31/01/2026
በወንዶች እጥረት ሳቢያ ማህበራዊ ቀውስ የገጠማት የአውሮፓ ሀገር
I በሰሜን ምስራቅ አውሮፓ የምትገኘው ላቲቪያ፣ በዓለም ላይ በሴቶች እና በወንዶች የቁጥር ስርጭት መካከል ከፍተኛ ልዩነት ከሚታይባቸው ሀገራት ቀዳሚዋ ሆና ተመዝግባለች። ይህ "የወንዶች እጥረት" በሀገሪቱ የፍቅር ህይወት፣ ትዳር እና ማህበራዊ መዋቅር ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ይገኛል።
እንደ መረጃዎች ገለጻ፣ በላቲቪያ ያለው የሴቶች ቁጥር ከወንዶች በ 8 በመቶ ገደማ ይበልጣል። ይህ ልዩነት በተለይ በወጣቱ እና በጎልማሳው የዕድሜ ክልል ላይ ጎልቶ የሚታይ ሲሆን፣ ሴቶች የሚመጥናቸውን የትዳር አጋር ለማግኘት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቸገሩ ይነገራል።
ችግሩ የወንዶች አለመወለድ ሳይሆን፣ በወንዶች ላይ የሚታየው የሞት መጠን መናር መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ለዚህም ዋና ዋና ምክንያቶች፦
ከልክ ያለፈ የአልኮል አጠቃቀም እና የሲጋራ ሱስ በላቲቪያ ወንዶች ዘንድ በስፋት መታየቱ። በልብ ህመም እና በድንገተኛ አደጋዎች የሚሞቱ ወንዶች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ። በሀገሪቱ ሴቶች ከወንዶች በአማካይ 10 ዓመታት ብልጫ ያለው የዕድሜ ጣሪያ አላቸው።
ማህበራዊ ተጽዕኖው
ይህ የስነ-ሕዝብ መዛባት ብዙ የተማሩ እና ስኬታማ የላቲቪያ ሴቶች የትዳር አጋር ለማግኘት ወደ ውጭ ሀገራት እንዲመለከቱ አስገድዷቸዋል። በተጨማሪም በሀገሪቱ ውስጥ ያለው የፍቺ መጠን እንዲጨምር እና የቤተሰብ መዋቅር እንዲላላ ምክንያት መሆኑ ይነገራል።
የላቲቪያ መንግስት የወንዶችን ጤና እና የአኗኗር ዘይቤ ለማሻሻል የተለያዩ ፖሊሲዎችን ቢቀርጽም፣ እስካሁን በቁጥሮቹ ላይ የታየ ትልቅ ለውጥ የለም።
source Fast Merege