17/12/2025
መረጃዎችን ለማግኘት አርቆ መቆፈር የሚፈልገውን እና በቀላሉ የማይገኙ ብዙ ገድላትን እንዲሁም የብራና መዛግብትን ማገላበጥ የሚጠይቀውን አድካሚ ሥራ ደክመው ስለ ሠሩልን መ/ር በኃይሉ በቀለን እናመሰግናለን። ይህ ትውልድ ዕድለኛ ነው!
የፊታችን ቅዳሜ ታኅሣሥ 11 በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ አዳራሽ “ነገረ አበው ኢትዮጵያውያን” የተሰኘው አዲስ መጽሐፍ ይመረቃል። ይህን ጉባኤ መቅረት ብዙ ያጎድላል!
15/12/2025
በኵረ መዘምራን ኪነ ጥበብ ወልደ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን ካፈራቻቸው ቃላቸው ከሚጣፍጥ፣ የጉሮሯቸው ዜማ እንደ ማር ከሚጥም አንጋፋ ዘማርያን መካከል ቀዳሚው ነው። ከዓመት በፊት ክፍለ አገር ለጉባኤ አብሮ የመውጣት ዕድል ገጥሞኝ በብዙ መሥዋዕትነት ያለፈውን እና በውጣ ውረድ የታጀበ የአገልግሎት ሕይወቱን አጫውቶኝ፣ ጋሽ ኪነ ራሱ “የአማርኛ መዝሙር ታሪክ አይደል እንዴ?!” ብዬ ተገርሜ ነበር። ምን አለ ይህን ብንጽፈው ብዬም በቁጭት ጠይቄው ነበር። ይኸው ዛሬ ባማረ መልኩ በራሱ አንደበት ተተርኮ ቀረበልን። የአገልግሎት ጽናት፣ ለቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልገውን ሁሉ ዋጋ መክፈል፣ ልከኛ ሰው መሆን መልክ ቢኖረው “ኪነ ጥበብን ይመስላል!”
የኪነን መዝሙር መስማት ያስተክዛል፤ ምረረ ገሃነምን ያሳስባል። የኪነን መዝሙር መስማት ደስ ያሰኛል፤ ጣዕመ መንግስተ ሰማያትን ያዘክራል”
ከዚህ ምድር ከፍ እንድንል ለነፍሳችን አክናፍ (ክንፎች) የሚሆኑ ያማሩ መዝሙራት ስለ ሰጠኸን በኵረ መዘምራን ኪነ ጥበብ ሆይ እጥፍ ክብር ይገባሃል!!!
ኪነ ጥበባዊ ዘመናት
©️ Janderebaw MediaWriter and Creative Director - Deacon Henok Haile Narration - Mikiyas Liyew Director - Mikiyas Liyew Interviewers - Deacon Berketesillas...
12/12/2025
+++ የማርያም ጠበል ነው! +++
“በሳይንስ የጎለበተው ጭንቅላቴ ይህንን ተአምር ለመቀበል ጊዜ ፈጅቶበታል”
