Woreta Senior Secondary & Preparatory School

Woreta Senior  Secondary & Preparatory School Woreta Senior Secondary and Preparatory School
is founded in 1959E.C

Woreta senior and secondary and preparatory school of woreta town was found in 1959EC initially the school was called Woreta Giorgis secondary school this name was used 1959-1990EC the name Woreta senior and secondary school start functioning in the yea

09/06/2022

በAbiy Ahmed የመደመር ስሌት — የአንድ ኢትዮጵያዊ ነፍስ ስንት ያወጣል?

/በትዕግሥት የሚነበብ!/

አብይ አህመድ በ5ሺህ የክብር ዘብና በ50 ጠባቂ ጠረንገሎዎች ታጅቦ ይንጎማለላል፡፡ ሳዑዲ ተልከው የመኪና አክሮባት በሠለጠኑ ሹፌሮቹ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ አለ የተባለ በመዓት ሺህ ዶላሮች ተከስክሶባቸው ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችንና ተሽከርካሪዎችን ታጥቀው አብይ ሲሮጥ ይሮጣሉ፣ ሲቆም ይቆማሉ፣ ሲተኛ ነቅተው ይጠብቃሉ፡፡

እንግዲህ ሰውየው የሚኖረው በጠላት ሀገር ላይ አይደለም፡፡ ሥራቸው አብይን ከራሱ ህዝብ መጠበቅ ነው፡፡ ለነፍሱ ጥበቃ የሚከሰክሰው የተጋነነ ወጪ መጠን የአብይ አህመድን ፈሪነት አይደለም የሚያመለክተው፡፡ ህዝቡን የፈራበትን መጠን ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ሪፐብሊካን ጋርድ ወጪ የሚከፈለው እህ ብሎ አምጦ ወገቡን አጉብጦ ሲሠራ ከሚውለው ከእያንዳንዱ ጭቁን ኢትዮጵያዊ ጉሮሮ ተነጥቆ ነው፡፡

የደሃው ልጅስ? የደሃው ልጅ ደሞ ለጌቶች ነፍስ ጥበቃ ከጎበጠ ወገቡ የሚገፈግፈው አንሶ፣ እነ አብይ አህመድ እፍ ብለው በቆሰቆሱት የጦርነት እሳት እየተላከ፣ ኮቾሮ እየቆረጠመ፣ አፈር ልሶ፣ አፈር ለብሶ፣ አፈር መስሎ፣ በየጥሻው ሲንፏቀቅ፣ በጥይት አረር ሲጨረገድ፣ እና ከገዛ ወገኑ ጋር ደም ሲፋሰስ፣ ነፍስ ሲነጣጠቅ ይውላል!

በየዕለቱ የደሃን ልጅ ነፍስ እንደ ባህርዛፍ ቅጠል እያረገፈ፣ በሚሊየን ዶላሮች በተጌጠ የሲቹዌሽን ሩም ሳሎን ውስጥ ቁጭ ብሎ፣ በሚሊየኖች ብሮች ባስገነባቸው መናፈሻዎች ችግኞችን ሲተክልና፣ በማታ በቦቴ መኪና ችግኞቹን ውሃ ሲያጠጣ እየተከተለ የሚያነሳውን ፎቶግራፈር በሄደበት እያስከተለ የልጅ አምሮቱን ይወጣል፡፡ ድል ቁርሱ፣ ትንታጉ፣ ነበልባሉ፣ ሀገር-ወዳዱ እያለ በደሃው ደም ውስኪ ለሚረጫጩት፣ በደሃው አጥንት ላይ ለሚረማመዱት ድልብ ጄኔራሎች የዳቦ ስም ያወጣል!

አብይ አህመድ የምላስ ወለምታ አያውቅም፡፡ ንቀት፡፡ ከፍ ያለ ንቀት ነው ያለው ለህዝቡ፡፡ ህዝቡ ሜሞሪው አጭር ነው - ብሎ ተናግሮ ይቅርታ አትጠብቅ፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ - የሕዝቡ የመዘንጋት ችግር እንዳለ ሆኖ.. ብሎ የፓርላማ ንግግሩን ይጀምራል፡፡ አብይ አህመድ የኢኮኖሚክስ ዶክተር ማለት የአንድ ሀብታምን ታሪክ የጻፈ ነው፣ የእናንተን፣ ለራሱ መኪና ያልገዛ ምሁር፣ ምሁር ነው ወይ? ያልተማረ ባለገንዘብ ይበልጠዋል የኛን ሀገር ፕሮፌሰር ሲል በተማሩት ይሳለቃል፡፡ ያው የፓርቲው ውርዴ መሆኑ ነው፡፡ ምሁር ጠልነት፡፡

ራሱ ስለምን ጽፎ ዶክትሬት እንዳገኘ በበኩሌ አላውቅም፡፡ ባንድ ወቅት የካርል ማርክስን ስም እጠራለሁ ብሎ ህዝብ በተሰበሰበበት አዳራሽ ‹‹ማርክ!›› እያለ እንደቆሎ ጓደኛው ሲቆነጽለው - ‹‹ሃይ ጋይስ›› እላለሁ ብሎ ‹‹ሄይ ጌይስ›› ያለው የጥንቱን ወዳጄን ያስታውሰኛል፡፡ ሳሞራ የኑስ ፕሮፌሰር በሆነባት ሀገር፣ ምን የማይቻል ነገር አለ?

አብይ አህመድ እኮ - ፕሮፌሰር መስፍን በአንድ ወቅት - በዓለም ላይ እንደእሱ ያለ ጭንቅላቱ የመጠቀ ሰው አይቼ አላውቅም - ብለው የመሰከሩለት ባለብሩህ አዕምሮ ሰው እኮ ነው፡፡ ከእሳቸው ጋር አንጋጠህ አትታገል እንግዲህ፡፡ መቀበል ነው ያለህ አማራጭ፡፡ ግን የሚገርመው እሳቸው በአንድ ወቅት በመጽሐፍ ሁሉ አትመው ‹ከደብተራም ያነሰ ድቁናውን የጣለ ደደብ› ብለው ያብጠለጠሉት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እኮ ነው ንግግሩን እንኳ የሚጽፍለት!

ዓለም አስቂኝ ናት! ነብርን ፍየል ስትመራው ብታገኝ፣ ጂኒየሱን ደደቡ ንግግሩን ሲጽፍለት ብታገኝ አይግረምህ! ዓለም እንዲህ ነች! በበኩሌ ግን በብዙ ፈርጆች ቢመዘን ፕሮፌሰር ሳሞራ የኑስ ከዶክተር አብይ እጅግ የተሻለ የህይወት ልምድም ወታደራዊ እውቀትም ብስለትም ያካበተ ሰው እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ከአብይ አንጻር ነው ያልኩት፡፡ አብይ አህመድ አንዴ ብቻ ነጯን ሲናገር ስሰማው በፍቅር ገድሎኝ ነበር፡፡ ከአማካሪዎቹ ከእነ ዶክተር ብርሃኑ ጋር በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግሮች ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ሲያቀርብ - ‹‹እኔም እንደምሁር ተቆጥሬ ከናንተ ጋር በማቅረቤ አመሰግናለሁ›› ብሎ ነበር፡፡ ይህን ያህል ትሁት ከሆነ፣ የማብጠልጠል መብት አይኖርም፡፡ ይቅር ለእግዜር፡፡

በዚህች ጎረቤት ለጎረቤት እንጀራና ወጥ እየተበዳደረ በሚኖርባት ደሃ ሀገር ላይ - አብይ አህመድ የማርጋሬት ታቸርን እንደ ብረት የጠነከረ ነጭ ካፒታሊዝም አራምዳለሁ ብሎ ብዙ ጊዜ ሲናገርና ሲያስነግር ለሰማው ሰውየው በሕልም ዓለም እንደሚኖር ማንም አይጠራጠርም፡፡ ድንገት ይነሳና ሀብታሞችን የሚሊዮን ብር እራት ይጠራቸዋል፡፡

በግብዣው ላይ የሼሁ ስንተኛ ሚስት የሆነች አር-ቲስት ትነሳና በሼሁ ስም የሆኑ ሚሊየኖችን ለአብይ አህመድ ትለቅበታለች፡፡ ፓርላማ ሲጠይቀው - ይሄ ፓርላማ በጀት ቆርጦ ያልሰጠኝን፣ ለምኜ ያመጣሁትን ገንዘብ ሰባራ ሳንቲም ሊጠይቀኝ አይችልም! ብሎ በድፍረት የመለሰ ሰው ነው፡፡ ቄሮ ሆቴሉን አቃጥሎ አመድ ያደረገበት ኃይሌ ገብረስላሴ ይመጣና የሚሊዮን ብር ራት አብልቶ ፓርላማውን አትጠይቀኝ ላለው - እና የመለመን ፀጋ አለኝ ይሳካልኛል ብሎ - የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚሽኑን ስምዖን መቻሌን ላስቀናው - ለአብይ አህመድ ባደባባይ አዲስ ከነዳጅ የነጻች መኪና ቁልፍ በሥጦታ ያበረክትለታል!

‹‹ሀብታም ለሀብታም ይጠቃቀሱ፣ ደሃ ለደሃ ይለቃቀሱ›› ይላሉ አበው - የእኛን ዓይነቱን አያዎ ህይወት ሲመለከቱ፡፡ በአብይና ጭፍሮቹ አመለካከት - ደሃው ሕዝብ (የኢኮኖሚክስ ዶክተርም ቢሆን መኪና ከሌለው!) በሀገሩ ላይ ሲኖር፣ ነፍሱ አስፈላጊ የሆነች፣ ቢሞት ቤተሰቡንና ሀገሩን የሚያጎድል፣ ቢኖር ራሱን፣ ዘመድአዝማዱን፣ ቤተሰቡን ሀገሩን የሚጠቅም ክቡር የሰው ልጅ ሆኖ ሳይሆን፣ ተራ አሃዝ፣ ተራ ቁጥር ሆኖ መኖር እንዳለበት ደምድመዋል፡፡

ከላይ እንዳልኩት በዚህች ሀገር ላይ - የአብይ አህመድ አንዲት ነጠላ ነፍስ በቢሊየን ብር ባጀት በሚመደብላቸውና በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ አስቂኝ ትርዒትና አጀብ በሚያደገድጉ፣ ከፍ ያለ ሥልጠናና ወጪ በሚወጣባቸው ሪፐብሊካን ጋርዶች ትጠበቃለች፡፡ የደሃው ልጅ ነፍስስ? በዚህች የህይወት ኢንሹራንስ ህዝቡን ባላዳረሰባት ምስኪን ሀገር የደሃውንስ ነፍስ ማን ይጠብቃት? ደሃውማ ምን ጠባቂ ያስፈልገዋል? ደሃ ጠባቂ ቢያስፈልገው በቡራዩ ላይ ያለጠባቂ አይጨፈጨፍም፡፡

ደሃ ጠባቂ እንደሚያስፈልገው አብይ አህመድ ቢያምን በዝዋይ፣ በሻሸመኔ፣ በወለጋ፣ በመተከል፣ በባሌ፣ በሐረርጌ፣ በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች - ህዝብ - ያለ ጠባቂ፣ ያለህግ፣ ያለ ተከላካይ - በመቶ ሺኅዎች በግፍ አይገደልም፡፡ በግፍ በአደባባይ አይቃጠልም፡፡ በግፍ አይፈናቀልም፡፡ በግፍ የእርጉዝ ሆድ አይዘከዘክም፡፡ ሰው የራሱን አንዲት ነፍስ በቢሊዮን ብሮች ባጀት መድቦ በብርጌድ ሲያስጠብቅ፣ እንዴት የመቶ ሺህዎችና የሚሊዮን ዜጎችን ነፍስ እንደ በረሮ ነፍስ ቆጥሮ ሀገር ምድሩን የአራጅና የወንበዴ መፈንጫ ያደርገዋል?

ይሄ ይቅር! እነ አብይ አህመድ ይቅርና ከእነ አብይ አህመድ ጋር የተሞዳሞዱ ተቃዋሚዎች ሁሉ የነፍሳቸው ጠባቂ ጋርድና ታጣቂ ተመድቦላቸው ከዚህ ከደሃው ህዝብ ላይ ከሚሰበሰብ ታክስ ደመወዝ እየተቆረጠለት በየሄዱበት እንደጥላ እየተከተለ ለክብራቸው ሲያደገድግና ነፍሳቸውን ሲጠብቅ፣ ደሃው ኢትዮጵያዊ ግን ሠላሙም አርሮበት - በመቶ ሺኅዎች የሚቆጠር የደሃ ልጅ ከየጎጆው እየተጋዘ፣ ከሌላው ከፈረደበት ወገኑ ጋር፣ ባላገደደውና ባልፈተፈተው ጉዳይ፣ ባልጫረውና ባልቆሰቆሰው፣ በማያውቀው የጦርነት እሳት ውስጥ እንዲማገድ እየተደረገ… በዚህች በፈረደባት ‹‹እናት ሀገር›› ስም ከገዛ ወገኑ ጋር ሥጋ ለሥጋ፣ አጥንት ለአጥንት ሲሞሸላለቅ ይከርማል!

