29/09/2022
አመራር!!! ልናመልጠው የማንችለው እውነታ!!!
ብዙ ሰዎች ስለ አመራር ማወቅ የሚገባቸው በድርጅት ወይም በማሕበራዊ አመራር መስክ ውስጥ የተሰማሩ ሰዎች ብቻ ናቸው ብለው ያስባሉ፡፡ ይህ ግን ከእውነት የራቀ አመለካከት ነው፡፡
ስለ አመራር ትርጉም፣ ባህሪይና ሂደት መገንዘብ ራሳችሁን ከመምራት ጀምሮ ታላቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ራእያችን ለመጀመርና ለማስቀጠል፣ የትምህርት ሂደታችንን በተሳካ ሁኔታ ለመከታተል፣ ስራችንን በስኬታማ ሁኔታ ለመስራት፣ ቤተሰባችንንና አልፎም ሕብረተሰቡን በበቂ ሁኔታ ለመምራት በአመራር ጥበብና ግንዛቤ መብሰል የግድ ነው፡፡
ራሱን በመምራት የአመራር ግንዛቤና ክህሎት ያሳደገ ሰው ቢወድም ባይወድም በሌች ሰዎች ላይ መልካም ተጽእኖን ስለሚመጣ በማሕበራዊው፣ በንግዱ፣ በስራውና በመሳሰለሉት መስኮች የአመራርን ደረጃና ከፍታ መውጣቱ እይቀርም፡፡ የተጽእኖ ሰው የሚኮነው እንደዚህ እየተባለ ነው፡፡
የአመራር ትርጓሜና አስፈላጊነት
“መሪ ሰዎች መሄድ ወደሚፈልጉበት ቦታ ይወስዳቸዋል፡፡ ታላቅ መሪ ግን ሰዎች መሄድ ባይፈልጉም ለጥቅማቸው መሄድ ወደሚገባቸው ቦታ ይወስዳቸዋል” - Rosalynn Carter
አመራር ከሁሉ በፊት የግል ሕይወት የሚመለከት ጉዳይ ሲሆን፣ መንግስታዊ የሆኑና ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ የትምህርት ተቋሞችን፣ ቤተሰብንና የመሳሰሉትን የተለያዩ ሕብረተሰባዊ ተቋሞችን ሁሉ የሚነካ ዘርፈ-ብዙ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ማህበራዊ ስብስቦች የቆሙላቸው ዓላማዎች ስላላቸው አነዚያን ዓላማዎች እውን ለማድረግ አመራር የግድ ነው፡፡ ለዚህ ነው “አመራር” የሚለውን ቃል ፍቺ በሚገባ ማጤን ያለብን፡፡
የቃሉ አመጣጥ
“መምራት” (በእንግሊዝኛው “to lead”) የሚለው ቃል “ሌድን” (“leden”) ወይም “ሎዳን” (“loadan”) ከሚለው ጥንታዊ የእንግሊዝኛ ቃል የመጣ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ትርጓሜውም፣ “ወደ ፊት ማስኬድ”፣ “ምሪት መስጠት”፣ “መንገዱን ማሳየት” ነው፡፡
አመራር የሚያካትታቸው እውነታዎች
አመራር የሚያካትታቸው እውነታዎች በርካታ ቢሆኑም በቀላሉ ሰብስበን ስናስቀምጣቸው የሚከተሉትን አራት ዋና ዋና ሃሳቦች እናገኛለን፡፡
1. ራዕይ - መሪውም ሆነ ተከታዮቹ በውስጣቸው ያዩት አንድ ሊያከናውኑት የሚፈልጉት ተግባር ወይም ሊደርሱበት የሚፈልጉት ግብ፡፡