ከጥቂት ወራት በፊት ጎንደር በምሠራበት ወቅት አንድ ሰውዬ ሴት ልጁን አስከትሎ ወደ ሕክምና መጥቶ ነበር። ሰውዬው በሃምሳዎቹ መጨረሻ አካባቢ የሚገኝ በጣም ዝምተኛ እና ረጋ ያለ ሰው ነው ። ወደ ሕክምና የመጣው የቆየ የሆድ ሕመም ስለነበረው ሲሆን በብዛት በቀኝ በኩል ነበር የሚሰማው፤ ከዚህ በፊት ብዙ ምርመራዎችን እንዳሠራ እና የጨጓራ በሽታ ነው ተብሎ ብዙ መድኃኒቶችን ሲወስድ ቢሰነብትም ለውጥ እንዳልነበረው ከዚያ ውጪ እንደ ማስመለስ ፣ የሰገራ ቀለም መቀየር እና ክብደት መቀነስ የመሳሰሉት ምልክቶች እንደሌሉት ነገረኝ ።
በመካከል ልጁ አቋረጠችውና ሕመሙ በምንም መልኩ ሊሻለው እንዳልቻለ እና እንደተሰቃየ ፤ ተስፋ ቆርጦ ክትትሉንም ለአንድ ዓመት እንዳቋረጠው አውርታኝ በደምብ እንድመረምረው ተማጸነችኝ።
የሕመሙን ምልክቶች በዝርዝር ከነገረኝ በኋላ ሙሉ አካላዊ ምርመራ ሰርቼለት ምንም ነገር ሳላገኝ ቀረው። ስለዚህ የደም ምርመራ ፣ የሰገራ ምርመራ እንዲሁም አልትራሳውንድ እንዲያሠራ ላኩት።
ውጤቱ ደርሶ ተቀብዬ ስመለከተው በጣም ደነገጥኩ ፣ ልቤ ተሰበረ መናገር እንኳን አቃተኝ። ዙሪያ ዙሪያውን ስል ቆይቼ በመጨረሻም ምርመራው የሃሞት ቱቦ ካንሰር( colangiocarcinoma) እንደሚያሳይና የበለጠ እርግጠኛ ለመሆን ሲቲ ስካን ማሠራት እንዳለበት ስነግረው ፊቱ ምንም አልተረበሸም። ማዘዣውን ተቀብሎኝ አመስግኖ ሄደ።
ውጤቱን አሠርቶ ይዞልኝ ሲመጣ ጥርጣርሬዬ እርግጥ ሆነ። ያገኘሁትን የምርመራ ውጤት ሳስረዳቸው ልጅቷ ልትቀበለው አልቻለችም። እንደ ገና ሌላ አልትራሳውንድ ማሠራት እንደምትፈልግ ነገረችኝ፤ ተስማማሁና ወደ ሌላ ራዲዮሎጂስት ለአልትራሳውንድ ላኳቸው። ሲመጣ ውጤቱ ተመሳሳይ ነበረ። ልጅቷም ከተማው ውስጥ አዲስ ሲቲ ስካን ማሽን መምጣቱን እንደሰማችና እዛ ማስደገም እንደምትፈልግ ነገረችኝ፣ ተሳማማሁ። ከዚያ ግን ሲስ ቲስካኑን ስልክ አብሬ CA 19- 9 የተባለ የደም ምርመራ ላኩኝ። የሲቲ ስካኑ ውጤት ተመሳሳይ ቢሆንም የደም መርመራው ግን ኔጌቲቭ ነበረ።
አረጋግቼ በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለባቸው መንገር ጀመርኩ። ክትትል እንደሚያስፈልገውና ከካንሰርና ከቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት ጋር ውይይት ማድረግ እንዳለበት ሳስረዳው ልብ ብሎ ካደመጠኝ በኋላ፣ ስላደረኩለት ሁሉ አመስግኖኝ አንድ ወር ብቻ እንድሰጠው ወሩ ሲያልቅም ተመልሶ እንደሚመጣ ፤ የዛኔም ያልኩትን ሁሉ ለማድረግ ፍቃደኛ እንደሚሆነ ነገረኝ።
አንድ ወር ረጅም ጊዜ እንደሆነ እና በሽታው ተባብሶ የመታከም እድሉ እንደሚቀንስ አጥብቄ ባስጠነቅቀውም አንድ ወር ብቻ እንደሚቆይ ነግሮኝ ተሰናብቶኝ ወጥቶ ሄደ።
