25/08/2026
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚፈጸሙ የሙስና እና የስነ-ምግባር ግድፈቶችን ተጠያቂነትን በማስፈንና የአሰራር ሥርዓትን በመዘርጋት መከላከል እንደሚገባ ተጠቆመ።
በትምህርት ሚኒስቴር ከዩኒቨርስቲ የሥነ ምግባር መከታተያ ሥራ አስፈጻሚዎች ጋር ውይይት ተደርጓል።
------------------------ // -------------------------
(ነሐሴ 19/2018 ዓ.ም) የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኮራ ጡሹኔ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚፈጸሙ የሙስና እና የስነ-ምግባር ግደፈቶችን ለመከላከል ተጠያቂነትንና የአሰራር ሥርዓትን መዘርጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ተጠያቂነትንና የአሰራር ስርዓትን ከመገንባት ባሻገር በመዋቅር ፣ በአሰራርና በሰው ሃይል ስምሪት ነገሮችን መለወጥና ማስተካከል እንደሚገባ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከገንዘብና ንብረት ሙስና ውጪ የተማሪ ምደባን ጨምሮ ከዲጂታል ቴክኖሎጂ እድገት ጋር ተያይዞ ቀድሞ ያልነበሩ አዳዲስ የሙስና ስጋቶች መኖራቸውንም ክቡር አቶ ኮራ ጠቁመዋል።
በመሆኑም የዩኒቨርስቲ የሥነ ምግባር መከታተያ ሥራ አስፈጻሚዎች በምሉዕነት የህዝብና የጋራ ጥቅሞችን በማስቀደም የትምህርት ጥራት ጸር የሆነውን ሙስና እና ብልሹ አሰራርን በጽናት መታገል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር የሥነ ምግባር መከታተያ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ነጻነት ተክሌ በበኩላቸው ለአገራዊ የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን መከላከል ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
የሥነ ምግባርና የጸረ ሙስና ሥራ የአንድ የሥራ ክፍል ብቻ ኃላፊነት ሳይሆን በየደረጃው እስከ ትምህርት ተቋማት የሚዘልቅና የጋራ ኃላፊነትን የሚጠይቅ ተግባር መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የከፍተኛ ትምህርት የሥነ ምግባር መከተታተያ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በሥራ ቦታ ስነ ምግባር በግዢ ሂደት በንብረት አያያዝ አጠቃቀምና ማስወገድና በሌሎችም አገልግሎቶች ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን በማስፈን ኃላፊነትን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
የፌዴራል ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው አገራዊ የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ ቀጣይነት ያለው ተግባር በመሆኑ የዩኒቨርስቲ የሥነ ምግባር መከታተያ ሥራ አስፈጻሚዎች ተግባራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሀላፊዎቹ አክለውም የከፍተኛ ትምህርት የሥነ ምግባር መከታተያ ሥራ አስፈጻሚዎች የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታና በሌሎችም ሙስና የመከላከል ሥራዎቻቸው በእቅዶቻቸው የተቀመጡ ተግባራትን በቅንጅት፣ በጠንካራ ክትትልና በትጋት ለማስፈጸም ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የትምህርት ዘርፍ የሥነ ምግባር መከታተያ ሥራ አስፈጻሚ የመካከለኛ ዘመን ከ2019-2021 በጀት ዓመት ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
It was emphasized that measures should be taken to prevent corruption and ethical violations in higher education institutions by ensuring accountability and establishing clear procedures.
A discussion was held at the Ministry of Education with executive directors of university ethics and anti-corruption offices.