ጌቴሴማኒ-Getesemani

ጌቴሴማኒ-Getesemani

Share

ጌቴሴማኒ የተሰኘ የዩቱብ ቻናል መንፈሳዊ እውቀቶቸን ፣የቅዱ?

የኢትዮጵያ ዘመን ኣቆጣጠር ለምን በአመት7 አመት፣ በወር 8 ወር እና በቀናት 7-11 ቀን ልዩነት ተፈጠረ ከአውሮፓውያን፣ የኢትዮጵያ የእለታት ስያሜ ምንጩስ 28/05/2023

https://www.youtube.com/watch?v=UQ0DaCV8bNc

የኢትዮጵያ ዘመን ኣቆጣጠር ለምን በአመት7 አመት፣ በወር 8 ወር እና በቀናት 7-11 ቀን ልዩነት ተፈጠረ ከአውሮፓውያን፣ የኢትዮጵያ የእለታት ስያሜ ምንጩስ የኢትዮጵያ ዘመን ከአውሮጳ ለምን በ7 አመት፣ በ8 ወር እና በቀናት 7-11 ቀናት ተለየ | Why the Ethiopian era differed from European by 7 years, 8 months, and days 7-11 days. |Subscribeli...

11/04/2023

አምስቱ ቅንዋተ መስቀል ችንካሮች
ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራ እና ሮዳስ ይባላሉ።
ትርጉማቸውም እንዲህ ነው፦
እየሱስ ክርስቶስ
1. ሳዶር፦ ሳዶር ማለት ቀኝ እጁ የተቸነከረበት ነው።
2. አላዶር፦ አላዶር ማለት ግራ እጁ የተቸነከሩበት ነው።
3. ዳናት፦ ዳናቴ ማለት እግሮቹ የቸችነከሩበት ነው።
4. ሮዳስ፦ ሮዳስ ማለት ከወገቡ (እምብርቱን) አጣብቆ እንዲይዘው የተቸነከሩበት ነው።
5. አዴራ፦ አዴራ ማለት ደረቱን አጣብቆ እንዲይዘው የተቸነከሩበት ነው።

11/04/2023

የሰሙነ ሕማማት ትርጓሜ፣ ክንዋኔና ሚስጢር
(ምንጭ፦ ስምዐ ጽድቅ ልዩ እትም ዘሰሙነ ሕማማት መጋቢት 2002)
ጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ከገባ ጀምሮ ያሳለፈውና ከትንሳኤው በፊት ያለው አንድ ሳምንት ” የመጨረሻ ሳምንት ” ተብሎ ይጠራል፡፡ በሌላ አጠራር ደግሞ ” ሰሙነ ሕማማት ” ይባላል፡፡ በጌታ ላይ የሞት ምክር የተመከረበትና በብዙ መከራና ሕማማት የተገደለበት ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህም ሰሙነ ሕማማት የሚለው ስያሜ ጌታ የተቀበለውን ፀዋትዎ መከራን ለማዘከር የሰጠ ስያሜ ነው፡፡ የጌታ የመስቀሉ ሕማሞች ወይም ” ሕማማት መስቀል ” ተብለው የሚዘከሩት አሥራ ሦስት ሲሆኑ እነዚህም፦

1. በብረት ሐብለ መጋፊያና መጋፊያው እስኪጋጠም ድረስ የኋሊት መታሰሩ
2. ከአፍንጫው ደም እስኪውጣ ድረስ 25 ጊዜ በጡጫ መመታቱ
3. 65 ጊዜ ከግንድ ማጋጨታቸው
4. 120 ጊዜ በድንጋይ ፊቱን መመታቱ
5. 365 ጊዜ በሽመል መደብደቡ
6. 80 ጊዜ ጽህሙን መነጨቱ
7. 6666 ጊዜ መገረፉ
8. አክሊለ ሦክ በራሱ ላይ መደፋቱ
9. 136 ጊዜ በምድር ላይ መውደቁ
10. ሳዶር፡ አላዶር፡ ኤዴራ፡ ዳናትና ሮዳስ በሚባሉ 5ቱ ቅንዋተ መስቀል በችንካር መቸንከሩ
11. መራራ ሐሞትን መጠጣቱ
12. መስቀሉን ተሸክሞ መንገላታቱ
13. በመስቀል መሰቀሉ ናቸው።
በዚህ ሳምንት ውስጥ ካህናትና ምዕመናን በአፀደ ቤተ ክርስትያን ተሰብስበው ከሀጥያት ርቀው ከምግብና ከመጠጥ ተቆጥቦ በጾምና በጸሎት የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን ዜማ ሲያዜሙ ግብረ ሕማም የሚባለውን መጽሐፍ እያነበቡ ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ።

ከአባታችን አዳም በደል ወይንም ስሕተት በኋላ በሕማማት፣ በደዌያት፣ በመቅሰፍታት፣ ወዘተ በብዙ መከራ የሰው ልጅ ሊኖርባቸው ግድ የሆነባቸው ዘመናት ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ ጥሮ ግሮ ወጥቶ ወርዶ ለፍቶ ማስኖ የዕለት ጉርስ የቀን ልብስ ማግኘት እጅግ አዳጋች ነበር፡፡ ሁልጊዜ የሰው ልጅ ቢያጠፋ ቢበድል ከሕገ እግዚአብሔር ቢወጣ እንኳ የዋህ፣ ታጋሽ፣ ቸር፣ አዛኝ የሆነ አምላክ የጠፋውን ሊፈለግ የተራበውን ሊያጠግብ የታረዘውን ሊያለብስ፣ ፍቅር ያጣውን ፍጹም ፍቅር ሊለግስ፣ ሰላም ለሌለው ፍጹም ሰላም ሊሰጥ፣ ተስፋ የሌለውን ተስፋ ሊያጐናጽፍ ከሰማይ ወረደ፤ ከድንግል ማርያም ተወለደ፤ በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ ቀንና ሌሊት ጾመ፡፡ በጾሙም የኃጡአት ሥሮች ወይም ራሶች የተባሉትን ስስትን፣ ትዕቢትንና ፍቅረ ንዋይን ድል አደረገልን፡፡ እኛ እርሱ የጾመውን ጾም እንድናከብር እንድንጾም ምሳሌ ሆነን፡፡ ዲያብሎስን ድል አድርጐ ድል እንድንነሣው ኃይልና ምሳሌ ሆነን፡፡

ሰሙነ ሕማማት ምንድን ነው?

ሰመነ ስምንት /ሳምንት/ አደረገ ማለት ነው፡፡ ይኸውም ከዕለተ ሆሣዕና ሰርክ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ያለውን ጊዜ ወይም ቀናት የሚያመለክት ነው፡፡ ሐመ ማለት ታመመ ማለት ሲሆን ይህም የሰውን ዘር ሁሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነፃ ለማውጣት ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ የተቀበላቸውን ጸዋትወ መከራዎች የሚያሳስብ ነው፡፡ ዕለታቱ የዓመተ ኩነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት፣ የሚያለቅሱበት፣ የሚሰግዱበት ቤት ንብረታቸውን ትተው ከሌላው ቀናትና ጊዜያት በተለየ መልኩ ቤተ ክርስቲያናቸውን የሚማጸኑበት፤ ጧት ማታ ደጅ የሚጠኑበት፤ ኃጢአታቸውን በቤተ ክርስቲያን አደባባይ ለካህኑ የሚናዘዙበት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ሳምንት ነው፡፡

በዚህ ሳምንት ብዙ አዝማደ መባልእት አይበሉም፤ ይልቁን በመራብ በመጠማት በመውጣት በመውረድ በመስገድ በመጸለይ በመጾም በየሰዓቱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራዎች በማሰብ አብዝቶ ይሰገዳል፡፡ መከራውን፣ ሕማሙን፣ ድካሙን የሚያስታውሱ ከቅዱሳት መጻሕፍት ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ መዝሙረ ዳዊት ግብረ ሕማማት ወዘተ በየሰዓቱ ይነበባል፡፡

መስቀል መሳለም የለም፡፡ ካህናትም እግዚአብሔር ይፍታህ አይሉም የሳምንቱ ሥርዓተ ፍትሐት አይደረግም፡፡ ይኸውም ይህ ሳምንት ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት ከጨለማ ወደ ብርሃን የተጓዝንበት የመሸጋገሪያ ወቅት ምሳሌ በመሆኑ ነው፡፡ በዕለተ ምጽአት መላእክት የመለከት ድምጽ በማሰማት የዳግም ምጽአትን ዕለት ለማሳሰብ ምእመናን ጥሪውን ሰምተው ለዚህም አስቀድመው ተዘጋጅተው የበዓሉ ታዳሚዎች መሆናቸውን በማጠየቅ በዚህ ሳምንት ዲያቆኑ ቃጭል እየመታ በየሰዓቱ ምእመናኑን ያሳስባል፡፡

