04/12/2020
ደብተራ ማለት ምን ማለት ነው?
ስለኢትዮጵያ ታሪክ አንስተህ በጥንት ጊዜ እንዲህ ነበር፣ ይህ ተፈፅሞ ነበር፣ ይህ በዚያ የዘመን መንፈስ እንዲህ ነበር የሚታየው፣ ያን ዘመን በዚህ ዘመን መነፅር መመልከት አግባብ አይደለም….. እያልክ ስትከራከር አንዳንድ ከእውቀት የፀዱ፣ ምንጫቸው ፅንፈኞች፣ ለፅንፈኞች ሀሳብ ያቃበሉ መሰሪ ሚሲዮናውያን፣ በዚህ ዘመን ደግሞ ዊከፒድያን የመሰሉ ማንም እየገባ ከሚፀዳዳበት ድረገፅ ያገኙትን ትርክት እንደ እውቀት የሚወስዱ ሰዎች ከላይ እንደመግቢያ ስላነሳሁት ሀሳብ አንድ አይነት መልስ አላቸው። እሱም:—
“የደብተራ ተረት?!”
አብዛኞቹን ደብተራ ማለት ትክክለኛ ትርጉሙ ምንድነው? ብሎ ለጠየቀ ትክክለኛ መልስ አልሰጡም። ስህተቱ ከእውቀት ማነስ ጋር ይያያዛል። ምንጩ ደብተራ ማለት ምን ማለት ነው? ማነው ደብተራ? ለሚለው ጥያቄ የተብራራ መልስ ካለማግኘት ጋር ይገናኛል። እስቲ ዛሬ የሚሰሙኝ ከሆነ ስለደብተራ የሚከተለውን ፅሁፍ ላጋራ።
ለመሆኑ ደብተራ ማለት ምን ማለት ነው?
‹ደብተራ› የሚለው ቃል ጥሬ ትርጉሙ ‹ድንኳን› ማለት ነው፡፡ እንዲሁ መደበኛው አይነት ድንኳን ሳይሆን ከጥንት ዘመን ጀምሮ ነገስታቱ ከሀገር ሀገር ለማስተዳደርና አቤቱታ ለመስማት፣ ያመፀን ለማስገበር ይዟዟሩ ስለነበረ፣ አብራቸው የምትጓዝ የጸሎት ታቦት አብራቸው ትጓዝ ነበር፡፡ ለዚህች ታቦት የምትሆን ጥብቅ የተለየች ድንኳን ይዘጋጅ ነበር፡፡ ታቦቷ በቤተ መንግሥት ግቢ ተተክላ ትቀመጥና ንጉሡ ከቦታ ወደ ቦታ ሲንቀሳቀስ ተነቅላ ትንቀሳቀስ ነበር፡፡ በዚህች ድንኳን ውስጥ ማንም ዘው ብሎ አይገባም። የተለዩ ጠቢብ ካህናት ናቸው የሚገቡት። በድንኳን መቅደስ ውስጥ ለአገልግሎት የሚመረጡት በዕውቀታቸውና በንጽሕናቸው፣ በስነምግባራቸው፣ በአስተሳሰብና እውቀታቸው የተመሰገኑ ካህናት ናቸው። ባጠቃላይ ከእኩዮቻቸው በእኛ የዘመኑ አነጋገር “የሰቀሉ” ጠቢባን ብቻ ናቸው ፡፡
በዚህች ቤተ መቅደስ የሚያገለግሉት ካህናት አንዱ ሥራቸው ንጉሣውያን ቤተሰቦችን ማስተማር ስለነበር የችሎታቸው አስፈላጊነት ለድርድር አይቀርብም ነበር።
ደብተራ የድንኳኑ መጠሪያ ከሆነ አሁን ለምን ውስጡ ላሉ ጠቢባን ተንሻፎና ተንጋዶ አሉታዊ እንድምታን እንዲይዝ ሆነ?
ነገሩ ወዲህ ነው።
በነዚህ የቤተ መንግሥት መቅደስ ድንኳን ውስጥ የሚያገለግሉ ካህናት ‹በማደሪያው አዳሪው፣ በአዳሪውም ማደሪያው ይጠራል› በሚባለው መሠረት በደንኳኗ (በደብተራ) እነርሱም ‹ካህናተ ደብተራ› እየተባሉ መጠራት ስለጀመሩ፣ ቋንቋ እየተሸረፈ፣ እያጠረ መምጣቱ ሀቅ ነውና ቆይቶ ቆይቶ ‹ካህናት› የሚለው ስም ተገርዞ ‹ደብተራ› ብቻ ቀረና “ካህናተ ደብተራ” ወደ “ደብተራ” አጥሮ መጠሪያቸው ሆኖ ቀረ፡፡ ከመነሻው ታሪኩን በወጉ ለተከተለ “ደብተራ” ማለት በዕውቀትና በሕይወት ተመርጦ የቤተ መንግሥቱን የደብተራ ቤተ መቅደስ ድንኳን ለማገልገል የተሰየመ ሊቅ ካህን ማለት ነው ትክክለኛ ትርጉሙ፡፡
አሉታዊው ትርጉም እንዴት መሰረቱን ጣለ?
ደብተራዎች ከንጉሡ ጋር የተሻለ ቀረቤታ በማግኘታቸው በኋላ ዘመን የርስትና የሹመት ተካፋዮች ሆኑ፡፡ ይህ የሚያጓጓ ጥቅም እያባባ መጣ። ይህን ላለማጣት ሲሉም አንዳንዶቹ ቀኖናው ከሚያዛቸው ይልቅ ንጉሡ የሚያዛቸውን መቀበል ጀመሩ፡፡ ከስርዓት እያፈገፈጉ ሞያቸው በስልጣንና ጥቅም እየተሸረሸረ መጣ። በዚህ የተነሣም “ካህናተ ደብተራ” ለንጉሡ የሚያደሉና ለእውነት የማይቆሙ እየሆኑ መጡ። ይህም ክብራቸውን እያወረደው መጣ።
በሌላ በኩል ደግሞ ከንጉሱ ያች ድንኳን ያልገቡ፣ ማለት “ሰቃይ” ያልነበሩ ጠቢባን ደብተራዎች ወደ ታሪክ፣ ወደ የህክምና ጥበብ፣ ወደ የክዋክብት ጥናት፣ ወደ ፍልስፍና፣ ወደ ቲዎሎጂ ገብተው በርካታ ስራዎችን ሰርተዋል። የነዚህም ጠቢባን ክብርና መልካም ስራ በሌሎች እየተጋረደ መምጣቱ አልቀረም።
ምክንያቱ ደግሞ፣
በኋላ ዘመን አንዳንዶቹ ከማኅበረሰቡ በተሻለ የተማሩ መሆናቸውን በመጠቅም ጥንቆላና አስማት እንችላለን በማለታቸው በድብትርና ከለላነት ሀይማኖቱ የማይፈቅደውን ተግባር ላይ ተሰማሩ። በዚህም ‹ደብተራ› የሚለው ስም የምሁርነትና የጠቢባን ስም መሆኑ ቀርቶ ከጥንቆላና መተት ጋር የተያያዘ ስም እየሆነ መጣ፡፡ እንደማንኛውም ሞያ፣ ድብትርናም የተከበረ ሞያ መሆኑ ቀርቶ ‘ኮራፕት‘ ሆኖ ቀረ።
ደብተራ› የሚለው ስም አጠፋፍ ›ሐኪም› ከሚለው ስም አጠፋፍ ጋር ይመሳሰላል ይላሉ አንዳንድ ሰዎች፡፡ ‹ሐኪም› የሚለው ስም ትርጉሙ ‹ብልህ፣ ጠቢብ› ማለት ነው፡፡ ሐኪም አሁን የጤና ባለሞያ ነው። ጥንት ግን ሐኪም ሙያን ሳይሆን ጥበብን የሚመለከት ነበር፡፡ ‹ወስመ መምህሩ ዘመሀሮ ጥበበ አርስጣጣሊስ ሐኪም› ሲባል፣ ‹ጥበብን ያስተማረው መምህሩ ጠቢቡ አሪስጣጣሊስ ነው› ለማለት ነው፡፡