በዚህ መሐል የሞተ ተጎዳ፣ የተረፈ አንድዬ አተረፈው! ይኸው ነው! ዞር ብሎ የሚያየው የለም! ቢማረክም ባለቤት የለውም! ቢሞትም ሞቱ አይታመንለትም! የክብር ሜዳይ የለውም! ሀገርና ሕዝብ የተዋደቁላቸውን ጀግኖቻቸውን በስም አያውቁም! ስም የሌላቸው፣ ክብር የሌላቸው፣ ጠባቂ የሌላቸው፣ ግፋ ቢል በቁጥር 20 ሺህ ሰራዊት አለቀብን እየተባለ በጅምላ ቁጥራቸው የሚታመንላቸው፣ የደሃ ልጆች በሠላም ሀገር፣ የሠላም ኖቤል በተሸለመና በብርጌድ ነፍሱን በሚያስጠብቅ መሪ ዓይን ስር እንደ ቆሎ ይረግፋሉ!

ይህ ነው የዘመኑ የምስኪኑ የደሃው ኢትዮጵያዊ ልጅ የተፈረደበት አሳዛኝ የህይወትና የሞት እጣ ፈንታ! ይህንኑ ሸሽተው ለመሰደድ ስንቱ ባህር የሚበላቸው፣ ስንት አውሬ የሚጫወትባቸው፣ ወጥተው የቀሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ፣ በአስከፊ የሽሽት ሞታቸው የሥርዓቱን አስከፊነት የሚያጋልጡ ናቸውና የክብር ሽኝት አያገኙም፡፡ ስማቸው በሚዲያ አይነዛም፡፡ የሀዘን ባንዲራ አይወርድላቸውም፡፡ ዝም፡፡

ህዝባችን በዝምታ እያለቀ ነው፡፡ ወጣቶቻችን በዝምታ እያለቁ ነው፡፡ መሪው ደግሞ በቢሊየን ብሮች መሐል መስቀል አደባባይ ላይ አስፋልት እየቆፈረ የማሳመር ሥራ ይሰራና፣ በጓደኛው ያሬድ ሹመቴ ኤግዚቢሽን ማዕከል ሲኒማ ፊት ለፊት ቁጭ ብሎ ሲዝናና መከረኛውን ካሜራማን ጠርቶ ፎቶ ተነስቶ ኑሮው ላረረበት፣ ሕይወቱ ላረረበት ሕዝብ ይለቃል፡፡

‹ዘ ፓወር ኦፍ ፖዘቲቭ ቲንኪንግ!› ‹የብልጽግና ወንጌል!› ይህ መሆኑ ነው! ስለማሸነፍ ነው ማውራት ያለብህ! ስለብልጽግና ነው! ስለሥልጣን ብልግና አይወራም! ኢትዮጵያ አሸንፋለች! በቅርቡ ከዓለም ሁለት ኃያላን ሀገራት አንዷ ትሆናለች! (ይህን የሚለው ባለ ክቡሩ ባለራዕዩ መሪያችን ዶክተሩ አብይ አህመድ አሊ ነው! እግዚአብሔር በኃያላን ጦር ያስወጋህ! ማለት ያሰኛልኮ አንዳንዴ - ይህን ሕዝብ እንዴት እንደሚጫወትበት ሲታይ!)

ዛሬ ሀገራችን ወደ ትልቅ የሀዘን ቤት ድንኳንነት ተቀይራለች፡፡ ሀገር በጦር እሳት እየተንገበገበች ባለችበት በዚህ መራር ወቅት - እውነተኛው ሀገር-ወዳዱ - እና ያለችውን አንድዬ ነፍስ በሀገር ስም የሚነጠቀው ወጣት ኢትዮጵያዊ - ከኢትዮጵያዊም መሐል የፈረደበት የደሃው ልጅ - አጥንቱ በየሜዳው በሺህዎች እየተከሰከሰ ነው፡፡ ልጅ ያለው ልጆቹ ዘለዓለም ዓለማቸውን ያለአባት፣ ወላጆቹ ያለ ደጋፊ፣ እርሱ ያለ ስም፣ ቤተሰቡ ያለ ጧሪና ቀባሪ ያቺኑ የኮሰሰች ኑሮ ያለአጋር ሲገፏት ይኖራሉ!

ቅዱሷና ከዜጎች ሁሉ ነፍስ እጅግ የከበረችው የእነ አብይ አህመድ ነፍስ ደግሞ - አስር ቢሊዮን በጀት በየዓመቱ እየተመደበላት - በአምስት ሺህ የክብር ዘቦችና በሃምሳ ጠባቂ ጠረንገሎዎች - ባህረሰላጤውን ተሻግረው በሳዑዲ አረቢያ የመኪና አክሮባት በሠለጠኑ ሹፌሮች - እና በመዓት ደህንነቶች እየተጠበቀች ከቀን ወደቀን ደህንነቷ ተጠብቆ ትለመለልማለች፡፡

አብዮት ልጆቿን ትበላለች - የሚባለው የፈረንሳይ አብዮቶች ቃል ዳግመኛ በሀገራችን ምድር በቃል የደረሰው አሁን በአብዮት አህመድ የአገዛዝ ወቅት ላይ ነው፡፡ አብዮት - የራሱን ነፍስ በሺኅ ሪፐብሊካን ጋርዶች እያስጠበቀ - የሀገሪቱን ልጆች ነፍስ ቅርጥፍ አድርጎ እየበላውና እያስበላው ነው፡፡ እሱ በስም ላይ ስም፣ በዝና ላይ ዝና፣ በፉከራ ላይ ፉከራ እየደረበ የድል-ቁርሱዎችን ስም ለጋሻ-ጃግሬዎቹ እያደለ ሲንጎማለል ይኖራል! ደሃው ስም የለውም! ሙት ሲባል መሞት! ሂድ ሲባል መታዘዝ! ውጣ ሲባል ምስስ ብሎ ወደተዘጋጀለት መትረፊያ ካምፕ መግባት ብቻ!

የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን የጌቶችና የባሮች ግንኙነት እንዴት አሜን ብሎ እንደሚቀበል ብዙዎችን የዓለም ሕዝቦችን ግራ ያጋባውን ያህል እኔንም ግራ ያጋባኛል፡፡ ፈጣሪ እኩል አድርጎ አይደል ወይ የፈጠረን በአንድ ሰማይ ሥር? የእነ ታዬ ደንደአና የእነ ሽመልስ አብዲሳ የእነ አባዱላና የእነ ደመቀ መኮንን ልጆች ከፍተኛ የሀገሪቱ ሀብት እየተንጠፈጠፈላቸው፣ በቦዲ ጋርዶች እየተጠበቁ፣ በሰላም ውለው ያድራሉ፡፡

የድሃው ኢትዮጵያዊ ልጆች ግን የአውሮፕላን ቦምብ የሚዘንብባቸው፣ ወይ ጥይት አዝናቢም፣ በጥይት ተጠዝጣዥም ሆነው - ቤተሰቦቻቸው እየተለዩ ሆነ ተብሎ በቁርሾና በሥልጣን መቧጨቅ በተመሳሳይ ሀሳብ ተጋሪ ሰዎች መሐል በተቀሰቀሰ ጦርነት የሚማገዱበት፣ እንጥፍጣፊ ተስፋቸው የሞት ጨለማ የሚደረገምባት - ይህን ዓይን ያወጣ፣ ሰው-በላና ዘረኛ ሥርዓት እንዴት - በዚህ በሰለጠነ ዘመን፣ እና ብዙ የዓለም መረጃ በፍጥነት በሚዘዋወርባት ዘመናይት ዓለም ላይ እየኖርን - የሚያመዛዝን የሰው ልጅ ህሊና እሺ ብሎ ይቀበለዋል?

ለመሆኑ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ.. አብርሃ ሄዶ በመገርሳ ስለተተካ፣ ጎይቶም ተባሮ በዲማ ስለተለወጠ፣ ኩማ በሹመት ተዛውሩ በሱ እግር ደመላሽ ስለተተካበት፣ በንቲ ሄዶ ባቲ ስለመጣ፣… በቃ ለውጥ መጣልን ማለት ነው? የትኛው ለውጥ ነው ይህ ሁሉ የዜጎች ደም የሚገበርለት? የየትኛው ደሃ ኑሮ ነው የተሻሻለው? ከሶስት ዓመት በፊት ትግራይ ውስጥ ኮሽ የሚል የፀጥታ ችግር ነበር? አሁንስ? ከጥቂት ዓመታት በፊት ወለጋ ላይ ሰዎች በሰላም አይኖሩም ነበር? አሁንስ?

ድጋሚ ወደድሮው! እርስ በርስ ሚሳይል መተኳኮስ፣ ዲሽቃ መለካካት፣ በአውሮፕላን ሕዝብን በቦምብ መደብደብና አውሮፕላን መጣል! ድጋሚ ወዳለፍነው የእርስ በእርስ ጦርነት ለመግባት ነው የደሃው ልጅ ነፍስ ጭዳ የሚሆነው? ማን ነው በለውጡ ያተረፈው? ያለጥርጥር ብቸኛዎቹ የለውጡ አትራፊዎች በሪፐብሊካን ጋርድ የሚጠበቁት ብቻ ናቸው! ሌላ ማንም ለውጡ ጠቀመኝ ያለ አይገኝም! በመጫረስ ብቻ ነው ወይ ለውጥ የሚመጣው? ወይስ በደሃው ልጅ ኪሳራ የህዝብ ቁጥር ለመቀነስ ነው ዓላማችን?

ጥቂቶች ከሁሉም በልጠው፣ የጥቂቶች ነፍስ ከሁሉም ነፍስ ተለይታ እየለመለመች፣ የጥቂቶች ነፍስ በብዙ ሺህ ነፍሶች እየተጠበቀች - የአብዛኛው የሀገሪቱ ህዝብ ነፍስ የደምና የሞት እሳት እንዲነድበት የተፈረደበትን ኑሮ እንድንገፋ የጣፈን የትኛው ፈጣሪ ይሆን? ለግፍ ልክ የለውም ወይ? በየቀኑ በገዢዎቹ መቀላመድና ድንፋታ ወደ እሳት የሚማገደው የደሃው ልጅ መሪውን ‹‹በቃህ! የሚለው መቼ ነው?

‹‹በቃህ! እስቲ አንተ ደሞ እንደ እኔ ከሞቀ ቤትህ ውጣና እንደ ጀግና ተዋግተህ አሳየኝ! እስቲ አንተም እንደኛ ሙትና አሳየን! እስቲ አንተም ቁሰልና፣ አፈር ምሰልና አሳየኝ! ከዚያ እኔም፣ እኛም፣ ሁላችንም ፈለግህን እንከተልሃለን!›› ብሎ የሚያፋጥጥበት ወቅት መቼ ነው? ‹‹መሪ ነኝ›› ሲል ‹‹ናና መንገዱን አሳየን እስቲ!›› አይባልም ወይ ሰው? እሱ በሺህ ጠባቂዎች አንዲት ነፍሱን እያስጠበቀ፣ የደሃውን የመቶ ሺህ ኢትዮጵያውያንን ነፍስ እንደ ቀላል በወራት ዕድሜ ለሞት ሲማግድ? በቃን አይባልም ወይ?!!

ያንተስ ነፍስ፣ ያንቺስ ነፍስ፣ የእኛስ ነፍስ.. ነፍስ አይደለችም ወይ? አይበቃንም ወይ በሞታችን ለሌሎች ጥቂቶች የልጅነት ምኞት መሣካት ተቀጣጣይ ማገዶ መሆን? አይበቃንም ወይ ለንጉሦቻችንና ለመኳንንቶቻችን የቀን ቅዠት ሲባል አንዲቱን ጓዳችንን የምታጎድለውን ያለችንን ብቸኛ ተስፋ - አንድዬ ህይወታችንን - ለእርስ በእርስ መበላላት ዓላማ ተሰላፊ ሆነን ለውጥ ለሌለው ከንቱ የገዢዎች ምኞትና መቆራቆስ በከንቱ መማገድ?