በሰሙነ ሕማማት የሚገኙ ዕለታትና ስያሜያት

ዕለተ ሰኑይ /ሰኞ/

ይህ ዕለት አንጾሖተ ቤተ መቅደስ /የቤተ መቅደስ መንጻት/ እና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፡፡ /ማር.11-11፣ ማቴ.21-18-22 ሉቃ.13-6-9/፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ «ወመሰለ ሎሙ ወይቤሎሙ አሐዱ ብእሲ በለሰ ቦቱ ውስተ አጸደ ወይኑ ወየሐውር ይንሣእ ፍሬሃ ወኢይረክብ …»፤ ይህንም ምሳሌ አለ ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው ፍሬም ሊፈልግባት ወጥቶ ምንም አላገኘም፡፡ በማለት በበለስ ስለተመሰለ የሰው ልጅ ሕይወት በማሰብ እንዲመለስ ንስሐ እንዲገባ በሕይወትም እንዲኖር እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ማሳሰቡን ያጠይቃል፡፡ ንስሐ አልገባም አልመለስም ያለም በለሷ እንደጠወለገችና እንደተቆረጠች ሁሉ ፍሬ ባለማፍራታቸው እንደሚቆረጡ እንዲሁም ወደ እሳት እንደሚጣሉ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል፡፡ በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ፍሬ የተባለ ደግሞ ሃይማኖትና ምግባርን ነው፡፡ ሁላችን ቤተ እስራኤላውያን ፍሬ ሃይማኖት ወምግባር አስተባብረን ይዘን መገኘት ይገባናል፡፡ ፍሬ አልባ እንዳንሆን ጌታ ሲመጣም እንዳናፍር የመጽሐፉን ቃል ልንጠብቅና ልንፈጽም ይገባናል፡፡ በዚህ የሕማማት የመጀመሪያ ቀን ዕለተ ሰኑይ የምናስበው የምንዘክረው የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ በቸልተኝነት እንዳይደክም እንዳይጠወለግ እንዳይደርቅ ወደ እሳትም እንዳይጣል ማድረግ ይገባናል፡፡

ዕለተ ሠሉስ /ማክሰኞ/

ይህ ቀን ጌታችን ሰኞ በተናገረውና ባደረገው ላይ አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት እርሱም መልስ በመስጠት ያስተማረበት ዕለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የጥያቄ እና የትምህርት ቀን በመባል ይታወቃል፡፡ ጥያቄውም ጌታ ባደረገው አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ምክንያት ለጸሐፍትና ፈሪሳውያን ይኸውም ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?» የሚል ነበር፡፡ /ማቴ.21-23-27/፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ «ወይቤሎሙ ኢየሱስ አማን እብለክሙ ከመ መጸብሓውያን ወዘማውያት ይቀድሙክሙ ውስተ መንግሥተ እግዚአብሔር»፤ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው እውነት እላችኋለሁ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል ሲል አስተምሯል፡፡ /ማቴ.21-28/

ዕለተ ረቡዕ/እሮብ/

ይህ ዕለት ደግሞ የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚችሉ ምክር የጀመሩበት ቀን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዕለቱ” የምክር ቀን” በመባል ይጠራል፡፡” መልካም መዓዛ ያለው” እና “የእንባ”ቀንም ይባላል። ምክንያቱም ማርያም ዕንተ እፍረት ዋጋው ብዙ የሆነ ሽቶ ጌታችንን በመቀባታና ስለ ሀጥያቷ ስቅስቅ ብላ በማልቀሷ ይህንን ስያሜ ተሰጠ። ማቴ 26፦3_13 ማር 14፦ 1_11 ሉቃ 22፦3_6

ዕለተ ሐሙስ/ሐሙስ/

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ለመግለጥ እና ለአርአያነት ጸሐፍት ፈሪሳውያን የአይሁድ ካህናት መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ጸሎተ ሐሙስ በመባል ይታወቃል፡፡ ትሕትና ፍቅር መታዘዝ እንዲሁም የአገልግሎትን ትርጉም ለማስረዳትና ለማስገንዘብ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ሕጽበተ ሐሙስ በመባልም እንደሚጠራ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይናገራሉ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም «ወሶበ ኀፀቦሙ እገሪሆሙ ነሥአ አልባሲሁ ወረፈቀ ካዕበ ወይቤሎሙ አእመርክሙኑ ዘገበርኩ ለክሙ … ወሶበ አነ እንከ ሊቅክሙ ወእግዚእክሙ ኀፀብኩክሙ እገሪክሙ ከማሁኬ አንትሙኒ ይደልወክሙ ትኅፅቡ እግረ ቢጽክሙ፡፡»፤ «እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ እንዲህም አላቸው ያደረግሁላችሁን ታስተውሉታላችሁን?… እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በእርሳችሁ ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል ሲል ተናግሯል፡፡ /ዮሐ.13-12-20/፡፡

ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱ ጠጡ በማለት ምሥጢረ ቁርባንን የመሠረተበት ወይም ራሱ ምስጢረ ቁርባንን የጀመረበት ቀን በመሆኑ የምስጢር ቀን ተብሎ ይጠራል፡፡ ይኸውም የሰው ልጆች ሥጋውንና ደሙን ተቀብለን ከእርሱ ጋር አንድነትና ኅብረት እንዲኖረን ጥንተ ጠላት ዲለብሎስንም ፍጹም ድል ነሥተን ሰማያዊት ርስት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ለማስቻል ነው፡፡ /ማቴ.26-26-29/፡፡

አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ በእነርሱ ጥበብና ፍላጐት ቀስ ብለው መጥተው የያዙበት ቀን ስለሆነ በዚህ ዕለት በለሆሳስ /ብዙ የድምጽ ጩኸት ሳይሰማ/ የቅዳሴ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡ ስለሆነም መላው ሕዝበ ክርስቲያን በዚህ የሕጽበት፣ የምስጢር፣ የጸሎት ቀን በተባለው በዚህ ዕለት በንስሓ ታጥበው ሥጋ ወደሙ እንዲቀበሉ ቤተ ክርስቲያን በአጽንኦት ታስተምራለች፡፡

ዕለተ ዐርብ/ዓርብ/

ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ «አውቀውስ ቢሆን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት» /1ቆሮ.1-18/፡፡ እንዳለ ይህ ዕለት የአይሁድ ካህናት ያለበደል ያለጥፋት ንጹሕና ጻድቅ የሆነውን ጌታ የሰቀሉበት ዕለት ነው፡፡ ዕለቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ሁሉ መድኃኒት ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልእልተ መስቀል በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ መዋሉን የምናስብበት ታላቅ ቀን ነው፡፡ /ማቴ.27-35-75/፡፡ በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ፡፡ እነርሱ ግን እኛስ ምን አግዶን? አንተው ተጠንቀቅ አሉ፡፡ ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሔደና ታንቆ ሞተ፡፡ የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ፡፡ ተማክረውም የሸክላ ሠሪ መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት፡፡ ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተባለ፡፡ /ማቴ.27-3-9/
የሰው ልጆች በዘር ኃጢአት /ቁራኝነት/ ይኖሩበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመበት ፍጹም ድኅነት ያገኙባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ ክርስቲያኖች ሁልጊዜም ዕለተ ዓርብ ሲመጣ ሕማሙን ስቅለቱን ሞቱን የሚያስቡበት ጊዜ ነው፡፡ በሮማውያን ሕግና ሥርዓት መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የሕይወት መቅጫ አርማ ሆኖ ሳለ ለእኛ የዲያብሎስ ድል መንሻ ስላደረገው በስቅለቱና በሞቱም ሕይወትን ስለአገኘን በዚህም ምክንያት መልካሙ ዓርብ በመባል እንደሚታወቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያትታሉ፡፡

በመስቀል ላይ ሳለ 7 ነገሮችን ተናገረ/7ቱ ” አጽርሐ መስቀል ” በመባል ይታወቃሉ። እነሱም፦
” አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ” ማቴ 17፦46
” አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ሉቃ 23፦34
” ዛሬ በገነት ከኔ ጋር እንድትኖር በእውነት እነግርሀለሁ” ሉቃ 23፦4
” አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” ሉቃ 23፦ 46
” እነሆ ልጅሽ እነኋት እናትህ” ዮሐ 19፦26
” ተጠማሁ” ዮሐ 19፦28
” ሁሉ ተፈጸመ ” ዮሐ 19፦ 30

ጌታ ሁሉ ተፈጸመ ብሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ስጋው በራሱፈቃድ ከለየ በኋላ አምላክነቱን ለመግለፅ የታዩ ተአምራት የሚከተሉት ናቸው፤

በሰማይ፤ /ማቴ 24፦29 እና 27፦45/

1. ፀሐይ ጨለመች
2. ጨረቃ ደም ሆነች
3. ከዋክብት ረገፉ

በምድር፤/ማቴ 27፦51_53/
1. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይእስከ ታች ተቀደደ
2. ምድር ተናወጠች
3. መቃብሮች ተከፈቱ
4. ሙታን ተነሱ

ቀዳሜ ስዑር/ቅዳሜ/

ዕለተ ቅዳሜ እግዚአብሔር የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሄዱትን እና በክንፍ የሚበሩትን በባሕር የሚዋኙትን እንስሳትን በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ያረፈበት ዕለት ነች፡፡ ይህች የመጀመሪያው ቅዳሜ ለእግዚአብሔር የዕረፍት ዕለት ናት እግዚአብሔርን ሥነ ፍጥረት ፈጥሮ ስላረፈበት ሰንበት ዐባይ /ታላቋ ሰንበት/ ትባላለች ታላቋን ሰንበት እስራኤላውያን እንዲያከብሯት ታዟል፡፡ ዘፍ.1፡3፡፡