ወር ሲሞላው በቃሉ መሠረት ተመልሶ መጣ ። መጀመርያ ሳየው አላስታወስኩትም ፤ ፊቱ የፈካና ሰላማዊ፣ ሰውነቱም የተረጋጋ ነበር። “በቃሌ መሠረት መጥቻለው፣ ካላስቸገርኩህ አንድ የመጨረሻ ምርመራ ትልክልኛለህ ?” ብሎ ጠየቀኝ። ወር ቆይቶ ስለመጣ እና የበሽታውን ሁኔታ ማውቅ ስለ ነበረብኝ ተስማማሁ። ለምርመራው ከመሄዱ በፊት ግን ለምን በድጋሚ መነሣት እንደፈለገ ጠየኩት። ለአንድ ወር ወደ ሆነ ቦታ እንደ ሄደና እዛ እንደቆየ ነግሮኝ ካንሰሩ ምን እንደ ደረሰ ማወቅ ስለፈለገ እንደሆነ ነገረኝ።
በውስጤ ምናልባትም ባሕላዊ ሕክምና ጀምሮ ሊሆን እንደሚችል እየጠረጠርኩ የአልትራሳውንድ ምርመራ ላኩለት። ውጤቱን ይዞት መጥቶ ተቀብዬ ስመለከተው ግን ያየሁትን ማመን አቃተኝ። ውጤቱ “ኖርማል” ነበር የሚለው ደጋግሜ ስሙን አንብቤ የራሱ ውጤት መሆኑን ካረጋገጥኩ በኋላ ለራሴም ግራ እየገባኝ ውጤቱ ምን እንደሚል ነገርኩት። ፈገግ ብሎ ሲያዳምጠኝ ቆየና ስጨርስ እርግጠኛ ለመሆን ሲቲ ስካን እልክለት ዘንድ ጠየቀኝ።
ተስማምቼ ከመላኬ በፊት ግን አንድ ወር የት እንደቆየ እንዲነገረኝ ጠየኩት። በፈግታ ትክ ብሎ ሲመለከተኝ ቆይቶ ምንም ሳይመልስልኝ ማዘዣውን ተቀብሎኝ ወጥቶ ሄደ።
የተላከው ሲቲ ስካን ሲደርስ ከአልትራሳውንዱ ጋር ተመሳሳይ ነበር። የተፈጠረውን ለማስረዳት ቃላቶች አጠሩኝ። የት እንደ ቆየ ለማወቅ በጣም ጓጓሁ። በድጋሚ ጠየኩት። በተረጋጋ አንደበቱ የማርያም ጠበል እንደ ቆየና ወሩን ሙሉ ጠበል ብቻ እንደጠጣ እና መጨረሻ አካባቢ ከአንጀቱ ውስጥ የሆነ ባዕድ ነገር ተጠቅልሎ እንደወጣ አጫወተኝ።
ከዚያ በኋላ ምንም ነገር መናገር አልቻልኩም። እርሱም አመስግኖኝ ወጥቶ ሄደ። የሰው ልጅ በዚች ምድር ላይ ሲኖር ብዙ ተአምረኛ ነገሮችን ፈጥሯል አግኝቷልም። በዚያም የተነሣ የብዙን ነገር ምክንያትና ውጤት ለመረዳት ችሏል ።ነገር ግን እንደነዚህ ዓይነት ገጠመኞች ሳይንስ ማስረዳት የማይችላቸው “ዱብዳዎች” ናቸው።
በሳይንስ የጎለበተው ጭንቅላቴ ይህንን ተአምር ለመቀበል ጊዜ ፈጅቶበታል። ምናልባትም HEPATIC FASCIOLA ሊሆን ይችላል ብዬም አስቤ ነበር። ነገር ግን እርሱስ ቢሆን….?
እስከዛሬ ድረስ ይህንን ታሪክ ለብዙ ሐኪም ጓደኞቼ ባጫውትም ማንም ሰው ግን በሽታው ምን እንደ ነበረ ለምንስ ሙሉ ለሙሉ እንደጠፋ ሊረዳ የቻለ ሰው አላገኘሁም። እናንተስ ምን ታስባላችሁ......ይህንን የምታነቡ ሃኪሞች ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ልትረዱት ያልቻላችሁት የህክምና እንቆቅልሽ አጋጥሟችሁ ያውቃል?