‹‹ወርቃማው ህግ!›› የሚባለው እኮ ይኸው ነው! በሰው እግር ሆኖ ማየት! እንደ ሰው ሆኖ መቆርቆር! የሰው ህመም፣ የሰው ሞት፣ የሰው ልጅ ስቃይ፣ የሰው ልጅ ከወገኑ ጋር ሲወጋጋ መድማት! ያ ሲሰማህ ነው ወርቃማው ህግ የሚገባህ፡፡ በራስህ እንዲደረግ የማትፈልገውን ነገር፣ ለምን በሰው ላይ ታደርጋለህ? ለምን በሰው ላይ ታስደርጋለህ? ለራስህ የምታደርገውን ጥንቃቄና የነፍስ ጥበቃ፣ ስለምን ከሚሊየኖች ህዝቦች ላይ ትነሳለህ? ወርቃማውን ህግ ለምን አትፈልገውም?

ቆይ ቆይ ለምን ቦታ ተለዋውጠን አንሞክረውም? ለምን እኛ ብዙሃኑ የደሃው ልጆች - በሥልጣን ላበጡትና በጥጋብ ለሚገጫጩት ባለጊዜዎች ብለን ነፍሳችንን ከምንገብር - ለምን እኛ የነጻ ትኬት ተሰጥቶን - ተገጫጪዎቹ ራሳቸውን ችለው - እንደ ግላዲያተሮች - በፍስፍሱ መድረክ ላይ ይውጡልንና - ጥቂቶቹ አጅሬዎች እርስበርሳቸው ሲጠዛጠዙ - እኛ ብዙሃኖቹ ተመልካቾች በተዘጋጀልን የሚስማር ተራ ሲቹዌሽን ሩምም ቢሆን፣ አረፍ ብለን - ጠላም ብትሆን እየተቃመስን - ለምን አንመለከትም?

የጌም ኦፍ ትሮንሱ - አሪፍ ጌም እንዲሆንልን - ለምን ጨዋታውን ገልብጠን አንጫወተውም? ለምን ቦታ ተለዋውጠን የደሃው ልጅ በሪፐብሊካን ጋርድ እየተጠበቀ ሲቹዌሽን ሩም ውስጥ 24 ሰዓት እየዋለ እያደረ፣ እናንተ ገዢዎቻችን ደግሞ ጦርሜዳ ኮቾሮና አፈር እየቃማችሁ፣ እየቆሰላችሁና እየተቆሳሰላችሁ፣ እየሞታችሁ… ለምን ጌሙን አገላብጠን አንሞክረውም ጌቶችዬ?

የአንዱ ነፍስ አፈር እየጠጣች፣ አፈር እንድትገባ የተፈረደባት፣ የአብይ አህመድና ጭፍሮቹ ነፍስ ግን በአምስት ሺህ ቦዲጋርድ እየተጠበቀች፣ ጥይት በማይበሳው ልብስና መድፍ በማይዘልቀው መኪና እየተከለለች፣ በዚያ ላይ ክፉ እንዳይነካት የኢትዮጵያ እናቶች በእንባ ታጅበው እየፀለዩላት የምትቀጥል ከሆነ - እንግዲህ ባንድ ሀገር ሰማይ ስር - ሁለት ዓይነት ነፍሶች እያሉ - በእኔ ጉሮሮ ጥይት ይሰንቀር፣ በጌቶች ጉሮሮ ምቾት ይንቆርቆር - እየተባባልን - እንዴት እኩል ዜጋ ነኝ ልንል እንችላለን? የሆነ ልክ ያልሆነ ነገርማ አለ!

እውነት እንዲህ የራሳቸውን ነፍስ በቢሊየን ብሮች በጀት የሚያስጠብቁ ገዢዎቻችን፣ የራሳቸውን ነፍስ እንዲህ ከፍ አድርገው አዋድደው ሲገምቷት… ግን ግን… ግን ለመሆኑ… የእኛን የአንድ የተራ የደሃውን ኢትዮጵያዊ ነፍስ… ስንት ያወጣል ብለው ቢገምቱ ነው ግን? እውነት በዛሬዋ በአብይ አህመዷ ኢትዮጵያ የአንድ ዜጋ ነፍስ ስንት ያወጣል?

የቀኃሥ ዘመን አዋጅ ማንም ባለቤት አልባ አስከሬን በመንገድ ላይ ወድቆ ቢገኝ የመንግሥት ሆስፒታል ለማዘጋጃ ቤት 30 ብር ከፍሎ ለህክምና ምርምር አገልግሎት እንዲያውለውና ሲያበቃ በክብር እንዲቀብረው ይፈቅድ ነበር፡፡ በዚያም የአንድ ሰው ነፍስ 30 ብር መሆኑን አወቅኩ፡፡ የያኔ 30 ብር የአሁን 3ሺህ ብር አይሆን ይሆን? ግድየለም ይሁን! ያ የነፍስ ዋጋ አይደለም! የሙት አካል ዋጋ ነው! አንዳንዴ ዋጋ የሌለው ነዋሪ ከመሆን እኮ፣ የምር፣ ቁርጡ የታወቀ ዋጋ ያለው ሟች መሆንም ይሻላል እኮ አንድ ፊቱን!

እንደው ሌላው ሁሉ ይቅርብንና - እነ አብይ አህመድ ግን የራሳቸውን ዋጋ እንዲያ ቆልለው - በቢሊየኖች በጀት በሚመደብለት ሪፐብሊካን ጋርድ ሲያስጠብቁ - የእኛን የአንድ ኢትዮጵያዊን ነፍስ ግን በስንት ይሆን የተመኑት? ምን ቢያስቡ፣ እና እንዴት ለአገዛዝ ምቹ ባሮች ሆነን ቢያገኙን ነው እንዲህ ነፍሳችንን አርክሰው በነጻ የገመቱን?

ኧረ ዋጋ ቀርቶ… ስንት እንዳለብን ቢነገረንምኮ ከፍለን እንገላገለውና ነጻ እንወጣ ነበር! ሰው እንዴት የሩሲያን የ19ኛ ክፍለዘመን ድርሰት፣ በዚህ በ21ኛው ክፍለዘመን ላይ ይኖረዋል? እንደ ኒኮላይ ጎጎል ‹‹ሙት ነፍሳት›› ድርሰት እኮ፣ ‹‹ሙት ነፍሳት›› አድርጎ ሊያስቀረን ምን ቀረው የኛው ጉዱ-ካሣ (አብዮት ካሳሁን በላይነህ)!?

በቃን! በቃን! በቃን! በቃችሁ! ኑ እናንተ ደሞ አነግቡልን መሣሪያውን! እስቲ ወግ ይድረሳችሁና እንደቀደሙት መሪዎቻችን ወደ ጦርሜዳው ወረድ ብላችሁ ምንሽር አነጣጥራችሁ ስትታኮሱ እንያችሁ! የሲቹዌሽን ሩሞቹ ጀግኖቻችን! እነ ድል-ቁርሱዎች! እነ ትንታጎች! እነ ሀገር-ወዳዶች! ጀግኖች ነን ያላችሁ - እስቲ እንያችሁ!? እስኪ ከጎራው ዘለቅ በሉና ባሩዱን መትረየሱን ስታንበለብሉት እንያችሁ?

ድል-ቁርሱ ነን ያላችሁ - እስቲ እንያችሁ!
እናቶች የሚጸልዩላችሁ - እስቲ እንያችሁ!
ለዚህች ሀገር ነፍሴን እሰጣለሁ ያላችሁ - እስቲ እንያችሁ!
ከጎራው ዘልቃችሁ - እስኪ እንያችሁ?
እናንተ ሩቅ ሆናችሁ - ቅጽል ስም እያወጣችሁ
በል,በለው ማለት - መች ነው የሚሰለቻችሁ!?

እናንተ በፍጹም አትሞቱም! በሲቹዌሽን ሩም ናችሁ! የደሃው ልጅ ግን ለእናንተ ይሞትላችኋል! በጦር ሜዳው ላይ ነው! ይሰማል ወይ? ያዋጣል? የማን ነፍስ ከማን ያንሳል? የነፍሳችን ዋጋ እንደ ውሎ አበል ተመን ይውጣላትማ!? አለዚያ ንቅንቅ የለም! ሳይስማሙ የምን ንቅንቅ ነው?!! አቦ ጉራጌ! አቦ ጉራጌ! አቦ ጉራጌ!

ያገሩ ጎጆ መርዶ ሆኖ፣ በእናንተ ቤት ድግስ ነው! ሙሉ ነው! እንዲህ ነው ወይ ሀገር? እንዲህ ነው ወይ መደመር? መደመሩ አንዳችን አፈር፣ አንዳችን ችግኝ፣ አንዳችን ጌቶች፣ አንዳችን አደግዳጊዎች፣ አንዳችን መከራና ገፈት ተቀባዮች፣ አንዳችን በአክሮባቲስት ሹፌሮች ተዝናኞች.. የምንሆንበት ነበር ማለት ነው? እንዲህ ነው እንዴ የመደመር ስሌቱ?

አንድ ቀን የዚህ ወደሞት የምትማግዱት የሚሊየኖች ድሆች እናቶች እንባ ጎርፍ ሆኖ ይወስዳችኋል! አንድ ቀን በደሙ የምትነግዱበት የዚህ ምስኪን ህዝብ ሀዘን ደራሽ ሆኖ ቤታችሁ ይገባል! ጠራርጎም ይወስዳችኋል! አንድ ቀን በአክሮባቲስት ሹፌሮች እየተነዳችሁ በህዝቡ ፊት ትቀበራላችሁ! አንድ ቀን በቁማችሁ እኩያው ልትሆኑት ባልፈቀዳችሁትና በናቃችሁት ህዝብ ፊት፣ በሞታችሁ እኩያ ሆናችሁ ታሸልባላችሁ!

እስከዚያም የድሃው ደም በእጃችሁ ላይ ነውና የህሊና ሠላም አይኖራችሁም! በሄዳችሁበት ትደነግጣላችሁ! ጥላችሁን የማታምኑ ተቅበዝባዦች ትሆናላችሁ! አምላክ ይፋረዳችኋል! የምስኪኑ ነፍስ ይፋረዳችኋል! ከታሪክና ከፈጣሪ ፍርድ የሚያመልጥ ማንም የለምና፣ የኢትዮጵያ አምላክ ብድራችንን ይክፈለን እንደየሥራችን፣ እንደየግፋችን መጠን! መንግሥቱ ነዋይ እንደዚያ ነበር ያለው!

ዛሬ ሀገሬ ብሎ ወጥቶ በየተራራው ክልትው ብሎ የቀረውን፣ ለገዢዎች እርካብና መንበር ሲባል እርስ በእርሱ የተላለቀውን፣ የተማረከውን፣ የተሰቃየውን፣ የአሞራ ራት የሆነውን፣ አስታዋሽ ያጣውን - የሚያምነው የቸገረውን ምስኪኑን እውነተኛ ሀገር-ወዳድ ኢትዮጵያዊ ወገናችንን - የኢትዮጵያ አምላክ በሚያውቀው እርሱ ብድራቱን ይመልስለት!

