08/08/2026
ስለ አቂዳ ምን ያህል ያውቃሉ?
አቂዳ በአረብኛ ቋንቋ ትርጓሜ መሠረት መቋጠር፣ ማጠንከር የሚል ፍቺ ሲኖረው በኢስላም ምሁራን አተረጓጎም አኳያ ደግሞ ቀልብ እውነት ብላ የተቀበለችው፣ ነፍስ የተረጋጋችበት፣ ጥርጣሬ የማይከተለው ቁርጥ ያለ እምነት ማለት ነው። ማንኛውም እሳቤ በዚህ ልክና መጠን ከታመነበት ትክክል ሆነም አልሆነ አቂዳ በሚል ይጠራል። እንደ እስልምና አስተምህሮ አቂዳ የስራዎች ሁሉ መሠረትና መነሻ ነው። አንድ አካል የሚሰራው መልካም ስራ ተቀባይነት እንዲኖረው እና ምንዳን እንዲያስገኝለት የሚያደርገው መሠረታዊ እና ዋነኛው ነገር የተስተካከለ አቂዳ ባለቤት መሆን ነዉ።
ኢስላማዊ አቂዳ ምንድን ነው ?
ካለምንም አጋር ካልነበርንበት ያስገኝንን አምላክ ለርሱ ተገቢ የሆኑ ሀቆችን ለማንም ሳናጋራ መስጠት እና በሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ነብይነት ማመን ላይ ተመርኩዞ በቀሪዎቹ የዲን መሠረቶች እንዲሁም መርሆች ላይ በማመን የሚገነባ እምነት ነው። የጌታችን አላህ ትልቁ ሀቅ ደሞ ተውሒድ ነው። ተውሒድ ማለት አላህን በአምላክነቱ ፣ በጌትነቱ ፣ በስምና ባህሪያቱ ብቸኛ ማድረግ ሲሆን በእስልምና ምሁራን ዘንድ በ 3 ዋና ዋና ክፍሎች በመመደብ ተብራርቷል። ይኸውም ፦
1)
2)
3)
1) ተውሒድ አል ሩቡቢያ
አላህ (ሱ.ወ) አለምን በብቸኝነት ፈጣሪ ፣ አስተናባሪ ፣ ህይወት ሰጪ እና ነሽ ፣ ሲሳይን ለጋሽ ፣ የጠንካራ ሀይል ባለቤት መሆኑን ማረጋገጥ ማለት ነዉ ።
ጌታችን አላህ በተከበረው ቃሉ እንዲህ ይላል ፦
"አላህ ያ የፈጠራችሁ ፣ ከዚያም ሲሳይን የሰጣችሁ ፣ ከዚያም የሚገድላችሁ ከዚያም ህያው የሚያደርጋችሁ ነው ።” [አል ሩም ፡40]
" አላህ እርሱ ሲሳይን ሰጪ የብርቱ ኃይል ባለቤት ነው።” [አል ዛሪያት ፡ 58]
" ነገሩም አንዳችን በሻ ጊዜ ኹን ማለት ነው። ወዲያውም ይኾናልም። [82] ያ የነገሩ ሁሉ ስልጣን በእጁ የኾነው ጌታ ጥራት ይገባው ። ወደ እርሱም ትመለሳላችሁ።” (ያሲን 82-83)
2) ተዉሒድ አል ኡሉሂያህ
ማንኛውንም የአምልኮ አይነት ለአላህ ብቻ በማድረግ እና ከሱ ውጭ ላለ ለየትኛውም አካል እንደማይገባ በማመን የሚገለፅ የተዉሂድ ክፍል ነው ። አምልኮ ማለት ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያህ እንዳብራሩት ለማንኛውም አላህ ለሚወደውና ለሚቀበለው በግልፅም ይሁን በስውር ለሚፈፀም ንግግር ወይም ተግባር የተሰጠ አጠቃላይ ስያሜ ነው ።
በቁርአን ውሰጥ ተውሂደል ኡሉሂያ ከሚያስገነዝቡ አንቀፆች መካከል፦
"እናንተ ሰዎች ሆይ! የፈጠራችሁን እነዚያንም ከናንተ በፊት የነበሩትን (የፈጠረው) አምላካችሁ ተገዙ፤ (ቅጣትን) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና።" [አል በቀራ፡21]
"አላህንም ተገዙ በእርሱ ምንንም አታጋሩ።"[አን ኒሳዕ፡36]
"ስግደቴ ፣ መገዛቴ ፣ ህይወቴም ፣ ሞቴም ለ አለማት ጌታ ለ አላህ ነው" በል።[አል -አንአም ፡12]
3)ተውሂድ አል አስማኡ ወሲፋት