በዐረብኛም ሆነ በእብራይስጥ ትርጉሙ ይሄው ነው፡፡ የእስልምና ወርቃማው ዘመን በሚባለው ጊዜ ‹ሐኪም› ማለት በእስልምና ሃይማኖት፣ በሳይንስ፣ በመድኃኒትና በፍልስፍና፣ በሂሳብ፣ በክዋከብት ባጠቃላይ ሁለገብ ዕውቀት ያለው ጠቢብ ሰው ስያሜ ነበር፡፡
በዕብራይስጥ ቋንቋም ሁለገብ ዕውቀት ላለው የሃይማኖት መሪ የሚሰጥ ስም ነው – ሐኪም፡፡
በሀገራችን ‹ሐኪም› የሚለው ስም ለጠቢብ የሚሰጥ ስም ነበረ፡፡ በኋላ ግን ባሕላዊ መድኃኒት ለሚያውቅ ባለሞያ ሁሉ መሰጠት ተጀመረ፡፡ በየጋዜጣው ዛሬ የባሕል መድኃኒት ዐዋቂዎች ‹ሐኪም እገሌ› እያሉ ራሳቸውን የሚያስተዋውቁት ለዚህ ነው፡፡ ዘመናዊ ሕክምና ሲጀመርም በሞያው የተሰማሩት በዚህ ስም ተጠርተዋል፡፡ ሐኪም ወርቅነህን ማስታወስ ለዚህ ይረዳል፡፡ አሁን አሁን ብዙዎቹ የባሕል መድኃኒት ዐዋቂዎች ይህንን ስም ስለሚጠቀሙት ስሙ እንደ “ደብተራ” ሁሉ ከጥበብና ሞያ ይልቅ ከጥንቆላ ጋር የመያያዝ ዕጣ እየገጠመው እንዳለ እሙን ነው፡።
የደብተራም ዕጣው እንዲህ ነው የሆነው፡፡ ‹ዐዋቂ፣ ጠቢብ፣ የተመረጠ› ነበር ትርጉሙ፡፡ በኋላ ያንዳንዶች ግብር ስምን ያጠፋልና የአንዳንድ ‹ደብተሮች› ሥራ ደብተራነትን ሞያዊ ልዕልና ና ክብሩን አጠፋው፡፡ ወያኔና ፅንፈኞችም የአንዳንድ ደብተሮችን ስህተት እያሳዩ ሁሉን ደብተራ ፈረጁት።
ለዚያም ነው “ባክህ ተወው የደብተራ ተረት ነው” የሚሉት።
“አክቲቪስት” ለምሳሌ ማህበሰብ አንቂ ማለት ነው። የዛሬ መቶ አመት “ቀጣፊ፣ አጋጭ፣ ጥላቻ ነዢ፣ መሰሪ” ሆኖ ትርጉሙ ሊዛባ ይችላል።
እንጂማ፣
ደብተሮች ታሪክ ሰንደው ቋንቋ አበልፅገው፣ ህክምናን አስተምረው፣ የክዋክብት ጥናትን አስተምረዋል። ስለማህበረሰብ፣ ስለሀገር፣ ስለነፃነት ስለፍልስፍና ፅፈዋል። በየትኛውም አለም ፊደልን ከብራና እያዋሐዱ የራስን የዘመን መንፈስ ከትቦ ለትውልድ ማስተላለፍ የሰለጠነ ማህበረሰብ መሆን ነው።
በዚህ በኩል በርካታ ተመሳሳይ ምሳሌዎችን ከተለያዩ ሀገራት ማንሳት ይችላል። በእስልምናው ወርቃማ ዘመናት ሀዲስን የሰነዱ፣ ቁርኣንን ከሀፊዞች በፅሁፍ ወደ ኪታብነት የመለሱት ደብተራዎች ናቸው። እነ ቡካሪ እነ ሙስሊም፣ እነ የመዝሃብ ባለቤቶች እነ ሀኒፋ ፣ ማሊኪ እነ ሻፊኢ ደብተራዎች ናቸው። በቻይናም ሆነ በህንድ ፊደል ቀርፀው ታሪክና ትውፊትን የሚሰንዱት በእኛው ሀገር ስያሜ “ደብተራዎች” ናቸው።
አፄ ቴድሮስ መቅደላ ላይ በመሰረተው ቤተ መፅሃፍት የነዚህን ደብተሮች ስራ አጠራቅሞ እንግሊዝ በብዙ ዝሆኖች ዘርፈው ሄደዋል። እንግሊዞች የደብተራዎችን ጥበብ ለመፈተሽና ለመሰልጠን ብለው ውዱን እና የተለፋበትን እውቀት የዘረፉት። እነ ጀምስ ብሩስና አልቫሬስ ኢትዮጵያን ሲያስሱ ዋነኛው ታርጌታቸው የደብተራዎችን ስራ ነበረ።
ኢትዮጵያ ሀገር በቀል መፍትሄን የምታገኝበት ሁነኛ የእውቀት ምንጯን ባለመጠቀሟ ተጎድታለች።
ኢትዮጵያ በጣም የተጎዳችው በተለይ በጣም በጣም የተጎዳችው የስልሳዎች ትውልድ የሀገሩን ታሪክ ሳያውቅ ሀገር ለማነፅ የሄደበት መንገድ የተውሶ እውቀት ላይ መመስረቱ እና ይህም የሀሰት ትርክት ለሀገራችን አንድነት በሚያሰጋ መልኩ የስርአት ችግርን እንደ ብሄር ተቃርኖ ጉዳዩን የህዝብ ለህዝብ ቅራኔ ማድረጋቸው፣ ለዚህም የኢትዮጵያን ታሪክ አንስቶ ለመሞገት “የደብተራ ተረት” በሚል የድንቁርና ጭንብል ትውልዱን መጋረዳቸው ከጉዳቶች ሁሉ የከፋ ጉዳት ሊሆን በቅቷል።
ስለዚህ እንዲሁ በደፈናው የደብተራ ተረት ነው የሚሉ ሰዎች የጥንቱን እውቀት መጣላቸው ብቻም ሳይሆን የሀገራቸውን ታሪክ አብረው ይጥላሉ። ከመጥፎው ለመማር፣ ከበጎው ለማስቀጠል እድሉ ይጠፋል። በፈረንጅ አፍ ብቻ የተፃፈን እንደ እውነት መቀበል እና የራስን ማናናቅ የአዕመሮ ባርነትን ያመጣል።
እውቀት ልፋትን ይፈልጋል። ወርቅ ከብዙ አፈርና ድንጋይ ተጣርቶ እንደሚወጣ ሁሉ፣ የማይዛነፍ እውቀት በርካታ መፅሃፍትን ማንበብና ማመሳከር ያስፈልጋል። አንድ መፅሃፍ ብቻ ካነበበ አደገኛ ሰው ራቅ የሚባለው ለዚህ ነው። “ተወው ባክህ የደብተራ ተረት ነው!” ከማለት እያነበቡ፣ እያመሳከሩ እውቀትን መፈለግ፣ አዕምሮን ማበልፀግ ያስፈልጋል።
01/05/2020
https://www.facebook.com/111234320567321/posts/117996633224423/?app=fbl
ሕይውት አዙሪት ናት🕖።
👉ረጅም ርቀት የተጓዝክ ቢመስልህም... የምትጨርሰው
ከጀመርክበት ነው።።።።።።።።።ራቁትክን ትወልዳለህ
እርቃንህን ወደ መቃብር ትወርዳለህ😟።።።።።
👉መስከረም..ጥቅምት ብሎ ያስጀመረህና....መስከም
መስከረም ብሎ ይመጣብሀል።።።።።🚶♀️🚶♀️
👉ሰኞ..ምክሰኞ ብለህ ተጉዘህ..እንደገና ሰኞ ትላለህ።
ሕይወት አዙሪት ናት!!!.........................