ሲያጌጡ ይመለጡ!!፤ የመዋቢያ ኬሚካሎች ኬሚስትሪ:“ሲያጌጡ ይመለጡ” የሚለው አባባል መነሻው ምን እንደሆነ ባላውቅም የዘመኑን መዋቢያና ጣጣውን በደንብ ይገልጽልኛል በማለት ለዛሬው መጣጥፌ ርእ...
07/06/2022

ሲያጌጡ ይመለጡ!!፤
የመዋቢያ ኬሚካሎች ኬሚስትሪ
:
“ሲያጌጡ ይመለጡ” የሚለው አባባል መነሻው ምን እንደሆነ ባላውቅም የዘመኑን መዋቢያና ጣጣውን በደንብ ይገልጽልኛል በማለት ለዛሬው መጣጥፌ ርእስ አድርጌዋለሁ፡፡ አባት አደር እውቀቶችን በተግሳጽ፣ በምክርና በአባባሎች ሰፍረው
እናገኛቸዋለን፡፡ ግን ምን ያህል እየተማርንባቸው እንደሆነ አይታወቅም፡፡ “ሲያጌጡ
ይመለጡ” ዓይነት አባባሎች የተወለዱት ከኑሮና ከልምድ
እንጅ ቤተ ሙከራ ውስጥ በተደረገ ፍተሻ አይደለም፡፡ አንዳንዴ ከቤተ ሙከራ ወለድ
እውቀቶች በልምድና በኑሮ የተገኙት ሚዛን ሊደፉ ይችላሉ፤ ከልምድ የተገኙ
እውቀቶችና አባባሎችን ብንፈትሻቸው በውስጣቸው የያዙት አስተምህሮት የአንድ
መጽሀፍ ይዘትን ሊያስከነዱ ይችላል፤ እነዚህ ትምህርት አስተላላፊ አባባሎች መናቅ
የለባቸውም፡፡...........................
“ውበት እንደተመልካቹ ነው” ይባላል፡፡ ለውጫዊ ውበት ሊሰራ ይችላል፡፡
ለውስጣዊ ውበትስ? የሰው ልጅ ብዙውን እድሜውን የሚያጠፋው በውበት ዙሪያ
ሲሽከረከር ያመስለኛል፡፡ በአጠቃላይ ስነ ጥበብ የተባለው የእውቀት ዘርፍ
መነሻውም መድረሻውም ውበት ይመስለኛል፡፡ ሌላው ቀርቶ ስለውበት የተቀነቀነውን
ሙዚቃ ብቻ ብንወስድ ነገሩን ፍንትው አድርጎ ያሳየናል፤ ሥነ
ስዕልም እንዲሁ፡፡ ውበት(መዋብ) የተፈጥሮ ህግ የሆነ ያህል ይሰማኛል፡፡ የሰው
ልጅ ውበትን ለምን አጥብቆ ፈለጋት? የሚለው ጥያቄ በጣም አከራካሪ ሊሆን
ይችላል፡፡ ለእኔ ግን ውበት (ለመዋብ መጣር) ተቀራኒ ጾታን አማሎ በቁጥጠር ስር
ለማዋል የሚደረግ ጥረት ይመስለኛል፤ የሚፈልጉትን ምርኮኛ ለማድረግ፡፡
የውበት ኀይል በጣም ብርቱ ክንድ አለው፡፡ ይህንን ብረቱ ኀይል በሰዎች ቀርቶ
በእንስሳትም ላይ መመልከት ይቻላል፡፡ እስኪ ወፎችን እንውሰድ፤ ወንድ ጣዖሶች
(ፒኮኮች) እንደዚያ ባለ ውብ ላባ የሚጀቦኑትና አስደማሚ ዳንስ የሚያሳዩት ተቀራኒ ጾታን ለማማለል ነው፡፡ የመስቀል ወፍም ያንን አስደማሚ ቀለም የሚላበሰው ሴቷን ለማማለል እንጅ እሱማ ያው ሁሌም የህል ጥራጊ ሲለቅም የምናየውና “ድንቢጥ” ብለን የምንጠራው ወፍ መሰለኝ፡፡ መዝሙር ለመለማመድ ብለው አንጎላቸውን የሚያሳድጉ
ወፎችም እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ይህ ባለ መረዋ ድምጽ ወንድ ወፍ ምኞቱ ሰምሮለት
ዝማሬውን ተምሮ የሚፈልጋትን አጋሩን አግኝቶ እነሆ በረከት ካለ በኋላ ያ
የተከመረ የአንጎል ህዋስ (ኒውሮን) ሙሽሽ ብሎ ይጠፋል፤ አላማውን ከፈጸመ
በኋላ ትርፉ ሃይል መሻማት ስለሚሆን መትፋት ነበረበት፡፡ ይህን የመሰለውን የተፈጥሮ
ህብር ማየት አንዱ የውበት አካል ነው፡፡ እንዴት ደስ ይላል፡፡..............................
ምን አለፋችሁ፣ መዋብ አንዱ የተፈጥሮ ግዴታ ነው ብለን እንለፈው፡፡ ከመሰረቱ ተፈጥሯዊ አመጣጡን ብናየው፣ ውበትን መፈለግ ማለት ተጣማጅን አሳምኖ አሸናፊ በመሆን ዘርን
ለማስቀጥል የሚደረግ ግብግብ ነው፤ የስሜት ሃይልን ማለዘብ እንዳለ ሆኖ ማለቴ ነው፡፡
ዛሬ ስለመዋቢያ ኬሚካሎች ብንነጋገር አይከፋም ብየ አጀንዳ ይዤ መጥቻለሁ፡፡ በእርግጥ በአንዳንድ ነገሮች ላይ ለመጻፍ ማሰብ ይጨንቃል፡፡ ስለ መዋቢያ ኬሚካሎች ለመጻፍ መሞከር አንዱ ነው፡፡ መጠጥ ፣ ማጨስ፣ ጫት መቃም በጣም የሚጎዱና ለጤና
የማይበጁ ደርጊቶች ናቸው፡፡ ቢሆንም፣ ብዙ ሰዎች ህይወታቸውን የሚመሩበት
ሥራ የተመሰረተው በእነዚህ ጎጂ ነገሮች ዙሪያ መሆኑም ግልጽ ነው፡፡ የነዚህን ሰዎች
ሥራ ማውገዝ ደግሞ የሆነ ጥሩ ስሜት የማይሰጥ ነገር አለው፡፡ ከዚያም ባሻገር
የዛሬውን ጽሁፌን ያነበበ/ ያነበበች የውበት አድናቂ “ጽረ- ውበት አመለካከት ነው”
ማለታቸው አይቀርም፡፡ “ለመሆኑ፣ ውበት ማለት ኬሚካል መለቅለቅ ነው ወይ?
የሚሉም ይኖራሉ፡፡ ለማነኛውም እንወያይበት፡፡ እኔ ልቀጥል፤ መዋብ ከምንም
በላይ ጠቀም ያለ አንጡራ ይጠይቃል፡፡ መዋብ ውድ ሸቀጥ ነው፡፡ እኔን ገንዘቡ
ብዙም አያሳስበኝም (እነ እጹብ ድንቅ ይጻፉበት)፡፡ እኔን የሚያሳስበኝ ገንዘቡ ሳይሆን
የጤናው ጉዳይ ነው፡፡ ለአውሮፓ ቀዝቃዛ አየር ጸባይ ተብለው የተመረቱ የመዋቢያ
ኬሚካሎች ወደ አፍሪካ ሞቃታማና ጸሐያማ ቦታዎች መጥተው የብዙ አፍሪካዊያን
እህቶቻችንን ፊት እንዳበላሹ በአንድ አለማቀፍ መጽሄት ላይ ማንበቤን በደንብ
አስታውሳለሁ፡፡ የመጽሄቱ ዘገባ በኬንያውያን ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያሳይ ነበር፡፡
የብዙዎችን ሴቶች ፊት ከጥቅም ውጭ ሆኖ በፎቶ የተደገፈ መረጃ ተመልክቻለሁ፡፡
ይህ ክስተት ለእኔ የሚያስደንቅ አይደለም፤ ለምን ብትሉኝ ኬሚካሎች ምን ሊሰሩ እንደሚችሉ በመጠኑ አውቃለሁና፡፡ በአጠቃላይ የመዋቢያ ቁሳቁሶች የከንፈር ቀለምን ጭምሮ ከብዙ ኬሚካሎች የሚሰሩ ሸቀጦች ናቸው፡፡ የመዋቢያ ሸቀጦች ብዙ
ነገሮችን እንዲያሟሉ ይጠበቃል፤ ይህ ደግሞ በጣም ብዙ ኬሚካሎችን እንደግባት
እንዲጠቀሙ ያደርጋል፡፡ በአብዛኛው (በሙሉም ማለት ይቻላል) ኬሚካሎች
የጉዳታቸው መጠን ቢለያይም ጎጅዎች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡................... .. ......
በመዋቢያ ሸቀጦች ውስጥ ለምን ብዙ ኬሚካሎች ይሰገሰጋሉ? ዋና ዋናዎቹን
እንመልከት፡፡
1. ለቀለም፤ “ኮስሜቲክስ” አምራቾች ለቀለም ሲባል ኮል ታር(coal tar) የተባለውን
የነዳጅ ዝቃጭ፣ ክሮሚየም ኦክሳይድ፣ የአሉሚኒየም ዱቄት፣ ማንጋኔዝ፣ አይረን
ኦክሳይድና ማይካ የተባሉትን ኬሚካሎች በብዛት ይጠቀማሉ፡፡ እነዚህ ኬሚካሎች ደግሞ አደገኞች ናቸው፡፡ ወደ ቆዳ ስር ከገቡ ቢያንስ አለርጂ ያስከትላሉ፡፡ ቀይ ሥር አንዱ ከእጸዋት የሚገኝ ሲሆን ሌላው ደግሞ ደርቆ ከተፈጨ ከትኋን መሰል ነፍሳት(cochineal insect) የሚገኝ ቀለም ነው:: ከሁሉም በብዛት ጥቅም ላይ የሚውለው “ከሬንጅ” የሚሰራው “ኮል ታር” ሲሆን ወደ ቆዳ ውሰጥ ሰርጎ ከገባ የቆዳ ካንሰር ማስከትል እንደሚችል የታወቀ ነው፡፡..............
2. ማጣበቂያ፤ ማጣበቂያ በደንብ ጥቅም ላይ የሚውለው ለከንፈር ቀለም ነው፡፡
ለከንፈር ቀለም መስሪያነት የጉሎ ዘይትና ሰም በደንብ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ እነዚህ
ኬሚካሎች መዋቢያው በውሃ አንዳይሟሟ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ የዘይቱ ጥቅም
የከንፈር ቀለሙ አንዳይደርቅና ወፈር ብሎ የማላጠቅ ባህርይ አንዲኖረው ሲያደርግ፤ ሰሙ ደግሞ ቀርጹን አንዳይለቅና ልክክ እንዲል ያደርጋል፡፡ ሌላው ከንፈር ቀለም ላይ የሚጨመር ኬሚካል “ኢስተር” የተባለው ኬሚካል ውህድ ነው፡፡ ይህ ኬሚካል የከንፈር ቀለሙ አብረቅራቂ ቀለም እንዲኖረውና ከንፈር ላይ ልክክ እንዲል ይረዳዋል፡፡ እነዚህ
ኬሚካሎች ቢያነስ ቡጉር ነገር ማስከተላቸው የማይቀር ነገር ነው፡፡.......
3. ማወፈሪያዎች፤ እዚህ ላይ አንድ ኬሚካል ላንሳ፤ በንግድ ስሙ “talc” ይባላል፡፡ ይህ
ኬሚካል “ማግኔዚየም ሲልኬት” ነው፡፡ ዋና ጥቅሙ ውሃ መምጠጥ ነው፡፡ በፊት
ላይ በሚደረጉ በዋቢያ ኬሚከሎች ላይ የሚደረግበት ምክንያት በውሃ ወይም
ከሰውነት በሚወጣ ላብ “የተጨመረውን ውበት” እንዳያበላሸው ነው፡፡
በተጨማሪም ኬሚካሉ ልስላሴ ያላብሰል፡፡ ይህ ኬሚካል በጣም አደገኛ
ኬሚካል ነው፡፡ ወሃ የመምጠት ጸባዩን መነሻ በማድረግ ለልጆች የሽንት መምጠጫ(ዳይፐር) መስሪያነት በብዛት ይውላል (ይውል ነበር)፡፡
በተደረገ ጥናት፣ ይህን ኬሚካል የጠጠቀሙ ሴት ኅፃናት ከመቶው 75 እጁ በዘር ፍሬ
ማመንጫ(ኦቫሪ) ካንሰር ተይዘው እንደተገኙ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡...................
4. የጸሐይ መከላከያ (sunscreen) እነዚህ ኬሚካሎች አደገኛ የፀሐይ ጨረርን ለመከላከል ተብለው የሚጨምሩ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ኬኪካሎች ዋናው “ፓራ አሚኖ ቤንዞይ አሲድ” (para aminobenzoic acid) ነው፡፡ ይህም ቢያነስ በቀላሉ አለርጅ
ይፈጥራል ብለን እንለፈው፡፡...............
5. ጥሩ ማእዛ እንዲሰጡ የሚጨመሩ፤ ለዚህ ስራ የሚጨመሩት ኬሚካሎች ለጥሩ ሽታ ብቻ ሳይሆን የተሰራው “ኮስሜቲከስ” በተፈጥሮው መጥፎ ሽታ ቢኖረው ያንን ለማጥፋት
የሚውሉ ሽታ አምካኝ ኬሚካሎች ጭምር ናቸው፡፡ እዚህ ላይ የምናየው ትግል
ምርትን ለመሸጥ እንጅ ለጤና እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡............
6. ጀርም ገዳዮች፤ እነዚህ ኬሚካሎች ካልጨመሩ ባክትሪያዎችና ፈንገሶች ቦርቀው የሚያድጉበት ምግብ ፊት ላይ እንደተመረገላቸው አስቡት፡፡ ለዚህ ደፈግሞ “ፓራቤን” የሚባሉት ኬሚካሎችና የሬሳ ማድረቂያ (ፎርማሊን) ፍቱን ስለሆኑ
ይጨመራሉ፡፡........
7. ለብዙ ጊዜ ሳይበላሽ እንዲቆይ የሚያደርግ ከሚካል፤ የመዋቢያ ሸቀጡ እድሜ
አራዛሚዎች(preservatives) ዋና ጥቅም ብዛት ያለው ኬሚካል ሲገናኝ ሌላ
ውህድ በመፍጠር የምርቱን ቀለም እንዳያጠፋ ታስቦ የሚጨመሩ ናቸው፡፡
ይህ ሁሉ የኬሚካል ክምር በማስታወቂያ ሃይል እየተነዳ “በውበት” ስም አማሎ
የተፈጥሮ ውበታችንን እንዳይነጥቀንና ጤናችን እንዳያውክብን በጥንቃቄና
በባለሙያ (የቆዳ ስፔሻሊስት ሐኪሞች) እርዳታ መዋብና ኢላማን መምታት ይቻላል፡፡
ሌለው ደግሞ ወደ እናት ተፈጥሮ መመለስና የእናቶችን የቆየ እውቀት መበርበሩ
ሳይጠቅም አይቀርም፡፡ በአጠቃላይ፣ ዘመኑ በዘፈቀደ የሚኖርበት ዘመን አይደለምና
የምናደርጋቸውን ነገሮች በጥንቃቄና በእውቀት እናደርግ፡፡
ለውስጣዊ ውበት ትልቅ ትኩረት በመስጠት፤ “ሕይወትን ቀለል አድርጎ መኖር የብልሆች ምርጫ ነው” ይባላል፡፡
ውስጣዊ ውበት ምንይሆን?

