05/03/2022
የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ላይ ተፈጻሚ የሚሆን አዲስ ኤችአር 6600 የተባለ ረቂቅ ሕግ አስተዋውቀዋል።
ይህ በኒው ጀርሲው የኮንግረስ አባል ቶም ማሊኖወስኪ ለአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተዋወቀው ረቂቅ ሕግ ተፈጻሚ የሚሆን ከሆነ "በኢትዮጵያ ላይ የሚያርፈው ጠንካራ የአሜሪካ ክንድ" ይሆናል ተብሎለታል።
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥት አጥብቀው የተቃወሙት ይህ ረቂቅ ሕግ በፕሬዝደንት ባይደን የሚጸድቅ ከሆነ አሜሪካ በደኅንነት፣ በፋይናንስ/በኢንቨስትመንት እና በኢሚግሬሽን ጉዳዮች ላይ አዲስ ማዕቀብ ትጥላለች።
የዚህ ረቂቅ ሕግ ይዘት ምንድን ነው?
ይህ ረቂቅ ሕግ ለአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 'የኢትዮጵያ የመረጋጋት፣ የሰላም እና የዲሞክራሲ ሕግ' (Ethiopia Stabilization, Peace, and Democracy Act) በሚል ስያሜ ቀርቧል።
ረቂቅ ሕጉን ለምክር ቤቱ ያስተዋወቁት የኮንግረስ አባላት ሕጉ ተፈጻሚ ቢሆን በኢትዮጵያ መረጋጋት፣ ሰላም እና የዲሞክራሲ ግንባታ ጥረቶችን ለመደገፍ ያስችላል ይላሉ።
ይህ ረቂቅ ሕግ ጥር 27 2014 ዓ.ም. ለውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ፣ ለሕግ ጉዳዮች ኮሚቴ፣ ለፋይናንስ አገልግሎቶች እና ለመከላከያ አገልግሎቶች ተመርቷል።
የቪዛ እና የንብረት እግድ
ይህ ረቂቅ ሕግ በኢትዮጵያ መረጋጋት እና የዲሞክራሲ ሥርዓት እንዳይኖር ምክንያት ናቸው በተባሉ ግለሰቦች ላይ ተጠያቂነትን ለማምጣት ፕሬዝደንት ባይደን ማዕቀብ እንዲጥሉባቸው የሚጠይቅ ነው።
ግለሰቦች ላይ የሚያነጣጥሩት ማዕቀቦች የንብረት እግድ እና የቪዛ ማዕቀቦችን ያጠቃልላሉ። በተጨማሪም፦
በትግራዩ ጦርነትም ሆነ በአገሪቱ ባሉ ሌሎች ግጭቶች ዙሪያ የተኩስ አቁም ወይም ድርድር እንዳይደረግ እንቅፋት የሆነ ወይም ስምምነት እንዳይደረስ ጥረት ያደረገ፤
የትግራዩ ግጭትም ወይም ሌሎች በአገሪቱ ያሉ ግጭቶች እንዲስፋፉ ምክንያት የሆነ ወይም የተባበረ፤
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸመ፣ የጦር ወንጀል፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል፣ የዘር ማጥፋት እና ሌሎች በደሎችን የፈጸመ፤
የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ እንቅፋት የሆነ እና በሰብዓዊ እርዳታ ሥራ ላይ የተሰማሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ሕብረት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ የሰብዓዊ ድርጅት ሠራተኞች ላይ ጥቃት የሰነዘረ፣ ለመሰንዘር ያቀደ፣ የመራ፤
በኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት የተሳተፈ ወይም በፋይናንስ የደገፈ፤
ንብረቱ እንዳይንቀሳቀስ በፕሬዝደንት ባይደን ይወሰናል። ከንብረት እግዱ በተጨማሪ ከላይ የተጠቀሱትን ወንጀሎች ፈጽመዋል የሚባሉ ግለሰቦች የጉዞ እገዳ ይጠብቃቸዋል።
ክልከላዎቹን ተላልፈው የሚገኙ ሰዎች ቀድሞ በነበራቸው ቪዛ አሜሪካ መግባት አይችሉም፤ አዲስ ቪዛ አመልክተው ማግኘት አይችሉም እንዲሁም ይዘው የሚገኙት ቪዛ ይሰረዛል።
እግዱ በላይ በተጠቀሱት ግለሰቦች ላይ ተፈጻሚ ለማድረግ የአሜሪካ መንግሥት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ከተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት፣ ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) አባል አገራት ጋር፣ ከአውሮፓ እና ከአፍሪካ ሕብረት እንዲሁም ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ይተባበራሉ ይላል ረቂቅ ሕጉ።
የደኅንነት እና ፀጥታ ድጋፍ ላይ የሚጣለው ገደብ
ይህ ረቂቅ ሕግ በፕሬዝደንቱ ከጸደቀበት ዕለት አንስቶ አሜሪካ ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ የምታደርገው የደኅንነት እና የፀጥታ ድጋፍ እንዲቋረጥ ይጠይቃል።
ይህ የአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ መልሶ የሚቀጥለው አሜሪካ ያስቀመጠቻቸው ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸው በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ በኩል ተረጋግጦ ለሚመለከተው የኮንግረስ ኮሚቴ ከቀረበበ