21/04/2024
!
፨፨////፨፨፨፨////፨፨
ቀናችሁን በፈገግታ ጀምሩ፣ በጠዋት ስሜታችሁን አስተካክሉ። የተበላሹ፣ ያልተሳኩ፣ የሚያበሳጩ፣ የሚያስጨንቁ ሀሳቦችን ለዛሬ ተዎአቸው። ስለዛሬ ቀናችሁ ብቻ አስቡ፣ አሁን ስላላችሁበት፣ አሁን በመዳፋችሁ ስለጨበጣችሁት፣ እግዚአብሔር ስላደላችሁ ፀጋ ብቻ አስቡ። ውስጡ እየተረበሸ ፈገግታን የመረጠ ሰው፣ በከባድ ሁኔታዎች መሃል እራሱን መንከባከብ የማይረሳ ሰው፣ ካጋጠመው ከባድ ሁኔታ በላይ ለእራሱ ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጥ ሰው በጣም ጠንቃራው ሰው ነው። ቀናችሁ ስጦታችሁ ነች፣ ህይወታችሁ በረከታችሁ ነች። የሚያስደስት ነገር ባትመለከቱባት እንኳን ተስፋ አትቁረጡባት፣ ችላ አትበሏት፣ ዋጋ አታሳጧት። ጥቂት የማይባል ሰው ፀሃይ ማየት ይናፍቀዋል፣ ግማሹ የመራመድን ስሜት ማጣጣም ይናፍቃል፣ አንዳንዱ ማውራትን ይመኛል። እናንተ ግን የሰውን ሁሉ ምኞት ያለምንም ክፍያ እያገኛችሁ ከሆነ ስለምን ለትርፍ ነገር ብላችሁ በትካዜ ትዋጣላችሁ? ስለምን ታይቶ በሚጠፋ ጊዜያዊ ችግር ተሰብራችሁ ትቀራላችሁ?
፨፨////፨፨፨፨////፨፨
አዎ! ፈገግ በሉ! እራሳችሁን ዘና አድርጉ፣ የምትወዱትን ምህዳር ለራሳችሁ ፍጠሩ። የወጪው ጩሀትና ወሬ ላይ አተኩራችሁ የእኔ የምትሉትን ንፁ ሰላማችሁን አትጡ። ውጪውን መቆጣጠር ባትችሉ ጆሯችሁ የሚሰማውን፣ አይናችሁ የሚያየውን፣ እግራችሁ የሚሔድበትን፣ እጃችሁ የሚያነሳውንና አፋችሁ የሚናገረውን መቆጣጠር ትችላላችሁ። ማናችንም በራሳችን ሰውነት ላይ ስልጣን እንዳለን በምንም ላይ ስልጣን የለንም። ነገር ግን ስልጣናችንን በአግባቡ እየተጠቀምነው ስለመሆናችን እርግጠኛ መሆን አንችልም። ባህርማዶ የተከናወነ ነገር ሲረብሸን፣ የማይመለከተን ክንውን ቀናችንን ሲያውከው፣ ከእኛ ህይወት ጋር የማይገናኝ ተግባር ሰላም ሲያሳጣን መመልከት ልማዳችን ሆኗል። የዓለምን ገፅ እናስተውል ብዙ ጥሩ ነገር ቢኖርም ከየአቅጣጫው የሚነገረን ነገር ግን አስከፊውና አሳዛኙ ነው፣ ብዙ ደጋግ ተግባራት ቢኖሩም በየዘርፉ ለእይታችን የሚቀርቡት ግን ጥፋትና በደሎች ናቸው። ስሜቱ የተጎዳን ሰው መግዛት፣ ውስጡ የተረበሸን ሰው መምራት ቀላል ነውና የሚላክብን ነገር ሁሉ ቸልተኛና ልፍስፍስ እንዲያደርገን ታስቦ የሚላክብን ለዚህ ነው።
፨፨////፨፨፨፨////፨፨
አዎ! ጀግናዬ..! ለቀንህ ዋጋ ስጥ፣ በሚገባ አስብለት። ውሎህ ያስጨንቅህ፣ ለስሜትህ መውጣትና መውረድ ትኩረት ስጥ። በምን ተከበህ ምን እየፈለክ እንደሆነ እወቅ፤ ምን መርጠህ የቱጋ እንደቆምክ አስተውል። ውዱን ፈገግታህን በማይመለከትህ ነገር አትጣው፣ ደስታህ በቀላሉ እንዲርቅህ አትፍቀድ። በሆነባልሆነው እየተበሳጨህ ህይወትህን አሰልቺ አታድርጋት። ስላለህበት ሁኔታ አንተ ታውቃለህ፣ እያንዳንዱ ያጋጠመህ ነገር ላንተ ግልፅ ነው። ነገር ግን ማወቅህ ውስጥህን እንዲረብሽ አትፍቀድ፣ የተረዳሀው ነገር ቀንህን እንዲያጨልም አታድርግ። ማንም የሚረዳህ በሌለበት ዓለም በየመንገዱ የውስጥ ስሜትህን እያሳየህ አትሂድ። የሚያበሳጭ ነገር ሲመጣ በልኩ ተበሳጭ፣ የሚያስጨንቅ ሁኔታም ቢገጥምህ በልኩ ተጨነቅ። የትኛውንም ስሜት እንደ አመጣጡ ማስተናገድ ተለማመድ። ፈገግታ የጠንካሮች ምልክት ነውና በስተመጨረሻ በእውነተኛ ፈገግታህ ማሳረግህን እንዳትረሳ።
ግሩም ድንቅ ቀን ይሁንልን!