11/05/2026
የንባብ ክፍል፡- ሰቆቃው ኤርምያስ 1፣ 2፣ 3፣ 4 እና 5
ሰቆ. ኤርምያስ 1፤ ሕዝብ ተሞልታ የነበረች ከተማ እንዴት የተተወች ሆና ቀረች! እንዴት እንደ መበለት ሆነች! ባሪያ ሆናለች፤ ታለቅሳለች የሚያጽናናት የለም፤ ይሁዳ ተማርካ ሄደች፤ ባለጋሮቿ ገዦቿ ሆኑ፤ ከኀጢአት ብዛት የተነሣ እግዚአብሔር ከባድ ሀዘን አምጥቶባታል፤ ጠላቶቿ ሳቁባት፤ ኢየሩሳሌም ከባድ ኀጢአት ሠርታለች፤ ስለዚህ የረከሰች ሆናለች፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ መከራዬን ተመልከት፤ ጽዮን እጆቿን ዘረጋች፤ የሚያጽናናትም የለም።
ሰቆ. ኤርማያስ 2፤ እግዚአብሔር የጽዮንን ሴት ልጅ በቁጣው ደመና እንዴት ጋረዳት! የያዕቆብን መኖሪያ ሁሉ እግዚአብሔር ያለ ርኅራኄ ዋጣቸው፤ በቁጣው አፈረሳቸው፤ ለቅሶና ሰቆቃ በዛ፤ እግዚአብሔር መቅደሱን ተወ፤ ቁስልሽ እንደ ባሕር ጥልቅ ነው፤ ማን ሊፈውስሽ ይችላል? እናቶች ሕፃኖቻቸውን ይብሉን? ካህኑና ነቢዩስ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ይገደሉን? ወጣትና ሽማግሌ አንድ ላይ ወደቁ።
ሰቆ. ኤርምያስ 3፤ በቁጣው በትር መከራ ያየ ሰው እኔ ነኝ፤ ጸሎቴን መስማት አልፈለገም፤ መንገዴን ዘጋ፤ ያለ ረዳት ተወኝ፤ መላገጫ ሆንሁኝ፤ ሆኖም ተስፋ አለኝ፤ ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና፤ ጌታ አይጥልም፤ ቢያሳዝንም እንደ ምሕረቱ ብዛት ይራራልና፤ መንገዳችንን እንመርምር፤ እንፈትን፤ ወደ እግዚአብሔርም እንመለስ፤ ዐምፀናል፤ ኀጢአትም ሠርተናል እንበል፤ እግዚአብሔር ከላይ ከሰማይ እስኪያይ ዐይኖቼ ዕንባ ያፈሳሉ፤ ፍርዴን ፍረድልኝ!
ሰቆ. ኤርምያስ 4፤ ወርቁ እንዴት ደበሰ! ንጹሑስ ወርቅ እንዴት ተለወጠ! እንደ ወርቅ ይቆጠሩ የነበሩ አሁን እንደ ሸክላ ዕቃ ሆኑ፤ ከውሃ ጥም የተነሣ የሕፃናት ምላስ ከላንቃቸው ጋር ተጣበቀ፤ በራብ ከሚሞቱት ይልቅ በሰይፍ የተገደሉት ይሻላሉ፤ ሴቶች በገዛ እጆቻቸው ልጆቻቸውን ቀቀሉ፤ ይህ ከነቢያት ኀጢአት፣ ከካህናቷም መተላለፍ የተነሣ ሆኖአል፤ ከሰማይ ንስሮች ይልቅ ጠላቶቻችን ፈጣኖች ናቸው።
ሰቆ. ኤርምያስ 5፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ በእኛ ላይ የደረሰውን አስብ፤ ውርደታችንን እይ፤ ተመልከትም፤ እንጨትና ውሃ በክፍያ፤ አባቶቻችን ኀጢአት ሠርተው አለፉ፤ እኛም የእነርሱን ቅጣት ተሸከምን፤ ደስታ ከልባችን ጠፍቷል፤ ወዮልን! ኀጢአት ሠርተናልና፤ ለምን ፈጽመህ ትረሳናለህ? ስለምንስ ለረጅም ጊዜ ትተወናለህ? ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን፤ ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ!
ከተማርኩት፡-
• የኀጢአት፣ እግዚአብሔርን ያለመስማት ውጤት ምን ያህል ከባድ እንደ ሆነ ይህ መጽሐፍ ያሳያል። እግዚአብሔር ባለመስማት በኀጢያታቸው የጸኑትን ይቀጣል፤ ቅጣቱም ከባድ ነው!
• ነቢዩ የቀደመችዋን ኢየሩሳሌም ከፈራረሰችው ጋር እያስተያየ በእግዚአብሔር ፊት ያለቀሰበት መንገድ ልብ የሚነካ ነው!
• ለእግዚአብሔር ፍርድ ዕውቅና በመስጠት በእውነተኛ ንስሐ መመለስ ያስፈልጋል።
• “ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኀራኄው አያልቅምና፤ ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትም ብዙ ነው።”
• “እግዚአብሔር ዕድል ፈንታዬ ነው፤ ስለዚህ ተስፋ አደርገዋለሁ። እርሱን ተስፋ ለሚያደርጉት ለሚፈልገውም ሰው እግዚአብሔር መልካም ነው፤ ሰው የእግዚአብሔርን ማዳን ዝም ብሎ ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው።”
• “እግዚአብሔር ሰውን ለዘላለም አይጥልምና፤ መከራ ቢያመጣ እንኳ ይራራል፤ ታላቅ ፍቅሩ አይለወጥምና።”
• “እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ መልሰን፤ እኛም እንመለሳለን፤ ዘመናችንን እንደ ቀድሞው አድስ!
ቃሉን እንጸልይ፡-
• በግል ሕይወታችን፣ በቤተ ሰባችን፣ በቤተ ክርስቲያንና በአገር ደረጃ ስለ ተለያዩ የፈራረሱ፣ የተበላሹ ነገሮች ወደ እግዚአብሔር እንጸልይ!
• እግዚአብሔር በሥራው ትክክለኛ አምላክ እንደ ሆነ ዕውቅና በመስጠት እውነተኛ ንስሐ እናድርግ!
• እግዚአብሔርን እንደምንታመነው እና ተስፋችን እርሱ ብቻ እንደ ሆነ በመግለጽ እንጸልይ!
ቢያሳዝንም እንደ ምሕረቱ ብዛት የሚራራ አምላክ ተስፋችን ነው! ጸጋ ይብዛልን!