መጀመሪያህ መጨረሻ ነው።።።
✍✍✍✍የጀመርክበትን አትርሳ:መጨረሻህ ነውና።
🙏ገለቶማ
23/01/2020
ጉባዔ ኢትዮጵያ(ለምታምኑ)
(የዮኃንስ ራዕይ-4)
----------
2፤ ወዲያው በመንፈስ ነበርሁ፤ እነሆም፥ ዙፋን በሰማይ ቆሞአል በዙፋኑም ላይ ተቀማጭ ነበረ፤
3፤ ተቀምጦም የነበረው በመልኩ የኢያስጲድንና የሰርዲኖን ዕንቍ ይመስል ነበር። በመልኩም መረግድን የመሰለ ቀስተ ደመና በዙፋኑ ዙሪያ ነበረ።
፩.ኖሕ
በዶፍ ዝናብ መካከል ቀስተ ደመና የለም። ዙሪያ ገቡን ዘግቶ ሲዘንብ የፀሐይ ጮራ መስረቂያ(መሽሎኪያ) የለውም። ኖሕና ቤተሰቡ ለአርባ ቀን የቆዩት በዚህ ዶፍ ውስጥ ነው። የመከራው ዝናብ እንዳለቀ አምላክ ለኖሕ ምልክትን ሰጠው። ዳግመኛ ያለመጥፋቱ ማረጋገጫ ናት ምልክቷ። ከዚህ ኪዳን በኋላ ኖሕ ዝናብ ሲዘንብ ሲያይ ቢያንስ ለአርባ ቀናት እንደማይዘንብበት ያምናል። ፀሐይ በደመና ውስጥ ስትሰርቅ ሲያይ እምነቱን ያረጋግጣል። ቀስተ ደመና የብርሐን ውስጣዊ መልክ ነው። ቀስተ ደመና ካለ ፀሐይ አለች ማለት ነው....ዝናቡ ይቆማል ማለት ነው። ኖሕ ከእድሜውጋ እኩል መጠን ያላት መርከብ ሰርቶ ከመከራው አምልጧል። ሰው መርከብ ነው።ኖሕ የሰራው እራሱን ነው።ቀስተ ደመና የተሰራ ሰው ምልክት ናት።
፪.ተወዳጁ
ከላይ ያነሳሁት የመጽሐፍ ኃይለ ቃል የተጠቀሰው ዮኃንስ በራዕይ አንድ አስድናቂ ስራን ከተመለከተ በኋላ የጻፈው ነው።እርሱ በተወዳጁ ሆኖ የኖረውን ሕይወት አምላክ መልሶ በመንፈስ ይተርክለታል። በሰባት ክፍል የተነገረችን አዲስ ሰብእና በሰባት አብያተ ክርስትያናት አንጻር ያሳየዋል።ሰብዕናዋ ተጀምራ እስክታልቅ ተመለከተ። ቅዱሱ አባት በልጁ በኩል የፈጠረውን አዲስ አዳም አገኘው። ይህ ተወዳጅ ዙፋኑ አደረገው። በዚህ ዙፋን ዙሪያ ቀስተ ደመና አለ። ቀስተ ደመናው ዳግም ያለመጥፋት ምልክት ነው። ጳውሎስ'ክርስቶስን ባለመጥፋት ከሚያምኑትጋ ጸጋ ይሁን 'የሚለውም ለዚህ ነው።ይህ በደመናው መካከል ብርሐን የወጣለት ሰው ንግግር ነው።ሰባቱን አብያተ ክርስቲያናት በሰባት ቀለማት አድርጎ በዙፋኑ ዙሪያ ያቆመን ተወዳጁ ነው።ከሰባቱ ውጭ ክርስትና የለም።ሁሉም ከእነዚህ በአንዱ ይጠቀለላሉ። አሮጌውን(ብሉይን) ከአዲሱ እያወጣን የምንጽፈውም ቀስተ ደመናውን ልንተወው ስለማይቻለን ነው። እርሱ ጥልቅ የሆነ የመዳናችን ኪዳን ነው።
ኡትዮጵያ በዚህ የቀስተ ደመና ኪዳን ተመስርታለች። ይህን የሁሉም ክርስቲያኖች ምልክት በሰንደቅ በመወከል ባለብዙ መስተጋብር ማንነትን መስርታለች። ይህ ሂደት በመጨረሻ ለዛሬው ሰንደቅ ዓላማ ዋንኛ መሰረት ሆኗል። ክርስቲያናዊ ምስጢሩ እንዳለ ሆኖ ፣ዛሬ ግን የሁላችንም የሆነ ብሔራዊ ማንነታችን ነው። ማንነትን ደግሞ ያሳድጉታል እንጂ አይተውትም።
'ይህ ዓለም የተወዳጁ ጠላት ሆኖ ይመላለሳል' እንዲል መጽሐፍ፣ቀስተ ደመናውን የማሳደዱ ድብቅ መግፍኤም ተወዳጁን የመግደሉ አንድ አካል ነው። ይሁንና በትንሣኤው ኃይል ዕለት፣ዕለት ስለምንነሳ ለየዕለቱ ሞት አንደነግጥም። ጨርቁ ሊቃጠል፣ሰውም ሊሞት ይችላል ። ከሰው ባህርይጋ የተጋመደን እውነት ማጥፋት ግን አይቻልም።አንዴ ድል አድርጎ በዙፋን ተቀምጧል። ዙፋን ነን።
ቀስተ ደመናው ነጸብራቅ ነው።የተወዳጁ ብርሐንነት ያለው እርሱ ማንጸባረቁን ይቀጥላል። ቀስተ ደመና የተሰራና የዳነ ሰው ምልክት ናት። ከተሰራን ቆይተናል። የሰንደቅ ነገር እንግዲህ እስከ ነፍሳችን የዘለቀ ነው። ነፍስን ማጥፋት አይቻልም።
እምናምን ሰዎችም ባለቀስተ ደመናው ተወዳጅ ከእኛጋ ሳይሆን፣እንዲሁ በምልክቷ ጉዳይ ብቻ እየባከኑ ከመቅረት እንራቅ። ወዲህም
ቀስተ ደመና የብዙ ቀለማት ስምምነት ነው።ፍቅር እንደማለት!!
ከደሞዝ ጎሽሜ
19/01/2020
መልከ ጼዴቅ ማነው???
በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (የመልከ ጼዴቅን በረከት በመፈለግ ጳጉሜን 3 ማታ በድጋሚ ተጻፈ)
ይኽ መልከ ጼዴቅ ዐፅመ አዳምን እንደ ታቦት አድርጎ በኅብስት በወይን መሥዋዕት ያቀርብ የነበረ የኢትዮጵያውያን የክህነት አባት የሆነ ደገኛ ካህን ነበር (ዘፍ ፲፬፥፲፰)፡፡ ይኸውም ሊቃውንት እንደጻፉልን ኖኅ ከጥፋት ውሃ በኋላ ከመርከብ ሲወጣ ከዚኽ ኹሉ ላዳነኝ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባዋል ሲል፤ ዐፅመ አዳምን እንደታቦት አድርጎ መሥዋዕት ሠዋ፡፡
ከዚኽም በኋላ ሴምን ጠርቶ “ዐጽመ አዳምን ወስደኽ እግዚአብሔር ወዳዘዘኽ ቦታ አኑር” ብሎታል፡፡ ሴምም አፍሪካ በዕጣ ከደረሰችው ከካም ወገን የተወለደው መልከ ጼዴቅን ከናት ካባቱ አሰናብቶ ዐጽሙን አሸክሞ ይዞት ኼደ፤ መላእክት እየመሩ መስቀል ከሚተከልበት ቀራንዮ አደረሱት እዛም ሲደርስ ምድር ተከፈተችለት፤ ዐፅመ አዳምንም አግብቶ አኖረ መልከ ጼዴቅም ዐፅመ አዳምን እንደታቦት አድርጎ ዐሥራ ኹለት ደንጊያዎችን በመትከል መሥዋዕት ጸሎት ያቀርብ ነበር፡፡
የሶርያ ሰዎች በነገር ተከራክረው ወደ ርሱ ሲኼዱ እውነት ይፈርድላቸው ስለነበር “ንጉሠ ጽድቅ” ሲሉት፤ ቢጣሉ ስለሚያስታርቃቸው “ንጉሠ ሰላም” ብለው ጠርተውታል፡፡
ክህነቱም ከሌዊ የሚበልጥ ደገኛ ክህነት ነበርና በስንዴና በወይን ሲያስታኩት ኖሯል፡፡ ምግቡንም መላእክት ያመጡለት ነበር፤ ልብሱም ዳባ ነበር፡፡
የትውልዱንም ነገር ዮሐንስ መደብር ባራተኛው ክፍል ላይ:-
“መልከ ጼዴቅ ውእቱ ዘወፅአ እምነገደ ሴዱ ወልደ ንጉሠ ምስር ወኖባ፤ ወውእቱ ሴዱ ዘነግሠ ከነዓን፣ ወውእቱ አምነገደ ጽኑዓን፤ ወውእቱ ተጻብኦሙ ወተቀንዩ ሎቱ፤ ወሶበ አስተፍሥሕዎ ነበረ ውስቴታ ወሐነጸ ሀገረ ወሰመያ በስመ ዚኣሁ ሳይዳ፤ ወእስከ ዮም ትሰመይ ሳይዳ ወአቡሁ ለመልከ ጼዴቅ ወቦአ እምነ ሳይዳ”
(የኖብና የምስር ንጉሥ ልጅ ከሚኾን ከሴዱ ነገድ የወጣ (የተወለደ) መልከ ጼዴቅ ነው፡፡ ያውም ሴዱ በከነዓን የነገሠ ነው፤ ርሱም ከጠንካሮቹ ነገድ ነው፤ ርሱም ተዋጋቸውና ተገዙለት፤ በስደቱም ጊዜ በውስጧ ተቀመጠ፤ ከተማንም ሠርቶ በርሱ ስም ሳይዳ ብሎ ጠራት፣ እስከ ዛሬም ሳይዳ በመባል ትታወቀለች፤ የመልከ ጼዴቅ አባትም ከሳይዳ ወጣ) ይለዋል፡፡
በኦሪት ዘፍጥረት ምዕ ፲፬ ላይ እንደምናነበው ዐምስቱ ነገሥተ ሰዶም ወገሞራ ለአራቱ ነገሥተ ኮሎዶጎሞር ፲፪ ዓመት ገብረው በ፲፫ኛው ዓመት አንገብርም በማለታቸው፤ በዐዘቅተ ኤሌቅ በተዋጉት ውጊያ፤ አራቱ ነገሥተ ኮሎዶጎሞር ድል አድርገው ሎጥን ከዚያ አግኝተው ማርከውታል፤ አብርሃምም ይኽነን ሰምቶ ከቤተሰቦቹ ፫፻፲፰ት ሰዎች ይዞ ኼዶ ነገሥተ ኮሎዶጎምርን ድል ነሥቶ የተማረከ ወንድሙ ሎጥን መልሶታል፡፡
ይኽም ምሳሌ ነው አብርሃም የጌታ፤ ሎጥ የሃይማኖት፤ ፫፻፲፰ቱ የ፫፻፲፰ ሊቃውንት፤ አራቱ ነገሥተ ኮሎዶጎሞር የመናፍቃን፤ ዐምስቱ ነገሥተ ሰዶም የምእመናን ምሳሌ፤ አብርሃም ፫፻፲፰ ሰው ይዞ አሕዛብን ድል ነሥቶ ሎጥን እንደመለሰ ጌታም በ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ዐድሮ ሃይማኖትን የመመለሱ ምሳሌ እንደኾነ መርተርጒማነ ብሉይ ያስተምራሉ፡፡
ከዚኽ በኋላ አብርሃም ደስ ብሎት ለአዳምና ለልጆቹ የድኅነት ተስፋን የሰጠ አምላክን በዐይነ ሥጋ ለማየት ተመኝቶ “በመዋዕልየኑ ትፌኑ ወልደከ ወሚመ ታርእየኒ ኪያሃ ዕለተ” (ልጅኽን በዘመኔ ትልከዋለኽ? ወይንስ ዕለቷን ታሳየኛለኽ) አለው፤ ጌታም “አኮ ዘአርእየከ ኪያሃ አላ አምሳሊሃ ዕድዎ ለዮርዳኖስ ወትረክቦ ለመልከ ጼዴቅ” (ያችንስ ዕለት የማሳይኽ አይደለም፤ ምሳሌዋን እንጂ፤ ዮርዳኖስን ተሻገር መልከ ጼዴቅን ታገኘዋለኽ) ብሎ ምሳሌውን ጠቆመው።
አብርሃምም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ሲኼድ ታላቅ ግርማ የነበረውን መልከ ጼዴቅን አይቶ ደነገጠ፤ መልከ ጼዴቅም አብርሃምን “አትፍራ፤ አንተን ወደ ዮርዳኖስ እንድትሻገር ያዘዘኽ እግዚአብሔር እኔን ኅብስተ አኰቴት ጽዋዐ በረከት ይዤ ወደ ዮርዳኖስ እንድመጣ ለአንተ እንድሰጥኽ አዝዞኝ” ነው፤ በማለት ከያዘው ኅብስትና ወይን ለአብርሃም ሰጥቶ ባርኮታል፤ አብርሃምም ከያዘው ኹሉ ዐሥራትን ሰጠው፡፡
ይኽ አብርሃምም በኋላ ዘመን አካላዊ ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ሥጋውን ደሙን በኅብስት በወይን የሚሰጥ መኾኑን በማወቁ እጅጉን ተደስቷል፤ ጌታም ይኽቺን ታላቅ ሰዓት አብርሃም ለማየት እንደተመኘ ለአይሁድ “አባታችኍ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት ዐደረገ፤ አየም ደስም አለው” በማለት ነግሯቸዋል (ዮሐ ፰፥፶፮)፡፡
ሊቁ አባ ጊዮርጊስም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ለመጣ ለአብርሃም መልከ ጼዴቅ በመሶብ ከያዘው ከስንዴው ኅብስት በጽዋው ከያዘው ከወይኑ እንደሰጠው ኹሉ፤ ዘመኑ ሲፈጸም አካላዊ ቃል ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ተወልዶ፤ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማሕፀነ ዮርዳኖስ ለተወለድነው ክርስቲያኖች፤ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን በስንዴና በወይን አምሳል የሰጠን መኾኑን በእንዚራ ስብሐት መጽሐፉ ላይ፡-
"መካነ ሞጻሕቱ አንቲ ለመልከ ጼዴቅ
በኅብስተ ሥርናይ ወወይን ዘከሠተ ምሥጢረ ጽድቅ"
(በወይንና በስንዴ የእውነትን ምስጢር የገለጠ የመልከ ጼዴቅ የመሠዊያ ቦታ አንቺ ነሽ) በማለት ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ተወልዶ ቅዱስ ሥጋውን በአምሳለ ኅብስት የሰጠ ምግበ ርኁባን፤ ክቡር ደሙን በአርአያ ወይን የሰጠ ስቴ ጽሙኣን፤ አማናዊ ካህን ኢየሱስ ክርስቶስን ያገኘንባት መኾኗን መስክሯል።
በተመሳሳይ መልኩ ሊቁ በነገረ ማርያም ላይ፦ "ወአጸደ ወይን ዘጽድቅ ዘሐንበበቶ ለአስካለ መለኮት ዘርእየ አምሳሊሁ መልከ ጼዴቅ አመ አውጽሐ በኅብስተ ሥርናይ ወበደመ ወይን" (መልከ ጼዴቅ በስንዴ ኅብስትና በወይን ደም ባስታኮተ ጊዜ፤ ምሳሌውን ያየው የመለኮት ፍሬን ያፈራቺው እውነተኛ የወይን ቦታ ርሷ ናት) በማለት ያመሰጥራል።
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ጌታን ከመልከ ጼዴቅ ጋር አነጻጽሮ ቢጠቅስም መልከ ጼዴቅ ግን ምሳሌ ብቻ እንደኾነ ሳይጠቅስ አላለፈም፤ ይኸውም በዕብራውያን ክታቡ ምዕ ፯፥፩-፫ ላይ:-