ዛሬ የባዕታ ቀን፣ የቅድስት ማርያም በዓል ነው። ለእምነቱ ተከታዮች መልካም የባዕታ ቀን እመኛለሁ።
በጎንደር ዩንቨርስቲ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሰገነት ብዙነህ የዛሬውን በዓል አስታከው በLinkedIn ገጻቸው ላይ ካጋሩት የተወሰደ።
09/12/2025
+++ አታስመስል +++
ጌታችን ከአደገባት ናዝሬት ወደ ስድስት ኪሎ ሜትር ርቃ ያለች ሴፎሪስ (Sepphoris) የምትባል በገሊላ የምትገኝ ከተማ ነበረች። ይህችም ከተማ በጣም ደማቅ በመሆኗ "የገሊላ ጌጥ" ተብላ ትጠራለች። በውስጧም ታላቅ የቴያትር አዳራሽ ነበራት። በጥንታውያን የሮምና የግሪክ ቴያትር ታሪክ ልክ እንደ ዛሬው ገጸ ባሕርይን ለመላበስ (ለመምሰል) የሚረዳ የሜካፕ ሙያ ሳይመጣ በፊት፣ ተዋናይዎቹ የኃዘንና የደስታ መልክ ያላቸውን ጭንብሎች ለብሰው ነበር የሚተውኑት። እነዚህም ጭንብሎች "persona" የሚል መጠሪያ ሲኖራቸው ትርጉሙም "ጭንብል"/"mask" ማለት ነው። (በነገራችን ላይ personality የሚለው ቃል persona or mask ከተባለው ከዚሁ ግንድ መውጣቱን ልብ ይሏል።)
የሥነ ቅርስ ተመራማሪዎችን ትኩረት ከሳቡ እና በብዛት የኀሠሣ ቁፋሮ ከሚደረግባቸው የዓለማችን ክፍሎች አንዷ ሴፎሪስ ነች። ታዲያ ጌታችን ላደገባት ናዝሬት ቅርብ በሆነች በዚህች ከተማ በተደረገ የarcheology ቁፋሮ የተለያዩ የቴያትር ጭንብሎች ተገኝተው ነበር።
ጌታችን በወንጌል ጻፎችና ፈሪሳውያንን "ግብዞች"
እያለ ይጠራቸው ነበር። ግብዝ የሚለው ቃል ደግሞ በግሪኩ "Hypocrite" የሚለው ሲሆን ትርጉሙም "ተዋናይ"/"Actor or play maker" ማለት ነው። በመሆኑም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገሩትን የማይኖሩ ነገር ግን በሰው ፊት ፍጹም መስለው ለመታየት የሚፈልጉትን አይሁድ፣ በዘመኑ በነበሩትና ጭንብል ለብሰው በሚጫወቱት የቴያትር ባለሙያዎች ስም "ተዋናይ" ብሎ መጥራቱ ያለ ምክንያት አይደለም።
ኑሮው በግልጽ የሚታወቅ እውነተኛ ሰው ቢሳሳት እንኳን ተመክሮ የመታረምና የመመለስ እድል አለው። የሚያስመስል ሰው ግን ለትምህርትና ለተግሳጽ እንኳን ያስቸግራል። እንዲሁ እንዳስመሰለም የእውነት ሳይኖር ይሞታል። ታዲያ ከዚህ ሰው በላይ ራሱን የሚበድል ከየት ይገኛል?
ጻድቅ መስሎ በሕዝብ ተከብሮ ከመኖር ይልቅ ድክመቱን ያመነ ኃጥእ ሆኖ በሰው ፊት መመላለስ ይሻላል። ፈጣሪ አንድ ቀን የኃጢአቱን ብዛት የሚቀንስለት፣ ከእሳት ነጥቆ የሚያወጣው ቸር መካሪ አያሳጣውምና።
ከአስመሳይ ጻድቅ እውነተኛ ኃጥእ ይሻላል!
አናስመስል!!!
ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
Telegram Channel: https://t.me/Dnabel
https://youtu.be/8z2qcQbR0lU
30/11/2025
“ጽዮንን ክበቡአት፥ በዙሪያዋም ተመላለሱ፥ ግንቦችዋንም ቍጠሩ፤ በብርታትዋ ልባችሁን አኑሩ”
መዝ 48:12
24/11/2025