2. መሪ - ራእዩን እውን ለማድረግ በተከታዮች ምርጫ ወይም ራእዩን በማምጣትና ፈር-ቀዳጅ በመሆን ራሱን ለመሪነት የሚሰጥ ሰው፡፡
3. ተከታዮች - ለታየው ራእይና ለታለመው ግብ ስኬታማነት በፈቃደኝነት መሪውን ለመከተልና ለመደገፍ ራሳቸውን ያቀረቡ ሰዎች፡፡
4. የአመራር ሂደት - ወደታየው ራእይ ተከታዮችን ለማድረስና ግብንና ቁልፍ የሆኑ መርሆችን በመያዝ የሚደረግ ጉዞና ተግባር፡፡
እነዚህ ከላይ የዘረዘርናቸው ነጥቦች አመራርን ወደ መኖር የሚያመጡ ቅድመ-ሁኔታዎች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ እውነታዎች እንዱ ከጎደለ አመራር የሚለው ሃሳብ መሰረት ይናጋል፡፡
ስለ አመራር እውነታ በሚገባ ስትገነዘቡና ስትበስሉ ወደ ማሕበራዊ የአመራር መስክ ማደጋችሁ አይይቀርም፡፡ ወደዚያ ከማደጋችሁ በፈመድረሳችሁ በፊት ግን ሁለት ነገሮች ይታዩባችኋል፡-
1. ራሳችሁን በመልካም ዲሲፕሊን የመምራት ሁኔታ፡- የምናደርገውን ነገር አለማወቅ፣ አንድን ነገር መጀመር አለመቻልና የጀመሩትን እስከመጨረሻው አለመቀጠል የአመራርን እውነት ያለመገንዘብና ራስን በመምራት ጥበብ ያለመብሰል ምልክቶች ናቸው፡፡
2. በቤት፣ በት/ቤት፣ በስራና በመሳሰሉት መስኮች መሪዎች የመገንዘብና የመታዘዝ ሁኔታ፡- በአመራር ግንዛቤ የበሰለ ሰው መሪዎችን ይገነዘባል፡፡ የአመራርን አስቸጋሪነትና ሂደት በሚገባ ስለሚገነዘብ መሪዎችን መደገፍና ለመሪዎች መታዘዝ አያስቸግረውም፡፡
“አንድ ሰው ራሱን ለመምራት የሚያሰፈልጉት መሰረታዊ ዲሲፕሊኖች ምን ምን ናቸው?”
የአመራር ብቃት - የተፈጥሮ ስጦታ ወይስ ሂደት? (Nature or Nurture?)
“መሪዎች በሂደት ወደ መሆን ይመጣሉ እንጂ መሪ ሆነው አይወለዱም፡፡ እንደማንኛውም ነገር በብርቱ ስራና ጥረት ወደ መሆን ይመጣሉ” - Vince Lombardi
አንድ ሰው በአመራሩ አስገራሚ የሆነን ስኬት ሲያዝመዘግብ “የአመራር ተሰጥኦ ያለው ሰው ነው” በመባል ይነገርለታል፡፡ ይህ አባባል የአመራር ብቃት ጉዳይ በሂደት የሚዳብር ሳይሆን በተፈጥሮ የሚመጣ እንደሆነ የመጠቆም ባህሪይ አለው፡፡ ከዚህ አመለካከት በመነሳት አንዳንዶች እንደሚያምኑትና እንደሚናገሩት አንድ ሰው ወደ አመራር ለመምጣት በተፈጥሮ መሪ ሆኖ ወይም የአመራርን ብቃት ተክኖ መወለድ አለበት፡፡
በእነዚህ ሰዎች አመለካከት አንድ ሰው ሲወለድ፣ ወይ መሪ ነው ወይም ደግሞ አይደለም ብለው ያምናሉ፡፡ ይህም አመለካከት ልዩ “የተፈጥሮ ባህሪይ ጽንሰ-ሃሳብ” (Great Man Theory) በመባል ይታወቃል፡፡ በተቃራኒው በሌሎች አመለካከት አመራር የሂደት ጉዳይ ነው - ሰዎች በሂደት የሚማሩት፣ የሚለምዱትና የሚያዳብሩት፡፡