“የሳሌም ንጉሥና የልዑል እግዚአብሔር ካህን የኾነ ይኽ መልከ ጼዴቅ አብርሃም ነገሥታትን ገድሎ ሲመለስ ከርሱ ጋር ተገናኝቶ ባረከው፤ ለርሱም ደግሞ አብርሃም ከኹሉ ዐሥራትን አካፈለው የስሙም ትርጓሜ በመዠመሪያ የጽድቅ ንጉሥ ነው፥ ኋላም ደግሞ የሳሌም ንጉሥ ማለት የሰላም ንጉሥ ነው፤ አባትና እናት የትውልድም ቍጥር የሉትም፥ ለዘመኑም ጥንት ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ኾኖ ይኖራል” ይለዋል፡፡
ይኸውም ምሳሌነቱ በመተርጉማን እንደተተነተነው ካህኑ መልከ ጼዴቅ በስንዴና በወይን ያስታኩት እንደነበር ሊቀ ካህናት ጌታም ሥጋውን ደሙን በስንዴና በወይን ሰጥቶናልና (ዘፍ ፲፬፥፲፰፤ ማቴ ፳፮፥፳፮-፳፯)፡፡
መልከ ጼዴቅ ሹመቱን ከእግዚአብሔር ተሾሞታል እንጂ ከእገሌ ተሾመው እንዳይባል፤ ሊቀ ካህናት ጌታም ሥልጣኑ የባሕርዩ ነው እንጂ ከሌላ የተሰጠው አይደለምና፡፡
መልከ ጼዴቅ አባትና እናት ቢኖሩትም ቅሉ በሌሎች መጻሕፍት እንጂ በሌዋውያን መጽሐፍ የአባቱና የእናቱ ነገር እንዳልተጻፈ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በእውነት ለቀዳማዊ ልደቱ እናት፤ ለደኀራዊ ልደቱ አባት የለውምና፡፡
መልከ ጼዴቅ ምንም መነሻና መድረሻ ቢኖረውም ቅሉ ለዘመኑ ጥንት ለአነዋወሩ ፍጻሜ አለው ብሎ የጻፈለት የሌዋውያን መጽሐፍ እንደሌለ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አማን በአማን ለዘመኑ ጥንት ለአነዋወሩ ፍጻሜ የሌለው፤ ቅድመ ዓለም የነበረ፤ አኹንም ያለ፤ ዓለምንም አሳልፎ የሚኖር ነውና፡፡
አብርሃም ለመልከ ጼዴቅ ከዐሥር አንድ እንደሰጠው፤ ምእመናንም ዘወትር ዐሥራተ ጾም ዐሥራተ ጸሎታቸውን ለጌታ ይሰጣሉና፡፡
መልከ ጼዴቅ የስሙ ትርጓሜ “የእውነት ንጉሥ” እንደኾነ፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ለመንግሥቱ ፍጻሜ የሌለው ንጉሠ ነገሥት ነውና፡፡
ዳግመኛም ይኽ መልከ ጼዴቅ “የሰላም ንጉሥ” ተብሎ እንደተጠራ፤ ጌታም በከበረ ደሙ ፈሳሽነት ለኹሉም ሰላምን ያደለ “ወሀቤ ሰላም፣ ንጉሠ ሰላም” ነውና ተመስሎበታል (ኤፌ ፪፥፲፬-፲፯፤ ዮሐ ፲፬፥፳፯)፡፡
ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ የመልከ ጼዴቅን ምሳሌነት ስለዚኽ ነገር አምልቶ አስፍቶ ሲያስረዳ፡-
☞ “ናሁኬ አብጽሐ ዘይንእስ ኀበ ዘየዐብዮ ወዘይቴሐት ኀበ ዘይትሌዐሎ መሥዋዕተ መልከ ጼዴቅ…” (እነሆ የሚያንሰው ወደሚበልጠው ዝቅ ዝቅ የሚለውም የመልከ ጼዴቅ መሥዋዕት አደረሰ፤ የመልከ ጼዴቅስ መሥዋዕት የመለኮት ኀይል በላዩ አላደረም፤ የርሱን ሥጋና ደም ብሎ ይጠራው ዘንድ ያን ጊዜ ክርስቶስ ሰው አልኾነምና፤ ዳሩ ግን ለምእመናን እንደሚሰጥ የተጸለየበት ኅብስትና የተባረከ ጽዋ ክብር ነበረው (ዘፍ ፲፬፥፲፰) የመልከ ጼዴቅም ክህነት እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ክህነት ፍጹም አልኾነም፤ አብ ከሰማይ “የምወድደው ልጄ ይኽ ነው፤ ርሱን ስሙት” ብሎ አልመሰከረለትምና፤ መልከ ጼዴቅ አምላክ አይደለምና፨
መልከ ጼዴቅ አብርሃምን እንደባረከው (ዘፍ ፲፬፥፳) ክርስቶስም ደቀ መዛሙርቱን ባረካቸው (ሉቃ ፳፬፥፶)፤
መልከ ጼዴቅ ከአብርሃም ከዐሥር አንድ እንደተቀበለ ክርስቶስም ከሰብአ ሰገል እጅ መንሻ ተቀበለ (ማቴ ፪፥፲፩)፤
መልከ ጼዴቅ በኦሪት መጽሐፍ የእግዚአብሔር ካህን ተብሎ እንደተጠራ (ዘፍ ፲፬፥፲፰፤ መዝ ፻፱፥፬) ክርስቶስም በጳውሎስ አንደበት ሊቀ ካህናት ተባለ (ዕብ ፭፥፱-፲)፤
መልከ ጼዴቅ የሳሌም ንጉሥ እንደተባለ ክርስቶስም የእስራኤል ንጉሥ ተብሎ ተጠራ፤ ሚክያስ የኤፍራታ ምድር የኾንሽ አንቺ ቤተልሔም ከይሁዳ መሳፍንት አታንሺም፤ ወገኖቼ እስራኤልን የሚጠብቃቸው ንጉሥ ከአንቺ ይወጣልና ብሎ ተናግሯልና (ሚክ ፭፥፪)) ይላል፨
ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በተአምኆ ቅዱሳን መጽሐፉ ላይ፦
“ሰላም ለመልከ ጼዴቅ ዐቢይ ካህን አምሳሊሁ ለወልደ እግዚአብሔር
ዘእእመረ ምስጢሮ ኅቡአ ዘሀሎ ይትገበር”
(ሊከናወን (ሊፈጸም) ዘንድ ያለውን ስዉር (ድብቅ) ምስጢሩን ያወቀ፤ ለእግዚአብሔር ልጅ ምሳሌው ለኾነ ለታላቁ ካህን ለመልከ ጼዴቅ ሰላምታ ይገባል) ብሎ ሰላምታ አቅርቦለታል፨
ኢትዮጵያዊው ሊቅ ዐርከ ሥሉስም በዐርኬው ላይ፦
"ሰላም ለመልከ ጼዴቅ አምሳሉ ወሱታፉ
ለዘመጽአ ቃል በደመና ድንግል ዐፅፉ
ጠቢባን ግብሮ በከመ ጸሐፉ
ለሥጋ አቡነ አዳም ኀበ ተሐንጸ ምዕራፉ
ዝንቱ ካህን ይነብር ለዝሉፉ"
(በደመና የተመሰለች የድንግልን ሥጋ ተጎናፅፎ (ተዋሕዶ) ለመጣው ሥግው ቃል ምሳሌው ለኾነ ለመልከ ጼዴቅ ሰላምታ ይገባል፤ ጠቢባን ሥራውን እንደጻፉ የአባታችን አዳም የሥጋው ማረፊያ በታነጸበት ይኽ ካህን ለዘወትር ይቀመጣል) በማለት ድንቅ ውዳሴን ያቀርብለታል
ታላላቅ ሊቃውንት ሕገ ኦሪት ሳይሠራ ገና በሕገ ልቡና አበ ብዙኃን አብርሃምን የባረከው የወልደ እግዚአብሔር ምሳሌ የኾነው መልከ ጼዴቅ ከነገደ ሴም ሳይኾን ከነገደ ካም በመኾኑ የርሱም ርስት አህጉራችን አፍሪካና ምስርን ኖባን አንድ አድርጋ የገዛች ኢትዮጵያ ናትና ታላቋ ሀገራችን ኢትዮጵያ ገና ሕገ ኦሪት ለእስራኤል ሳይሠራ በሕገ ልቡና አምላኳ እግዚአብሔርን በመልከ ጼዴቅ በኩል ስታመልክ የኖረች ናት ይላሉ፨
ካም የነበረበት ከአምላካችን ከክርስቶስ ልደት በፊት 3244 ዓመት ሲኾን በዚኽ ላይ የሐዲስ ኪዳንን የ2011 ዓመተ ምሕረትን ስንጨምርበት 5255 ዓመታት ሳታቋርጥ በሦስቱ ኪዳናት በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪት፣ በሕገ ወንጌል አምላኳ ፈጣሪዋ ልዑል እግዚአብሔርን ስታመልክ ኖራለች፤ እስከ ዕለተ ምጽአትም ንጹሕ ምስጋናዋን ለፈጣሪዋ ለክርስቶስ ታቀርባለች፨
"ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚማልዱኝ የተበተኑት ሴቶች ልጆቼ ቍርባኔን ያመጡልኛል። "
(ትንቢተ ሶፎንያስ 3: 10)
"የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር" (ትንቢተ አሞጽ 9: 7)
[የመልከ ጼዴቅ በረከት ይደርብን]
በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ጽሑፉን ሲወስዱ ምንጩን መጥቀስ አዋቂነት ነው)
ምንጭ፦----ተሰአቱ ቅዱሳን 480ዓ.ም
10/01/2020
ኢትዮጵያውያኑ ሰብአ ሰገል
ሰብአ ሰገል የግእዝ ቃል ነው። ሰብአ ማለት ሰው ሲሆን ሰገል ደግሞ ጥበብ ማለት ነው። የጥበብ ሰዎች። ስለነዚህ ጠቢባን የማቴዎስ ወንጌል እንዲህ ሲል ይነግረናል
“ ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል። የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።…ኮከቡንም ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው።ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት።”
የማቴዎስ ወንጌል 2: 1-2
ሰብአ ሰገል ማናቸው?
