሳኔያችን የተፀፀትንባቸው ጊዜያቶች ይኖሩ ይሆናል። ነገር ግን አንድ ነገርን በማወቃችን ከቶ ልባችን ዝቅ አይልም። እርሱም "እግዚአብሔርን ማወቅ" ነው።

እስኪ መለስ ብለን ራሳችንን እንጠይቀው። እግዚአብሔርን እናውቀዋለን ወይስ ስለ እግዚአብሔር እናውቃለን? በሁለቱ መካከል ትልቅ የሆነ ልዩነት መኖሩን ልብ ይሏል። ወገኖቼ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀና ግላዊ የሆነ ግንኙነት ሊኖረን ይገባል። ስለ እርሱ በሰሚ ሰሚ ማወቅ ሳይሆን መንፈሱን ተጠማጥመን ራሱን እንዲገልጥልን ልንቃትት ያሻናል። የተለወጠ ህይወት መኖር የምንችለው ከእርሱ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ህብረት ማድረግ ስንችል ብቻ ነው።

“በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጐዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና።” (ኢሳ 11፥9) አምናለሁ ይህ በቅርቡ ተፈፃሚ እንደ 'ሚሆን።

🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ አንተን በግሌ ማወቅና ፍቅርህን በሙላት ማስተዋል እንድችል በፀጋህ እርዳኝ። አሜን።

12/08/2026

ፃዲቅና ታማኝ
============================

📖“የወገቡ መታጠቂያ ጽድቅ፥ የጎኑም መቀነት ታማኝነት ይሆናል።”

— ኢሳይያስ 11፥5

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሕፀፅ አልባ የሆነ ፃዲቅ ነው። የምድር ላይም ቆይታው ኃጢአትን ድል በመንሳት የተጠናቀቀ ነበር። ለታማኝነቱ ከቶ ወደር የለውም። እርሱ ትላንት፣ ዛሬና ነገ ሁሌም ለልጆቹ ታማኝ አምላክ ነው።

እነዚህን ሁለት የክርስቶስ ባህሪያት ኢሳይያስ “የወገቡ መታጠቂያ ጽድቅ፥ የጎኑም መቀነት ታማኝነት ይሆናል።” (ኢሳ 11፥5) በማለት ስዕላዊ በሆነ መልኩ ሲገልጠው እንመለከታለን።

አንደኛ፣ ጽድቅ

በፅድቅ መንገድ ያላለፈ አካል ስለ ፅድቅ ሊያወራ አይችልም። ተከታዮቹንም ሊያፀድቅ አይነሳም። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ፃዲቅ በመሆኑ በኃጢአት ምክንያት ፅድቃቸው የመርገም ጨርቅ ለሆነባቸው መላ ሰብዓዊን የፅድቅ አድራጊና ፈፃሚ ሆኖ መጣ። በእርሱ በተደረገውም ቤዛነትና የመስቀል ላይ ስራ ፀደቅን። “...ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል።” (1ኛ ቆሮ 6፥11)

ሁለተኛ፣ ታማኝነት

እርሱ ፃዲቅ ብቻ ሳይሆን ታማኝም አምላክ ነው። የተናገረውን ይረሳ፣ ቃል የገባውንም ያጥፍ ዘንድ ከቶ ሰው አይደለም። ታማኝነቱ ራሱን እስከ መስጠት አድርሶታል። ታዲያ ይህን በማስተዋል ታማኝ ለሆነልን ጌታ ታማኞች ልንሆን ያስፈልጋል።

🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ ጽድቅን የተጎናፀፍክና ታማኝነትን የደረብክ ፈላጊዬ ስለሆንክ አመሰግንሃለሁ። አቤቱ፣ እኔም ከአንተ ዘንድ የቀረበልኝን ፅድቅ በመቀበል ለአንተ ዘውትር ታማኝ መሆን እንድችል በፀጋህ እርዳኝ። አሜን።