ዕለተ ቀዳሚት /ሰንበት ዐባይ/ በዘመነ ሐዲስም የተለየ የደኅነት ሥራ ተከናውኖባታል፡፡ ጥንት ሥነ ፈጥረትን በመፍጠር ዕረፍት እንደ ተደረገባት ሁሉ የፍጥረት ሁሉ ቁንጮ የሆነውን አዳምን ለማዳን ሕማምና ሞት የተቀበለው ቸሩ አምላክ በመቃብር አርፎባታል፡፡ ማቴ.27፡61፡፡

በዚህች ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሰ መቃብር ዐርፎ የዋለባት ዕለት በመሆኗ «ቀዳሜ ስዑር » ትሰኛለች፡፡ ስዑር ቀዳሜ የተባለችው በዓመት አንድ ቀን ስለ ምትጾም ነው፡፡ ምክንያቱም እናቱ ድንግል ማርያም ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታ ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት አንስተው ብርሃነ ትንሣኤውን እስኪያዩ ድረስ እህል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደረጉት የነበረ አምላካቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ሞቱን በማሰብ ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡
ከቅዱሳን ሐዋርያት ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው ትውፊት መሠረት ቅዱሳን ሐዋርያት በማዘን በመጾምና በመጸለይ ዕለቷ እንዳከበሯት የተዋሕዶ ልጆች የተቻላቸው ከዓርብ ጀምረው የሚያከፍሉ /የሚጾሙ/ ለሁለት ቀን እህል ውኃ ሳይቀምሱ ያድራሉ ያልተቻላቸው ደግሞ ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡

በዚህ ዕለት ከሰኞ ከሆሣዕና ማግሥት ጀምረው እስከ ስቅለተ ዓርብ ድረስ በስግደት እና በጾም ያሳለፉ ምእመናን በዕለተ ቅዳሜ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፡፡ የጠዋቱ ጸሎት ሲፈጸም ካህናቱ «ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፡-በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ» የምሥራች እያሉ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰቡት ምእመናን ቄጠማ ይታደላል ቄጠማው የምሥራች ምልክት ነው፡፡ ቄጠማው የምሥራች ምልክት ተደርጐ የተወሰደው በኖህ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ጋር በማቆራኘት ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሕዝቦች ከሕገ እግዚአብሔር ውጪ ሆነው እጅግ የሚያሳዝን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ በንፍር ውኃ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዞአቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጉደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፤ እርሷም ቄጠማ በአፍዋ ይዛ ትመልሳለች፡፡ ዘፍ.9-1-29፡፡ ኖኅም በዚህ ቄጠማ የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ተደስቷል፡፡

«ቄጠማ»፣ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደሆነ አሁንም በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ ስትል ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የሆነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፡፡
የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሚያቃጥለው ዋዕየ ሲኦል /የሲኦል ቃጠሎ/ ወደ ልምላሜ ገነት ጥንተ ማኅደራቸው መመለሳቸውን በዚህ አኳሃን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡

ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ክንዋኔዎች በሰሙነ ሕማማት

በዐቢይ ጾም ከሠርክ ሆሣዕና ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ዕለታት የሚገኙበት ሳምንታት ሰሙነ ሕማማት ይባላሉ፡፡ ዕለታቱም የዓመተ ፍዳ፣ የዓመተ ኩነኔ መታሰቢያ ናቸው፡፡ በእነዚህ ዕለታት ውስጥ የተለያዩ ትውፊታዊ እና ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች አሉ፡፡ ከነዚህ ክንዋኔዎች ውስጥ አለ መሳሳም፣ አክፍሎት፣ ቄጤማ ማሰር፣ ጥብጣብ፣ ጉልባን እና ሕጽበተ እግር ይገኙበታል፡፡ ስለእነዚህ ክንዋኔዎች በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስላለው ትውፊታዊ አፈጻጸም መዛግብት አገላብጠን እና በኢትዮጵያ ኣርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ አባል የሆኑትን ሊቀ ካህሃት ክንፈ ገብርኤል አልታዬን አነጋግረን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

አለመሳሳም

በሰሙነ ሕማማት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች መስቀል እንደማይሳለሙት ሁሉ መጨባበጥ፣ መሳሳምና የትከሻ ሰላምታ መለዋወጠን አይፈጽሙም፡፡ ሰላምታ የማንለዋወጥበት ምክንያት፣ አይሁድ ጌታን ለመስቀል ሰኞ እና ማክሰኞ መከሩ አልሠመረላቸውም፡፡ ምክራቸው የተፈጸመው ረቡዕ ነው፡፡

ስለዚህ አይሁድ አያንሾካሾኩ “እንስቀለው… አንግደለው” ብለው ይማከሩ ነበር፡፡ ያነን ለማስታወስ ሰላምታ አንለዋወጥም፡፡ መስቀልም አንሳለምም፡፡ ሳምንቱ የክፋት ምክር የተመከረበት እንጂ የፍቅርና የደስታ ሰላምታ የታየበት ባለመሆኑ ይህንን በማሰብ ሰላምታ አንለዋወጥም፡፡
ይሁዳ ጌታን በጠላቶቹ ለማስያዝ “እኔ የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት” ብሎ በሰላምታው ምልክት ሰጣቸው ይህ ሰላምታ አምሐ ቅድሳት አይደለም፤ ተንኮል የተሞላበት እንጂ፡፡ የዲያቢሎስም ሰላምታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሔዋንን “ሰላም ለኪ” ብሎ ነው ያታለላት፣ የዲያቢሎስ እና የይሁዳ ሰላምታ ሰይጣናዊ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ወቅትና ሁኔታ ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ሰላምታ ልውውጥ የለም፡፡ ዛሬ እየተስተዋለ ያለው ይኸው ሰላምታ ያለመለዋወጥ ሁኔታ ሥርወ መሠረቱ ይህ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ እዚህ ትውልድ ላይ ደርሷል ይቀጥላልም፡፡

ሕጽበተ እግር

ጌታ በፍጹም ትሕትና የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበት፣ ከሐዋርያት ጋር ግብር የገባበትና የክርስትና ሕይወት ማሕተም የሆነውን ምሥጢረ ቁርባን ያከናወነበት ዕለት ነው ጸሎተ ሐሙስ፡፡

ሕጽበተ እግር ጌታችን በዚህ ዕለት “አናንተ ለወንድማችሁ አንዲህ አድርጉ” ለማለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ምክንያት የተሰጠ ምሳሌ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው “አኔ ለአናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና፤ እውነት እውነት እላችኋለሁ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም፣ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም፤ ይህን ብታውቁ ብታደርጉትም ብፁዓን ናቸሁ” /ዮሐ.13÷16-17/ በማለት ትሕትናውን አሳይቷል፡፡

ጌታ በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር ሲያጥብ “እኔ መምህራችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኳችሁ አርአያዬን ሰጥቻችኋለሁ፤ እናንተም የወንድማችሁን እግር ታጥቡ ዘንድ ይገባል፡፡ ነገር ግን ከእናንተ አንዱ ለሞት አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም “ማን ይሆን?” አሉ፡፡ ጌታም “ኅብስት ቆርሼ፣ ከወጡ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው” አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ደነገጡ፡፡ ይሁዳን ማመልከቱ ደነገጡ፡፡ ይሁደን ማመልከቱ ነበር፤ ለጊዜው አልገባቸውም፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን የሐዋርያቱን እግር በማጠብ ትሕትናን ካስተማራቸው በኋላ፤ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሰጣቸው፤ የኦሪትን መሥዋዕት የሻረው እና መሥዋዕተ ሐዲስን የሠራው በዚሁ ዕለት ነው፡፡

በዚህ ሃይማኖታዊ መነሻነትም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚከናወኑ ድርጊቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- በወሎና በጎንደር ከጉልባን በተጨማሪ በተለይ በጸሎተ ሐሙስ ዕለት ብቻ የሚጋገር የተለየ ዳቦ አለ፡፡ ይህ ልዩ ዳቦ በወሎ “ትኩሴ” በጎንደር ደግሞ “ሙጌራ” ይባላል፡፡ ይህ ዳቦ ጌታ ለሐዋርያት የሰጣቸው ኅብስት አምሳያ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ከዚህ ቀን ውጪ በሌላ ጊዜ አይጋገርም፡፡ በመሆኑም ሰው ሁሉ ዳቦውን ለመብላት የሚጠባበቀው በታላቅ ጉጉት ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን ሃይማኖታዊ ሥርዓት በሚከበርባቸው እንደ ማኅበርና ሰንበቴ በመሳሰሉት መንፈሳዊና ማኅበራዊ ትውፊቶች የሚቀርብበት ጊዜ አለ፡፡
በትግራይ በዕለተ ስቅለት ከተለመደው የጾምና የስግደት ሥርዓት በተጨማሪ የሚከናወኑ ድርጊቶች አሉ፡፡ በዕለቱ ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት መታሰቢያ ሲባል ወንዶች ልጆች በሙሉ ፀጉራቸውን እንዲላጩ ይደረጋል፡፡ ያን ቀን ያልተላጨ ልጅ “ኃጢአት ይሆንበታል” ስለሚባል ሳይላጭ የሚውል ልጅ የለም። ልጃገረዶች በበኩላቸው በዛፍ ላይ ገመድ በማሰር ዥዋዥዌ ይጫወታሉ፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት የጌታን እንግልትና መስቀል ለማዘከር ነው ይባላል፡፡
እነሆ ይህንን ዕለት በማስታወስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሐዶ ቤተ ክርስቲያን ከሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ እስከ ቀሳውስት ያሉት አባቶች በያሉበት አጥቢያ /ደብር/ በመገኘት በመዓርግ የሚያንሷቸውን የካህናት፣ ዲያቆናት እና የምእመናንን እግር ያጥባሉ፤ የሚያጥቡትም የወይራ እና የወይን ቅጠል በመዘፍዘፍ ነው፡፡