በውጭው ካሉት ይልቅ በአንተ ውስጥ የሚገኙት ፍትወታት ጠንካራ ጠላቶችህ ናቸው። ልክ ያልተሠራለት ምኞት ከባቢሎን እሳት ይልቅ ያቃጥላል። አልጠግብ ባይነትም ከጥፉት ውኃ ይልቅ ያሰጥማል። ያልተገራ ፍላጎት ማንነትን አስጥሎ የሰይጣን ባሪያ ያደርጋል። ራስን መግዛት የሰው ልጆች ጌጥ ነው። ዮሴፍ ግብጽን ከፈርዖን ሁለተኛ ሆኖ ከገዛበት ታላቅ ሥልጣን ይልቅ፣ በጌታው ሚስት ፊት ያሳየው ራስን መግዛት ይበልጥ ይደነቃል። ጠቢቡ "በመንፈሱ ላይ የሚገዛ ከተማ ከሚወስዱ (ከሚገዙ) ይበልጣል" እንዳለ።(ምሳ 16፥32)
ራስህን ነጻ ማውጣት ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ ከውስጥህ ጀምር። ሁል ጊዜ ካልበላሁ የሚለው ሆድህ ስስት አስለምዶ በወንድምህ ላይ ጨካኝ እንዳያደርግህ ለሰውነትህ ጾም አስተምረው። "ነገ እሞታለሁና ልብላ ልጠጣ" የሚለውን የዐሣማ ፍልስፍናህን (Pig philosophy) ተውና አንተ በፈቃድህ እየተራብህ (እየጾምህ) ያለ ፈቃዱ የተራበው ወንድምህን በምጽዋት አጥግበው።
ጌታ ወደ ገሊላ የተመለሰው ሄሮድስ ከሞተ በኋላ ነበር።(ማቴ 2፥20) አንተ ውስጥ ያለውን ሄሮድስ የተባለ ክፉ ምኞት እንዲሞት ካላደረግኸው በቀር የተሰደደው ክርስቶስ ወደ አንተ ሊመለስ አይችልም። ይህ ክርስቶስን ከልብህ የሚያሳድድብህን ሄሮድስ እንዴት ልትገድለው ትችላለህ? እርሱንስ ወግተህ የምትጥልበት የብረት ካስማ ምን ይሆን? ለዚህስ ከጾም እና ከጸሎት የሚበረታ ምንም ዓይነት የጦር ዕቃ አታገኝም። በል እነዚህን ይዘህ ዝመትበት።
መልካም የነቢያት ጾም ይሁንልን!
ዲያቆን አቤል ካሳሁን
Telegram: Contact @Dnabel
04/11/2025
ኦርቶዶክሳውያን በመጣው በሄደው ሁሉ እንዲህ መጫወቻ ሲሆኑ፣ ሕይወታቸውም ዋጋ እንደ ሌለው እንደ ከንቱ ነገር ተቆጥሮ ደማቸው በየአውራጃው ሲፈስ ከማየት በላይ አእምሮን የሚያሳምም ምን ነገር አለ?
ምንም የማያውቁ ሕፃናት ሰውነታቸው ከአውሬ በከፋ ጭካኔ በካራ ሲተረተር ስናይ ይህን “ኦርቶዶክስ ጠልነት” በምን ምክንያት ልናስተባብለው እንችላለን? ግፍ እና ጭፍጨፋው የሚቆመው መቼ ነው?
ብዙ ጥያቄ አልጠየቅንም። ጥያቄያችን አንድ ነው፦ “በግፍ አንገደል”፣ “ሕፃናቶቻችን በማተባቸው ምክንያት የአረመኔዎች ስለት መጫወቻ አይሁኑ!”፣ “ቢያንስ እንደ ሰው እንድንኖር ተዉን” የሚል። በዚህ ሁሉ የመከራ ድግስ መሐል በስቃያችን ላይ የሚላግጡ እና ጻድቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን ፍርድ እንዳሻቸው አግድም ሊነዱ የሚያምራቸው ነውረኞችን “እግዚአብሔር እንደ ሥራቸው ይመልስላቸው!” ከማለት በቀር ሌላ ምን ቃል አለን? በእርግጥም የእግዚአብሔርን የፈራጅነቱን ፊት ማየት ፈልገው እንደ ሆነ እንደ ምኞታቸው ፊተኞች ቀዳሚ ያድርጋቸው።
29/10/2025
“ቅዱስ ጳውሎስ” እሑድ ጥቅምት 16 2018 ዓ. ም. በድሬደዋ ከተማ እጅግ ባማረ ሁኔታ ተመረቀ። በመርኃ ግብሩ ላይ መምህር ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ የመጽሐፍ ዳሰሳውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ዘማሪት ሰላማዊት መላኩ ደግሞ በዝማሬው አገልግሎት አብራን ነበረች።
