በሪፓርተር
ታሪክ ለዘመናት ከአንዱ ወደ ሌላው እየተቀባበሉ በሚያልፉ ትውልዶች የሚሠራ የአገር ቅርስ ነው፡፡ ታሪክ አገርን በመገንባት፣ ከወራሪዎችና ከአጥቂዎች በመከላከል፣ ግዛትን በማስፋትና በማካለል፣ በአስተዳደራዊና በተለያዩ መስተጋብሮች ይገለጻል፡፡ ታሪክ ያለፉ ዘመናትን ኩነቶች በመረዳት የወደፊቱን ለመተንበይ ከመርዳቱም በተጨማሪ፣ ስህተቶችን ላለመደጋገም ያግዛል፡፡ ታሪክን በቅጡ ባወቅን ቁጥር ዕውቀታችንና የአስተሳሰብ አድማሳችን ሲሰፋ፣ ካላስፈላጊ ድርጊቶች ለመቆጠብም ይጠቅማል፡፡ በሀቅ ላይ የተመሠረተ ታሪክ ለአንድ ማኅበረሰብ ሁለንተናዊ ዕድገትና ለውጥ መሠረታዊ ጉዳይ ሲሆን፣ ታሪክን አጣሞ ለመረዳት መሞክር ግን ለውድቀት ይዳርጋል፡፡ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዘመናት የተለያዩ ታሪኮች ተፈራርቀውባታል፡፡ በደግና በክፉ የሚወሱ የታሪክ ውርሶች ባለቤት ናት፡፡ ሕዝቧም በዘመናት ቅብብሎሽ ደግ ደጉን እየተቀባበለ ክፉ ክፉውን ደግሞ ከአጠገቡ እያራቀ፣ አገሩን በከፍተኛ ፍቅርና ወኔ በጋራ ሲጠብቅ ኖሯል፡፡ ስኬቶችንና በደሎችን የጋራ አድርጎ በፍቅርና በመተሳሰብ ዘመናትን ተሻግሮ እዚህ ደርሷል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተዋይነቱና ጨዋነቱ ከሚገለጽባቸው የጋራ እሴቶቹ መካከል፣ ለአገሩ ያለው የማይናወፅ ፍቅር ነው፡፡ ይኼንን ደግሞ ታሪክ በደማቁ መዝግቦታል፡፡ መቼም ቢሆን መካድ አይቻልም፡፡
በዚህ ዘመን ከታሪክ ጋር የሚወዛገቡ ኃይሎች የአገሪቱንና የሕዝቡን ታሪክ እያጣመሙ ነው፡፡ አንዱ ይነሳና የሌላውን ህልውና በመካድ አገር አልባ ሊያደርገው ይፈልጋል፡፡ ሌላው ደግሞ በትውልድ ቅብብሎሽ ሕዝብ አንድ ላይ ሆኖ አገሩን በጋራ ሲጠብቅ እንደነበረ ሊክድ ይዳዳዋል፡፡ የፖለቲካ ሥልጣን በተሳሳተ መንገድ ለመጨበጥ ብቻ፣ የጋራ አገር እንደሌለች ዓይናቸውን በጨው አጥበው ሐሰተኛ መረጃ የሚለቁ አሉ፡፡ ታሪክን በሚፈልጉት መንገድ ብቻ እየጠመዘዙ አንዱን ወገን ብፁዕ፣ ሌላውን ወገን እርኩስ አድርገው የሚስሉ የዘመናችን ቴአትረኞች እንደ አሸን እየፈሉ ነው፡፡ ማስረጃ አቅርቡ ቢባሉ ወገቤን የሚሉበት ተረት ተሸክመው የሚዞሩም እንዲሁ፡፡ ታሪክ መሥራት የማይችሉ ታሪክ ለማበላሸት ግን ብዙ ይጥራሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የዜሮ ድምር ፖለቲካ ውስጥ የተዘፈቁ ኃይሎች፣ በተለያዩ መንገዶች የአገር ሰላም እያደፈረሱ ነው፡፡ በሕዝብ መሀል መቃቃር እንዲፈጠርና ግጭት እንዲቀሰቀስ ተግተው እየሠሩ ነው፡፡ ይህ ድርጊት መቆም አለበት፡፡ የእልህና የብሽሽቅ ፖለቲካ ውጤቱ ታሪክ እያዛቡ አገር ማመስ በመሆኑ ሃይ ማለት ያስፈልጋል፡፡ አገርን ለማጥፋት መሯሯጥ ለማንም አይጠቅምም፡፡
