01/05/2026
ሎጂካል ኮሌጅ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጀመሪያ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 210 ተማሪዎች እሁድ ያስመርቃል።
ሎጂካል ኮሌጅ በመጀመሪያ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 210 ተማሪዎች መጪው እሁድ ሚያዚያ 25 ቀን 2018 ዓ.ም በሚዛን አማን ከተማ እንደሚያስመርቅ አስታውቋል።
ኮሌጁ በዚህ የምረቃ መርሃ ግብር በአካውንቲንግ፣ በማናጅመንት፣ በአግሪካልቸራል ኢኮኖሚክስ እና በማርኬቲንግ ማናጅመንት የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች የሚያስመርቅ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 5ቱ ተማሪዎች በኢኮኖሚ አቅም ማነስ ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል ያልቻሉና በኮሌጁ ሙሉ የነፃ ትምህርት ዕድል ተጠቃሚ የነበሩ ናቸው።
የኮሌጁ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መሰረት አስፋው እንደገለፁት፤ ኮሌጁ ትውልድን በዕውቀት የማነፅ ስራውን ከማህበራዊ ኃላፊነት ጋር በማጣመር ውጤታማ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም አቅም ደካሞችንና የኢኮኖሚ ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ከፍተኛ ትምህርት በማምጣት የነገ ብሩህ ተስፋቸውን እንዲያሳኩ የማድረግ ስራ በትኩረት እየተሰራበት መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው አብራርተዋል።
አቶ መሰረት አክለውም እንደገለፁት፤ ሎጂካል ኮሌጅ ከኢፌዴሪ ትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን እውቅና ባገኘባቸው በ5 የዲግሪ እና በ2 የዲፕሎማ የትምህርት ዘርፎች ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ስልጠና እየሰጠ የሚገኝ ተቋም መሆኑንም አብራርተዋል።
ኮሌጁ በትምህርት ስራ ላይ ከተሰማራበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ከ2,000 በላይ ብቁና በዕውቀት የሰለጠኑ ተማሪዎችን አስመርቆ ለሀገርና ለክልሉ ብሎም ለአከባቢው ልማት ማበርከት እየቻለ መሆኑንም አመላክተዋል።
ኮሌጁ እስካሁን ባደረገው የማህበረሰብ ተጠቃሚነት እንቅስቃሴ 37 ተማሪዎች በኮሌጁ ሙሉ የነፃ የትምህርት ዕድል አግኝተው ትምህርታቸውን በስኬት ማጠናቀቃቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።
ተቋሙ እነዚህን ተማሪዎች በነፃ አስተምሮ ከማስመረቅ ባለፈ ህይወታቸውን እንዲመሩና ራሳቸውን እንዲችሉ የስራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው በማድረግ ረገድ የበኩሉን ከፍተኛ ድርሻ ተወጥቷል።