ይህን ምርቃት አስቦ በማቀድ እና ውብ አድርጎ በማሰናዳት የድሬ ቅርጫፍ የኢጃት ቤተሰቦች እንዲሁም የሳ/ደ/ኃ/ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ፍሬ ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት ያልተሰሰተ ጉልበታቸውን ስላፈሰሱ እጅግ አድርገን እናመሰግናቸዋለን።
“ቅዱስ ጳውሎስን የጠራኸው ጥዑመ ስም ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፣ እኛንም በሰማያት በሚሆነው ሰርግህ ላይ ጥራን”
አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
28/10/2025
+++ "ጠባቡ በር" +++
ብዙ ቅዱሳን እጅግ አጥብቀው ይፈልጓታል። እርሷንም ለማግኘት ብዙ ዋጋ ይከፍላሉ። እስከ ደም ጠብታ ደርሰው ይጋደላሉ። ባገኙዋትም ጊዜ ውስጣቸው በጸጥታ ይሞላል። ሕዋሳቶቻቸውም እንደ አመዳይ የነጹ እንደ ባዘቶም የጠሩ ይሆናሉ። ይህች ቅዱሳኑ ብዙ የሚደክሙላትና ደጅ የሚጠኗት ጸጋ ማን ትሆን? በአጭር ቃል "ዝምታ" ትሰኛለች።
አንዳንድ ሰው "ንግግር ዋጋ ያለው እና የሚጠቅም ነገር ሆኖ ሳለ፣ ታዲያ ለምን ዝምታ ጥሩ እና የበጎ ሥራዎች ሁሉ ቁንጮ ተደርጎ ይወሰዳል?" ሲል ሊጠይቅ ይችላል። ለዚህ መልሱ ቀላል ነው። የሰው ልጅ በጣም በቀላሉና ብዙ ጊዜ የሚበድልበት ሕዋሱ አንደበቱ ነው። የትም ሳይጓዝ፣ ምንም ሳያይ፣ በጣምም ሳይደክም ባለበት ብቻ ጥቂት ተንቀሳቅሶ ትልቅ ጥፋት ሊያደርስ የሚችል በሰው ውስጥ ያለ ትንሽ ነገር ቢኖር ምላስ ነው። ይህ ስለሆነም አንደበት "ዝምታ" የሚባል ንቁ ጠባቂ፣ ጠንካራ ልጓም ያስፈልገዋል።
ሳይንሱ ሰው የንግግር ችሎታውን ማዳበር እንዲችል ብዙ እንዲናገር ያበረታታል። ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ርቱዕ ተናጋሪ ለመሆን ዝምታ ዓይነተኛ መንገድ መሆኑን ታስተምራለች። ቅዱስ ባስልዮስ ዘየዐቢ "በማይቋረጥ የዝምታ ልምምድ ውስጥ ካልተገባ በቀር መልካም ንግግር (ተናጋሪነት) አይገኝም" ይለናል። ቅዱስ ይሩማሲስም "የኋላ ንግግራችንን ማቅናት እንችል ዘንድ ከሁሉ በፊት ዝምታን እንማር" ሲል ይመክረናል። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙም ይህን ይለናል "ንግግራችን የዝምታ ያህል ጥቅም ያለው ይሆን ዘንድ እመኛለሁ... እንድናገር ግድ በተባልኩ ጊዜ የሚሰሙትን ወደ ጸጥታ በንግግር እና በዝምታም ጭምር እመራቸው ዘንድ ስለ "ዝምታ" ካልሆነ በቀር ስለ ሌላ ነገር አላወራሁም። ይህም ስለ ዝምታ ያለኝ የእኔ እይታ፣ ስለ ንግግርም ያለኝ የእኔ ፍልስፍና ነው"። በሥጋዊ ጥበብ የዐዋቂነት መገለጫው መናገርና ጥሩ ተሟጋች መሆን ሊሆን ይችላል። በመንፈሳዊው ዓለም ያሉ ጠበብት ግን ብዙ ሲያውቁ ብዙ የማይናገሩ በመሆን ይታወቃሉ። በጣም ሲራቀቁ ደግሞ ዝምታና ተመስጦ መገለጫቸው ይሆናል።