11/08/2026

የእግዚአብሔር መንፈስ
============================

📖“የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።”

— ኢሳይያስ 11፥2

መፅሐፍ ቅዱስ ነገሮች እንዲሁ በአጋጣሚ የሚሆንበትን ታሪክ መዝግቦልን አናገኝም። የሆነው ሁሉ የሆነው፣ እንዲሁም ሊሆን ያለው በእግዚአብሔር ሀሳብ ነው። ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር ለመግለጥ ትንቢት አንደኛውና ዋነኛው መሳሪያ ሆኖ እናገኘዋለን። የጌታችን የእየሱስ ክርስቶስ ስጋ ለብሶ ወደ ምድር መምጣት እንዲሁ የሆነ ነገር ሳይሆን የታሰበበት ጉዳይ ነበር።

ይህን ለመግለጥ መረጃ ከሚሆኑን ክፍሎች መካከል አንዱ “ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፥ ከሥሩም ቍጥቋጥ ያፈራል።” (ኢሳ 11፥1) የሚለው ተጠቃሽ ነው። ቀጠል አድርጎም ስለ ባህሪው ይናገራል። “የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል። እግዚአብሔርን በመፍራት ደስታውን ያያል። ዓይኑም እንደምታይ አይፈርድም፥ ጆሮውም እንደምትሰማ አይበይንም፤” (ቁ 2፣3)

“በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን።” (ፊል 2፥5) ተብሎ እንደ ተፃፈ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ማደሪያ ስፍራዎች እንድንሆን ያስፈልጋል። ይህ የእግዚአብሔር መንፈስ ጥበብ ለጎደለው ጥበብን፣ ማስተዋልን ላጣ ማስተዋልን፣ አቅጣጫን ለሚፈልግ ምክርን፣ አቅመ ቢሶ ለሆነ ኃይልን፣ መገንዘብ ለከበደው እውቀትን፣ እንደ ቃሉ ለመኖር ደግሞ የሚያግዘን ታላቅ ስጦታ ነው። በዚህ የእግዚአብሔር መንፈስ ስንሞላ እግዚአብሔርን በመፍራታችን ሀሴት እናደርጋለን።

🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ ህይወቴ እንዲሁ በአጋጣሚ የሚመራ ሳይሆን በአንተ ሀሳብ መሆኑን እንድረዳ ስላስተማርከኝ አመሰግንሃለሁ። አቤቱ፣ “የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ” በሆነው ስጦታ ትሞላኝ ዘንድ እማፀንሃለሁ። አሜን።

11/08/2026

ያለቀ የተቈረጠ
============================

📖“የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ያለቀ የተቈረጠ ነገርን በምድር ሁሉ መካከል ይፈጽማል።”

— ኢሳይያስ 10፥23

በአሦር ላይ የሚሆነውን የእግዚአብሔር ፍርድ ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ አስር ያስቃኘናል። የአሦር ንጉስ በልቡ ካለው ትዕቢትና ንቀት የተነሳ በእግዚአብሔር ህዝብ ላይ ሲያላግጥ እንመለከታለን። “እርሱ እንዲህ ብሎአልና፦ አስተዋይ ነኝና በእጄ ኃይልና በጥበቤ አደረግሁት፤ የአሕዛብን ድንበሮች አራቅሁ፥ ሀብታቸውንም ዘረፍሁ፥ እንደ ጀግናም ሆኜ በምድር የተቀመጡትን አዋረድሁ፤” (ኢሳ 10፥13) ነገር ግን ፍፃሜው የተሸላለመ እንደማይሆን ዝቅ ብለን ስናነብ እናገኛለን። “ስለዚህም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በወፍራሞች ላይ ክሳትን ይልካል፤ ከክብሩም በታች ቃጠሎው እንደ እሳት መቃጠል ይነድዳል። የእስራኤልም ብርሃን እንደ እሳት ቅዱስም እንደ ነበልባል ይሆናል፤ እሾሁንና ኵርንችቱን በአንድ ቀን ያቃጥላል ይበላውማል።” (ቁ 16-17)