ያለፉ ዘመናት ትውልዶችን በዛሬ ዕይታ ወይም እሳቤ እየመዘኑ መውቀስም ሆነ፣ ከመጠን ያለፈ ውዳሴ እያቀረቡ በየጎራው መቆራቆስ ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ጥፋቶችን እንደገና ላለመድገም በሚገባ እየተጠነቁቁ ከመልካም ተግባራት ደግሞ ልምድ መቅሰም ሲገባ፣ ለታሪክ በማይመጥን ደረጃ እየተርመጠመጡ የግጭት አውድማ መፍጠር ለ21ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ አይመጥንም፡፡ አሁን ያለችው ኢትዮጵያና የበፊቷ ኢትዮጵያ በብዙ ነገሮች ይለያያሉ፡፡ ትውልዱም እንዲሁ በጣም የተለያየ ነው፡፡ የአሁኑ ካለፈው የበለጠ ታሪክ ሠርቶ አገሩን በዓለም አደባባይ ማስጠራት ሲገባው፣ ዘጠኝ ትንንሽ አድርጎ የዘመነ መሣፍንት ዓይነት ግዛት ለመፍጠር ከተሯሯጠ ያሳፍራል፡፡ ዓለም ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተቀራረበ ጥቅሙንና ህልውናውን እያቆራኘ ባለበት ዘመን፣ አገርን እንደ ቆዳ ጠቅልሎ ትንሽ ለማድረግ መከራ ማየት ከማሳፈር በላይ ምን ይባላል? በዚህ ዘመን ዋስትና ያለው ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ለማስፈን ጠንክሮ መሥራት ሲገባ፣ አስተዳደራዊ ወሰኖችንና ማንነቶችን ምክንያት እያደረጉ ግጭት በመቀስቀስ የንፁኃንን ደም ማፍሰስ ያሳዝናል፡፡ አገርና ሕዝብን ማዕከል አድርጎ ለኅብረ ብሔራዊ የጋራ ግብ መሠለፍ ሲገባ፣ እያደር መጥበብና ለግጭት መውረግረግ ተገቢ አይደለም፡፡ ትውልድና ታሪክ ይታዘባሉ፡፡
የሚያጋጥሙ ችግሮችን በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ መፍታት ሲገባ፣ በማንነትና በወሰን እያሳበቡ መጠፋፋት ለዚህ ዘመን አይመጥንም፡፡ በእልህና በብሽሽቅ የሚመራ ፖለቲካ ለሰጥቶ መቀበል መርህ ስለማይገዛ መነጋገርና መደራደር አይቻልም፡፡ የዘመናትን ቁስል እያከኩ በማድማት በዛቻና በድንፋታ የሚመራ ፖለቲካ አገር ያፈርሳል እንጂ አይገነባም፡፡ ፖለቲከኞች ከሴራና ከአሻጥር አስተሳሰብ ወጥተው ለውይይትና ለድርድር ዝግጁ መሆን ሲገባቸው፣ በተለመደው የስህተት ጎዳና ላይ መመላለስ ከጀመሩ ውጤቱ ውድመት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከሥልጣኔ ጋር የተቆራረጠ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ከመሆኑም በላይ፣ እንደ አገር ለመቀጠል የሚደረገውን ጥረት ያመክነዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚቀሰቀሱ ግጭቶች፣ የንፁኃንን ሕይወት ከመቅጠፍ ውጪ ምንም እንደማይረቡ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ በማንነትም ሆነ በአስተዳደራዊ ወሰኖች ምክንያት የሚፈጠሩ ውዝግቦችን በሰላማዊ መንገድ ለምን መፍታት አይቻልም? ይኼንን ለማድረግ ደግሞ ሕጋዊ ማዕቀፎች ወይም ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥልቶች አሉ፡፡ በዚህ ዘመን የሕዝብን ፍላጎት ተረድቶ በሕጋዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ችግሮችን መፍታት ለምን ያቅታል? ሕዝብ ለዘመናት አስጠብቆ ያኖራቸውን የጋራ እሴቶቹን በመናድና ታሪክ በማዛባት የመከራ ጊዜ ለማምጣት ጥድፊያው ለምን አስፈለገ? ይኼ ችግር በቅጡ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ የራስን ፍላጎት ሌላው ላይ ለመጫን የሚደረገው ከንቱነትም መታረም አለበት፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ እየገነባ የመጣውን ታሪክ የበለጠ ለመገንባት የማይቻል ከሆነም፣ በተቻለ መጠን ላለማፍረስ መተባበር ዕገዛ እንደማድረግ ይቆጠራል፡፡ ሕዝብ ውስጥ ተደብቆ አዛኝና ተቆርቋሪ በመምሰል ከበስተጀርባው ማድባት ነውር ነው፡፡ በተለይ ማኅበራዊ ሚዲያው ውስጥ ተወሽቆ ‹ግፋ በለው!