04/06/2026
#ሞያተኛ ናችሁ ወይስ እረኛ? #
"እረኛ ያልሆነው፥ በጎቹም የሱ ያልሆኑት ሞያተኛ ግን ተኩላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኩላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል።" (ዮሐንስ 10፥12)
ይህንን ጥያቄ ዛሬ በታላቅ ሃዘንና በቁጭት ሆነን በክብር ወንበር ላይ ለተቀመጣችሁት አባቶቻችን እንጠይቃለን። ዛሬ በጎቹ በየአቅጣጫው እየተበተኑ፣ ተኩላው መንጋውን እየበላው ነው። እናንተ ግን የት ናችሁ
እውነተኛ እረኛ፦ በጎቹን በስማቸው ያውቃቸዋል፤ ህመማቸው ያመዋል፣ ዕንባቸው ይገደዋል፤ ከፊት ቀድሞ እየመራ ከተኩላ ይጠብቃቸዋል። አደጋ ሲመጣ ራሱን ጋሻ አድርጎ "እኔን ግደሉኝ፣ በጎቼን ግን አትንኩ" ይላል።
ሞያተኛ ግን፦ በጎቹ የሱ ስላልሆኑ ጥቅሙን እንጂ ህይወታቸውን አይፈልግም። ደሞዝ እና ክብር እስካለ ድረስ ብቻ አብሮ ይቆማል። አደጋና መከራ ሲመጣ ግን ጥቅሙንና ህይወቱን ለማዳን በጎቹን ለተኩላ ጥሎ ይሸሻል።
ዛሬ ክርስቲያኖች ግፍ ሲፈጸምባቸው፣ እናቶች ሲያለቅሱ፣ ቤተክርስቲያን በእሳት ስትጋይ ዝምታን መምረጣችሁ... እረኛነታችሁን ትታችሁ "ሞያተኛ" (ቀጣሪ) መሆናችሁን በተግባር አሳይታችኋል።
ራስን መካድ የታለ?
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦ "ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር፥ እራሱን ይክደው መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ" (ማቴ. 16፥24) ብሎ ነበር።
እናንተ ግን ራሳችሁን መካድ ቀርቶ፣ የያዛችሁትን ምድራዊ ክብር መተው አቃታችሁ።
ስለ አደራችሁ መታሰርን ፈራችሁ?
ለገነባችሁት ዘመናዊ ህንፃ፣ ለገዛችሁት የቅንጦት መኪና እና ላፈራችሁት ምድራዊ ንብረት ስትሉ ነው ዝምታን የመረጣችሁት?
ለስጋችሁ እና ለንብረታችሁ በመስጋት መንጋውን ለተኩላ አሳልፋችሁ ሰጣችሁ?
ከክርስቶስ መንበር በላይ የንብረታችሁ ፍቅርና የእስራት ፍርሃት ከበለጠባችሁ፣ እባካችሁን ያፈራችሁትን ንብረት፣ የገነባችሁትን ህንፃና የገዛችሁትን መኪና ሁሉ ይዛችሁ፣ ያንን ያልመጠነችሁትን ከባድ አባታዊ ስልጣን መልሱ!
የበጎቹ ዕንባና ደም ሳይጠይቃችሁ በፊት ወደ ፈለጋችሁበት ሂዱ። ቤተክርስቲያን ስለ በጎቹ ነፍሳቸውን አሳልፈው የሚሰጡ፣ እንደ አባቶቻችን እንደነ አቡነ ጴጥሮስ ያሉ የእውነት እረኞችን ትፈልጋለች እንጂ ለቪላና ለመኪና የሚሰሱ ሞያተኞችን አትሻም።
አባቶቻችን ሆይ!
"ሞያተኛ" መሆናችሁ ይብቃና እውነተኛ "እረኛ" መሆናችሁን በተግባር አሳዩን። ካልሆነ ግን መንገዱን ልቀቁ፤ እረኛ የሌለው በግ መሆን ሰለቸን!
# #ቤተክርስቲያን #ፍትህ