አማራ ግን ምን ሆኖ ነው?Where is my Romantic Ethiopia😀🙃🙂ይቺ የካናዳ 10 ዶላር ላይ ያለችው የ Violla Desmond ትባላለች። የንግሥት ኤልሳቤጥ የልጅ ልጅ የመሠለችው...
02/06/2022

አማራ ግን ምን ሆኖ ነው?

Where is my Romantic Ethiopia😀🙃🙂

ይቺ የካናዳ 10 ዶላር ላይ ያለችው የ Violla Desmond ትባላለች። የንግሥት ኤልሳቤጥ የልጅ ልጅ የመሠለችው ካለ፣ ይቅርታ አይደለችም።

ልክ በአሜሪካ የአውቶቡስ መቀመጫዋን ለነጭ ተሳፋሪ እንድትለቅ እንደተገደደችውና አልነሳም በማለቷ የአሜሪካን የcivil rights movement እንዳቀጣጠለችው Rosa Parks እንደተባለችው ጥቁር አሜሪካዊት ሴት የመሠለ ታሪክ ያላት ጥቁር ካናዳዊት ነች።

ቪዮላ ዴዝሞንድ ያኔ ነጮች ብቻ መግባት በሚፈቀድላቸው ትያትር ቤት ውስጥ ገባች። ትያትር ቤት ሲባል ጨለማ ነው፣ ማንም አያየኝም ብላ መሠለኝ። እና በመሐል ለዕረፍት መብራቱ ቦግ ሲል ወንበር ይዛ ተመቻችታ ዱቅ (ወይም ጉብ) ብላለች።

ከዚያ ወንበርሽን ልቀቂ ብቻ አይደለም፣ ትያትር ቤቱንም ልቀቂልን ተብላ በትህትና ተጠየቀች። እሷ ግን ለጥበብ ሟች መሠለችኝ። ትያትሩን ሳልጨርስ ንቅንቅ አልልም አለች። ተነሺ። አልነሳም። ሰይጣኗን ቀሰቀሱባት። ጩኸትና መጓተት ሆነ። ፖሊስ ተጠራ።

ፖሊስ ገላጋይ አልነቀረም ያኔ😀🙃 እና "ውሻ፣ ምን አገባት ከሰው እርሻ" ብለው እያላጉ አስወጧት። እና ታላቁ የህይወት ዘመን የሰው ልጆች እኩልነት ትግል በምድረ ካናዳ ተቀጣጠለ።

በነገራችን ላይ በዚህ ብር ጀርባ ደግሞ የሚገኘው ምስል፣ በካናዳ ዊኒፔግ የተገነባው እጅግ ትልቁ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ተቋምና ሙዝየም ፎቶግራፍ ነው።

በዚህ መልክ፣ ካናዳዎች በቀደመ ታሪካቸው የተዛቡ የዜጎች ግንኙነታቸውን ዕውቅና ሰጥተው ስህተቶቻቸውን ለማረምና የሁሉም ዓይነት ዜጎች መብቶች የተከበሩባትን multicultural nation ለመፍጠር አጥብቀው ይተጋሉ።

አንዳንዴ ሳስበው፣ ምናለበት እኛም ሀገር አማራ ከእኛ እኩል ትያትርቤት አትገቢም ብሎ የከለከላት አንዲት ኦሮሞ ታጋይ ብትገኝና ፎቶዋን ለጥፈን በተገላገልን እያልኩ እፈነድቃለሁ like a fantasy!

ወይ አማራ ከኛ ጋር አቶቢስ አትሳፈሪም ብሎ የአለከላት ትግሬ፣ ወይ አደሬ፣ ወይ የሆነች የጭቁን ብሔር ታጋይ ብናገኝ፣ በቃ ታሪኳን እያወሳን፣ ፎቶዋን እያስተዋወቅን፣ የተዛባ ግንኙነታችንን እንደ አሜሪካኖቹና ካናዳዎቹ እያረምን፣ የሆነ romantic የእርቅ story መፍጠር እንችል ነበር...😀🙏💔

ምን አሰብክ? ምን አሰብክ? የእኛ የአማራ የበላይነት እኮ በእንደዚህ ዓይነት ታሪኮች ተደግፎ ቢቀርብልን አምነን እንቀበለውና እናርመው ነበር! ችግሩ የኛ ሀገር የበላይ ዘር አማራ፣ እንደ ፈረንጆቹ ጨክኖ ሌላውን ዘር ከትምህርት ቤት አልከለከለም።

የአማራ ገርነት የሚያናድደው እንደ ፈረንጆቹ ከትያትር ቤት በባርነት የገዛቸውን ዘሮች እየለቀመ አላስነሳም። ከቅኔ ቤት አላባረረም። ከስፖርት አላገለለም። ከሥልጣን አላባረረም። ከንጉሣን ጋብቻና አምቻ አልነቀለም። ከፊልም ቤትና ጭፈራ ቤት ዘር እየመዘነ መንቅሮ አላስወጣም።

አማራ ጅል ነው። ምናለ ቢያንስ እንደ ፈረንጆቹ የበላይነት ያላቸው ሕዝቦች፣ ትንሽ ተንከሲስነት ኖሮት ዘመናቱን ቢዘልቅና፣ አሁን ባረምነው?! የምሬንኮ ነው። አሁንኮ ስም ብቻኮ ነው የተረፈው አማራ። የቀደመው አማራ ስም ነው የተረፈው። ያሁኑ አማራ ደሞ ኩነኔው ነው የደረሰው።

አሜሪካኖች ከነጮች መኪና ውረጅ ስለተባለችዋ ሮዛ ፓርክ እያነሱ ሲተርኩ፣ እኛ ጋር ያቺ ሮዛ ከየት ትገኝ? እኛ ሀገርኮ አቶቡስ ሀ ብሎ የጀመረው በማሞ ካቻ እና በአመዴ ለማ ነው። አሁን ምን ተብሎ ይነገራል የኛ ሀገር ታሪክ?

ባልበላበት፣ ባልዋለበት፣ አይጥ በበላ፣ እርሱ በዳዋ የተመታ እጀ-ሰባራ ሕዝብ! አይ አማራ! ይህን ስል ማን ትዝ አለኝ? የጂጂጋው ነቄ ፖለቲከኛ ሙስጠፌ አህመድ!! ሙስጠፌ የተናገራት ቃል እስካሁን ውስጤ ቀርታለች። እንዲህ ነበር ያለው ሙስጠፌ እንደ ዘበት፦

"በነገራችን ላይ እኛ ሶማሌዎች የአማራና
የሌላውን ኢትዮጵያዊ የጨቋኝ-ተጨቋኝ
ትርክት የማንቀበለው ለፖለቲካ ፍጆታ ብለን
ሳይሆን፣ በትክክልም እውነት ስላልሆነ ነው፣
አማራ ብቸኛ ጨቋኝ ብሔር ሆኖ ሌላውን
የገዛበት ታሪክ የለም፣ ፍፁም የተሳሳተ
ትርክት ነው፣ የማንቀበለውም እውነት
ስላልሆነ ነው!"

ምን ላርግህ ወንድሜ ሙስጠፌ! አላህ ጨምሮ አብዝቶ ይስጥህ!

ለዛሬ አበቃሁ።

በኢትዮጵያ የተሠራ - ታላቅ የሰው ልጆች ተስፋ!"A great hope made in Ethiopia."ሰዎች በራሳቸው እጅ ስለራሳቸው የፃፏቸውን ወይ በሌሎች ሰዎች እጅ የተፃፈላቸውን የህይወት ታ...
31/05/2022

በኢትዮጵያ የተሠራ - ታላቅ የሰው ልጆች ተስፋ!

"A great hope made in Ethiopia."

ሰዎች በራሳቸው እጅ ስለራሳቸው የፃፏቸውን ወይ በሌሎች ሰዎች እጅ የተፃፈላቸውን የህይወት ታሪክ ማንበብ የሚመስጠኝ ሰው ነኝ። እና የብዙ ሰዎችን የህይወት ታሪክ ባነበብኩ ቁጥር የተረዳሁት (እና ሁሌ የሚደንቀኝ) ሁሉም ሰው የሚጋራው አንድ እውነት አለ።

አንድ ወጥ ተደርጎ በሚነገር የአንድ ሰው አንድ የህይወት ታሪክ ውስጥ በአንድ መፅሐፍ ሽፋኖች ሥር ባንድላይ የተጠረዙ ብዙ አጫጭር ታሪኮች የመኖራቸው እውነት። ይህ ታዲያ ምኑ ይደንቃል?

የሚደንቀውማ የሰው ልጅ ጥልቅ መሆኑን ስለሚነግርህ ነው። እያንዳንዱ ሰው በትንሽ በትንሹ እየተቆነጠረ ጊዜና ቦታ እየተጠቀሰ የሚነገር ተሰፍሮ የማያልቅ ታሪኮች ባለቤት መሆኑን ትረዳለህ።

በአንድ ወጥ የሚመስል የአንድ ሰው አንድ ማንነት ውስጥ ዘርፈ ብዙ ማንነቶች እንደሚገኙ ታስተውላለህ። እና በቃ የሰውን ግለ ታሪክ አንብብ - የሰው ልጅ ጥልቅ መሆኑን ብቻ ሳይሆን የሰው ህይወት እልፍ ቅኔ መሆኑን ታምናለህ።

ዛሬ ግለ ታሪካቸውን የማነሳሳላችሁ አፍሪቃዊ ሰውም ከላይ ከጠቀስኩት የሰው ልጆች ሁሉ የወል እውነት የተለየ ማንነት የላቸውም።

ባለታሪኩን ዓለም ሁሉ ያውቃቸዋል። በህይወት ዘመናቸው ረዥም የመከራ መንገድን በፅናት የተጓዙ የሰላማዊ ትግል መሪ ናቸው። የእርቅና የሠላም አባት ናቸው። የፅሞናና የሚዛናዊነት ተምሳሌት ናቸው። ባጭሩ የሚታወቁበት ጉልህ ማንነት ይሄው ነው።

ሙሉ ስማቸው ኔልሰን ሮሊህላህላ ማንዴላ። የውሸት ስማቸው ዴቪድ ሞትሳማዪ። የፍቅር መጠሪያቸው ማዲባ።

ቅድም እንዳልኩት - የሰላምና የእርቅ አባት የሆኑት ማዲባም - ይህን ከህልፈታቸው በኋላም በጉልህ የሚታወሱበትን ሠላማዊ የህይወት ጉዞ እና ማንነት ወይም ሰብዕና በአንድ ጀምበር ይዘውት አልተወለዱም።