ልብ በኩራት ሲወጠር መጨረሻው መልካም አይሆንም። በፈጠረን አምላክ ላይ ጀርባችንን እንድንሰጥ ከማድረጉም በተጨማሪ ራስ ተኮሮች እንሆናለን። ይህም ወደ ለየለት የጥፋት ግዳና ይወስደናል። ሉሲፈር ሰይጣን የሆነው "እኔ፣ እኔ፣ እኔ" ማለት በጀመረ ጊዜ እንደነበር ልብ ይሏል።

“የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ያለቀ የተቈረጠ ነገርን በምድር ሁሉ መካከል ይፈጽማል።” (ቁ 23) ይህ ተስፋ የተነገረው ከእስራኤል ዘር ለተረፉት ነበር። እርሱ "የወሰነውን" ጥፋት እንደ 'ሚያመጣና አሦራውያንን ከቶ እንዳይፈሯቸው አበረታታቸው።

የክፋት አለቃ የሆነውና በኃጢአት ጠምዝዞ ወደ ራሱ ሊስበን ሌት ተቀን የሚለፋው ጠላት "የተወሰነው" ጥፋት በእርሱ ላይ ተፈፃሚ የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። ታዲያ ያለው ሰዓት ጥቂት መሆኑን አውቆ እንደ ተራበ አንበሳ ሊውጠን አፉን አሞጥሙጦ ዙሪያችን ያደባል። ነገር ግን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ጋር ነውና ከቶ አያገኘንም። ይህም ትልቅ እምነትና ድፍረት ይሆነናል።

🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ ሁሌም ለልጆችህ የምትጠነቀቅ መልካም አባት ስለሆንክ አመሰግንሃለሁ። አቤቱ፣ ጠላትን የማሸንፍበትን ፀጋና ኃይል ሙላብኝ በማለት እፀልያለሁ። አሜን።

07/08/2026

ክፍል አምስት፣ አባትና ሰላም
============================

📖“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።”

— ኢሳይያስ 9፥6

የጨለማ ህይወታችንን የሚገፍልን አምላክ "የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።" አባትነትን ከሰላም ጋር አዋህዶ በመያዝ ወደ ኤደን የምናደርገውን ጉዟችንን በብርሃን ይመራናል።

አንደኛ፣ የዘላለም አባት

አባት መከታ ነው። የቤቱ ዋልታና ማገር ያለው በእርሱ ነው። ስጋ ደግሞ ሟች በመሆኑ አባት ከአጠገብ ሲታጣ ብዙ ነገር ይጎድላል። በሰማይ ያለው አምላክ አባትነቱ ዘላለማዊ በመሆኑ ከቶ አናጣውም። ሁሌም ቅርብ ነው። እንዲህም በማለት የከበረውን ተስፋ ሰጠን፦ “ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ።” (ዮሐ 14፥18)

ሁለተኛ፣ የሰላም አለቃ

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ "የዘላለም አባት" ብቻ ሳይሆን "የሰላም አለቃ" ጭምር ነው። እርሱን ወደ ህይወታችን ስናስገባ የምናገኘው ሰላም ወደር የለውም። የተቅበዘበዘች ነፍስ እረፍትን ታገኛለች። ምን አልባት ዛሬ ሰላምን በማጣት እየባዘንን ያለን ሰዎች እንኖር ይሆናል። ወደዚህ "የሰላም አለቃ" ትመጡ ዘንድ በፍቅር አድማችኃለሁ። “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም።” (ዮሐ 14፥27) በማለት ቃል ገብቷልና።