አንደበትን መግዛት ማለት የሥነልቡና ባለሙያዎች "Suppression" እንደሚሉት ዓይነት ስሜትን መጨቆን ወይም ማፈን አይደለም። አንደበትን በመቆጣጠርና ስሜትን በማፈን መካከል በጣም ሰፊ ልዩነት አለ። በውስጥ የሚቀጣጠለውን ፍትወት ከፍርሐት የተነሣ በንግግር ወይም በድርጊት መግለጥ ሳይቻል ሲቀር ስሜትን ማመቅ (Suppression) ይባላል። አንደበትን መግዛት ግን ምላስን ለበጎ ንግግር መለየት፣ ማንጻት ነው። በአጭሩ ያኛው Suppression ይህኛው ደግሞ purification ነው።
ዝምታ ራሳችንን የምናይበት ጥሩ መጽሔት(መስታወት) ነው። አብዛኛውን ሰዓት በወሬ ተጠምዶ የሚውል ሰው ራሱን የሚመለከትበት እድል አይኖረውም። በሌሎች ኃጢአት ሲፈርድ፣ ሲተችና ሲያማ ስለሚውል የራሱን ስህተትና ውድቀት ለማወቅ ይቸገራል። ቀኑን ሙሉ እንዲሁ ሲያወራ የሚውል ሰው የሚያሳዝነው ዝም አለማለቱ ብቻ ሳይሆን የሚጠቅም ነገር የማይናገር መሆኑም ጭምር ነው። ነገር ግን ማር ይስሐቅ እንደሚለው "አንድ ሰው ከሰዎች ጋር ብዙ ማውራት ባቆመ ጊዜ ወደ ራሱ ይመለሳል። በእግዚአብሔርም ፊት ምግባሩን ማቅናት ይጀምራል"።
የሥጋ አንደበታችንን መቆጣጠርና ዝም ማስባል ስንችል የነፍስ ጆሮአችን ንቁህ መሆን ይጀምራል። ስለዚህም ነፍሳችን ሳይሰለች ከልባችን ደጅ ቆሞ የሚያንኳኳውን የመልካሙን እረኛ ድምጽ ትሰማለች። ደጇንም ከፍታ ታስገባዋለች። ከእርሱም ጋር ለእራት ትሰየማለች።(ራእይ 3፥20) በእውነት ይህ እንደ ምን ያለ መታደል ነው? ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር "የዝምተኛ ሰው ጆሮ የእግዚአብሔርን ድንቆች ትሰማለች" ያለው ለዚህ ይሆን?!
ታዲያ ለብዙ ዘመናት ከልባችን ደጅ ቆሞ የሚንኳኳውን ትጉህ እረኛ ድምጹን ሰምተን ለማስገባት ለምን ዝም አላልንም? ራሳችንንስ ከሁከት እና ከከንቱ መለፍለፍ ስለ ምን አልጠበቅንም? አንደበትን መግታት ቀላል አይደለማ! በአንድ ወቅት ቅዱስ እንጦንስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሎ ነበር :- "ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጠባቡ በር እንገባ ዘንድ አዝዞናል።አንደበትን ከኃጢአት መጠበቅ ካልሆነ በቀር ይህ ጠባብ በር ምንድር ነው? እንግዲያውስ ደካማ እና ክፉ የሆነውን ቃል እንዳያወጣ እየተጋደልን ለአንደበታችን ብርቱ ዘብ እናቁም"
በጠባቡ በር እንግባ!
ዲያቆን አቤል ካሳሁን
https://t.me/Dnabel
25/10/2025
+++ ‹‹በእግዚአብሔር ፈንታ›› +++
የአእምሮ ሕመም ሕክምና ይሰጥባቸው ከነበሩ ማዕከላት በአንዱ እንዲህ ሆነ፡፡ ነርሷ ሕመምተኛውን ‹‹አንተ ማን ነህ?›› ስትል ትጠይቀዋለች፡፡ እርሱም ‹‹ናፖሌዎን›› ነኝ ብሎ ይመልሳል፡፡ ‹‹ናፖሌዎን መሆንህን ማን ነገረህ?›› ብትለው ‹‹እግዚአብሔር ነዋ›› ሲል ፈርጠም ብሎ መለሰ፡፡ ይህን ጊዜ ከአጠገባቸው ሆኖ ምልልሱን ይሰማ የነበረ ሌላ ታካሚ ድንገት ጣልቃ ገብቶ ‹‹ኸረ እኔ አልነገርኩት›› አለ፡፡
ይህን ታሪክ ስትሰማ ፈገግ አላልህም? ‹ሰው ራሱን ‹‹እንደ እግዚአብሔር›› አድርጎ የሚቆጥረው አእምሮውን ሲታመም ብቻ ነው› ብለህስ አላሰብህም፡፡ እውነታው ግን ሌላ ነው፡፡ ጤነኛ አእምሮ እንዳለን የምናስብ ብዙዎቻችን ኑሯችን እና እንቅስቃሴያችንን ብንፈትሽ ነገረ ሥራችን ሁሉ ‹‹በአምላክ ፋንታ›› ነው፡፡ አፍ አውጥተን ‹‹እኔ እግዚአብሔር ነኝ›› አንበል እንጂ እንዲህ ከማለት የማይተናነስ ሥራ ግን እንሠራለን፡፡