› እያሉ ንፁኃንን ሰለባ በማድረግ መልሶ የዓዞ ዕንባ ማንባት ኃጢያት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በእንዲህ ዓይነቱ የወረደ ድርጊት አይታወቁም፡፡ ታሪካቸውም አይመሰክርም፡፡ በዚህ ዘመን ግን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ያደቡ ኃይሎች፣ በክልሎች መካከል የእርስ በርስ ጦርነት እንዲነሳና ሕዝብ እንዲተላለቅ እንቅልፍ አጥተው እየሠሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የሚባለውን ትልቁን ማንነት በጠባብነት እየጋረዱ አገር ሊያጠፉ ተነስተዋል፡፡ እነሱ ምቾት ውስጥ ሆነው ደሃውን አርሶ አደር እርስ በርሱ አባልተው፣ በዓለም አቀፍ ሚዲያ አውታሮች ግንባር ቀደም የዜና ርዕስ ሊያደርጉት ቋምጠዋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ንፁኃንን ሰለባ ለማድረግ እየተደረገ ያለው ቅስቀሳ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚታወቀው አገሩን በጋራ ሲጠብቅ እንጂ እርስ በርሱ ሲፋጅ አይደለም፡፡ ታሪክ የሚመሰክረው ይኼንን ገድል ነው፡፡
ሕዝብን በማፋጀትና አገርን ቀውስ ውስጥ በመክተት ታሪክ አይሠራም፡፡ ታሪክ መሥራት ማለት አገርን ዘመኑ በደረሰበት የዕድገት ደረጃ ማሳደግ ነው፡፡ አገር ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና የምትቀዳጀው ልጆቿ ልዩነታቸውን በሠለጠነ መንገድ እያስተናገዱ አንድ ላይ መቆም ሲችሉ ነው፡፡ አንድነት ማለት ልዩነትን አጥብቦ የጋራ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መስማማት ማለት ነው፡፡ ይኼንን ማድረግ የማይችል ማንኛውም ግለሰብ ሆነ የፖለቲካ ድርጅት ፖለቲከኛ መሆን አይቻለውም፡፡ ፖለቲከኛ እንደ ዲፕሎማት ብልኃተኛ ሲሆን፣ እንደ ወታደራዊ ስትራቴጂስት ደግሞ መቼ እንደሚያጠቃና እንደሚከላከል የሚያውቅ ነው፡፡ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ወቅቱን እየመዘነ ትርፍና ኪሳራውን እንደሚያሰላ ነጋዴ ተደራዳሪ ነው፡፡ አገር የመምራት ጥበብ በተፈጥሮና በትምህርት የሚገኝ ሲሆን፣ የዳበረ ልምድ ሲታከልበት ደግሞ የተሟላ ይሆናል፡፡ ከዚህ ውጪ የሚንቀሳቀስ ግን ፖለቲከኛ ለመሆን አሳሩን ከሚያይ ይልቅ ሌላ መተዳደሪያ ቢፈልግ ይሻለዋል፡፡ አገር በጥበብ እንጂ በነሲብ አትመራም፡፡ ነውጠኝነትና ጀብደኝነት ለዚህ ዘመን አይመጥኑም፡፡ ታሪክን እያጣመሙ ለማጭበርበር መሞከርም ፋይዳ የለውም፡፡ ታሪክ አልባ ሆነው ታሪክ ያላቸውን ኢትዮጵያዊያን ለማንቋሸሽም ሆነ ለማዋረድ መሞከር ትንሽነት ነው፡፡ ታሪክ ይሠሩታል እንጂ አይታገሉትም፡፡ ለዚህም ነው ታሪክ መሥራት ቢያቅት ማበላሸት ነውር ነው የሚባለው!