ታላቁ የቤተ ክርስትያን መምህር አለቃ አያሌው ታምሩ “የኢትዮጵያ እምነት በሶስቱ ህግጋት” በተባለው መጽሀፋቸው የነዚህ ጠቢባን ስም ሚሊቹር ፣ ማንቲሶራ ፣ በዲዳስፋር እንደሆነ ሲገልጹ የምእራብያውያን የታሪክና የሃይማኖት ሊቃውንት ደግሞ Melichior ,Balthasar and Caspar ይሏቸዋል:: ስማቸው ላይ የድምጽት ልዩነት ያለ ቢመስልም ዞሮ ዞሮ ያው ነው። ብዙም አይራራቅም።
በርካታ ውዝግብ ያለው ግን “እነዚህ ጠቢባን የየት ሀገር ዜጋ ናቸው” የሚለው ላይ ነው::አለቃ አያሌው ሶስቱም ኢትዮጵያውያን መኳንንት መሆናቸውን ሲያትምሩ ሌሎች ደግሞ አንዱ ነጭ አንደኛው ኤዥያዊ እና ሌላኛው ኢትዮጵያዊ እንደሆኑ ይናገራሉ:: በርካታ የም እራብያውያን ሊቃውንትም ያለቃ አያሌውን አስተምህሮ ይደግፋሉ:: ለምሳሌ William Leo Hansbery and E Harper Johnson Africa’s Golden Past Historical facts challenging notion that Christianity isn’t religion of West በሚለው ጽሁፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ያትታሉ
“But it is in general agreed that the reverent visitors were members’ of the order of the Magi and they are usually identified as Caspar king of Ethiopia; Melchior king of Nubia; and Balthazar king of Saba which was for a thousand years the capital city of the African Kingdom… and here too it may be of interest to note the gold, frankincense and myrrh… are all natural product of , and very abundant in, the African regions embraced by Nubia, Ethiopia and Sudan ”
ሌሎቹ የምእራብያውያን ታሪክ ጸሃፊዎችና የሃይማኖት ሰዎች የሚስማሙበት ታሪክ ደግሞ ለጌታችን የጅ መንሻ ያቀረቡት ሶስቱ ጠቢባን ኢትዮጵያዊ ኤዥያዊና ነጭ ናቸው። ከሶስቱ በድሜ አነስተኛ የሆነው ነጭ ሲሆን ያቀረበው ስጦታም ከርቤን ነው። ሁለተኛው ከአረብ ወይም ከ ኤዥያ የመጣ ሲሆን ያቀረበውም የወርቅ ስጦታን ነው። ሶስተኛው ደግሞ ያለ ጥርጥር ኢትዮጵያዊ ሲሆን ያቀረበውም እጣን ነው። በማለት ያስተምራሉ። ሁሉም የታሪክም ሆነ የሃይማኖት ሊቃውንት ያለ መከፋፈል የሚስማሙበት ነገር ግን አንድ ነው። ከሶስቱ አንዱ ኢትዮጵያዊ ነው።
“Balthasar came from Ethiopia or Saba. He is often portrayed as a black man of about forty years of age. He brought the gift of frankincense. Frankincense is the dried resin of Boswellia trees which, at the time of Christ, grew in Arabia, India, and Ethiopia. It was used in perfumes (Song 3:6; 4:6) and incense for the temple worship (Ex 30:9, 34-38; Lev 2:1-12; 6:14-28; 24:7). Because incense represents the prayers of the faithful rising towards Heaven, the gift of frankincense symbolizes sacrifice, Christ’s divine nature, and His titles of High Priest and Son of God. The wise men were given the gift of Faith for their frankincense.”
ለሰብአ ሰገል ትንቢት
ስለ ሰብአ ሰገል የተለያዩ ትንቢቶች በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፈዋል። ልበ አምላክ በመባል የሚታወቀው ንጉስ ዳዊት ማን ጌታችን መድሃኒታችን ፊት ቀርቦ እንደሚሰግድና ማን የእጅ መንሻን ይዞለት እንዲሚመጣ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናግሮ ነበር
”
9 በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ፥
10 የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ የዓረብና የሳባ ነገሥታት እጅ መንሻን ያቀርባሉ።
መዝ 72 :9-11
እዚህ ላይ ቅዱስ ዳዊት “የሳባና የአረብ ነገስታት” ብሎ ነው የጻፈው። ሳባ የአረብ ግዛት ብትሆን ኖሮ “የአረብ ግዛት የሆነችው ሳባ “ብሎ ይጽፍ ነበር። ነገር ግን ሳባ ና አረብ የተለያዩ መሆናቸውን ለማስገንዘብ ” የሳባና የአረብ ነገስታት ” በማለት መጻፉን ያጤኗል።
በመቀጠልም አበይት ከሚባሉት አንዱ የሆነው ነብዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናግሯል
“የግመሎች ብዛት፥ የምድያምና የጌፌር ግመሎች፥ ይሸፍኑሻል ሁሉ ከሳባ ይመጣሉ፥ ወርቅንና ዕጣንን ያመጣሉ የእግዚአብሔርንም ምስጋና ያወራሉ።” ኢሳ 60 :2
ሁለቱም ነብያት ኢትዮጵያውያን የሆኑት ሳባውያን የጅ መንሻ ይዘው እንደሚመጡ በግልጽ ተንብየዋል።
ኢትዮጵያውያን የጅ መንሻ ይዘውና ለመሳለም ኢየሩሳሌም ሲሄዱም የመጀመርያቸው አይደለም ። ለምሳሌ ንግስት ሳባ የሶሎሞንን ጥበብ ለማየት ከኢትዮጵያ ተነስታ የንጉስ ሶሎሞን መዲና ወደሆነችው ኢየሩሳሌም ተጉዛለች።
“የሳባም ንግሥት በእግዚአብሔር ስም የወጣለትን የሰሎሞንን ዝና በሰማች ጊዜ በእንቆቅልሽ ትፈትነው ዘንድ መጣች። በግመሎችም ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቍ አስጭና ከታላቅ ጓዝ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ገባችወደ ሰሎሞንም በመጣች ጊዜ በልብዋ ያለውን ሁሉ አጫወተችው።ለንጉሡም መቶ ሀያ መክሊት ወርቅ እጅግም ብዙ ሽቱ የከበረም ዕንቍ ሰጠችው የሳባ ንግሥት ለንጉሡ ለሰሎሞን እንደ ሰጠችው ያለ የሽቱ ብዛት ከዚያ ወዲያ አልመጣም ነበር።
የመጽሀፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት መዝገበ መክሊትን የክብደት መመዘኛ መሆኑንና አንድ መክሊት ደግሞ 42 ሺህ ግራም መሆኑን ያስረዳል:: ስለዚህ ንግስት ሳባ ያመጣችው ወርቅ ባሁኑ የወርቅ አለካክ ይሄንን ይመስላል ማለት ነውመክሊት 42 ሺህ ግራም ወይም 42 ኪሎ ግራም ነው።
መቶሃያ መክሊት ማለት 120*42 ኪሎ ግራም= 5040 ኪሎ ግራም ወርቅ ማለት ነው።
እንግዲህ ኢትዮጵያዊቷ ንግስት ሳባ ለንጉስ ሶሎሞን ይዛለት የሄደችው ወርቅ 5040 ኪሎ ግራም ነበር ማለት ነው::
ምናልባም ሰብ አ ሰገል ያቀረቡለት ወርቅ ከዛ የተወሰደ ይሆን??
