15/09/2026
በኤርትራ ጨለማ እስር ቤት የተረሳችው ሲሃም!🥹💔
: የአስራ አምስት ዓመት ታዳጊ እያለች የነፃነት አየሯን የተነጠቀችው ፤ ዛሬ የ29 ዓመት ወጣት ሆናለች ፤ ሲሃም አሊ አብዱ።
ሲሃም አሊ ፤ ላለፉት 14 አሰቃቂ ዓመታት ያለ ምንም የፍርድ ቤት ክስ፣ በወንጀል ሳትጠየቅ፣ እና የት እንዳለች እንኳ በውል ሳይታወቅ በለጋ እድሜዋ በእስር እየማቀቀ ትገኛለች ።
የዚህች አሜሪካዊ ዜግነት ያላት ንፁህ ታዳጊ ወንጀል አንድ እና አንድ ብቻ ነበር፤ የኤርትራ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩት አባቷ ከፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር በፈጠሩት የፖለቲካ ፀብ የቂም ሰለባ መሆኗ።
አቶ አሊ አብዱ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር እና የፕሬዚዳንቱ ቀኝ እጅ ነበሩ። ከትጥቅ ትግሉ ዘመን አንስቶ አብረው የዘለቁት አቶ አሊ፣ ምናልባትም ቀጣዩ የሃገሪቱ መሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ በብዙዎች ዘንድ ይገመት ነበር። ነገር ግን፣ ሁሉም ነገር በአንድ አሳዛኝ ቅፅበት ተቀለበሰ።
የጥል መንስኤው የዓለምን ትኩረት የሳበው ያ ታዋቂ የአልጀዚራ ቃለ-መጠይቅ ነበር። ጋዜጠኛዋ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስን "አምባገነን ነዎት፤ አካባቢውን በሁከት እያመሱ ነው" ብላ ፊት ለፊት ስትሞግታቸው፣ ፕሬዚዳንቱ የደም ስሮቻቸው እስኪገተሩ እና ላባቸው እስኪጠምቅ ድረስ በንዴት ጦፉ። በካሜራ ፊት የታየው ይሄው አሳፋሪ ስሜታዊነት፣ በመሪው ልብ ውስጥ መርዝ ፀነሰ።
ቃለ-መጠይቁ እንደተጠናቀቀም፣ ፕሬዚዳንቱ ሚኒስትራቸውን አሊ አብዱን አስጠርተው ቪዲዮው እንዳይተላለፍ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጡ። ሚኒስትሩ "ይህ የዓለም አቀፍ ሚዲያ ጉዳይ በመሆኑ ከእኛ አቅም ውጪ ነው" የሚል እውነታ ሲያስረዱ፣ ፕሬዚዳንቱ በቁጣ ገነፈሉ፤ ሚኒስትራቸውንም በቦክስ እና በርግጫ ደበደቡ።
ከዚህች እጣ ፈንታ ቀያሪ ቀን በኋላ፣ አሊ አብዱ የፕሬዚዳንቱን በቀለኛነት ጠንቅቀው ስለሚያውቁ አገር ጥለው ለመሰደድ ወሰኑ። ለስራ ወደ ጀርመን በተጓዙበት አጋጣሚ ስርዓቱን ከድተው ወደ አውስትራሊያ ኮበለሉ። ይህ ውሳኔያቸው ግን በአስመራ ለቀረችው የ15 ዓመቷ ልጃቸው የሲኦል በር ከፋች ሆነ።
አባቷ ልጃቸውን ለማትረፍ በሚል 7,000 ዶላር ከፍለው በህገ-ወጥ መንገድ በሱዳን በኩል እንድትወጣ ለማድረግ ቢሞክሩም፣ ሲሃም የሱዳንን ድንበር ልትረግጥ ጥቂት ሲቀራት በኤርትራ የደህንነት ኃይሎች እጅ ወደቀች። ከዚያች ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬዋ ሰዓት ድረስ፣ ሲሃም ያለችበት ቦታ በእርግጠኝነት አይታወቅም።
ነገር ግን የተለያዩ የመብት ተሟጋቾች መረጃ እንደሚያሳየው፣ ይህቺ ምስኪን ወጣት የተጣለችው 'ኤራ ኤሮ' በተባለው፣ በበረሃ ውስጥ በሚገኝ እና ከሰው እይታ በተሰወረ የምድር ስር የኮንቴነር እስር ቤት ውስጥ ነው። ይህ ስፍራ የቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣናት ያለ ፀሐይ ብርሃን በስቃይ ህይወታቸው ያለፈበት የምድር ላይ ሲኦል ነው።
የአባቷን የፖለቲካ ሸክም እንድትሸከም የተፈረደባት ሲሃም፣ የልጅነት ህልሟ፣ የወጣትነት ብሩህ ተስፋዋ፣ እና ነፃነቷ ሙሉ በሙሉ ተነጥቋል። ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች ድምፃቸውን ቢያሰሙም፣ የኤርትራ መንግስት ዛሬም ድረስ ስለ እርሷ ህያውነት ትንፍሽ አላለም። የ15 ዓመቷ ህፃን፣ አሁንም በጨለማ ውስጥ የፍትህ ደወል የሚደወልበትን ቀን እየጠበቀች ትገኛለች።