አንዳንድ ሰዎች በተፈጥሮአቸው የመሪነትን ዝንባሌ ይዘው መወለዳቸውን ልንክደው የማንችለው እውነት ነው፡፡ ነገር ግን አነዚህ ሰዎች ያንን ይዘው የተወለዱትን የተፈጥሮ ዝንባሌ ካላሳደጉት በውጤታቸው ከማንም ሰው አይለዩም፡፡ ውጤታማ መሪዎችን ለየት የሚያደርጋቸው ዋነኛ ባህሪይ መማርና መሻሻል ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ሂደትን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡
በመሪነት ዝንባሌ መወለድ - ሁለት አይነት ሰዎች
• በመሪነት ዝንባሌ የተወለደ፣ ዝንባሌውን ግን ያላሳደገ፡፡ ይህ አይነቱ ሰው በውስጡ ይዞ የተወለደውን የመሪነት ዝንባሌ እንዲያሳድግ ይመከራል፡፡
• በመሪነት ዝንባሌ የተወለደ፣ ዝንባሌውንም ያሳደገ፡፡ ይህ አይነቱ ሰው ራሱን በማሻሻሉ እንዲገፋበት ይመከራል፡፡
ከመሪነት ዝንባሌ ውጪ መወለድ - ሁለት አይነት ሰዎች
• ከመሪነት ዝንባሌ ውጪ የተወለደ፣ ዝንባሌውንም ያላሳደገ፡፡ ይህ ሰው ከአመራር ብቃት እጅግ የራቀ ሰው ነው፡፡ ያለችውን “ጠባብ” እድል ግን ተጠቅሞ ራሱን ለመሻሻል መስጠትና ማደግ ይችላል፡፡
• ከመሪነት ዝንባሌ ውጪ የተወለደ፣ ከጊዜ በኋላ ግን የመሪነትን ዝንባሌ ያሳደገ፡፡ ይህ አይነቱ ሰው ራሱን ለማሻሻል ባለው ጥረት ወደ ብቃት በማደግ ላይ ያለ ሰው ነው፡፡
አንድ ሰው ሲወለድ የመሪነትን ዝንባሌ ይዞ መጣም አልመጣ በሂደት ወደ መሪነት ሙላት ሊደርስ እንደሚችል ማሰቡ አሳማኝ ነው፡፡ አመራር ከተፈጥሮ ባህሪይ ጋርና ከሂደት ጋር የመዛመዱን እውነታ ሚዛናዊ ለማድረግ የሚከተሉትን ነጥቦች እለግሳለሁ፡፡
1. ለጊዜው አመራር አልተሳካልንም ማለት ወደ መሪነት ማደግ አንችልም ማለት አይደለም፡፡
2. ብንወድም ባንወድም ከመሪነት ራሳችንን ማግለል አንደማንችል እንገንዘብ፡፡
3. የአመራርን ችሎታ የማይጠይቅ ምንም አይነት ተግባር በምድር ላይ እንደሌለ እናስታውስ፡፡
4. ወደሚቀጥለው የአመራር ደረጃ ለመድረስ ማድረግ የሚገባንን ነገር እናድርግ፡፡
5. በፍፁም ከመማር አናቋርጥ፡፡
በነገው ፖሰቴ ተጨማሪ የአመራር እውነታዎችን ይዤ እሰከምመለስ ይህንን በዚህ ጥያቄ ላይ ያላችሁን የግል ግንዛቤ ፖስት በማድረግ አጋሩን፡-
“አንድ ሰው በዛም አነሰም በተፈጥሮ ያገኘውን የአመራር ብቃት ለማሳደግ ምን አይነት መንገዶችን መጠቀም ይችላል?”
Dr. Eyob Mamo
👇👇👇👇👇
(ራስንም ሆነ ሌሎችን በመምራት ለማደግ “አመራር A to Z” የተሰኘውን መጽሐፌን አንብቡት)