ኮከብ ቆጣሪዎች ወይስ የሃይማኖት ሰዎች?
እንደቤተክርስትያን ሊቃውንት አስተምህሮ ሶስቱ ጠቢባን ማለትም ሰብአ ሰገልን ይመራቸው የነበረው በኮከብ የተመሰለ መልአክ እንጂ በማታ የምናያቸው ኮከቦች አይደሉም:: ኮከብ ጸሐይ ስትጠልቅ የሚታይ የብርሃን አካል ነው እንጂ ኮከብ በቀን አይታይም:: ምክንያቱም ግልጽ ነው:: በቀን ባለው የጸሐይ ብርሃን ስለሚዋጥምንም አይነት ኮከብ ቢሆን በቀን አይታይም:: ይክ ኮከብ ግን የጥበብ ሰዎቹን በቀን ና በሌሊት እየመራ
ቤተልሔም ውስጥ አድርሷቸዋል:: ይህም ኮከብ ከጥንት ጀምሮ ለበቁት አባቶች የሚታይ መልአክ አንደነበርና ንግግሩም ምሳሌያዊ እንደሆነ የቤተክርስትያን መምህራን ያስተምራሉ:: “ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፥ ከእስራኤል በትር
ይነሣል፥” ዘኁ 24 : 17
እጅ መንሻን ካቀረቡ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተጓዙ;; ጉዞውም የፈጀባቸው 40 ቀን ነበር:: እንደደረሱም የጌታን መወለድ አበሰሩ:: የጌታችን መወለድ አስተማሩ:: የኢትዮጵያ የመጀመርያ የወንጌል መምህራንም እነሱ ነበሩ:: ኢትዮጵያ ጌታችን ሲወለድ ንጉሷ ተገኝቶ ጌታን አይቶ የጅ መንሻ አቀረበ:: ህዝቡንም ስለ ጌታ ልደት አስተማረ:: በሃዋርያት ዘመን ደግሞ የቤተ መንግስቱ ጃንደረባ ኢየሩሳሌም ድረስ ሄዶ ጥምቀትን አመጣልን:: ጥምቀትን አስተማረ:: እስከዛሬ ድረስ ጥምቀትና ልደት ለኢትዮጵያ ልዩ በአላት ናቸው:: የምናከብረውም በቦታው ተገኝተው ያዩ አባቶቻችን በነገሩን ባስተማሩን ቀን ነው::
ይሄንን ሁሉ ታሪክ ባለቤትና ተረካቢ የሆነችውና ታሪኩን ጠብቃ ላቆየችልን ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን
ምስጋና ይሁን !!
08/01/2020
ቅዱስ ያሬድ ማን ነው?
ኢትዮጵያዊው ርእሰ ሊቃውንት ቅዱስ ያሬድ ፡ ሚያዝያ ፭ (5) ቀን ፬፻፺፫ (493) ዓ፡ም፡ በአክሱም ከተማ
ተወለደ ። አባቱ አዳም የሚባል ሲሆን ፥ እናቱ ታውክሊያ ትባላለች ። የትውልድ ሐረጉም ከአክሱም
ካህናት ነው ፡፡ የ፮ ዓመት ሕፃን ሲሆን ፡ አባቱና እናቱ ይስሐቅ ለሚባል ለአክሱማዊው መምህር
አስተምርልን ብለው ሰጡት ፡፡ ይሁን እንጂ ትምህር አልገባው ብሎ ስለተቸገረና መምህሩንም ስላስቸገረ
መምህሩ ያሬድን መልሶ ወደ አባቱ ዘንድ ላከው ፡፡ በመሐሉም ወላጅ አባቱ ስለሞተበት እናቱ ታውክሊያ
ለአክሱም ቄሰ ገበዝ ለአባ ጌዴዎን እንዲያሳድገ ውና እንዲያስተምረው ሰጠችው ፡፡ አባ
ጌዴዎንም በአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት መምህር ነበርና
በግዕዝ ፡ በእብራይስጥ በግሪክና በዓረብ ቋንቋዎች ይተረጉማቸው ነበር ፡፡ አባ ጌዴዎን ያሬድን
አብሯቸው እንዲኖር በማድረግ ቢያስተምሩ ትም ለብዙ ዓመታት መዝሙረ ዳዊትን ማጥናት አቅቶት
አብረውት ከሚማሩት ሕዓናት ጋር ሊወዳደር ባለመቻሉና ወደኋላ በመቅረቱ አባ ጌዴዎን ያሬድን በየጊዜው
ይመክሩትና ይገሥፁት ነበር ፡፡ ያሬድ በትምህርት ደካማ ስለነበረ አስተማሪዎች የሚስጡትን ትምህርት
ደጋ ግሞ ቢያጠናም አልሆንለት ስለአለ የትምህርት ጓደኞቹ ሲቀልዱበትና ሲያፌዙበት ይውሉ ነበር ።
አጎቱ አባ ጌዴዎን በያሬድ ስንፍና ተማሮ አንድ ቀን ለምን እንደሌሎቹ ጓደኞችህ በደምብ አታጠናምመ
ብሎ ያሬድን ክፉኛ ገረፈው ፡፡ ያሬድ በአጋጠመው የትምህርት አለመሳካትት ተስፋ ቆርጦ የትም ሔዶ
አዲስ ሕይወት ለመጀመር ቁርጥ ሐሳብ አደረገ ፡፡
ያሬድ ከተማሪ ቤቱ ጠፍቶ ወደ አጎቱ አገር ወደ መደባይ ወለል ሲሔድ ኃይለኛ ዝናብ ስለዘነበ ከአክሱም
ከተማ ፬ (4) ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ክምትገኝ ማይከራኸ ከምትባል ምንጭ ውኃ አጠገብ ወደአለው
ዛፍ ሥር ተጠግቶ መጠለል ግድ ሆነበት ፡፡ ዛፉን ተጠግቶ ደገፍ ብሎ አንደቆመ በምን ምክንያት
በትምህርት ከጓደኞቹ በታች እንደሆነ ሊያስብና ሲያሰላስል ሲያዝንና ሲተክዝ ከቆየ በኋላ ፡ ሐሳቡን
የሚያስለውጥ ነገር በድንገት ተመለከተ ፡፡ ይኸውም አንድ ጉንዳን አንድ የእህል ፍሬ ተሸክሞ ወደዛፍ
ለመውጣት ከፍተኛ ሙከራ ሲያደርግ አየ። ጉንዳኑ የተሸከመውን ይዞ ስድስት ጊዜ ለመውጣት ጥረት
ቢያደርግም ሊሳካለት አልቻለም ፡፡ ነገር ግን ተስፋ ሳይቆርጥ ክብዙ ድካምና ጥረት በኋላ በሰባተኛወ
ሙከራ የተሸከማትን የእህል ፍሬ ይዞ ወጣ ። በሙሉ አትኩሮት ይመለከተውና ይከታተለው የነበረው
ያሬድም በድንገት ስሜቱ ተነካ ፡፡ ይህ አነስተኛ ፍጡር ከብዙ ጥረት በኋላ ያሰበውን ሲፈጽም የእኔ ተስፋ
መቁረጥ ምን ይባላል ሲል ራሱን በራሱ ወቀሰ ከጉንዳኑ ያገኘው ትምህርት ልቡን ስለነካው ስሜቱንም