አላህ (ሱ.ወ) በቁርአን ላይ እራሱን የገለፀበትን እና ከመልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) በሶሂህ ሀዲስ ተዘግበው በመጡ የአላህ ስምና ባህሪያት ማመን እና አላህ ና መልዕክተኛው ከአላህ ያራቁትን ባህሪያት ማራቅን በአንድነት ይይዛል።
የላቀዉ አላህ እንዲ ይላል ፦
"ለአላህ መልካም ስሞች አሉት። (ስትፀልዩም) በእርሷ ጥሩት"። [አል አዕራፍ ፡180]
የአላህን ስሞችና ባህሪያት በምናፀድቅበት ጊዜ ከየትኛውም ፍጡር ጋር ሳናመሳስል እና እንዴትነቱን ሳንመራመር እንዲሁም ሳናዛባ/ሳናንሻፍፍ ሊሆን ይገባል።
"የሚመስለው ምንም ነገር የለም። እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው።"[አሽ ሹራ፡ 11]
በሦስቱም የተውሂድ ክፍሎች ማመን በሁሉም የሰው ልጅ ላይ ግዴታ የሆነ ነገር ነው። ምክንያቱም የሰው ልጆችና ጋኔኖች የተፈጠሩበት፣ በየዘመናቱ መፅሐፍቶች የወረዱበትና መልዕክተኞች የተላኩበት ዋና ምክንያት ተውሂድን ማረጋገጥ ስለሆነ፣ ይህም በቁርአን ላይ በግልፅ ተቀምጧል:
"ጋኔንንና ሰውንም ሊገዙኝ እንጂ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም።" [አል-ዛሪያት: 56]
በየህዝቡም ሁሉ ውስጥ "አላህን ተገዙ፣ ጣኦትንም ራቁ" በማለት መልዕክተኛን በእርግጥ ልከናል:: [አል-ነህል: 36]
ከላይ እንጸተገለፀውም ለመልካም ስራ ቅቡልነት ሊሟላ የሚገባው ወሳኝ ቅድመ መስፈርት የተውሂድ መስተካከል ነው።
"እነዚያ ያመኑ፣ መልካም ስራዎችንም የሰሩ፣ ሶላትንም ያዘወተሩ፣ ዘካንም የሰጡ ለእነሱ በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው አላቸው። በእነሱም ላይ ፍርሃት የለባቸውም እነሱም አያዝኑም።" [አል-በቀራ: 277]
"እነዚያ ያመኑትና መልካም ስራዎችንም የሰሩ ለእነሱ የፀጋ ገነቶች አሏቸው።" [ሉቅማን: 8]
ተውሂድን ከማስተካከል ጋር ተቆራኝቶ የሚገለጽ ወይም ሊታመን የሚገባው ነገር በነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ነብይነት ማመን የሚለው አስተምህሮ ነው። ይኸውም ያዘዙትን በመታዘዝ ፣ የተናገሩትን ሁሉ እውነት ነው ብሎ በመቀበል፣ ከከለከሉት እና ካስጠነቀቁት ነገር በመራቅ እንዲሁም አላህን እርሳቸው ባስተማሩት መንገድ ብቻ በመገዛት የሚገለጽ እምነት ነው።
ይህ ከላይ በጥቂቱም ቢሆን ለመዳሰስ የሞከርነው ኢስላማዊ አቂዳ የመልዕክተኛው ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)፣ የሶሀቦቻቸው ከዚያም የታቢኢዮች እና የነርሱ ተከታዮች መንገድ ነው። እነዚህ አካላት በተጓዙበት መጓዝ ለመመራት ዋስትና እንደሆነ የላቀው አላህ እንዲህ በማለት ይናገራል:
"...በእርሱ ባመናችሁበት ቢጤ ቢያምኑ በርግጥ ተመሩ።"[አል በቀራ፡ 139]
ስለዚህም መመራትን የፈለገ ማንኛውም ግለሰብ ይህን ኢስላማዊ አቂዳ በትክክል በማመን እና በመተግበር ላይ ሊተጋ ይገባዋል።
[ወላሁ አዕለም]
=======
በዳዕወቱል አንቢያ ኢስላማዊ ድርጅት ተማሪዎች ተዘጋጅቶ የቀረበ።
(ነሐሴ 01, 2018)
የቴሌግራም ቻናል:-
http://t.me/daio_TG07
http://t.me/daio_TG07