Dr Henok Yitbarek

Dr Henok Yitbarek

Share

To create healthy mind through an interactive teaching process of evidence based psychiatric practice.

18/10/2023

የአዕምሮ ጤና የማህበረሰብ ጤና ነው የሚባለው ለዚህ ነው ።
============================
ብዙ የአዕምሮ ህሙማንን በየጎዳናው ላይ የአዕምሮ ህክምና አገልግሎት ሳያገኙ ሁልጊዜ እየታመሙ መመልከት የተለመደ ነው ።

ዘንድሮም የአለም የአዕምሮ ጤና ቀን ሲከበር መሪ ቃሉ እንደሚለው " የአዕምሮ ጤና የማንኛውም ሰው ሰብዓዊ መብት ነው " በሚል መከበሩ ይታወሳል ።

ስለሆነም ይሄንን ቃል ወደ መሬት በማውረድ ተፈፃሚነቱን ለማረጋገጥ የሁሉም ዜጌችን ድጋፍ እና ርብርብ በማድረግ የማህበረሰባችንን ጤና ለማረጋገጥ ቀጣይ እና ዘለቄታዊ ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ነው ።

ይህንን መልዕክት እንድፅፍ ያደረገኝ ሰሞኑን በአካል ከገጠመኝ እውነተኛ የጎዳና ታሪክ በመነሳት ነው ።

ታሪኩ እንዲህ ነው ፤ እኔ በምኖርበት አካባቢ አንዲት እናት በወራት እድሜ የሚገመተውን የገዛ ራሷን ልጅ በአደባባይ መሃል ለመግደል ሙከራ ስታደርግ በማህበረሰቡ ርብርብ ህፃኑ ለጊዜው ሊተርፍ ችሏል ።

ሁኔታው በጣም ስላሳሰብኝ እና ሙያዊ ግዴታዬም በመሆኑ ቀረብ በማለት ስለሁኔታው ለመረዳት ሞከርኩ ። አብዛኛው ሰው ባለማወቅ ወይም ባለመረዳት ወላጅ እናት ላይ ወቀሳ ፣ ተግፃፅ እንዲሁም አንዳንድ ሰዎች አካላዊ ጥቃት ሁሉ ለማድረስ ሲሞክሩባት ተመለከትኩ ።

በሰዓቱ የአካባቢው የፀጥታ አካላት ባደረጉት ጥረት ወላጅ እናትን እና ህፃኑን አስቸኳይ እርዳታ በማድረግ ወደ ህጋዊ ከለላ ወስደው የመጀመሪያ እርዳታ አድርገውላታል ።

በመቀጠል ሁኔታዎቹ ሲረጋጉ የምችለውን ያህል በአጠገቤ ካሉት ሰዎች ጋር ስለሁኔታው በመረዳት የአዕምሮ ህመም ሊሆን እንደሚችል በማሰረዳት መጀመር እንዳለብኝ ወሰንኩ ። ከአጠገቤ የነበሩት ሰዎችም ጥሩ መረዳት እንዳለቸው እንዲሁም ወላጅ እናትንም ሆነ ህፃኑን ለመርዳትም ዝግጁ እንደሆኑ ሲነግሩኝ ፣ ጥሩ የማህበረሰባችን አካላት እንደሆኑ ተረዳሁ ።

በመሆኑም ጉዳዩን የበለጠ ገፋ አድርጌ አንድ ርቀት በመሄድ የፖሊስ ፅ/ቤቱ ድረስ በመሄድ የምችለውን ያህል ለመርዳትም ሆነ ሙያዊ አስተያየት በመስጠት የአዕምሮ ህክምና በማግኘት ቀጣይ ህክምና እንድታገኝ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለብኝ በማመን ተከትዬ ሄድኩ ።

የፀጥታ አካላቱ ተደጋጋሚ የህይወት ገጠመኝ ስለነበራቸው ሁኔታውን ለመረዳት ብዙም አልተቸገሩም ። እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ሲከሰቱ የህግ ምርመራ እና አገልግሎታቸውን ሲጨርሱ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ማንኛም የጤና ተቋም አገልግሎት እንዲያገኙ ከሚመለከተው አካል ጋር እንደሚሰሩ ሲነግሩኝ የቤት ስራው ተስፋ ሰጪ እንደሆነ በመረዳት አመስግኜያቸው ወጣሁ ።

ወደ ዋናው መልዕክቴ ስገባ : -

በአዕምሮ ህመም የሚሰቃዩ የጎዳና ላይ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያት በቤታቸው ውስጥ ታስረው የአዕምሮ ህክምና አገልግሎት የተነፈጉ የማህበረሰባችን አባላት በርካታ ናቸው ።