ስለቀሰቀሰውና የጉንዳኑን ትጋትም አይቶ ስለ ተደነቀ በራሱ ደካማነት ተጸጽቶ አለቀሰ ፡፡ ያሬድ በዚሁ
አነስተኛ ፍጡር ጥረትና ተስፋ አለመቁረጥ ተደንቆ ራሱን እንዲመረምር ስሜቱን ስለሎረኮረው ፥ ወደ
አክሱም ተመልሶ ትምህርቱን ለመቀጠል ወሰነ ። የሰው አፈጣጠር ከዚህ አነስተኛ ፍጥረት እጅግ በጣም
የላቀ መሆኑን ስለተገነዘበ ፡ ያጉቱን ምክርና ተግሣፅ ለሕይወቱ የሚጠቅም እንደሆነ በመረዳት ያለውንም
ትምህርት በትጋት ቢማርና ቢያጠና የተሻለ ውጤት ሊያገኝ እንደሚችል በማመን ወደ አጉቱና ወደ
መንፈሳዊ መምህሩ ወደ አባ ጌዴዎን ተመልሶ በመምጣት አባቴ ሆይ ይቅር በለኝና እንደ ቀድሞ
አስተምረኝ ብሎ አጉቱ እግር ላይ ወደቀ፡፡ መምህሩ አባ ጌዴዎንም ፈቅደውለት ዳዊቱን ያስተምሩት ጀመር
። ሕፃኑ ያሬድም ትምህርቱን እየተማረ ሁልጊዜ በጽሞና ወደ አክሱም ጽዮን ቤተክርስቲ ያን እየገባ
"መሖሪ እግዚአብሔር ዐይነ ልቦናየን አብራልኝ" እያለ በየቀኑ በንጹሕ ልቦና ይጸልይ ነበር ። መሐሪውና
የቅር ባዩ እግዚአብሔር ርም ልመናውን ሰምቶ ዐይነ ልቦናውን አበራለትና ትምህርቱ ተገለጸለት። ባጭር
ጊዜ ውስጥ እንዲህ ዐይነት ከፍተኛና የማይታሰብ ለውጥ በማምጣቱ ጓደኞቹና መምህራኑ እጅግ በጣም
ተደነቁ ፡፡ በዚህ ፈጣን የትምህርት መቀበል ችሎታ የብሉይ ኪዳንንና የአዲስ ኪዳንን ትርጓሜ መጻሕፍት
በአጭር ጊዜ ውስጥ ጨረሰ።
ያሬድ ከፍተኛ የትምህርት ተሰጥዎ ያለው በመሆኑ ትምህርቱን በጣም አስደናቂ በሆነ መንገድ ፈጽሞ
ዲያቆን ሆነ ፡፡ ከመምህሩ ከአባ ጌዴዎን በተማረው መሠረት የእብራይስጥና የግሪክ ቋንቋዎችን ደህና
አድርጉ ያውቅ ነበር ይባላል ፡፡ ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስና እንዲሁም በውጭ አገር ቋንቋዎች የአጉቱን
የመምህር ጌዴዎንን ሙያ አጠናቆ ቻለ ፡፡ ያሬድ አጉቱ ሲሞት የዐሥራ አራት አመት ልጅ ቢሆንም የአጉቱን
ሙያና የትምህርት ወንበር ተረክቦ ማስተማር ጀመረ። በግንቦት ፲፩ (11) ቀን ስንክሳር በተባለው
የቅዱሳን የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ውስጥ "ያሬድ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶና ተነሣሥቶ የዜማ ድርሰቶቹን
አዘጋጀ" ይላል። በዚሁ ስንክሳር እንደ ተጻፈው እግዚአብሔር በዚች ምድር እንዲመስገን በፈለገ ጊዜ
ያሬድን በራሱ ቋንቋ ሰማያዊ ዜማ እንዲያስተምሩት በአእዋፍ አምሳል ሦስት መላእክትን ከገነት ላከለት
ይላል ፥፡ እነሱም ያሬድ ካለበት ሥፍራ አንጻር ባለው አየር ላይ ረበው (አንዣብበው) ጣዕም ያለውና
ልብን የሚመስጥ አዲስ ዜማ አሰሙት ፡፡ ያን ጊዜ ያሬድ በጣዕመ ዜማቸው ተመስጦ ቁሞ ሲያዳምጥ
ወዲያውኑ ወፎቹ በግዕዝ ቋንቋ "ብጹዕ ወክቡር አንተ ያሬድ ብጽፅት ከርሥ አንተ ጾረተከ ውብጹዓት
አጥባት አላ ሐአናከ" ብለው በአንድነት አመስግኑት። ትርጉሙ "የተመሰገንክና የተክበርክ ያሬድ ሆይ ፡
አንተን የተሸከመች ማኅፀን የተመስገነች ናት ፡፡ አንተን ያሳደጉ ጡቶችም የተመሰገኑ ናቸው" ብለው
አመሰገኑት ፡፡ ከዚያም ሐያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ዜማ ወደ ሚዘምሩበት ወጋ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም
አሳረጉት ፡፡ ቅዱስ ያሬድም በመንበረ ጸባዖት ፊጓ ቁሞ ከሐያ አራቱ ካህናተ ሰማይ በፍጥነት የሰማው
ማኀሌት ሁቦ በመንፈስ እግዚአብሔር ተገለጸለትና በልቦናው የተሣለበትን ጰዋትዜ ዜማ በቃሉ ያዜም
ጀመር ፡፡ ከዚያም ወደ ቀድሞ ቦታው ወደ አክሱም በተመለሰ ጊዜ ክጥዋቱ በ፫ ሰዓት ወደ አክሱም ቤተ
ክርስቲያን ውስጥ ገብቶ በታቦተ ጽዮን አንጻር ቆሞ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘርግቶ ፡ በከፍተኛ ድምፅ
በአራራይ ዜማ ሃሌ ሉያ ለአብ ፡ ሃሌ ሉያ ለወልድ ፡ ሃሌ ሉያ ወለመንፈስ ቅዱስ ቅዳሜሃ ለጽዮን ሰማየ
ሳረረ ወዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘክመ ይገብር ግብራ ለደብተራ" ብሉ ሥነፍጥረቱንና ሰማያዊት ጽዮንን
አሰመልክቶ ዘመረ ይህችንም ማኅሌት አርያም ብሎ ጠራት ዞ አርያምም ማለት ልዕልና ሰባተኛ ሰማይ
መንበረ እግዚአብሔር ማለት ነው ፡፡ ያሬድ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተመርቶ መላእክት እንደ ከበሮ
እንቢልታ፣ ጸናጽል ፣ ማሲንቆና በገና በመሳሰሉት የማኅሌት መሣሪያዎች እየዘመሩ አምላካቸውን
እግዚአብሔርን ሊያመሰግኑ ስለስማ እነዚህን መሣሪያዎች በሥራ ላይ እንዲውሉ አደረጋቸው ፡፡
ምንጭ:-
- "የኢትዮጵያ ሥልጣኔ"፣ በላይ ግደይ