28/03/2026
ቀን፦ ሀሙስ፣ መጋቢት 18፣ 2018 ዓ.ም
ለተወደደችሁ የቤተልሔም ዩዝ አካዳሚ የ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና ተፈታኝ ተማሪ ወላጆች በሙሉ፦
በመጀመሪያ ለልጆቻችሁ የትምህርት ስኬት የምታደርጉትን ያልተቆጠበ ድጋፍ እያመሰገንን የ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ (ሚኒስትሪ) ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎቻችን ለፈተናው በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ፣ በራስ መተማመናቸው እንዲጎለብትና አስፈላጊው የስነ-ልቦና ዝግጅት እንዲኖራቸው የሚያግዝ ልዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በዛሬው ዕለት መሰጠቱን በደስታ እንገልጻለን።
ትምህርት ቤታችን ካለው የተማሪዎች ውጤታማነት ራዕይ በመነሳት ከዚህ ቀደምም ተማሪዎቻችን ራሳቸውን ለከተማ አቀፍ ፈተና ዝግጁ እንዲያደርጉ የሚያስችሉ ተከታታይ ስልጠናዎች በትምህርት ቤቱ አስተዳደር በኩል ሲሰጣቸው መቆየቱ ይታወሳል። የዛሬው ስልጠናም የዚሁ ቀጣይነት አካል ሲሆን ውጤታማ ተማሪዎችን በማፍራት የረጅም ዓመት ልምድ ባለው በመምህር ናሆም ፍቅሩ አማካኝነት የቀረቡት ዓበይት ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፦
1. የዕድገት አስተሳሰብ (Growth Mindset) ግንባታ፦ ተማሪዎች ተግዳሮቶችን የመጋፈጥ፣ ጥረት ወደ ስኬት እንደሚመራ የማመን እና "አንጎል እንደ ጡንቻ ነው - ብዙ በተጠቀምንበት መጠን እየጠነከረ ይሄዳል" የሚለውን ጽንሰ-ሐሳብ እንዲረዱ ተደርጓል።
2. የግብ መተለምና የማቀድ ክህሎት (SMART Goals)፦ በቀሩት ጥቂት ወራት ሊተገብሯቸው የሚገቡ ግልጽ፣ ሊለኩ የሚችሉና በጊዜ የተገደቡ ግቦችን በማውጣት ለውጤት መስራት እንደሚገባቸው ስልጠና ተሰጥቷል።
3. ውጤታማ የጊዜ አጠቃቀም (Eisenhower Matrix)፦ ተግባራትን እንደ አስፈላጊነታቸውና አስቸኳይነታቸው ቅደም ተከተል በማስያዝ፣ መዘናጋትን በማስወገድ ጊዜን በአግባቡ ስለመጠቀም ተመክረዋል።
4. ውጤታማ የአጠናን ስልቶች፦ የፖሞዶሮ ቴክኒክ (በጥናት መሃል ዕረፍት መውሰድ)፣ አጫጭር ማስታወሻዎችን ማዘጋጀትና ጽንሰ-ሐሳቦችን በጥልቀት የመረዳት (Conceptualization) ዘዴዎች በዝርዝር ቀርበዋል።
5. የፈተና አሰራር ስልቶች (Exam-Taking Strategies)፦ ትዕዛዛትን በጥንቃቄ ማንበብ፣ የሰዓት አጠቃቀም እና ለከባባድ የምርጫ ጥያቄዎች የማስወገድ ዘዴን (Elimination techniques) ስለመጠቀም ተግባራዊ ምክረ-ሐሳቦች ተሰጥተዋል።
ስልጠናው በዚህ ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን በቀጣይም ተማሪዎቻችን የዝግጅት አቅማቸውን የሚያሳድጉበት፣ ፈተናውን በብቃት በመስራት የላቀ ውጤት ባለቤት እንዲሆኑ የሚረዳ ተጨማሪ ስልጠና የሚሰጣቸው መሆኑን በደስታ እንገልጻለን።
ይሁን እንጂ ፈተናው ከመቼውም ጊዜ በላይ እየቀረበ በመሆኑ በቀሩት ጥቂት ወራት ልጆቻችሁ በቤት ውስጥ ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ ልዩ ትኩረትና ድጋፍ እንድታደርጉላቸው በአፅንዖት እናሳስባለን። በተለይም በዚህ ወሳኝ ወቅት ተማሪዎች ትኩረታቸውን ከሚበታትኑ እንደ ማህበራዊ ሚዲያ (Facebook, TikTok, YouTube ወዘተ) አጠቃቀም፣ ከልክ ያለፈ ጨዋታና ፊልም ከማየት ራሳቸውን እንዲያርቁ እና ጊዜያቸውን ሙሉ በሙሉ ለጥናት እንዲያውሉ በቅርበትና በጥብቅ እንድትከታተሏቸው በአክብሮት እንጠይቃለን።
በመጨረሻም ልጆቻችን በስልጠናው ያገኟቸውን ፅንሰ-ሐሳቦች በተግባር እንዲያውሉና ለታላቅ ስኬት እንዲበቁ የእናንተ የቤት ውስጥ ክትትልና ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን በድጋሚ እናሳስባለን።
ከሰላምታ ጋር!
የትምህርት ቤቱ አስተዳደር
ለመልካም ሥነ-ምግባርና ለትምህርት ጥራት እንተጋለን!
We Strive for Virtue and Quality of Education!