በአንድ ወቅት የጎዳና ላይ የአዕምሮ ህሙማንን ከህጋዊ የፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በማንሳት የአዕምሮ ህክምና እንዲያገኙ የተሰሩ ስራዎች ቢኖሩም ፤ የሚመለከታቸው አጋር ተቋማት ዘለቄታዊ የአሰራር ስርዓት ስላልነበራቸው ተመልሶ የጎዳና ላይ የአዕምሮ ታማሚዎችን እየተመለከትን ነው ።

ምንም እንኳን ሰዎችን ለመርዳት ቀና እና መልካም ማህበረሰብ ቢኖረንም ፤ በማህበረሰባችን ውስጥ ያሉት መረዳቶች እና አስተሳሰቦች ለአገልግሎቱ ተሳታፊ የሆነ በቂ ማህበረሰብ ለመፍጠር አልቻልንም ።
ማነቆ ከሆኑብን የማህበረሰባችን የተዛቡ አመለካከቶች መካከል :-
1. የአዕምሮ ጤና የጤና ተቋማት ስራ ብቻ አድርጎ ማሰብ ።
2. የአዕምሮ ጤና የሁላችንም የቤት ስራ አድርገን ለመውሰድ ቁርጠኛ አለመሆን ።
3. የአዕምሮ ህመም የእኔ ህመም አይደለም የሚሉ የተዛቡ አስተሳሰቦች ።
4. በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ምን አገባኝ በሚሉ ስሜቶች ነገሮችን በዝምታ መመልከት ።
5. የአዕምሮ ህመም ህክምና የለውም የሚሉ የተዛቡ አመለካከቶች ።
6. የማህበረሰብ ጤና የእኔም ጤና ነው የሚል ማህበረሰብ በበቂ ሁኔታ አለመፍጠር ።
7. የግንዛቤ እና የዕውቀት ማነስ
8. ወዘተ ....

ቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች :-
===================
• በአሁን ሰዓት ያሉት የግል / የማህበረሰብ ድጋፍ ሰጪ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ቁጥራቸውን በመጨመር ከጤና ተቋማት ጋር የአዕምሮ ህክምና ትስስር በመዘርጋት ሳይንሳዊ ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ።

• በየጎዳናው ላይ ወድቀው የሚገኙትን የአዕምሮ ህሙማን ሁሉም የማህበረሰብ አካላት የእኔም ኃላፊነት ነው በማለት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በጋራ በመስራት ቢያንስ አንድ ሰው ለማሳከም መርዳት ።

• የአዕምሮ ህመም እንደሚታከም እና ለውጥ እንደሚያመጣ ከታች ለሚገኙት ማህበረሰብ ሁልጊዜም ግንዛቤ በመስጠት ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ ።

• ከህመማቸው ያገገሙ ታማሚዎችን የህይወት ተሞክሮ እና ጤናማ ለውጥ ዕለት በዕለት በምናገኛቸው አጋጣሚዎች ምስክር በመሆን ተነሳሽነታቸውን መጨመር ።

• የጤናው ተቋም የአንበሳውን ድርሻ እንደመውሰዱ መጠን ፤ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ዘለቄታዊ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት የማህበረሰቡን ተነሳሽነት እና ተሳትፎ በመጨመር ከማህበረሰባችን ጋር በጋራ መስራት ።

• ተከታታይነት እና ዘለቄታዊነት ያለው የድጋፍ እና ክትትል በማድረግ የአዕምሮ ህክምና የተደራሽነት አድማሱን ማስፋት ።

• ነባራዊ በሆኑት የጤና ስርዓት መዋቅር ውስጥ የአዕምሮ ጤናን ትኩረት አግኝቶ እየተሰራ ቢሆንም ፣ የበለጠ ትኩረት በመስጠት አጠናክሮ መስራት ።

• የአዕምሮ ጤና በተቋም ደረጃ ተቋቁሞ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ፣ ሰፊ የሆኑ የፓሊሲ ስራዎችንም ጨምሮ እንዲሰራ በመካከለኛም ሆነ በረጅም ጊዜ ዕቅድ ውስጥ የአዕምሮ ጤና በተቋም ደረጃ እንዲሰራ ዝግጁነትን ማሰብ ይፈልጋል ።

ዶ/ር ሔኖክ ይትባረክ (የአዕምሮ ሐኪም )
አማኑኤል ሆ/ል

Want your school to be the top-listed School/college in Addis Ababa?

Click here to claim your Sponsored Listing.

Location

Category

Website

Address

Addis Ababa