አክፍሎት

በሰሙነ ሕማማት ዕለተ ዓርብ ከስግደት በኋላ ምእመናን በየቤታቸው ጥቂት ነገር ለቁመተ ሥጋ ቀምሰው እስከ እሑድ /የትንሣኤ ሰዓት/ ይሰነብታሉ፡፡ ይህ አክፍሎት ይባላል፡፡ ብዙው ምዕመን ከዓርብ ጀምሮ የሚያከፍል ሲሆን አንዳንዶች ግን ከሐሙስ ጀምረው ያከፍላሉ፡፡ ይህም እመቤታችን፣ ያዕቆብ እና ዮሐንስ የጌታን ትንሣኤ ሳናይ እህል ውኃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሣኤ መቆየታቸውን ተከትሎ የመጣ ትውፊት ነው፡፡

ይህንን ትውፊት አስመልክቶ ሄሬኔዎስ፣ አውሳብዮስ የተባሉ ጸሐፍት፤ ሐዋርያት በሰሙነ ሕማማት ከደረቅ ዳቦ አና ከትንሽ ውኃ በቀር እንደማይመገቡ እና ከሐሙስ ጀምረው እንደሚያከፍሉ ጽፈዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሐዋርያት ሌሎቹንም እንዲያከፍሉ እንዳሳሰቡና ከሐሙስ ጀምሮ ያልተቻለው ቢያንስ ከዓርብ ጀምሮ እንዲያከፍል ማዘዛቸውን ጽፈዋል፡፡ የእኛ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትም ይኸው ነው፡፡ ቅዳሜ ይበላል ማለት ግን ቅዳሴው ሌሊት ስለሆነ በልቶ ማስቀደስ ነውና በልቶ እንደመቁረብ ይቆጠራል፡፡

ጉልባን እና ቄጤማ

ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚባላ ንፍሮ ነው፡፡ የጉልባን ትውፊት እስራኤላውያን ከግብፅ ተሰደው በሚወጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር፤ አቡክተው ጋግረው መብላት ያለመቻላቸውን ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ያን ጊዜ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መብላት፤ ንፍሮም ቀቅለው ስንቅ መያዝ ተግባራቸው ነበር፡፡ ይህን ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ቂጣና ጉልባን በማዘጋጀት በዓሉ ይታሰባል፡፡
በጸሎተ ሐሙስ ይህንን መሠረት በማድረግ የሚዘጋጀው ጉልባን አንዲህም ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ጨው ውኃ የሚያስጠማ በመሆኑ የጌታን መጠማት ያስታውሳል፡፡ ይህ ትውፊታዊ ሥርዓት ከእስራኤላውያን የመጣ ሲሆን በኢትዮጵያም አብዛኛዎቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ሥርዓቱ ዛሬም ይከበራል፡፡

ጥብጣብ

በሰሙነ ሕማማት ዕለተ ዓርብ የስቅለቱ መታሰቢያ ነው፡፡ ምእመናኑ በሰሙነ ሕማማት የሠሩትን ይናዘዛሉ፡፡ ካህናቱም በወይራ ቅጠል ትከሻቸወን እየጠበጠቡ ቀን ከሰገዱት ስግደት በተጨማሪ ሌላ ስግደት ያዟቸዋል፡፡ ጥብጠባው የተግሳፅ ምሳሌ ነው፡፡ ጥብጣብ የሚደረግለት ሰው በሕማማቱ ወቅት የፈጸመው በደል ወይንም ኃጢአት ካለ ይህንኑ በመናገር የስግደቱ ቁጥር ከፍ እንዲል ይደረጋል፡፡
ይህ በስቅለት ቀን የሚፈጸም ሥነ ሥርዓት ሲሆን፤ ጠብጣቤ ማለት ቸብ ቸብ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዕለተ ስቅለት ሲሰግድ ሲጸልይ፣ ሲያነብ ከዋለ በኋላ ሰርሆተ ሕዝብ /የሕዝብ መሰነባበቻ/ ከመሆኑ በፊት፤ በወይራ ቅጠል እያንዳንዱን ምእመን ጀርባ ቸብ ቸብ መደረጉ፣ የጌታን ግርፋት ያስታውሳል፡፡

ቀጤማ

በቀዳም ስዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለ ዓዋዲ/ እየመቱ “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃደ” የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር፤ ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠን እና ትንሣኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር፤ ቀጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመናኑም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ፡፡ ቀጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ የደፉበትን ድርጊት የሚያስታውስ ነው፡፡
በዚህ ዕለት ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት ቀጤማ ተሸክመው ቃጭል ሲያቃጭሉ መታየታቸው ዕለተ ትንሣኤውን ለሚናፍቅ ምእመን ትልቅ ብስራት ነው፡፡

ሆሣዕና hosaina 08/04/2023

https://www.youtube.com/watch?v=gx0dDA_8mWU

ሆሣዕና hosaina ሆሣዕና ማለት የዕብራይስጥ ቃል ሲኾን “ሆሻአና” ሲባል ትርጒሙም “አቤቱ አኹን አድን” ማለት ነው፤ ይኽ በዓለ ሆሣዕና ከ9ኙ ዐበይት የጌታ በዓላት ውስጥ ሲኾን ኪሩቤል ሱራፌል በፍርሀት ....

02/04/2023

በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን የበዓላት ቀኖና መሰረት ሰባተኛው የዐቢይ ጾም ሰንበት ኒቆዲሞስ ይባላል፡፡ በግሪክ ቋንቋ ኒቆዲሞስ ማለት “አሸናፊ/ነት” ማለት ነው፡፡ በዚህ ሰንበት በዮሐ 3፡1-21 እንደተገለጸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ለተባለ የአይሁድ አለቃ ያስተማረው ትምህርት እንዲሁም የኒቆዲሞስ አስተማሪ ስብእና ይነበባል፣ ይተረጎማል፣ ይዜማል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓ የሰባተኛ ሣምንት መንፈሳዊ ድርሰቱ የኒቆዲሞስን በዓል አስመልክቶ ሲዘምር “ሖረ ኀቤሁ ዘስሙ ኒቆዲሞስ ወይቤሎ ለኢየሱስ ረቢ ሊቅ ንሕነ ነአምን ብከ ከመ እምኀበ አብ መጻእከ ከመ ትኩን መምህረ፤ ዕጓለ አንበሳ ሰከብከ ወኖምከ አንሥአኒ በትንሣኤከ ክርስቶስ/ኒቆዲሞስ የተባለው ሰው ወደ ጌታችን ኢየሱስ ሄደ፤ መምሕር ሆይ ልታስተምር ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ እንደመጣህ እናምንብሃለን አለው። የአንበሳ ደቦል ተኛህ፣ አንቀላፋህም፤ በትንሣኤህ አንሣኝ/ ብሏል፡፡ ይህም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ያስተማረውን ትምህርት የሚያመሰጥር ድንቅ ዜማ ነው፡፡ የዚህች አጭር የአስተምህሮ ጦማር ዓላማም ከኒቆዲሞስ ሕይወት መማር እንችል ዘንድ የኒቆዲሞስን ጠንካራ ስብእና እና መንፈሳዊነት የሚያሳዩ መገለጫዎችን መተንተንና እኛም አርዓያውን እነድንከተል መምከር ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከኒቆዲሞስ ሕይወት የምንማራቸው ቁም ነገሮችም እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

አትኅቶ ርዕስ (ራስን ዝቅ ማድረግ) – ኒቆዲሞስ መምህር ሲሆን ራሱን ዝቅ አድርጎ የተማረ የትህትና አርአያ ነው፡፡

ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ ብቻ ሳይሆን የፈሪሳውያን አለቃ፣ የኦሪት መምህር ብቻ ሳይሆን የኦሪት ምሁርም ነበር፡፡ በእርሱ ደረጃ የነበሩ ታላላቅ የአይሁድ ምሁራን መንፈሳዊ ስልጣናቸውና ሹመታቸው የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን ረስተው በህዝቡ ላይ የሚመፃደቁ ነበሩ፡፡ በዘመናቸው እውቀትን የሚገልጥ እውነተኛ አምላክ፣ የካህናት አለቃ ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም ሲገለጥ የአይሁድ ምሁራን የጌታን መገለጥ አልወደዱትም፡፡ የእርሱ ትህትና የእነርሱን ትዕቢት የሚያጋልጥ ነበርና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሄዱትን ሁሉ ይነቅፉ ይከስሱ ነበር፡፡ ባለማወቅ ያደነደኑት የትዕቢት ልቦና ትህትናቸውን አጥፍቶባቸው ነበርና ዝቅ ብሎ በሰው ዘንድ በተናቁት በናዝሬትና በገሊላ እየተመላለሰ የሚያስተምር የዓለም ቤዛ የክርስቶስን ትምህርት እንዳይሰሙ ልባቸው ተዘግቶ ነበር፡፡ ጌታችንም የፈሪሳውያን ሀሳባቸው በግብዝነት የተሞላና ከንቱም እንደሆነ ነግሯቸዋል፡፡ ለደቀመዛሙርቱም ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ የሚበልጥ ሥራን እንዲሰሩ አስጠንቅቋቸዋል (ማቴ 5: 20 ማቴ 16:6)፡፡