🛐ፀሎት፡ አምላኬ ሆይ፣ አባቴና ሰላሜ ነህ፤ አመሰግንሃለሁ። አቤቱ፣ ዘላለሜን ከፊትህ እንዳልታጣ በፀጋህ እርዳኝ። አሜን።

06/08/2026

ክፍል አራት፣ ድንቅ መካር ኃያል
============================

📖“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።”

— ኢሳይያስ 9፥6

መጠሪያ ስሜን እወደዋለሁ። አባቴ እንዳወጣልኝ ሳስብ ደግሞ ይበልጥ ደስ ይለኛል። በስሜ አንድም ቀን አፍሬም ሆነ ተሸማቅቄ አላውቅም።

ምንም እንኳን በዚህ ዘመን ስም ማንነትን የመግለጥ እንብዛም አቅም ባይኖረውም በቀደመው ጊዜ ግን ጥልቅ ትርጉም ነበረው።

ከጨለማ ስፍራ በማላቀቅ በብርሃን የሚያራምደን ጌታ ስሙ "ድንቅ መካርና ኃያል" በመባል ቀርቦ እናነባለን። የክርስቶስ ስም እንዲሁ እንደሌሎች ስሞች አይደለም። ስሙ ከስሞች ሁሉ ይለያል። በስሙ ደዌያን ተፈውሰዋል፣ አንካሶች ዘለዋል፣ ዲዳዎች ሰምተዋል፣ ሞት ተሸንፏል።

አዎ፣ ስሙ ድንቅና ኃያል ነው። ድንቅ የሆነን ነገር ማድረግ ይችላል። ለሰው ሁሉ ያቃተ ጉዳይ በስሙ ሲመጣ ቀሊል ይሆናል። ተራራን የመዳን ኃይል ያለው ስሙ ዛሬም ገዝፈው የታዩን ነገሮች ሁሉ ደልዳላ ሜዳ ያደርጋቸዋል።

🛐ፀሎት፣ አምላኬ ሆይ፣ በሕይወቴ ድንቅ የሆነውን ነገር ስለምታደርግ እጅግ አድርጌ አመሰግንሃለሁ። አቤቱ፣ ለኃያሉ ስምህ ደግሞ ክብርን መስጠት እንድችል በፀጋህ እርዳኝ። አሜን።

05/08/2026

ክፍል ሶስት፣ አለቃ
============================

📖“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።”

— ኢሳይያስ 9፥6

የተወለደው ሕፃን ስጦታ ብቻ ሳይሆን አለቃም ጭምር ነው። አለቃ የሚያዘው ሁሉ የሚደረግለት ስልጣን አለው። ያሻውንና ልክ የመሰለውን ነገር ቢከውን ከልካይ የለውም። አለቃ ነውና።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ አለቃ ሆኖ ግን የባሪያን መልክ ያዘ። የከፍታን ስፍራ በፈቃዱ በመልቀቅ የከብቶች በረት ውስጥ ተወለደ። ሁሉን ማድረግ ሲቻለው ግን እኛን ለማዳን ሲል በሸላቾቹ ፊት ዝም አለ።

ፍቅር አለቃነትን አስትቶ አገልጋይ ያደርጋል። ይህም በገሃድ ተንፀባርቋል። አምላክ ሰው በመሆን የዓለምን ህዝብ ሁሉ ይቤዥ ዘንድ በመስቀል ላይ ራቁቱን ተንጠለጠለ።

🛐ፀሎት፣ አምላኬ ሆይ፣ እኔን ከፍ ለማድረግ አንተ ስንቴ ዝቅ አልክ። አባት ሆይ፣ አለቃነትን አስትቶ አገልጋይ ለሚያደርገው ፍቅር መገዛት እንድችል በፀጋህ እርዳኝ። አሜን።

Address

Ras Desta Damtew Street
Addis Ababa

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when AY Bible Club የወጣቶች መጽሐፍ ቅዱስ ማሕበር posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The School

Send a message to AY Bible Club የወጣቶች መጽሐፍ ቅዱስ ማሕበር:

Shortcuts

Share