ፍርድ የእግዚአብሔር ነው፡፡ እኛ ግን ወንድሞቻችን ላይ በመጨከን ስንት ጊዜ በክርስቶስ የፍርዱ ዙፋን ላይ ተቀመጥን፡፡ የሰውን ድካም ሳንረዳ ፈጥነን በመፍረድ ስንት ጊዜ ራሳችንን በእግዚአብሔር ቦታ አስገባን? እስኪ ዮሴፍን እናስበው፡፡ ወደ ግብጽ ባሪያ አድርገው በግፍ የሸጡት ወንድሞቹ ከአባታቸው ሞት በኋላ እርሱ ወደ ተሾመበት ግብጽ መምጣት በፈለጉ ጊዜ፣ የክፋታችንን ብድራት ያስከፍለናል ብለው ስለፈሩ ‹‹በደላችንን ተውልን›› ሲሉ መልእክተኛ ልከውበት ነበር፡፡ የዋሁ ዮሴፍም ይህንን ሲሰማ እያለቀሰ እንዲህ አላቸው ‹‹አትፍሩ፤ እኔ በእግዚአብሔር ፋንታ ነኝን?››፤ አይደለም ሳታውቀው ዐውቀኸው እንኳን በበደለህ ወገንህ ላይ ለመፍረድ ልብህ በከጀለህ ጊዜ ለራስህ የዮሴፍን ጥያቄ ጠይቀው፡፡ ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፋንታ ነኝን?›› (ዘፍ 50፡19)
ራሱን መምራት ያልቻለ ደካማ ሌላው ላይ በፍርድ ለመሠልጠን ሲሞክር ከማየት በላይ እግዚአብሔርን ምን የሚያሳዝን ነገር አለ?
ሁሉን የሚያውቅ እግዚአብሔር ነው፡፡ ነገር ግን የሁሉ ጥበብ መፍለቂያዎች እንደ ሆንን፣ ከእኛ የተሠወረ አንዳች እንደሌለ እያሰብን ‹‹አምላክ አምላክ የምንጫወት›› ጥቂቶች አይደለንም፡፡ የእኛ ጣት ያልገባበት ሁሉ የማይጥመንና ትክክል የማይመስለን፣ እኛ ካልመራን፣ የእኛ ቡራኬ ከሌለበት የምናራክስ፣ ‹‹አላውቅምን›› የማናውቅ፣ ብዙኃኑን እንደ ጨዋ (ምንም የማያውቅ) የምንቆጥር አያሌ ነን፡፡ የሚያሳዝነው ግን ዓለም በአንድ ወይም በጥቂት ሰው ፈቃድ ስላልተገነባች በአንድ ወይም በጥቂቶች ፈቃድ ብቻ ልትመራ አትችልም፡፡ ሁሉን በሁሉ ማድረግ የሚችለው ሁሉን የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡
‹‹ዕረፉ፤ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ ዕወቁ›› መዝ 46፡10
ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
ጥቅምት 15/ 2015 ዓ.ም.
https://t.me/Dnabel
22/10/2025
“ቅዱስ ጳውሎስ” ወደ ድሬ መንገድ ጀምሯል። የፊታችን እሑድ 9:00 ሰዓት ላይ በሳ/ደ/ኃ/ ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ፍሬ ሃይማኖት ሰ/ት/ቤት አዳራሽ እንገናኝ።
ኑ የጳውሎስ የፍቅሩ ማኅበርተኞች እንሁን!
18/10/2025
“ቅዱስ ጳውሎስ” 2ኛ እትም ዛሬ ወጥቷል። የመጀመሪያው እትመት ቁጥሩ ብዙ ቢሆንም በዚህ ፍጥነት በማለቁ እናንተ አንባብያንን እናመሰግናለን። ስላደረሳችሁንም ፍቅር የተሞላበት ቀና ምላሾች ቅዱሱ ይስጥልን።
“ኑ የጳውሎስ የፍቅሩ ማኅበርተኞች እንሁን!”
#መጽሐፉ በአርጋኖን መጻሕፍት መደብር ይከፋፈላል!
አርጋኖን መጻሕፍት መደብር 5ኪሎ ቅድስት ማርያም ሕንፃ ፊት ለፊት
0988888589/0967171111