ኒቆዲሞስ ግን ከእነዚህ ከፈሪሳዊያን መካከል የተገኘ ልዩ ምሁረ ኦሪት ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ራሱን ለእውነት ልቡን ለእምነት አዘጋጅቶ ከዅሉ ቀድሞ በሌሊት ክርስቶስን ፍለጋ የመጣ ከእነዚህ ፈሪሳዊያን ወገን ተለይቶ እንደ አባታችን አብርሃም ወደ ጽድቅ መንገድ የተጠራ ነው፡፡ ሹመት እያለው ሁሉ ሳይጎድልበት በዙርያው የነበሩት ከእኛ በላይ ማን አዋቂ አለ የሚሉ ከእውነት ጋር የተጣሉ ጌታችንን የሚያሳድዱ በእርሱም የሚቀኑና ጌታችንንም ለመግደልም ዕለት ዕለት የሚመክሩ ሁነው ሳለ ኒቆዲሞስ ግን እውነትን ለማወቅ እልቅናው ሳይታሰበው ከአካባቢው ጋር መመሳሰልን ሳይመርጥ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሊማር በሌሊት መጣ፡፡ መምህረ ትህትና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የኒቆዲሞስን ትህትናውን ተቀብሎ “ለምን በቀን አትመጣም?” ሳይለው እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ትውልድ ሁሉ የሚማርበትን ረቂቁን ምስጢረ ጥምቀትን አስተማረው፡፡

አልዕሎ ልቡና (ልቡናን ከፍ ከፍ ማድረግ) – ኒቆዲሞስ ዳግመኛ የመወለድን ምስጢርን ለማወቅ ልቡናውን ከፍ ከፍ አደረገ፡፡

ለሥጋዊ ሕይወታችን እውቀት እንደሚያስገፈልገን ሁሉ ነፍስም ዕውቀት መንፈሳዊ ዕውቀት ያስፈልጋታል (ምሳ. 19፥2)፡፡ ኒቆዲሞስ በመጀመርያ የጥምቀትን ነገር ሲሰማ ለመቀበል ተቸግሮ ነበር፡፡ ጌታችን ግን የኒቆዲሞስን አመጣጥ በማየት ልቡናውንም ከፍ ከፍ ስላደረገ ምስጢረ ጥምቀትን ገለጸለት፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በሥርዓተ ቅዳሴ ምእመናንን በማነቃቃት ልቡናቸውን ከፍ እንዲያደርጉ “አልዕሉ አልባቢክሙ/ልቦናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ” ብሎ የሚያዘው ምእመናን የቅዱስ ሥጋውና የክቡር ደሙ ምስጢር እንዲገለጽልን፣ ከሥጋዊው መብል ሃሳብ ወደ ሰማያዊው መብል ልቡናችንን እንድናነሳ ሲያሳስብ ነው፡፡ ምእመናንም በጸሎተ ቅዳሴ ካህኑ የቅዱስ ኤጲፋንዮስን ትዕዛዝ ሲያሰማ “በአምላካችን በእግዚአብሔር ዘንድ አለን” በማለት እንመልሳለን።

መንፈሳዊ መረዳት የሚኖረንና በፈተናዎች ውስጥ ድል መንሳትን የምናገኘው ልቡናን ከፍ በማድረግ ከሁሉም የሚበልጠውን መንፈሳዊውን መንገድ በመከተል ነው፡፡ ግያዝ ከነብዩ ኤልሳዕ ጋር ሳለ ልቡናው ቁሳዊውን የሚመለከት እንጂ ሰማያዊውን ኃይል የተረዳ አልነበረም፡፡ ነብዩ ኤልሳዕ ግን ይህንን ምስጢር እንዲያይ ገለጸለት (2 ነገ 6:17)፡፡ እኛም ክርስቲያኖች በጸጋ የተሰጡንን ስጦታዎቻችንን እንድናውቅ ልቡናችንን ከፍ ከፍ አድርገን በመንፈሳዊ እውቀትና ልዕልና፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመረዳት፣ እንዴት በጽድቅ መመላለስ እንዲገባንና ስለምንወርሳት መንግስተ ሰማይ መማር ማወቅ ይገባናል፡፡ “ቅዱሱን ማወቅ ማስተዋል ነው” ተብሎ በምሳሌ መጽሐፍ እንደተጻፈ (ምሳ 9፥11) ኒቆዲሞስ ከፈሪሳውያን ህብረት ወጥቶ በትህትና ወንጌልን ለመማር በሃይማኖት ልቡናውን ለእግዚአብሔር ቃል አዘጋጀ፡፡ ለአብርሃም የግዝረትን ጸጋ የሰጠ ጌታ በትህትና ለቀረበው ኒቆዲሞስ የግዝረት ጸጋ ፍጻሜ የሆነች የልጅነት ጥምቀትን ነገር አስተምሮታል፡፡

ትግሃ ሌሊት (በሌሊት መትጋት) – ኒቆዲሞስ ቀን እየሠራ በሌሊት ወደ ጌታ በመሄድ ለትጋት አብነት ሆነን፡፡

ኒቆዲሞስ ወደ መድኃኔዓለም ለመማር የሄደው በሌሊት ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ በሚታሰብበት የዐቢይ ጾም ሰንበት በጸሎተ ቅዳሴ የሚዜመው የክቡር ዳዊት መዝሙር “ሐወፅከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ፡፡ አመከርከኒ ወኢተረክበ ዐመፃ በላዕሌየ፡፡ ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ ዕጓለ እመሕያው/በሌሊት ጎበኘኸኝ፤ ልቤንም ፈተንኸው፣ ፈተንኸኝ፣ ዐመፅም አልተገኘብኝም፡፡ የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር” (መዝ. 16፡3)ይህን የሚያስረዳ ነው፡፡ ሌሊት በባህሪው ሕሊናን ለመሰብሰብ በተመስጦ ለመማር የሚመች ነው፡፡ ክርስትናም በተጋድሎ ሕይወት በመትጋት ሥጋን በቀንና ሌሊት ለነፍስ እንዲገዛ በማድረግ የሚኖር ሕይወት ነው፡፡ ጌታችን ሐዋርያቱን “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ” ባለው መሠረት ቤተክርስቲያንም በቀንና በሌሊት በኪዳኑ በቅዳሴው በማህሌቱ እግዚአብሔርን ታመሰግናለች፡፡ የቅዱሳን አባቶቻችን (አባ ቢሾይ) በሌሊት ጸሎት እንቅልፍ እንዳያስቸግራቸው ፀጉራቸውን ከዛፍ ቅርንጫፍ በማሰር ይተጉ ነበር፡፡ ለኒቆዲሞስ በሌሊት ገስግሶ ወደ ጌታችን መምጣት ልጅነትን ለምናገኝበት የምስጢረ ጥምቀት ትምህርት እንደተገለጠለት እኛም በሌሊት በነግህ ጸሎት በመትጋት ረቂቅ የሆነውን መንፈሳዊ እውቀት ሰማያዊ ምስጢር ይገለጥልናል፡፡

በዘመናችን ከቀድሞ ይልቅ ፈተና የሚገጥመን በሌሊት ከመትጋት ይልቅ አርአያነት በጎደለው ሕይወት ውስጥ ስንገኝ ነው፡፡ “ሌሊት ጌታን ለማመስገን የተፈጠረ ድንቅ ጊዜ ነው” እንዳለ ሊቁ ማር ይስሐቅ ራስን በቀንም በሌሊት ከሚመጣ ፈተና መጠበቅ ይገባል፡፡ እግዚአብሔር የሙሴን አገልጋይ የነዌን ልጅ ኢያሱን እንደተናገረው በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ማንም እንዳይረታው፣ ከሙሴ ጋር እንደነበረ ከእርሱ ጋር እንዲኖር “ለአባቶቻቸው እሰጣቸዋለሁ” ብሎ የማለላቸውን ምድር እንዲወርስ በሚሔድበት ሁሉ እንዲከናወንለት ወደ ቀኝም ወደ ግራም እንዳይል ሃሳቡም እንዲቀና የምጽሐፉን ሕግ ከአፉ እንዳይለይ እንዲጠብቀውም በቀንም በሌሊትም ማሰብ እንደሚገባ ይነግረናል (ኢያ 1:1-8):: ቅዱስ ይስሐቅ ሶርያዊ “ከመኝታህ በፊት የምታደርገውን ጸሎት ትተህ እንድትተኛ መንፈስህ ሲገፋፋህ እሺ ብለህ አትቀበለው፡፡ እንዲያውም መዝሙረ ዳዊትን ጨምርና ሌሊቱን በሙሉ ስትጸልይ እደር’ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት “በሌሊት በቤተ መቅደስ ውስጥ እጆቻችሁን አንሡ፥ እግዚአብሔርንም ባርኩ።” መዝ 134:1-3 እንዳለ እኛም ከዚህ የፈተና ዓለም ለማምለጥ በኦርቶዶክሳዊ ሰውነት እንድንጸና በትጋት ወደ ቤተ ክርስቲያን በቀንና በሌሊት ልንገሰግስ በኪዳኑ በማኅሌቱ በቅዳሴው ጸሎት ልንሳተፍ ያስፈልጋል፡፡