በእርሳቸው አንድ ህይወት ውስጥ ጎልቶ የወጣውን ትልቁን ፍፁም ሠላማዊ ማንነት ተጋግዘው የገመዱ ብዙ ትላልቅና ትናንሽ የህይወት ሰበዞች አሉ።

እኚህ ሰው ብዙ ትምህርቶችን ከደጓም ከአስከፊዋም ህይወት ቀስመው ከራሳቸው ጋር እርቅን ያወረዱ፣ የጠብ መንገዳቸውን በእርቅ መንገድ የቀየሩ ናቸው።

በቅድሚያ ከማንም በፊት ራሳቸውን ያሸነፉ፣ ከዚያም ህዝባቸውን ያሸነፉ፣ ከዚያ ደግሞ ዓለምን በፍቅር መንገዳቸው ያሸነፉ ናቸው።

የብዙ የህይወት ፈለጎች፣ የብዙ የተረገጡ ዳናዎች፣ የብዙ የታለፉ ወቅቶች... በያቅጣጫው እንደሠማይ ከዋክብት የተበተኑ የብዙ ጉልህና የብዙ ደብዛዛ ዱካዎች ባለቤት ናቸው። አስደናቂ እውነተኛ የታሪክ ባለገድል - አስደናቂ የሠላም አርበኛ ናቸው።

እኚህ አስደናቂ የሠላም ባለታሪክ - በአንድ ወቅት በህዝባቸው ላይ የደረሰው በደልና መድልዎ ትዕግስታቸውን አስጨርሷቸው ነበር።

የህዝቤ ጭቆና በሰላምና በክርክር፣ በጩኸትና በግርግር ብቻ አይፈታም ብለውም በሠላሙ መንገድ ተስፋ ቆርጠው "ኡምክሆንቶ ዊ ሲዝዌ" (በምህፃረ ቃል፦ "ኤም ኬ") በመባል የሚታወቀውን የታጠቀ አሸባሪ ቡድን የመሠረቱ ቁጡ ሰው ነበሩ።

እኚህ የእርቅ ሰው በጅምራቸው ላይ የሽምቅ ውጊያ ቡድን ሲመሰርቱ ወታደራዊ ሥልጠናና ዕውቀት እንደሚያስፈልጋቸው በማመን ስለጦርነት ስልትና ወሳኝ የውጊያ ብልቶች በማብራራት በዓለም ዝነኛ የሆነውን የካርል ቮን ክላውሶቪችን "ኦን ዎር" የተሰኘ ጥራዝ ለወራት ሲያጠኑ የቆዩ ሰው ነበሩ።

ማጥናት ብቻም አይደለም። ድንበሮችን አቆራርጠው ወደ ነፃይቱ አፍሪቃዊት ሀገር ወደ አቢሲኒያ በጃንሆይ መልካም ፈቃድ በመምጣት በአዲስ አበባ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ከተማ ይፍሩ በእንግድነት በክብር ተቀብለዋቸዋል።

ኔልሰን ማንዴላ ኮልፌ የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ካምፕ ማሰልጠኛ ውስጥ ገብተው በሌ/ኮ ወንድይሁን በፍቃዱ አማካይነት የጦር መሣሪያ ፈትቶ መግጠምን፣ የጠብመንጃ አተኳኮስን ተምረዋል።

ፈንጂ መቅበርና ማምከንን፣ በአስቸጋሪ ጫካ ውስጥ ለቀናት በፅናት በህይወት መሰንበትን፣ የሽምቅ ውጊያ ስልቶችን፣ የአካል ብቃትን፣ ወታደራዊ ማጥቃትና መከላከልንም ሁለት ወራት ሙሉ ሳይታክቱ ተምረዋል።

እኚህ የሰላም አባት ማዲባ - በኢትዮጵያ ቆይታቸው ወቅት - የሽምቅ ተዋጊዎችን አደረጃጀት፣ መሪነት፣ ስነልቦናና የሚከተሉትን ፀረ-ቅኝግዛት የነፃነት ርዕዮተ-ዓለም በተመለከተ ልምድ ቀስመዋል።

የዚያኔ ኮ/ል የነበሩት (ኋላ ጄነራል የሆኑትና በጃንሆይ ላይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ያሤሩት) ሌ/ኮ ታደሰ ብሩ በግርማዊ ጃንሆይ በመምህርነት ተመድበውላቸው የውትድርና ጥበብን ከፀና የፀረ-ፋሺስት ትግል ልምድ ጋር ትምህርት ሰጥተዋቸዋል።

እኚህ የሰላም መሪ - ኔልሰን ማንዴላ - በደብረዘይት ቆይታቸው - ቁጥራቸው 500 የሚሆኑ የነፃይቱ ኢትዮጵያ የክብር ዘበኛ ሥልጡን ወታደሮች በኢትዮጵያዊ ሻለቃ እየተመሩ ከነጠብመንጃቸው፣ ከነመለዮአቸውና ባንዲራቸው ጋር "ሁሉም እንደ አንድ ሰው ሆነው አስገራሚ ሰልፍ እየረገጡ በክብር ሲያልፉ" ተመልክተው ያደረባቸውን የመንፈስ ቅናትና ምኞት በግለታሪክ መፅሐፋቸው ይገልፃሉ።

በጥቁር አፍሪቃዊ የጦር አበጋዝ የሚታዘዝ ጥቁር አፍሪቃዊ ጦር ተመልክተው በአምሮትና በሕልም.. በአፓርታይድ የዘር ጭቆና ሥር ለወደቁ አፍሪካውያን ወገኖቻቸው ያንን ተመኝተው ምራቃቸውን መዋጣቸውን ይገልፃሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኢትዮጵያዊ አውሮፕላን አብራሪ እየተንሳፈፈ ከካርቱም አዲስ አበባ ሲያደርሳቸው ሲመለከቱ ከአድናቆት ብዛት የሚያደርጉት ጠፍቷቸው "ጥቁር ሰው ፓይለት መሆን ይችላል ማለት ነው?" ብለው በግርምትና በምኞት ህልም መያዛቸውን ይናገራሉ።

ኮ/ል ታደሰ በሥጦታ ያበረከቱላቸውን ሽጉጥና 200 ጥይት በዝናር ታጥቀው (አዝለው) - (ጃንሆይ የለገሷቸውንም) ብዙ ሺህ ፓውንድ በጉያቸው አጭቀው - ለሽምቅ ውጊያ ቆርጠው - ከአዲስ አበባ ካርቱም መግባታቸውን - ሳይደብቁ በመፅሐፋቸው የፃፉ የውጊያ ባለታሪክም ናቸው።

እንግዲህ ትርክቴ ረዝሟልና እዚህ ላይ ልቋጨው። ይሄንን የመሰለውን የሰው ልጅ ዘርፈ-ብዙ የህይወት ጉዞ ነው በመነሻዬ ላይ እጅግ ያስገርመኛል ያልኩት።

ከዚህ የኔልሰን ማንዴላ ታሪክ በላይ የሰው ልጅ እምቅ ኃይሉ ተሰፍሮ የማያልቅ፣ ጥልቅ፣ ህይወቱም ተፈትቶ የማያልቅ ቅኔ መሆኑን የሚመሰክር ህይወት ከወዴት ይምጣ?!

የእውነት ነው የምለው። ይሄ የሰው ልጅ ነገር እጅግ ያስገርመኛል። በዓለም ስለታወቀ የሠላማዊ ትግል መሪ፣ ታሪኩ ህያው ሆኖ ስለሚነገር አንድ የሠላምና የእርቅ ጀግና ግለታሪክ ትንሽ ጠለቅ ብለህ ስታነብ - መራር የነውጠኝነትን፣ የጦርነትን፣ የአክራሪነትን፣ የካራና የፍላፃን የኃይል መንገድ ታሪክም - ከዚያው ከራሱ የሰላም ሰው ህይወት ጋር አብሮ ተዳብሎ ታገኘዋለህ።

እና እየገረመህ ታነበዋለህ። የሠላም አባትነት ጉልህ መታወቂያው በሆነ በአንድ ሰው የህይወት ታሪክ ውስጥ፣ ሌሎች ብዙ ጉልህ አጫጭር የጦርነት ታሪኮችን እንደምታገኝ፣ አምነህ ትቀበላለህ።

እና ... በመጨረሻም ዛሬ ጦር ሲሰብቁ በምትመለከታቸው ሰዎች ላይ ተስፋ ያድርብሀል። ምን የሚል ተስፋ??

- እነዚሁ ዛሬ ጦር ሲነቀንቁ የማያቸው ያገሬ ሰዎች ራሳቸው - ነገ ደግሞ (እንደ ማንዴላ!) - የሰላም አርበኛ - የእርቅ ፈጣሪ - የመቻቻል ሐዋርያዎች ቢሆኑስ? የሚል ተስፋ!!

ቢሆኑስ? እንደ ማንዴላ የመሰለውን ሰው ታሪክ አነብብና፣ ማንዴላ ከፈንጂ ማጥመድና ማፈንዳት ወጥቶ የሠላምና የእርቅ ሃዋርያ ሊሆን ከቻለ፣ እኛስ መሐል... ያንን የመሠለ የሠላም ቀንዲል የማናገኝበት ምን አንዳች ምክንያት አለ? - "ምንም የለም!" - የሚል ትልቅ ተስፋ አሳድራለሁ።

ከእርስበርስ ጥላቻና ጦርነት ወጥተን፣ እናት ሀገራችንን ኢትዮጵያን፣ ለኑሮ የምትመረጥ፣ ለትውልዶቿ ብሩህ ተስፋን የምትዘራ - ታላቅ አፍሪቃዊት የሠላምና የስኬት ተምሳሌት እናደርጋት ዘንድ - ፈጣሪ አምላክ ጥበቡንና ተስፋውን በልባችን ውስጥ እንዲዘራልን - ከልብ - ከልብ - ተመኘሁ።

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!

በእምነት፣ በተስፋ፣ በፍቅር!!

አንድ አቁማዳ . . . !አንዴ በጎንደር እያለሁ ነው። ጥቂት ዓመታት አልፈውታል። በዕድሜ የገፉ አዛውንት (ባልና ሚስት) ቤተክርስትያን ተጠግተው ሰው ያለውን እየመፀወታቸው ይኖራሉ። ከስንት ...
01/05/2022

አንድ አቁማዳ . . . !

አንዴ በጎንደር እያለሁ ነው። ጥቂት ዓመታት አልፈውታል። በዕድሜ የገፉ አዛውንት (ባልና ሚስት) ቤተክርስትያን ተጠግተው ሰው ያለውን እየመፀወታቸው ይኖራሉ። ከስንት አንዴ፣ በተለይ ቅዳሜ ዕለት፣ ተያይዘው አጎንብሰው እያዘገሙ በተከራየሁበት ግቢ አልፈው ወጥተው ያገኟት በአቁፋዳቸው ይሸክፉና ወደ ደጀሰላማቸው ይመለሳሉ።

ሲመለሱ ግን ዳገት ነው። እና እኔ ወዳለሁበት ግቢ ጎራ ይሉና ለመኪና ማቆሚያ ተብሎ በተሰራው ሰፊ ኮንክሪት ወለል ላይ ጥላውን መርጠው አረፍ ይላሉ። የእኔ ክፍል ግራውንድ ላይ ነውና መሥኮቴ ሥር ባለው የውጪው ደፍ (የሲሚንቶ እርካብ) ላይ ነው የሚቀመጡት። ከዚያ ውሃ ጠምቶናል አጠጡን ይላሉ።

ከውሃ ሌላ የሚጠይቁት ነገር የለም። ሳንቲምም ብትሰጣቸው አሻፈረኝ የሚሉበት ጊዜም ነበር። "ግዴለም ልጀ ያዘው ይጠቅምሀል፣ እግዜር ይስጥህ"። ወይ "ሳንቲሙ ይቅርብንና፣ ባይሆን ዳቦ አለህ? ደጀሰላም ተካፍለን ስለምንበላ ዳቦ ካለህ ይዘን እንሄዳለን.. አሁን ግን ውሃው ብቻ ይበቃናል! እንዳጠጣኸን እግዜር ያጠጣህ ልጄ! እርሱ እሺ ይበልህ!"

