02/02/2026
ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት እየተዘዋወረ የሚገኘው የኮሜዲያን ያሲኖ አጭር ቪዲዮ ቀልድ ቢመስልም የውስጡ መራራ እውነታ ግን እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ልብ የሚሰብር ነው. በቪዲዮው ላይ ግለሰቡ በለቅሶ የታጀበ ድምፅ "እየሞከርኩኝ ነው" እያለ ሲጮኽ መስማት ዛሬ ላይ እያንዳንዱ አባት, እናት እና ወጣት ያለበትን ስነ-ልቦናዊ ጫና ቁልጭ አድርጎ ያሳያል. የቤት ኪራይ, የልጆች ትምህርት ቤት እና የምግብ ዋጋ በየቀኑ መጨመር ሰውን "እየኖረ" ሳይሆን "እየሞከረ" ብቻ እንዲቀጥል አድርጎታል. በተለይም የልጆቹን መጫወቻ ላፕቶፕ ለመሸጥ ሲገደድ የምናየው ትዕይንት ወላጆች መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት ያላቸውን የመጨረሻ ተስፋ እስከመሸጥ የሚደርሱበትን መሪር እውነታ ይገልጻል. ይህ የ"እየሞከርኩኝ ነው" ጩኸት በሀገራችን ያለውን አስከፊ የኑሮ ውድነት እና ማህበራዊ ቀውስ የሚተርክ ድምፅ ነው. ብዙዎቻችን ሀገራችን ላይ ሰርተን ለመለወጥ ብንፈልግም ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎችና የደላላ ክህደቶች ተስፋችንን እያጨለሙት ይገኛሉ. ሆኖም በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ሆነው ለቤተሰቦቻቸው እና ለልጆቻቸው ተስፋ ለመሆን "እየሞከሩ" ላሉ ብርቱ ወገኖቻችን ሁሉ ትልቅ ክብር ይገባቸዋል.