21/08/2022
በጋብቻ ውስጥ ለሚፈጠር ፈተና የሚጸለይ ጸሎት
(ለባለትዳሮችና ለሌሎችም ይደርስ ዘንድ ሼር አድርጉት)
t.me/abizeeotc
በስመ አብ በስመ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን።
የሕይወቴ መሪ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በጋብቻ እንድኖር የፈቀድህ አንተ ነህ። በጋብቻ ውስጥ ደስታና ተድላ ብቻ የሚያጋጥመኝ ይመስለኝ ነበር። ተስፋም አደርግ ነበር። ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አሁን ግን የጎጆዬ ምሰሶ ዘምሟል የቤቴም የፍቅር ድባብ ተገፏል።
በእኔና በባለቤቴ መካከል ልዩነት ተፈጥሯልና። አቤቱ አምላኬ ሆይ ለጊዜው የችግሮቹ መነሻና ምክንያት ለኔ ቢሸሸግም ለአንተ ግን ስውር አይደለም። አንተ ሁሉን ታውቃለህና በትዳሬ ጉዳይ የማቀርብልህን ልመና ብሶትና ሐዘኔን ታዳምጠኝ ዘንድ በድንግል ማርያም እማጸንሃለው።
ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ክፉውን በደግ ለመመለስ ቁጣን በዝምታ ለማሳለፍ እንድችል እንደ ኢዮብ ትዕግስትን ስጠኝ። በፍጹምነት በመታዘዝ የታማኝነትንም ፍቅር በመግለጥ የባለቤቴን ልብ ወደ ደህና መንገድ ለመመለስ አብቃኝ።
ከመጥፎ ሰዎች ምክርና በክፉ መንፈስ ከመመራትም ጠብቀኝ።
ለመለያየታችን ምክንያት የሆኑትን ነገሮች ሁሉ አስወግድልን።
ከእኔና ከልጆቻችን ፍቅር ይልቅ ባለቤቴን የማረኩትን (የማረኳትን) ነገሮች ሁሉ በገናናው ስምህ ቆርጠህ ጣልልኝ ወደ ቀድሞ ልቡናውም(ልቦናዋም) መልሰው(መልሳት) አሜን።
ልጆቼን ያለ አባት እና እናት እንዳያድጉ እኔም የተቀደሰውን የኪዳንህን ቃል እንዳላማርር ታደርገኝ ዘንድ እማጸንሃለው።
ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አንተ ብቻ ለትዳሬ መስ።ካከልና መመለስ መፍትሔ መሆንህን አምኜ ቀርቤያለሁና ደካማነቴን አይተህ ራራልኝ። የአንተ እርዳታ የደረሰብኝን መከራ መጠን ያቀልልኝ ዘንድ ፈቃድህ ይሁንልኝ። ከተዘፈቅሁበት ከዚህ ክፉ ፈተና አውጥተህ የቀደሙ አንድ ለአንድ ተወስነው ኖረው ወደ አንተ የመጡ የአባቶቼን የቅዱሳንን ቤትና ትዳር እንደባረክህ እንዲሁ የኔን የደካማውን ልጅህን ትዳር ትባርክልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ።
የችግራችን መነሻ ለአንተ አለመታዘዝ ከሆነ ይቅር ብለህ እምነትን ጨምርልን። በቃልህ በረከት ፍሬ እንድናፈራ አድርገን። ባለን የምንረካ በሰጠኸን ጸጋ የምናመሰግን እንድንሆን አብቃን አሜን።
ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የትዳራችን መሠረት እና ጉልላት አንተ ሁን። መናወጽንም አጥፋልን። በዚሁ ምክንያት በሚፈጠረው ቀውስ ልጆቻችንን በሰቆቃና በችግር እንዳይኖሩ እንዳይጎዱ አድርግልን። መሐሪ ጌታ ሆይ ለውጣ ውረዳችን ሁሉ መፍትሔ ሰጥተህ አስውበህ እና አስተካክለህ በበረከትና በሰላም እንድንኖር አድርገን አሜን።
የአብርሃም እና የሣራን ቤት እንደባረክህ የዶኪማስንም ቤት በበረከት እንደሞላህ የእኛንም ቤት ባርክ ለዘለዓለሙ አሜን።
አቡነ ዘበሰማያት
በሰላመ ገብርኤል
ሰላም ለኪ
አቤኔዘር ዘተዋሕዶ ገፅ
አቤኔዘር ሚዲያ Abenezer Media