ወይ ጉድ። ትንሽ ሥጦታ። ያውም የእግዜሩን ውሃ። እና ብዙ ምርቃት። ብዙ አይፈልጉም። እና ብዙ ምርቃት ያዘንቡብሀል። ምን ዓይነት መታደል ነው? ያለህን ሳትሰስት መስጠት! ሌላውም ነዋሪ እንደኔው ፈጥኖ ይታዘዛቸዋል። ማንም ቀድሞ ያገኛቸው ሰው ውሃ ከዚያው ከፊታቸው ካለው ቧንቧ ተቀድቶ ይሰጣቸዋል።

ጠጥተው፣ አረፍ ብለው፣ ሰዉን መርቀው ይሄዳሉ። ቢያንስ በሳምንት ሁለቴ። ይህን አይቼ አንድ ቀን ደስ የሚልና ወገቡ ቀጠን ያለ (ስለዚህ በገመድ ቢጤ አስሮ ለመያየሚያመች) YES የሚባለውን ፕላስቲክ የውሃ ኮዳ ለሁለቱም አንድ አንድ ሰጠኋቸው። በዚህች ይዛችሁ ሂዱ ብዬ። በጣም ደስ አላቸው። ምርቃት አዘነቡልኝ። በመጡ ቁጥር ሳንቲም ጣል አደርግላቸዋለሁ። ግን ብዙም ደስታ አያሳዩም። በውሃዋ ዕቃ ግን በጣም ተደሰቱ። እየተሳሳቁ ሁሉ ነው የወጡት።🙂

ታዲያ ቀናት አልፈው በአንዱ ቀን ለፊልድ ሥራ ከባልደረቦቼ ጋር ወጥተን በጎጃም በኩል እያለፍን ታታሪ የገጠር ወጣቶች እጃቸው ያፈራላቸውን ሁሉ በመንገድ ዳር አውጥተው፣ ለአላፊ መንገደኛ ይሸጣሉ። በቆዳ የተሰፋ በርኩማ መቀመጫ። በቆዳ የተለበጠ አገልግል። በሥጋጃ የተሰፋ የራስ ቆብ። በግሩም ጅማት መያዣው የተጠለፈ የፈረስ ጭራ። ወፍራም በእጅ የተሸመነ የሥጋጃ ምንጣፍ። እና ላያቸውን ሥጋጃ የተሰፋላቸው ጠንከር ያሉ በግምት 1 ሊትር የሚይዙ የፕላስቲክ የውሃ ኮዳዎች።

ይሄ የመጨረሻው ድንገት ቀልቤን ሳበው። ተጠግተን ዋጋ ስንጠያይቅ የውሃ አቁማዳዋን ሥጋጃ ጥቅም ብጠይቅ ሥጋጃውን ካረጠብከው ውሃውን ያቀዘቅዘዋል። ፍሪጅ ማለት ነው ተባልኩ። በዚያ ላይ ሥጋጃው ለውሃ መያዣዋ ጠንካራ ማንጠልጠያም ይሰጣታል። የኛ ሀገር ሰውኮ ዕድሉ አልተመቻቸለት ሆኖ ነው እንጂ፣ ባለችውና ሰው በሚወስድለት አቅም ብዙ ነገር ሲፈጥር ታገኘዋለህ።

ሁለት አቁማዳዎች ገዛሁ። በርካሽ። ካልተሳሳትኩ አንዱን በ10 ወይ በ15 ብር። አብረውኝ ያሉት ሳቁ በእኔ ለየት ያሉ ፍላጎቶች። አንዱንስ ደግሞ ለማን ነው? እያሉ። አብሬ ሳቅኩ። በሳምንቱ ይመስለኛል ቤቴ ደርሼ የገዛሁትን ስጦታ ልሰጥ ጆሮዎቼን በመስኮቴ አሻግሬ ቀስሬ መጠባበቅ ጀመርኩ።

አነዚያን ሁለት አዛውንት የኔቢጤዎችን እየተጠባበቅኩ ነው። አንዳንዴ ደግሞ ስትቸኩል፣ ስትጓጓ፣ የሚርቅብህ፣ የሚሸሽህ ነገር አለ። ቀናት አለፉ። ተፈላጊዎቹ ሁለት አዛውንት አልመጡም። በመጨረሻ አንድ ቀን አባትየው ብቻቸውን፣ እያዘገሙ አንከስ እንደማለት እያሉ፣ ወደ ግቢያችን ገብተው ከመሥኮቴ ሥር አረፍ አሉ። ሲመጡ ቤቴ በመገኘቴ ደስ አለኝ።

ሁለት ብርጭቆ ይዤ ወጥቼ፣ ወደ ቧንቧው እየተራመድኩ ለሠላምታ ዘወር ብል፣ እናትየው (ሴትዮይቱ) የሉም። እንግዳ ነገር ሆነብኝ። አዲሱ ቤቴ ዓመት ሞላኝ ሳውቃቸው። ተነጣጥለው አያውቁም። "እግዜር ይስጥህ ስለማሰብህ" ብለው ተቀበሉኝና በሚንቀጠቀጥ እጃቸው፣ ከውሃው ጋር ከጉሮሯቸው አልወርድ ብሏቸው ታገሉ። እና ጠጡ እንደምንም።

በትዕግሥት ጠብቄ መጠጫውን ተቀብዬ፣ "ጠብቁኝ አንዴ አባባ" ብዬ ተመለስኩና በመጋረጃ መስቀያው ላይ ያንጠለጠልኳቸውን ባለሥጋጃ የውሃ መያዣ ኮዳዎች ይዤላቸው ወጣሁ። ገና ሲያዩት በተቀመጡበት ደረቅ ካብ ላይ ባሉበት ፊታቸው በደስታ በራ። እና ወዲያው መልሶ ጭልም አለ። ፊት አሳባቂው። አይሸሽግም። ቦግ። ደግሞ እልም። ዓይኖቻቸው እንባ አቀረሩ። ምን ሆነዋል? ያላስተዋልኩ መሠልኩ።

"ከየት አግኝተሃቸው ነው ልጄ?"

"ከጎጃም ማንኩሳ ላይ ዲያቆኖች ሰርተው ሲሸጡ አግኝቼ ነው፣ ለእርስዎና ለእማማ ይሆናሉ ብዬ አመጣሁዋቸው" አልኳቸው። በዲያቆናት እጅ መሠራቱ፣ ከደብረሊባኖስ እንደሚገኘው የባልጩት ሻማ ማብሪያ፣ አንዳች የቅድስና ምንጭ አላብሶ ደስ ያሰኛቸው ይሆናል ብዬ እዚያው በቆምኩበት የመጣልኝ ውሸት ነበር።

ግን ውሸቴ ያዘልኝ መሠለኝ። በዲያቆን የተሠራ መሆኑ ይሁን፣ ወይስ ከማንኩሳ መጣ ሲባል፣ ብቻ ደስ ይላቸዋል ብዬ እንዳሰብኩት ደስ ተሰኙ። ነገር ግን እንባቸው መውረዱን ቀጥሏል። ማቆሚያ አጣ። ተጨነቅኩ። እስኪረጋጉ ወደቤት ገብቼ ትንሽ ቆየሁ። እና ከሆቴል አስጠቅልዬ ያመጣሁትን አነስ ያለ የሥጋ በርገር እንደተጠቀለለ ይዤው ወጣሁ።

እሳቸው ዳቦ ወይ እንጀራ ቢሆን ይመርጣሉ። ግን ሌላ የምሠጣቸው ነገር አልነበረኝም። "አባባ ይህችን ይውሰዱና ይቀማምሷት፣ በጣም ጣፋጭ ናት፣ ይወዷታል" ብዬ እየሰጠኋቸው።

"ምንድነው ግን ይሄ ልጄ? እስቲ ፍታውና ልየው፣ በዚህ ነው የምይዘው፣ መጠቅለያውን አልፈልገውም.."

አሉኝ። የተፈጨ ሥጋ በዳቦ መሆኑን ተናግሬ ስከፍተው፣ የተለቀለቀው ሊጥ የመሠለ ማዮኔዝና ከቻፕ፣ እላዩ ላይ ከነተበተነበት የተቃጠለ የድንች ጥብስ ጋር ሲያዩት ባንዴ ዘገነናቸው።

"አዬ ልጄ፣ ፈእኔ መች እወድ ብለህ እንዲህ ዓይነቱን የፈረንጅ ነገር፣ ይቅርብኝ ግዴለም ልጄ። እግዜር ይስጥህ፣ ይኸው በቂ አለኝ ዛሬ እግዚአብሔር ይመስገን!"

አሉኝ። በምፅዋት የሞላ አቁፋዳቸውን እያሳዩኝ። ተመለስኩና የምንተ ዕፍረቴን ሳንቲም ቢጤ አመጣሁ። እሱንም በጄ አላሉም። በግድ ሸጎጥኩላቸው። በመጨረሻ አንደኛውን ባለሥጋጃ ኮዳ መለሱልኝ።

"ይህኛው ብቻ ይበቃኛል ልጄ፣ ይኸንን ለራስህ ያዘው። ይጠቅምሀል። ለእኔ ይሄ ይበቃኛል"

"አባባ፣ ሌላኛውንኮ ያመጣሁት ለእማማ ነው። ለመያዝ አላመቸዎትም? ውሃ ያልቀዳሁበትኮ እንዳይከብድዎት አስቤ ነው፣ ወይስ አልወደዱትም አባ?"

"በተሰቀለው። ምኑን አመጣህብኝ። ይህን የመሠለ ሥጦታ። ከስንት ሀገር አክብረህ አምጥተህ? እንዴት አልወደው? ግን ልጄ... እሷንኮ በዪህ ሰሞን ሳይታሰብ አጣኋት። አንድ መፅናኛዬን ሞት ነጠቀኝ። ሞተችብኝ ልጄ።"

ብለው እንባቸው መንታ መንታ ሆኖ ከደከሙ ዓይኖቻቸው ዝርግፍ ዝርግፍ አለ። ክው ብዬ ቀረሁ። በማየው ሀዘን ሆዴ ተንቦጫቦጨብኝ። እሳቸውን ሳይ አሳዘኑኝ። እንባ ተናነቀኝ እኔንም።

"ምነው? ምን ሆነው ሞቱዘ? አዪዪዪዪ..."

"እየውልህ ከዚች ባጃጅ ከሚሏት ተሳፍረን፣ ከዪህ ከሥላሴ ቁልቁለቱ ላይ ስንደርስ፣ ተገልበጥነ። ሲል ነው መቼም ቀኗ ደርሶ። ባለ መኪናይቱም ዕፀድቅ ብሎ በነፃ ካላደረስኳችሁ ብሎ፣ ወርዶ ደግፎ አስገብቶን ነበር እየሄድን... ። ፈርዶበት ነው እሱም። ተገለበጥን.. እሱም እኛም። ጥቂት ቀናት ቆይታ አረፈች እሷ። ያማት ነበር። አቅምም የላት። በግድ ነው ለመላወሱምኮ። ይኸውጨብቻዬን ለእግዜሩ ጥላኝ ሄደች። ሐሙስ 12ቷ አለፈ።.."

በትካዜ በተሞሉ ዓይኖቻቸው የዳማከሴውን ተክል እያዩ ነው የሚያወሩኝ። አንዴ እናትየው ዳማከሴውን ሲያስፈቅዱኝ ዋናውን ቤት የተከራየችው መልካም ሴት ደርሳ፣ በፈለጋችሁ ሰዓት ሁሉ ማንንም ሳታስፈቅዱ ቆርጣችሁ ውሰዱ" ብላ ፈቅዳላቸው ነበር። አንዳንዴ ውሃቸውን ከጠጡ በኋላ ከውስጥ ሆኜ በመስኮቴ አያቸዋለሁ። እናትየዋ አንድ የዳማከሴ ዝንጣፊ ሳይይዙ አይወጡም። እስቅ ነበር። የሀበሻ ነገር! ምች የመታው ሰው እያፈላለጉ ይሆን የሚሰጡት በየሳምንቱ? እያልኩ።

አሁንሴትዮይቱ የሉም። አዛውንቱ ከቅጠሎቹ ይልቅ ጭራሮው በበዛው ዳማ ከሴ ላይ ዓይናቸውን ተክለው ተከዙ፣ ሌላ እንባዎች። ውሃና እንባ ተቀላቀሉብኝ። መፅናኛ የለም። ሰይጣንን በዳማከሴ ታባርረዋለህ። የልብ ሀዘንን ግን ምን ታደርገዋለህ? ቃላት አልነበሩኝም።

"አይዞዎት አባባ። ሞት ለሁላችንም አይቀርም። መበርታት ነው። የሚያግዝዎት አለ አሁን? ወይስ ብቻዎን ነዎት?"

