23/08/2019
በአለማችን ከሰይጣን ሀይል የተነሳ የሰው ክፋት እጅግም የበዛበት ሆኗል፤ ሰዎች በምድር ላይ አለን በሚሉት ነገር እርካታን፣ ሰላምን፣ ዋስትናን ማግኘት ያልቻሉበትም ወቅት ነው፡፡ በዚህ አስጨናቂ አለም ውስጥ በድል አድራጊነት በሰላምና በእፎይታ መኖር የሚቻለው በክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ወደዚህ በረከት ለመግባት ክርስቶስን የተቀበልንበት መንገድ ወሳኝ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ክርስቶስን በሀይማኖት መልክ፣ በፍልስፍና መልክ፣ በምድር ስለሚያገኙት ብልጽግናና ተአምራት፣ በመልካም ስራና በመሳሰሉት ተቀብለውታል፣ ግን ሰላምና በእርሱ የሚገኝ የእርካታ ህይወት የላቸውም፡፡ ኢየሱስ በምድር በነበረበት ወቅት ደቀመዛሙርቱን ሰዎች እኔን ማን ይላሉ? ካለ በኋላ በመቀጠል እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ? በማለት ጠይቋል፡፡ ጴጥሮስም አንተ ክርስቶስ የህያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ፡፡ ይህ መገለጥ ነበር፡፡ ክርስቶስ መገለጥ ነው፣ ክርስቶስ ህይወት ነው፣ ክርስቶስ ብርሀን ነው፣ ክርስቶስ እርሱ እውነተኛ መንገድ ህይወትና እውነትም ነው፣ ክርስቶስ እውነተኛም ነብይ ነው፣ ክርስቶስ እርሱ ንጉስ ነው፡፡
ክርስቶስን ስንቀበል አስደናቂ በረከቶች ወደ እኛ መጥተዋል፣ የመንግስት ለውጥ አድርገናል፣ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናል፣ መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ በማደር ይመራላል፣ ያስተምረናል፣ ይመክረናል፣ የዐሎት መልስ እናገኛለን፣ በቅዱሳን መልአክት ሁል ጊዜም ቢሆን የተጠበቅን ነን፣ የጨለማ ስልጣን ፈርሷል፣ ሰማያዊ ዜግነት አግኝተናል፣ ታላቁን ተልዕኮ የምንፈጽም አምባሳደሮች ነን፡፡ ከዚህ የተነሳ ሁልጊዜም ቢሆን በድል እንኖራለን፣ ክርስቶስን ለብሰናልና ለሰይጣን አስፈሪዎች ነን፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን የዘላለም ቃሉን በፍጹም ልብ በማመን ብቻ ነው፡፡