16/09/2024
በመኖር መንገድ መሀል "እግረ መንገድ ማግባት"
ገና ሲፈጥረው ማልዶ ሳይበረዝ ልብ ስስ ነው! ሲከፋው ቶሎ ዘንበል ይላል! አንገት መድፋት ሲችልበት! ማልቀስ ሲያውቅበት!
ልብ ደስታውም ቅርብ ነው! በሳቅ፣ መደሰት፣ መውደድና ማፍቀር መለያው ነው! ልብ ደግ ነው! መቸር ደስታው ነው!
በሁለቱም ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ግን አንድ የማይረሳው የዘወትር ተግባሩ ለሰውነት ክፍሎቻችን በተገቢው መንገድ ደም ማስተላለፉን ነው። ለሰከንድ ስራውን ቢዘነጋ ሕይወት ቀጥ ትላለች። ታዲያ ልብ ለምን ይክፋው!? ወደ ዋናው ጉዳዬ ልግባ።
በማህበራዊ ኑሮዬ ብዙም ተግባቢ አይደለሁም። መግባባት አለመቻል ሳይሆን ከሰው ጋር መሆንን አለመፈለግ። እስካሁን ባሳለፍኩት እድሜይ 3/4ኛ የሚሆነው እድሜዬ ብቻዬን ያሳለፍኩት ይመስለኛል። ይህ ማለት አልፎ አልፎም ቢሆን የምቀርባቸው ስዎች የሉም ማለት አይደለም።
ከእለታት አንዱ ቀን ከምቀርባቸው ሰዎች ከአንዷ ጋር መገናኛ አካባቢ (ሞቢል ጋር) በሚገኘው ሰላም ታወር ሁለተኛ ፎቅ ላይ ቁጭ ብለን ሻይ እየጠጣን ስለ ሕይወት ስናወጋ ስለ ስራና ሌሎችም ወሬዎች ካወራን በኋላ ስለ ፍቅር ሕይወት ማውራት አስከተልን።
እድሜሽ እየቆሰቆሰው ነው። እያየሁሽ ልታረጂ ነው። ሰላሳ ለመግባት ጥቂት ቀረሽ። የፍቅር ሕይወትሽ እንዴት ነው? ምንድነው እቅድሽ? ይህንን ጥያቄ ባልጠየኳት ብዬ ተረበሽኩ።
እያየኋት ቀዩ ፊቷ ከፍም እሳት ቀላብኝ። አጓነበሰች! ጠረጴዛው ላይ አፈጠጠች። በሁለቱም እጆቿ የስኳር እቃውን ታሽከረክራለች። መሀላችን አስፈሪ የሆነ ዝምታ ሰፈነ። በመሀል ቀና ብላ አየችኝ። የሚያማምሩት አይኖቿ እንባ አቅረዋል። ካልወረድኩ እያሉ ተፈታተኗት። ላለማልቀስ ታገለች። ላለመሸነፍ በረታች። በየመሀሉ ወፈር ያሉት ቀይ ከንፈሮቿን በምራቋ እያረጠበች ይበልጥ ለመብላት የሚያስጎመጅ ቀይ ስጋ መሰሉ።
ይበልጥ አስተውዬ እያየኋት ምነው ችግር አለ? ብዬ ጠየኳት። "አይ የለም" የሷ መልስ ነበር። እና ለምንድነው የተረበሽው? ስል የሀዘኗን መንስኤ ለማወቅ በመጓጓት ጠየኳት። አይገርምም!? ሰዎች ያዘኑበት ነገር ለማወቆም ያጓጓል። ራሴን ታዘብኩት። ግን የምር በሁኔታዋ ተከፍቼ ነበር። ከቆይታ በኋላ " ፍቅር የሚባለው ነገር ያደክማል አይደል?" ብላ በረጅሙ ተነፈሰች። እኔ'ንጃ ያደክማል እንዴ? ጥያቄዋን በጥያቄ መለስኩ። አስተውላ አየችኝ። እጆቼን በእጆቿ ያዘች። ጎን ለጎን በተቀመጥንበትን ሶፋ ራሷን አመቻችታ ወደ'ኔ ተጠግታ አንገቷን ሰበር አድርጋ ትከሻዬን አስደገፈችው። ትንሽ እዛው ቆየች። ቀና ብላ አየችኝ። ጥሩ ጣዕም ያለው ሞቃታማው ትንፋሿ ፊቴን ሙሉ ፊቴን ገረፈኝ። በጣም የምንቀራረብ ጓደኛሞች ከመሆናችን የተነሳ ይህ አቀራረቧ ለኔ እንግዳ አልነበረም። አይዞሽ በርቺ በሚል የሀዘን ስሜት ግንባሯን ስሜ ወደ ራሴ አስጠግቼ ሳቅፋት። ይበልጥ ሰነፈች። ማልቀስ መጀመሯን ያወኩት ወፋፍራም እንባዎቹ ሸሚዜን ሲያረጥቡት ነው። ቀና አድርጊያት እንባዋን ጠራረኩላት። ትንሽ ነገር የሚያስለቅሳት ምስኪን እርግብ ነች። የሁሉ ጊዜ እንባወቿን ብንገድብ ሌላ አባይን የሚስተካከል ግድብ ይኖረን ነበር። ሰው የሚያምኑ ስስ ልቦች። ቶሎ የሚከፉ፣ በትንሽ ነገር ወዲያውኑ የሚፈነድቁ። አንዳንድ ልቦች አሉ።