ስምዐ ጽድቅ (የእውነት ምስክርነት) – ኒቆዲሞስ ማንንም ሳይፈራ እውነትን በመመስከር ከሳሾችን አሳፈራቸው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እኔ ለእውነት ለመመስከር መጥቻለሁ›› በማለት እውነትን እንድንመሰክር አብነት ሆኖናል (ዮሐ.18፥37)፡፡ በተጨማሪም ‹‹በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፡፡ በሰው ፊት የሚክደኝን ሁሉ ደግሞ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ›› ሲል ስለ ሃይማኖታችን እውነትን መመስከር እንደሚገባን አስተምሮናል (ማቴ.10፥32-33)፡፡ እንዲሁም ለኒቆዲሞስ ሲያስተምረውም ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን›› በማለት ለእውነት መመስከር እንደሚገባ አስገንዝቦታል (ዮሐ 3፡11)፡፡ይህንን ቃል ከራሱ ጋር በማዋሀድ የአይሁድ የፋሲካ በዓል በቀረበበት ወቅት ጻፎችና የካህናት አለቆች ጌታን ለመያዝ፣ የሙሴን ሕግም አጣምመው ሊያስፈርዱበት በሚጥሩበት ጊዜ ኒቆዲሞስ የእውነት ምስክርነቱን አረጋገጠ፡፡ የሙሴ ፈጣሪ መሆኑን ባለማወቃቸው ምክንያት የካህናት አለቆች ተሰብስበው ክርስቶስን ለመያዝ ሲመካከሩ ከሙሴ መጽሐፍ ሕግ ጠቅሶ ሊቃውንተ ኦሪትን አፍ ያስያዛቸው እርሱ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ሳይስማሙ ወደየቤታቸው እንዲበታተኑ ምክንያት የሆነ ታላቅ ሰው ነው፡፡

ዮሐንስ ወንጌላዊ ይህንን የኒቆዲሞስን ምስክርነት “ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀድሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን? አላቸው። እነርሱም መለሱና፡- አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ አሉት። እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ሄደ።” በማለት ገልጾታል (ዮሐ 7-50-52)፡፡ ኒቆዲሞስ ያለፍርሐትና ያለ ሀፍረት በካህናቱ ፊት እውነትን መስክሯል፡፡ እውነትንና ፀሐይን ፈርቶ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ ካህናቱን መጽሐፍ ጠቅሶ እውነትን ተናግሮ አሳፍሯቸዋል፡፡ በመሪዎች ፊት በታላላቅ ሰዎች ፊት እውነትን መመስከር ክርስትናችን የሚያስገድደን ቁም ነገር ነው (ሉቃ 12፡ 8)፡፡ ቤተክርስቲያን “ሰማዕታት” እያለች የምትዘክራቸው ቅዱሣን በሙሉ ለእውነት ብለው ራሳቸውን ለክርስቶስ አሳልፈው የሰጡ ናቸው፡፡ በፍርሐትና በሀፍረት በይሉኝታና በሀዘኔታ እውነትን አለመመስከር በክርስቶስ ፊት ያስጠይቃል እንጅ አያስመሰግንም (ማቴ 10፡32)፡፡ ሐዋርያው “ለእውነት እንጅ በእውነት ላይ ምንም ማድረግ አንችልም” እንዳለ እኛም እንደ ኒቆዲሞስ የእውነት ምስክሮች እንሁን (2ቆሮ 13፡8)፡፡

ጽንዐ ሃይማኖት (በሃይማኖት መጽናት) – ኒቆዲሞስ እስከ መጨረሻው በመጽናት ለታላቅ ክብር በቃ፡፡

በጌታችን ትምህርት ተስበው ተዓምራቱን በማየት ከተከተሉት ሰዎች ውስጥ በቀራንዮ የተገኙት ጥቂት ናቸው፡፡ ከእነዚህ አንዱ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ ቀራንዮ የምግበ ነፍስ ቦታ ናትና ኒቆዲሞስም ፈተናን ሳይሰቀቅ እስከ መጨረሻው የጸና ፃድቅ ነው፡፡ የክርስትና አገልግሎት ሲመቸን የምንሳተፍበት ፈተና ሲበዛ የምንሸሽበት አይደለም፡፡ ክርስትና በጅምር የሚቀር ሳይሆን እውነትን ሳንፈራ በመመስከር በተጋድሎ የምናሳልፍበት ለፈጸሙትም የድል አክሊል የሚያገኙበት ሕይወት ነው (2ጢሞ 4:8)፡፡ ምሳሌ ከሚሆኑን ቅዱሳን አንዱ አባታችን ቅዱስ እንጦንስ በፍጹም መንፈሳዊ ተጋድሎ ለ35 ዓመታት ከዚህ ዓለም ተድላና ደስታ በመራቅ እንዲሁም በአህዛብ መካከል ክርስትናን በመግለጽ የጽናት ታላቅ አስተማሪ ነው::

ኒቆዲሞስም ከጌታችን በተማረው ትምህርት ጸንቶ ለመኖር የበቃ አባት ነው፡፡ የሃይማኖቱ ጽናትም በተግባር የተፈተነ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ የአርማትያስ ሰው ከሚሆን ከዮሴፍ ጋር በመሆን የአይሁድን ድንፋታ ሳይፈራ “እሱን ያገኘ ያገኘኛል” ሳይል በድፍረት የጌታችንን ቅዱስ ሥጋውን በንጹሕ የተልባ እግር በፍታ ገንዞ በአዲስ መቃብር፣ በጌቴሴማኒ የቀበረ ሰው ነው (ዮሐ 19፥ 38)፡፡ ኒቆዲሞስ ከሐዲስ ኪዳን ካህናት ቀድሞ የጌታችንን ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሀደው ክቡር ሥጋ ለመገነዝ የበቃ አባት ነው፡፡ የጌታችንን ክቡር ሥጋ ገንዘው ሲቀብሩም በጸናች የተዋህዶ እምነት ጌታ እንደገለጠላቸው “ቅዱስ እግዚአብሔር፣ ቅዱስ ኃያል፣ ቅዱስ ህያው ዘኢይመውት” የሚለውን ቤተክርስቲያናችን እስከ ዕለተ ምጽአት የክርስቶስን ሥጋና ደም ስትባርክ የምትጠቀምበትን ጸሎት እስከ ፍፃሜው እየጸለዩ ነበር፡፡ በዚህም ኒቆዲሞስ ከሐዲስ ኪዳን ካህናት ቀድሞ ምስጢረ ጥምቀትን ከጌታ እንደተማረ፣ የሐዲስ ኪዳንን የምስጢራት አክሊል ምስጢረ ቁርባንንም እንዲሁ ተማረ፡፡ ይህንንም በሚመለከት ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ አብሮት ይቀድስ የነበረውን ንፍቅ ካህን በባረከበት አንቀጽ “በዚህ ምስጢር እየተራዳኝ ከእኔ ጋር ያለ ይህንን ካህን እርሱንም እኔንም ሥጋህን እንደገነዙት እንደ ዮሴፍና እንደ ኒቆዲሞስ አድርገን” (ቅዳሴ ማርያም ቁጥር 115) ብሏል፡፡

እኛም እንደ ኒቆዲሞስ፡-

በዕውቀታችን፣ በስልጣናችን፣ በሀብታችን፣ ባለን ማንነት ሳንታበይ ራሳችንን ዝቅ በማድረግ የእውነተኛ አባቶችን ትምህርት፣ ምክርና ተግሳፅ ልናዳምጥ በተግባርም ልናውለው ይገባናል፡፡
የያዝነውን እውነተኛ እምነት በማጠንከር በሃይማኖት ልብ የቤተክርስቲያንን ምስጢራት በትህትና ለመሳተፍ ልቡናችንን ከፍ ከፍ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
ምድራዊ አመክንዮ ሳያሰናክለን በቀንና በሌሊት ወደ አማናዊት የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ለምስጋና መሄድ ይኖርብናል፡፡
እውነትን በማድረግ ሕይወት የሚገኝበትን ቃለ እግዚአብሔርን ያለኃፍረትና ያለፍርሀት ልንመሰክር ያስፈልጋል፡፡
ክርስትና ምድራዊ ስጦታና ተዓምራት በሚገለጥበት በገሊላ ባህር አጠገብ ብቻ ሳይሆን መከራና ስቃይ ባለበት በቀራንዮም መገኘትን ይጠይቃልና በፈተናና በመከራ ጊዜም ቢሆን በእምነት ልንጸና የበለጠም በመታመን ልናገለግል ይገባል፡፡
ከኒቆዲሞስ ሕይወት ተምረን በሃይማኖት እንድንጸና የአባቶቻችን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

