12/02/2022
የወር አበባ እያየሽ እርግዝና ይፈጠራል?
ስለ እርግዝና ሲነሳ የተለመደው እና ብዙ ጊዜም የሚነገረው በወር አበባ ወቅት እርግዝና አይፈጠርም የሚለው ሚት (myth) ነው። ምንም እንኳን በወር አበባ ወቅት የእርግዝና የመፈጠር እድል እጅግ ያነሰ ቢሆንም ዜሮ በሚባል ደረጃ ግን አስተማማኝ አይደለም። በወር አበባ ወቅት ስለሚደረግ ወሲባዊ ግንኙነት እና ስለ እርግዝና ጉዳይ የሚከተለውን ማወቅ ለግንዛቤ ይረዳል እና እነሆ….
☑️ ለመሆኑ እርግዝና እንዴት ነው የሚከሰተው?
እርግዝና የሚፈጠርበት ሂደት እና እድል አስገራሚ ነገር አለው። እርግዝና ለመፈጠር የሴቷን እንቁላል እና የወንዱን የዘር ፍሬ መገናኘት የሚፈልግ ሲሆን የሴቷ እንቁላል ከኦቫሪ ከተለቀቀ በኋላ ያለው እድሜ ከ12-24 ሰዓት ብቻ ነው።
የወንዱ የዘር ፍሬ ግን እስከ ሶስት ቀን የመቆየት አቅም አለው። ስለዚህ እርግዝና ሊከሰት የሚችለው የሴቷ እንቁላል ተለቆ በህይወት በሚቆይበት እድሜ የወንዱን የዘር ፍሬ የሚያገኝበት እድል ሲፈጠር ነው ማለት ነው።
በነገራችን ላይ መደበኛው የሴት ልጅ የወር አበባ ኡደት 28 ቀን ሲሆን የሴቷ እንቁላል የሚለቀቀው (ovulation) በ14ኛው ቀን ገደማ ነው። ይህም ማለት በ12,13 ወይም በ14ኛው ቀን ሊሆን ይችላል። ይሁንና ሁሉም ሴቶች በተመሳሳይ የ28 ቀን የወር አበባ ዑደት የላቸውም።
አንዳንድ ሴቶች እስከ 35 ቀን የሚደርስ ረዘም ያለ ዑደት ሲኖራቸው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ 21 ቀን ብቻ ሊኖራቸው ይችላል። ይህ የወር አበባ ዑደት ልዩነት ደግሞ ኦቩሌሽን የሚፈጠርበትንም ቀን የተለያየ እንዲሆን ያደርገዋል። በዚህም መሰረት ባለ 21 ቀኖቹ በ7ኛው ቀን ገደማ፤ ባለ35 ቀኖቹ ደግሞ በ21ኛው ቀን ገደማ ኦቩሌሽን (የእንቁላል መለቀቅ) ይኖራቸዋል።
☑️ ታዲያ አንዲት ሴት በወር አበባዋ ወቅት እንዴት ልታረግዝ ትችላለች?
አንዳንዴ ከሴት የመራቢያ አካል የሚወጣን ደም ከወር አበባ ጋር የማሳሳት ነገር ይፈጠራል። ይህም ማለት አንዲት ሴት ለእርግዝና ዝግጁ ሆና ሳለ የወር አበባዋ እንደመጣ ልታስብ ትችላለች። ይህ አንዱ ምክንያት ሊሆን ቢችልም ዋነኛው ግን ከወንድ ልጅ የዘር ፍሬ እድሜ ጋር የሚያያዝ ነው። የወንድ ልጅ የዘር ፍሬ እስከ 72 ሰዓታት በሴቷ አካል ውስጥ የመቆየት አቅም ስላለው አንዲት ሴት በወር አበባ መገባደጃ አከባቢ ወሲብ ብትፈጽም የማርገዝ እድል ይኖራታል።
የአብዛኞቹ ሴቶች የኦቩሌሽን ሳይክል ከ28-30 ቀን ነው። ይህም ማለት በወር አበባ ጊዜ ወሲብ ቢፈጸም ለብዙ ቀናት እርግዝና ላይከሰት ይችላል። ይሁንና አጭር የኦቩሌሽን ሳይክል ያላቸው ሴቶች በኦቩሌሽን እና በወር አበባ መካከል በቂ ቀን ላይኖራቸው ይችላል።
☑️ በወር አበባ ወቅት የእርግዝና መከሰት እድሉ ምን ያህል ነው?
አንዲት ሴት የወር አበባ ማየት በጀመረችበት ሁለት ተከታታይ ቀናት ወሲብ ብትፈጽም የማርገዝ እድሏ ዜሮ ነው ማለት ይቻላል። ይሁንና ከሶስተኛው ቀን ጀምሮ የማርገዝ እድሏ ቀስ በቀስ እያደገ ይሄድና ልክ 13ኛው ቀን ላይ 9% ይደርሳል። ይህ ቁጥር ቢቀንስ እንኳን መቶ ፐርሰንት እርግዝና እንደማይከሰት እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም።
🦋 ሲጠቃለል
የሴቶች የኦቩሌሽን ሳይክል የተለያየ ነው። ስለዚህ በስታቲስቲክስ አንዲት ሴት የወር አበባ ላይ ሆና የምታረግዝበት እድል ሊፈጠር ይችላል። ምንም እንኳን በወር አበባ የመጀመሪያዎቹ ቀናት እርግዝና የመከሰት እድሉ እጅግ ያነሰ ቢሆንም ቀን እየገፋ በሄደ ቁጥር ግን እርግዝና የመፈጠር ዕድሉ እያደገ ይሄዳል።
ምንጭ:- healthline, EthioTena