ጨነቀኝ እኮ ይቅርታ ምን ተፈጥሮ ነው? ግራ በተጋባ ስሜት ደግሜ ጠየኳት። "በአጭሩ ላስረዳህ ዝርዝር ውስጥ መግባት አልፈልግም። ከዚህ ቀደም በተለያየ ጊዜ ከተለያዩ 3 ወንዶች ጋር የፍቅር ግንኙነት ነበረኝ። ከአንዱ አንዱ ይሻላል ስል በተስፋ የጀመርኳቸው የፍቅር ግንኙነቶች በተለያየ ምክንያት ሳይሳኩ ቀሩ። ከዛም በኋላ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆኜ ሌላ ወንድ ለመቅረብ ሞከርኩ። ይህም ሳይሆን ሲቀር ከሁሉ ነገር ራሴን አራኩ። ከረጅም ጊዜ በኋላ ግን ከድሮዎቹ አንዱ ተመልሶ መጥቶ ካላገባሁሽ በሚል አስጨነቀኝ። እናም የትም ትክክል ካልሆነ እዚሁ ከተላመድኩት ጅብ መቆየቱን መረጥኩ። በቃ መኖሬ ካልቀረ እግረ መንገዴ አግብቼ ትዳር ያዘች ቤተሰብ መሰረተች ልባል ብዬ ወሰንኩ። ከወራት በኋላ አገባለሁ። " ለሷ ከማዘን ውጪ ምንም ማድረግ አልቻልኩም ነበር። ጊዜው ደርሶ ያለችው ሁሉ እንደሆነ በወሬ ነጋሪ ሰማሁ።
ሌላኛው ከዚሁ ጋር የተያያዘ የማስታውሰው ነገር አንዲት በስራ አጋጣሚ ያወኳት ልጅ ነበረች። ይህች እህቴ ከ 16 አመቷ ጀምሮ ከብዙ ወንዶች ጋር ግንኙነት እንደነበራትና ይህም ያዝናናት እንደነበር የነገረችኝ ሲሆን አሁን ላይ የ24 አመት ወጣት ብትሆንም ወደፊት በፍፁም የማግባት ፍላጎት እንደሌላት ጭምር ተማራ ስትናገር አስተውያታለሁ።
ዋናው ማንሳት የፈለኩት ነገር የመጀመሪያ ልጅ ታሪክ እና የሁለተኛዋ ልጅ ታሪክ የሚለየው የመጀመሪያዋ የፍቅር አጋርን ፍለጋ ሲሆን ሁለተኛዋ ደግሞ ስጋዊ ፍላጎትን የማሟላት ጉዞ ነው። ሁለቱም አንድ የሚያደርጋቸው የተከበረው ቅዱስ ገላቸውን ከተለያየ ወንድ ጋር ማርከሳቸው ነው። ምክንያታቸው ለየቅል ቢሆንም ተጠያቂነት ግን አንድ ያደርጋቸዋል። የወንዶችም እጅ አለበት።
የኔን ሀሳብ እዚህ ላይ ገታ ላድርግና የአዳም ረታ "መረቅ" በተሰኘው መፅሐፉ ላይ ገፅ 344 ከላይ ከፃፍኩት ሀሳብ ጋር የሚቀራረብ ፁሑፍ ላጋራችሁ ወደድኩ። እነሆ፡-
.. "ሌላ የምነግርህ ነገር ቢኖር እድሜህ ሳይገፋ ሚስት አግብተህ ልጅ መውለድ እንዳለብህ ነው። ሚስት ስታገባ ወንድ የማታውቅ አግባ። ሀብት ይኑራት አይኑራት አይደለም። መጠንቀቅ ያለብህ ለትዳር ድፍን ሴትን የመሰለ የለም። ለምን? በለኝ 'ለምን' ማለት ጥሩ ነው።
ድፍን ሴት ማለት ላይና ታቿ ልክ እንደ ሸንኮራ አገዳ የተዘጋ ነው። ውስጧ ማንም ያልነካው መረቅ ነው። በማህፀኗ ያለው አየር ክፋት ያልገባው ነው። ምድርና ሰማይ ሲፈጠር አዳምን ያቆመው፣ ከእግዜር ጋር አብሮ የማገው አየር እዛ ነው ያለው።
'ዮሀንስ አፈወርቅ፡- " ' የሀጢያት ምንፃፍ የማታውቅ ነውር የሌለባት ድንግል ሴት ክብር ናት። እንዲህ ያለችቱ ሴት ነፍሳት በፀጋና በክብር በተገኙበት ጊዜ ዋጋዋን ታገኛለች" ' ይላል። በዘመኑ እኮ የበኩር ልጅ እየጠፋ ነው። ... የበኩር ልጅ መጀመሪያ የተወለደ ወይም የተወለደች ማለት አይደለም። ቁጥር አይደለም። ያለ ድንግልና መበ'ከር የለም። ... "
* * * * * /////// * * * * *
ይህን መፅሐፍ ብታነቡት ታተርፋላችሁ። ከማንበብ አትስነፉ።
👉 ሌላኛው ነገር ፡- የሴቶቹን ጉዳይ ወንዶችንም ይመለከታል ባይ ነኝ። ብትችሉ ከጅምሩ ንፁህ ሁኑ። ድንገት ስጋዊ ነገር ቢያሸንፋችሁ እንኳን የኔ ከምትሏት ጋር በንሰሀ ታጥባችሁ አንዱ ሁኑ! አመሰግናለሁ!