30/03/2023

አባ ሙሴ ጸሊም ኢትዮጵያዊ
አባ ሙሴ ጸሊም በትውልዱ ኢትዮጵያዊ ሲሆን አስቀድሞ በውንብድና ኑሮ ሕይወቱን ይገፋ ነበር፡፡ ሰዎች ከገድሉ የተነሳ ያደንቁታል፡፡እርሱ አስቀድሞ መንግሥተ ሰማያትን ገፍቷት ነበርና እርሱ በሥጋው ጠንካራ ፤ በሥራውም ኃይለኛ ነበር፡፡
አባ ሙሴ ጸሊምም ፀሐይን ለሚያመልኩ ሰዎች አገልጋይ ነበረ ፤ ብዙ ጊዜም ወደ ፀሐይ እያንጋጠጠ ፀሐይ ሆይ አንተ አምክ ከሆንክ አነጋግረኝ ይል ነበር ፡፡ደግሞም በልቡ የማላውቅህ ሆይ ራስህን አሳውቀኝ ይል ነበር ፡፡

አባ ሙሴ ጸሊም ኢትዮጵያዊ

በአስቄጥስ ገዳም ያሉ መነኮሳት እግዚአብሔርን ያውቁታል ፤ ያዩታልም እያሉ ሲነጋገሩ ሰዎችን ሰማቸው፡፡ ያንጊዜም ተነሳ ሰይፉንም ታጥቆ ወደአስቄጥስ ገዳም ሄደ ፤ በደረሰም ጊዜ አባ ኤስድሮስን አገኘው ፤ አባ ኤስድሮስም ፈራው ሙሴ ጸሊምም እውነተኛውን አምላክ ታሳውቁኝና ታስረዱኝ ዘንድ ወደ እናንተ መጣሁ አለው ፡፡ አባ ኤስድሮስም ወደአባ መቃርስ ወስዶ አገናኘው፡፡ እርሱም ተቀብሎ ሃይማኖትን አስተማረው እንዲህም አለው ታግሰህ የማስተምርህን ከጠበቅህ እግዚአብሔርን ታየዋለህ
የክርስትና ጥምቀትን አጥምቆ አመነኮሰው ከብዙዎች ገድለኞች ቅዱሳን ይልቅ ብዙ እና ጽኑዕ ገድልን መጋደል ጀመረ፡፡፡፡በኋላም በገዳመ አስቄጥስ የገዳሙ አበምኔት የነበረው የአባ ኤስድሮስ ደቀ መዝሙር ሆነ፡፡ በአባ መቃርዮስ ምክር ወደ ጴጥራ ሂዶ በተባሕትዎ መኖር ቀጠለ፡፡ ከገድሉ ብዛት የተነሳ አረጋውያን መነኮሳት በሚተኙ ጊዜ ቤቶቻቸውን በመዞር ውሃ መቅጃዎቹን ወስዶ ውሃ ሞልቶ በየቤታቸው ደጃፍ ያኖር ነበር፡፡ ውሃው ከእነርሱ ሩቅ ነበርና እንዲህም እያደረገ በመጋደል ለብዙ ዘመናት ኖረ ፡፡
አባ ሙሴ ጸሊም በበአቱ እያለ የፈቲው ፆር ያሠቃየው ነበር፡፡ ፈተናውን ተቋቁሞ በበአቱ መቀመጥ ስላልቻለ ወደ ገዳሙ አበምኔት ወደ አባ ኤስድሮስ ዘንድ ሄደና ‹በበኣቴ መቀመጥ አልቻልኩም› አለው፡፡ አባ ኤስድሮስም ወደ በኣቱ ተመልሶ በዚያው እንዲጸና መከረው፡፡ ሙሴ ግን ‹ፈጽሞ አልችልም› አለ፡፡ በዚህ ጊዜ አባ ኤስድሮስ ሙሴን ይዞት ከገዳሙ ቅጥር ውጭ አወጣው ከዚያም ወደ ምዕራብ አዞረውና ‹ተመልከት› አለው፡፡ በዚያ አቅጣጫ የአጋንንት መንጋ ለወረራ ሲዘጋጁና ሲንጫጩ አሳየው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ወደ ምሥራቅ እንዲመለከት አደረገውና እልፍ አእላፍ መላእክት ብርሃን ተጐናጽፈው አሳየው፡፡ ከዚያም ‹እነዚህ የብርሃን መላእክት ቅዱሳንን ለመርዳት ከእግዚአብሔር የሚላኩ ናቸው እነዚህ ርኩሳን አጋንንት ደግሞ ቅዱሳንን ለመፈተን የሚዘምቱ ናቸው፡፡ የብርሃን መላእክት ኃይል ከአጋንንት ኃይል ይበልጣሉና ጸንተህ ተጋደል› ሲል መከረው አባ ሙሴም ወደ በኣቱ ተመለሰ፡፡
አባ ሙሴ በገዳመ አስቄጥስ እያለ ከገዳማውያን አንዱ ጥፋት ሠራና ማኅበሩ ለፍርድ ተሰበሰበ፡፡ አባ ሙሴ ግን በጉባኤው ላይ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ካህኑ ተልኰ ‹ና. ሁላችንም አንተን እየጠበቅን ነው› አለው፡፡ አባ ሙሴም በሚያፈስስ ከረጢት አሸዋ ሞልቶ ያንንም በጀርባው ተሸክሞ ከኋላው እያፈሰሰ ወደ ጉባኤው አመራ፡፡ ጉባኤተኞቹ ተገርመው ለምን እንደዚህ እንዳደረገ ጠየቁት፡፡ እርሱም ‹የእኔ ኃጢአቶች በኋላየ እንደዚህ አሸዋ በዝተው ይፈሳሉ፤ ነገር ግን ላያቸው አልቻልኩም ዛሬ ግን በሌላው ላይ ለመፍረድ መጥቻለሁ፡፡› አላቸው፡፡ ይህን ሲሰሙ ዝም አሉ፡፡ ያን ወንድምም በይቅርታ አለፉት፡፡
በሌላ ጊዜ በገዳመ አስቄጥስ ያሉ መነኰሳት ተሰበሰቡና የአባ ሙሴን ትዕግሥት ለመፈተን ሲሉ “ይህ ጥቁር መነኩሴ ለምን እዚህ መጣ “ ብለው ተናገሩት፡፡ እርሱም ዝም አለ፡፡ ጉባኤው ሲበተን “አባ ክፉ ስንናገርህ ምንም ሐዘን አልተሰማህም ነበርን ?” ሲሉ ጠየቁት፡፡ “ተሰምቶኛል፣ ነገር ግን እንዳልናገረው አንደበቴን ተቆጣጠርኩት” አላቸው፡፡
በአንድ ወቅት በገዳመ አስቄጥስ ጾም ታወጀ፡፡ በዚያ ሳምንት አባ ሙሴን ለማየት ከግብጽ ወንድሞች መጡ፡፡ አባ ሙሴም በእንግድነት ተቀበላቸውና ምግብ ያበስልላቸው ጀመር፡፡ የእሳቱን ጢስ የተመለከቱ ጐረቤቶቹ “አባ ሙሴ ትእዛዝ አፍርሶ ምግብ ያበስላል” ብለው ለገዳሙ ሓላፊዎች ተናገሩ፡፡ ሓላፊዎቹም ‹አሁን ተውት ሲመጣ እኛው ራሳችን እናናግረዋለን› አሏቸው፡፡ ሓላፊዎቹም አባ ሙሴን ጠርተው ለምን ምግብን እንዳበሰለ ተረዱ፡፡ በቀዳሚት ሰንበት ማኅበሩ ሁሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ በአደባባይ ‹አባ ሙሴ ሆይ የሰውን ትእዛዝ አልጠበቅኽም፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ (እንግዳ ሆኜ መጥቼ ተቀብላችሁኛል የሚለውን) ግን ጠብቀሃል› ብለው አመሰገኑት፡፡
አንድ ጊዜ የአካባቢው ገዥ ስለ አባ ሙሴ ዝና ሰምቶ ያየው ዘንድ ወደ ገዳመ አስቄጥስ መጣ፡፡ ይህን የሰማው አባ ሙሴ ሸሽቶ ወደ ጫካ ገባ፡፡ በመንገድም ላይ የገዥው መልእክተኞች አገኙትና ‹እባክህ አባ ሙሴ የት እንዳለ በኣቱን አሳየን› አሉት፡፡ ‹ከርሱ ምን ትሻላችሁ፤ እርሱ ኮ ቂላቂል ነው› አላቸው፡፡ ይህን የሰማው የአካባቢው ገዥ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ መጣና የሆነውን ሁሉ ለአገልጋዮች ነገራቸው፡፡ ‹ብዙ ሰዎች ስለ አባ ሙሴ ሲያወሩ ሰምቼ ለማግኘት መጥቼ ነበር፤ በመንገድ ላይ ያገኘነው አንድ አረጋዊ ሰው ግን የአባ ሙሴ በኣት የት እንደሆነ ስንጠይቀው ከርሱ ምን ትሻላችሁ እርሱ ኮ ቂላቂል ነው አለን› ብሎ ነገራቸው፡፡ አገልጋዮቹም በጣም ተናደዱና ‹ምን ዓይነት አረጋዊ ሰው ነው ስለ ቅዱሱ ይህን የሚናገር› ብለው ጠየቁት፡፡ ‹ትልቅ፣ ጠቆር ያለ፣ አሮጌ ልብስ የለበሰ ነው› አላቸው፡፡ አገልጋዮቹም ተገርመው ‹ይህማ ራሱ አባ ሙሴ ነው፤ ይህን ያለህ ሊያገኝህ ስላልፈለገ ነው› አሉት፡፡ የአካባቢው ገዥም ከአባ ሙሴ ሁኔታ ከንቱ ውዳሴን ስለ መሸሽ ትልቅ ትምህርት ተምሮ ተመለሰ፡፡
አባ ሙሴ በኣት ሠርቶ ወደ ጴጥራ ሲሄድ በአካባቢው ውኃ ስላልነበረ ተጨንቆ ነበር፡፡ አንድ ድምፅ ‹ሂድ ስለምንም ነገር አትጨነቅ› አለው፡፡ ስለዚህም በዚያ መኖር ጀመረ፡፡ አንድ ቀን በጴጥራ እያለ አበው ሊጐበኙት መጡ፡፡ የነበረችው ውኃ ጥቂት ነበረችና በርሷ ምግባቸውን አበሰለ፡፡ የሚያጠጣቸው ግን አላገኘም፡፡ ስለዚህ ወደ ውጭ እየወጣ ውኃ ይሰጠው ዘንድ እግዚአብሔርን ይለምን ነበር፡፡ በመጨረሻ ዝናብ ዘነበና የውኃ ማጠራቀሚያዎቹን ሁሉ ሞላቸው፡፡ እነዚያ አባቶችም ‹ትወጣና ትገባ የነበረው ለምን እንደሆነ እባክህ ንገረን› አሉት፡፡ ‹እናንተ በእንግድነት ስትመጡ ውኃ አልነበረኝም፣ ስለዚህ ያንተን አገልጋዮች ወደ እኔ ልከሃቸዋል፣ ነገር ግን ውኃ የለኝም፣ ስለዚህ እባክህ ውኃ ስጠኝ እያልኩ እግዚአብሔርን ለመለመን ነበር› አላቸው፡፡