"ቤተስኪያን ተጠግተን ደጀሰላም ስለምንኖር ምዕመኑም ቤተስኪያኗም ሰንበቴውም ሁሉም ያግዙኛል። ብዙ መነኮሳትኮ አሉ እዚያ ተጠግተው የሚኖሩ። ዕድሜያቸው የገፋ እንደኔው። ብዙ ነን። ብቻዬን አይደለሁም። ብቸኝነቴ በእሷ ነው። አለፈችብኝ እንጂ ብቻዬን ጥላኝ። ለሌላው ምንም አልሆን ልጄ።..."

ወይ ጉድ! ይቺ ዓለም። አይ ሰው። አንዳንዴ መፍትሄ የማልፈይድለትን ነገር ባላይ፣ ባልሰማ እመርጣለሁ። እንደዚህ። ለመሆኑ ልጆች የሏቸው ይሆን? ትውልዳቸው፣ ታሪካቸው፣ የየት ሀገር ሰዎች ይሆኑ? ህይወታቸውን በየት በኩል ዞረው፣ በምን በኩል አቋርጠው ይሆን ለዚህ የበቁት? አላውቅም። ለመጠየቅም ደፍሬ አላውቅም። ዝም ብዬ ተክዤ ቀረሁ።

"ታዲያ ይያዙታ ኮዳውን ለመቀየሪያ እኮ ይሆንዎታል። ይያዙት ሁለቱንም ግዴለዎትም።"

"አሄ ልጄ። እሷን ያስታውሰኛል እንጂ.. ከአንድ በላይ ምን ያደርግልኛል ብለህ? ግድየለህም እግዜር ይስጥህ! አውሎ ያግባህ ልጄ!"

ብለው እየመረቁኝ፣ የሰጠኋቸውን ሥጦታ መልሰው ሊሰጡኝ እጃቸውን ዘረጉ። ሁለት ያለው አንዱን ያካፍል ይላል መፅሐፉም። ካለቻቸው፣ ከተቀበሏት፣ ሁለት አቁማዳ፣ አንዷን መልሰው ሰጡ። ከዚህ ሌላ ፅድቅ ምንድነው? ከዚህ በቀር ሌላ ፅድቅ ምናለ? በበቃኝ ኑሯቸው እየተገረምኩ፣ እየተደመምኩ፣ በአክብሮት እጅ ነስቼ የዘረጉልኝን አቁማዳ መልሼ ተቀበልኩ።

ትንሽ ሲተካክዙ ቆይተው፣ አቁማዳቸውን ውሃ ሞልተው፣ አዟዙረው እያዩዋት፣ ውሃቸውን ተጎንጭተው፣ አንድ እግራቸውን እየጎተቱ ተነስተው ሄዱ። ባንዴ ጉስቁል እርጅት አሉብኝ። እርጅና። ሀዘን። መለየት። አጋር ማጣት። ጤና ማጣት። ሲደራረቡ ከዕድሜ በላይ ያስረጃሉ። እኚህ ፊቴ የቆሙ ጠንካራ አዛውንት፣ ገንዘብ ማጣታቸውን እንኳ የሚያስቡት አይመስለኝም።

አንዳንዴ የገንዘብን የመግዛት ኃይል ወይም ጥቅም ያልተረዱት እስኪመስለኝ ድረስ እኮ ነው ከገንዘብ ጋር ላለመነካካት ሲጥሩ የሚያቸው። ወይስ ሲቆርቡ "ገንዘብን ላልነካ..." የሚል መሐላ ይኖረው ይሆን? ስለዚህ ጉዳይ ጨዋ ነኝ። አንዳችም ነገር አላውቅም።

አንዳንዴ ሽማግሌ ናቸው፣ ደስ ይበላቸው ብለህ፣ አዲስ ያልታጠፈች 5 ብር አውጥተህ ልትሰጣቸው ስትል፣

"አዬ ልጄ ለምን ትቸገራለህ? ምን ይሠራልናል ብለህ ነው እኛ? አንተው ያዘው። ይጠቅምሀል።"

ነው የሚሉት። የቀረቻቸውን ዕድሜ፣ ከፈጣሪ ተጠግተው፣ ከእኩዮቻቸው ጋር በደጀሰላም እየኖሩ፣ ለዙረትም ለወሬም ለጥንካሬም የምትሆናቸውን ዞር ዞር ብለው ከየሰዉ ደጃፍ ያገኟትን ምፅዋት ይዘው ይመለሳሉ። እና ፈጣሪ የዘከራቸውን ከሌሎች ጋር ተካፍለው ተመስገን ብለው ያድራሉ።

ለመኖር ብዙም ጉጉት የላቸውም። ለመሞት የሚያስመኝ የማይቋቋሙት ምሬትም ደግሞ የለባቸውም። በቀላሉ። ከብዙ የቁስና የገንዘብ አምሮቶች ውጭ ሆነው። ቀላልና እርካታ የጎበኘው ህይወትን ይኖራሉ። መኖር ነው ትልቁና ብቸኛው የህይወት እሽክርክሪታቸው ማጠንጠኛ። ተመስገን ብሎ መኖር። ከዚህ ውጪ የሚፈልጉት ነገር አልነበረም።

ሁለቱም ቆብ ደፍተዋል። ቁርባን ይሁን ምንኩስና ወይስ ብህትውና ወይ በልማድ የሚያጠልቁት አላውቅም። በመጨረሻ አንደኛቸው ሞተው፣ ሌላኛቸው ብቻቸውን ሲቀሩ ሳይ። ልቤን ነኩት። ለአፍታ፣ ምናለ ሳይነጣጥላቸው አብሮ ቢወስዳቸው? ብዬ፣ በፈጣሪ እጅ በተፃፈች የፊልም ስክሪፕታቸው ውስጥ ጣልቃ መግባት አማረኝ።

ሽማግሌው በዲያቆን እጅ ተሠራች ያልኳቸውን አዲሷን ባለሥጋጃ የውሃ መጠጫቸውን አነግበው። በሌላ ጎን የማትለያቸውን እርጅት፣ ውይብ ያለች የቆዳ ማህደር ያላትን ዳዊታቸውን ከወገባቸው ላይ ታጥቀው። በአንገታቸው ካሰሯቸው ትላልቅ መስቀሎች የሚወጣ አንዳች ድምፅ በግቢው ላይ እያንሿሹ፣ አጎንብሰው፣ ምርኩዛቸውን አስቀድመው እየተፍገመገሙ፣ ግቢውን ለቅቀው። ከብዙ ምርቃቶች ጋር። ተለዩኝ።

እርሳቸው ከባለቤታቸው ጋር በግቢው በመጡ ቁጥር በሚያርፉባት ደፍ ፊትለፊት። በመስኮቴ ሥር ያሉትን። ግንቡን ታክከው የበቀሉትን ሰፋፊ የግራዋ ቅጠሎች። ባጭሩ ፈክተው ያለብዙ ድምቀት ከሚከስሙት የዳማከሴው ጥቃቅን አበቦች ጋር አዳብዬ እያየሁ። እንደ ሀውልት ባለሁበት ቆሜ ቀረሁ።

ከተማዋን ልሰናበት የቀሩኝ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ነበሩ። ከዚያ በኋላ አባባ አልተመለሱም። ግድ የሆነብኝን ዕቃዬን ጭኜ፣ የቀረኝን አከፋፍዬ፣ ወደ አዲስ አበባዬ ሄድኩ። ለጎረቤት ከበዛ አደራ ጋር እርሳቸው ከመጡ ከፍራሾቼ መሐል አንዲቱን ከነምንጣፏ እንዲሰጧቸው፣ (ቤታቸው ድረስ እንዲያደርሱላቸው፣ ከሳንቲም ጋር) ትቼላቸው ወጣሁ። ከአራት ወይ አምስት ወራት በኋላ በሥራ ጉዳይ ተመልሼ ሄድኩ።

የቀድሞ ጎረቤቶቼን ብጠይቅ እኚያ አዛውንት መጥተው እንደማያውቁ ነገሩኝ። ወደ ሥላሴ ወጥቼ ልጠይቅ አስቤ ነበር። ወላውዬ ተውኩት። መጨከን አቃተኝ። ሌላ ሞትን መስማት አሳቀቀኝ። ባገኛቸውም አልረባቸውም። "ካሉ፣ የተጠጉት እግዜር ይሁናቸው" ብዬ ሥራዬን አጠናቅቄ በሣልስቴ ተመለስኩ።

እነዚያ ሁለት አዛውንት በህይወት ባይኖሩም ብዙ ነገራቸው እስካሁንም በውስጤ ይኖራል። ከህይወት ብዙ ሣይጠይቁ፣ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው፣ ፈጣሪን እያመሠገኑ፣ በወገናቸው ቸርነት፣ በደስታ ረክተው የሚኖሩ ሰዎች ነበሩ። እውነት ግን ለሰው ልጅ ከዚህ በቀር ምን አለ?

አንድ ወዳጄ ነበር "ዋናው ምን አገኘህ? ሳይሆን ደስታን አገኘህ ወይ? ነው የምትጠየቀው ህይወትን ኖረሀት ጥለሀት ልትሄድ ስትል!" የሚል እየደጋገመ። እናማ... ኖረህ ኖረህ በመጨረሻ የሚቀርብልህ "በኖርካት፣ ባለህ፣ በእጅባለችው ህይወት ደስተኛ ነህ?" ነው ጥያቄው።

እነዚያ ሁለት አዛውንት ግርም የሚሉኝ ለዚህ ነው። ባጭሩ እነዚያ ሰዎች - ብዙዎቻችንን በተፀናወተን፣ "ሁሉን ነገር የማግበስበስና ባለንም ያለመጠርቃት" ፀረ-ደስታ ደዌ የተለከፉ ሰዎች አልነበሩም። ከጠኔ ተላቅቀው፣ በቀላሉ ረክቶ የመኖርን ደስታ የሚቋደሱ ምስኪን ነፍሶች ነበሩ።

ህይወት ብዙ ዓይነት ናት። ብዙዎች ቁስን ተጠምተው ኖረው ይሞታሉ። እነዚያ ሁለት ሰዎች ግን ከውሃ በቀር የሚጠሙት አልነበረም። ያንንም ከእግዜሩና ከደጋጎች ያገኙታል። ያም ህይወት ነው። ጥማቸውን አርክተው የሚኖሩበት ደስተኛ ህይወት። ሰዎቹ አልፈዋል። ሳስበው። እነዚህ የእኔቢጤ ወገኖቼ። ባላሰብኩት መንገድ። በልቤ የማይለቅ ሥፍራን ይዘው በትውስታዬ አሉ።

አንዲቱ ባለሥጋጃ የውሃ ኮዳ በየሄድኩበት በግድግዳዬ የማንጠለጥላት፣ በመደርደሪያዬ ላይ የማኖራት ነች። የተለያየ አጋጣሚ የፈጠራቸው ታሪኮችን ከጀርባቸው የያዙ ለየት ካሉ ብቻዊ ቅርሶቼ መሐል፣ አንዷ ልዩ መታሰቢያዬ ነበረች። አቁማዳዋ የሞቱ መነኩሴ ድርሻ ነች። በፍቅር ሰጥቼ፣ በፍቅር የተሰጠችኝ የሰው ድርሻ።

ባለድርሻዋ የሉም። አቁማዳ ተካፍለን የተለያየነው አዛውንትም በህይወት የሉም። ነገር ግን ቀና ብዬ ያቺን የውሃ አቁማዳ ባየሁ ቁጥር፣ የሁለቱ የህይወት ባለፀጎች አንዲት ምርቃት ትዝ ትለኝና፣ እንደ ብርሃን ፀዳል ሆና ቤቴን ትሞላዋለች። ልቤን ታሞቀዋለች።

"ልጄ፣ አውሎ ያግባህ!
ሠላም አውሎ ያግባህ ልጄ!
በሄድክበት ባለፍክበት ሁሉ
አውሎ ያግባህ ፈጣሪ አምላክ!
ሶስቱ ሥላሴዎች አውለው ያግቡህ ልጄ...!"

ሆሆይ! ወቸ ጉድ። እኮ ነው የምለው! ይሄንን ዓይነት ደግ ምርቃት የሚያጎርፍልህ ከእኛ ከሀበሾች ውጭ ያለ ሌላ ሕዝይኖር ይሆን? አላውቅም። ሌላውም የየራሱን ምርቃት የሚያጣ አይመስለኝም። የእኛ ግን እጅግ ግርም ይለኛል። ምን ዓይነት ደግ ምርቃት ነው ያላቸው?

Address

Bahir Dar To Gondar Road
Wereta

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Woreta Senior Secondary & Preparatory School posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The School

Send a message to Woreta Senior Secondary & Preparatory School:

Shortcuts

Share

Category