28/08/2022
ሊቀ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ
➱ "ወከዓዉ ደሞሙ///ደማቸውን አፈሰሱ"
✝️ደማቸውን አፈሰሱ የተባሉት እናማን ናቸው ? ለምን ይሆን ደማቸውን ያፈሰሱት?
✥" ለእናንተም ለወዳጆቼ እላችኋለሁ፥ ሥጋን የሚገድሉትን በኋላም አንድ ስንኳ የሚበልጥ ሊያደርጉ የማይችሉትን አትፍሩ። እኔ ግን የምትፈሩትን አሳያችኋለሁ፤ ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ለመጣል ሥልጣን ያለውን ፍሩ። አዎን እላችኋለሁ፥ እርሱን ፍሩ።" ሉቃ ፲፪÷፬
ቅዱስ ጊዮርጊስ አባቱ ዘሮንቶስ ይባላል። እናቱም ቴዎብስታ ትባላለች የዘር ሐረግዋም ከፍልስጥኤም ወገን ነው ። ቅዱስ ጊዮርጊስ ጥር ፪ ቀን ፪፻፸፯ ዓም/// በ፫ኛው መቶ ክ/ዘመን ተወለደ የተወለደባትም በሀገረ ልዳ ቀጰዶቅያ በተባለ ስፍራ ነው።
➱የተወለደው ጥር ፪ ቀን ፪፻፸፯ ዓ.ም
➱የአባት ስም አንስታቴዎስ (ዘሮንጦስ)
➱የእናት ስም ቴዎብስታ
➱የትውልድ ሀገር ቀጰዶቂያ
➱በዓለ ንግሥ(ዕረፍቱ)- ሚያዚያ ፳፫ ቀን
✝️የቤይሩት (የሊባኖስ) ሰዎች ደራጎን የተባለ ዘንዶ እያመልኩ ሴት ልጃቸውን ይገብሩለት ነበር፡፡ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስም ቤይሩታዊቷን ወጣት አዳናት ደራጎኑን በበትረ መስቀሉ ድል በማድረግ ገድሎታል፡፡በፋርስ (በኢራን) ዱድያኖስ የተባለ ንጉሥ ሰባ ነገሥታትን እየሰበሰበ ለሰባ ጣዖታት ሲሰግድና ሲያሰግድ ይኖር ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰማዕትም እንደ ኤልያስ ለእምነቱ ቀንቶ ንጉሡን መገሰጽ ጀመረ፡፡
ለሰባት ዓመታት ያህል ልዩ ልዩ መከራን እየተቀበለ በጽኑዕ ተጋድሎ ከኖረ በኋላ ሚያዝያ ፳፫ ቀን በ፳፯ ዓመቱ ሰማዕትነትን ተቀብሎ አርፏል፡፡
⛪️ቅዱስ ኤፍሬም በደረሰው በሐሙስ ውዳሴ ማርያም እንደተናገረው "አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዛ ዓለም ወከዓዉ ደሞሙ በእንተ እግዚአብሔር ወተዓገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግሥተ ሰማያት"/// “ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፤ ደማቸውን ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ ፤ ስለ መንግሥተ ሰማያት መራራ ሞትን ታገሱ፡፡
✝️"ሰዓል ለነ ጊዮርጊስ ኀበ እግዚአብሔር ወጸሊ በእንቲአነ ሀረድዎ ወገመድዎ ወዘረዉ ሥጋሁ ከመ ሐመድ ወወሰድዎ ኀበ ሰብዓ ነገሥት ረገጸ ምድረ አንስአ ሙታን አባ ጊዮርጊስ በሰላም ዐደወ መንግሥተ ክብር ወረሰ" #መሐረነ አብ
✝️" ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን?፤ ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።" ሮሜ ፰÷፴፭
✝️ ከሃዲው ንጉሥ ዱድያኖስ ግንድ አምጥተው ቅዱስ ጊዮርጊስን በግንድ ላይ እንዲቸነክሩት አዘዘ፤በላዩም ላይ ሰም አፍስሰው እሳት እንዲያነዱበት አደረገ ፤ ከዚህም በኃላ እንደመጭመቂያ ሆኖ ከተሰራ የስቃይ መሳሪያ (መንኰራኩር/ወፍጮ) ላይ አወጡት ሰውነቱን እንዲሰነጥቁት እንዲጨምቁት አዘዘ፤ አንጀቱ ሁሉ ወጥቶ ከምድር ላይ እስኪዘረገፍ ድረስ እንዲሁ አደረጉበት ነፍሱ ከስጋው ተለየች የሰማእቱን ሰጋ አቃጠሉት ፈጩት አመድም ሆነ በቀፎ አድርገው ይድራስ ወደሚባል ተራራ ላይ በነፋስ ዘሩት።
✝️ደብረ ይድራስ ማለት ምድረ በዳ ነው ወታደሮቹ የታዘዙትን ፈጽመው ተመለሱ። ያንጊዜም መብረቅ ነጎድጓድ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነ ምድርም ከመሰረቷ እስክትናወጽ ድረስ ከሰማይ ድምጽ ተሰማ ጌታችን መድሐኒታችን እየሱስ ክርስቶስ መላእክትን አስከትሎ በብሩ ደመና ወረደ በተራራውም ላይ ተቀመጠ አራቱን የምድር ነፋሳት የሰማእቱን ስጋ እንዲሰበሰቡ አዘዛቸው ከሞትም አስነሳው ኃይሉን አሳደረበት ባርኮትም ወደ ሰማይ አረገ፤ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ እየሮጠ ወታደሮቹን ተከተላቸው ወንድሞቼ ቆዩኝ ከናንተ ጋር ልሂድ እያለ ተጣራ የነዚህ የወታደሮች ቁጥር አራት ነው ስማቸው ህልቶን፤አግሎሲስ፤ሶሪስና አስፎሪስ ነው፤ይህንን ታላቅ ተአምራት አይተው አምነዋል፤ በኋላም በሰማእትነት ሞተዋል፤
➱ገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ምዕራፍ ፮ ፤ ፲፭-፲፰
ከሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ረድኤት በረከት ይክፈለን!!!
✥ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✥
ዲ/ን ሙሉቀን ግርማ
✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥✥
ለበለጠ መረጃ👉 "ዲያቆን ሙሉቀን ግርማ" ፔጁን ላይክ በማድረግ እለት እለት የቅዱሳኑን፣የጻድቃን፣የሰማዕታትን፣የነብያትን፣የሐዋርያትን ገድል ተአምራት ይከታተላሉ እንዲሁም ወቅታዊ የቤተክርስቲያን ጉዳዮች ላይ እንወያይ መልዕክት ይላኩ......ስለጎበኙን እግዚአብሔር አምላክ በረድኤት ይጎብኝልን፤ የእመቤታችን የድንግል ማርያም አማላጅነት፤የጻድቃን የሰማዕታት ተራዳኝነት አይለየን አሜን።✟
10/07/2022
29/06/2022
29/06/2022