አንድ ወንድም አባ ሙሴን ‹አንድን አገልጋይ ባጠፋው ጥፋት የተነሣ ጌታው መታው፡፡ አገልጋዩ ምን ማለት አለበት?› ብሎ ጠየቀው፡፡ አባ ሙሴም ‹አገልጋዩ ብፁዕ ከሆነ፣ አጥፍቻለሁና ይቅር በለኝ ማለት አለበት፡፡› አለው፡፡ ‹ሌላ አይጠበቅበትምን?› ሲል ያ ወንድም ጠየቀው፡፡ ‹አይጠበቅበትም፣ ለጊዜው ለጥፋቱ ሓላፊነቱን ወስዶ አጥፍቻለሁ ካለ ጌታው ይቅር ይለዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ዓለማው በባልጀራ ላይ ላለመፍረድ ነው፡፡ በእውነቱ ጌታችን የግብጽን በኩራት ሁሉ ሲመታ ሰው ያልሞተበት አንድም ቤት አልነበረም› አለና መለሰለት፡፡ ያም ወንድም ‹ምን ማለት ነው?› አለው፡፡ ‹ሁላችንም የየራሳችንን ጥፋቶች ካየን የባልንጀራችንን ለማየት ዕድል አንሰጥም፡፡ በራሱ ቤት ሰው የሞተበት በጐረቤቱ ልቅሶ ለማልቀስ አይሄድም፡፡ ለባልንጀራ መሞት ማለት ለራስ ጥፋት ትኩረት በመስጠት፣ የሌላውን ጥፋት ከቁም ነገር አለመቁጠር ነው፡፡ ማንንም አትጉዳ፣ በማንም ላይ ክፉ አታስብ፣ ክፉ የሚሠራውን ሰው አትናቀው፣ በባልንጀራው ላይ ክፉ በሚሠራ ሰው ላይ አትተማመን፣ በባልንጀራው ላይ ክፉ ከሚሠራ ሰው ጋር አትደሰት፣ ለባልንጀራ መዋቲ መሆን ማለት ይህ ነው፡፡ በማንም ላይ አትማረር፣ ነገር ግን ‹ሁሉንም እግዚአብሔር ያውቃል፡፡› በል፡፡ ከሚያማ ሰው ጋር አትተባበር፣ በሐሜቱም አትደሰት፣ ወንድሙን የሚያማውን ሰውም አትጸየፈው፡፡ አትፍረድ ማለት ትርጉሙ ይህ ነው፡፡ በማንም ላይ የጥላቻ ሓሳብ አይኑርህ፣ ጥላቻ ልብህን እንዲያሸንፈውም አትፍቀድለት፡፡ ባልንጀራውን የሚጠላውን አትጥላው፣ ሰላም ማግኘት ማለት ይህ ነው፡፡
አንድ ጊዜ በገዳመ አስቄጥስ ወንድሞች አብረውት እያሉ አባ ሙሴ ‹ተመልከቱ በርበሮች ገዳማችንን ሊያጠፉ እየመጡ ነው፡፡ ተነሡና ሽሹ› አላቸው፡፡ እነርሱ ግን ‹አባ አንተስ አትሸሽምን?› ሲሉ ጠየቁት፡፡ አባ ሙሴም ‹እኔማ ይህችን ቀን ለብዙ ዘመናት ስጠብቃት ኖሬአለሁ፡፡ ጌታ በወንጌል ‹ሰይፍን የሚያነሡ በሰይፍ ይጠፋሉ› ያለው ቃል (ማቴ. 25.52) ይፈጸማል፡፡› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹እኛም አንሸሽም፣ አብረን እንሞታለን እንጂ› አሉት፡፡ አባ ሙሴም ‹ያ ለእኔ ረብ የለውም፤ ሁሉም ሰው ለየራሱ ይወስን› ብሉ መለሰላቸው፡፡ በዚያ ለነበሩት ሰባት ወንድሞች ‹በርበሮች ወደ ገዳሙ ደጅ እየደረሱ ነው› ብሎ ነገራቸው፡፡ ወዲያውም በርበሮቹ ደርሰው ገዳማውያኑን በሰይፍ መቷቸው፡፡ ከሰባቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ሸሸና በተቆለለው ሰሌን ውስጥ ተደበቀ፤ ወዲያውም ሰባት አክሊላት ሲወርዱላቸው ተመለከተ፡፡
የአባ ሙሴ ጸሊም በረከት ይደርብን አሜን
ዋቢ ስንክሳር ሠኔ 24

ቡና ርኩስ ነውን? Coffee is unclean? 29/03/2023

ቡና ርኩስ ነውን? Coffee is unclean? ቡና_ርኩስ_ነውን ?ብዙዎች ቡናን በአፈ ታሪክ እና በዘልማድ አባባል ርኩሰነው ቡናን መጠጣትም ኃጥያት ነው በማለት በራሳቸው መላምት ሲተቹ ይታያሉ ግን ?(1) በመጽሐፍ ተከልክሏል?Coffee_Unclean?Many...

ቡና ርኩስ ነውን? Coffee is unclean? 29/03/2023

https://www.youtube.com/watch?v=5nB3hQGgDHE
ቡና_ርኩስ_ነውን ?
ብዙዎች ቡናን በአፈ ታሪክ እና በዘልማድ አባባል ርኩሰነው ቡናን መጠጣትም ኃጥያት ነው በማለት በራሳቸው መላምት ሲተቹ ይታያሉ ግን ?
(1) በመጽሐፍ ተከልክሏል ?
አንድ አንድ ሰዎች ቡና በድርሳነ ፅዮን እና በዜና ስላሴ ተከልክሉል ይላሉ ።እስካሁን ግን ምዕራፍ እና ቁጥር አንቀፅ እና ገፅ ጠቅሶ ይህንን ይላል የሚል የለም ።በእርግጥ መፀሐፍቱ ለምዕመኑ በቅርብ ባለመገኘታቸው ለማሳመኛ ተጠቅመውባቸው ካልሆነ በቀር በሁለቱም መፀሐፍት ቡና አትጠጡ የሚል እንደሌለ ሊቃውንትም መፀሐፉቱም ይናገራሉ።
(2) የዲያብሎስ ደም (መሥዋት ) ነው የሚሉም አሉ.........

ቡና ርኩስ ነውን? Coffee is unclean? ቡና_ርኩስ_ነውን ?ብዙዎች ቡናን በአፈ ታሪክ እና በዘልማድ አባባል ርኩሰነው ቡናን መጠጣትም ኃጥያት ነው በማለት በራሳቸው መላምት ሲተቹ ይታያሉ ግን ?(1) በመጽሐፍ ተከልክሏል?Coffee_Unclean?Many...

Want your school to be the top-listed School/college in Adama?

Click here to claim your Sponsored Listing.

Location

Telephone

Website

Address


Oromia
Adama
0000